ሶሪያ፣ የባዐዝ ዉልደት-ፍፃሜም፣ የአረብ አንድነት ሥርዓተ ቀብር ምድር
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 28 2017
የቀድሞዉ የኢትዮጵያ መሪ ኮለኔል መንግሥቱ ኃይለማርም ከሐገር በተሰደዱ ሳምንት አዲስ አበባ ደርገ-ኢሠፓን በማዉገዝ፣ ሐዉልት በማፍረስ፣ አፅም በመልቀም ተጠምዳ፣የሟቾችና የተሰወሩ ሰዎችን ፎቶ ባነገቡ ነዋሪዎችዋ ለቅሶ-ሙሾ ስታረግድ፣የምዕራባዉያን አድናቆት፣የድጋፍ ቃል ሲንቆረቆርላት አይተናል።በ2003 አጋማሽ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) በሳዳም ሁሴን ሥርዓት ፍፃሜ ማግሥት ባግዳዶች፣ በ2012 ማብቂያ ሙዓመር ቃዛፊ ከተገደሉ በኋላ ቤንጋዚዎችና ሌሎችም የአዲስ አበባዉን ትርዒት ደግመዉታል።ሶሪያ የአል አሰድ ሥርዓትን ዉድቀት አብስራ ወይም አርድታ ደማስቆ ቀዳሚዎችዋን ከመሰለች ወር ደፈነች።የአል አሰድ ሥርዓት መገርሰስ የባዓዝ ፓርቲ ፍፃሜ፣የአረብ አንድነት መንፈስ ሥርዓተ ቀብርም ጭምር ነዉ።ብሥራትና መርዶ።ላፍታ እንዴት ለምን እንበል።
ዓይን አዳኙ-ሐገር «አጥፊዉ» ፖለቲከኛ
ያባቱን አልጋ እንዲወርስ በወታደራዊዉ ሙያ፣ በፖለቲካ፣ በአስተዳደሩም የሰለጠነ ብዙ የተዘጋጀዉም ባሴል አል-አሰድ ነበር።መሐንዲስ፣ በወታደራዊ ሳይንስ ዶክተር፣ በማዕረግ ኮሎኔል፣ በስፖርቱ ፈረስ ጋላቢ ነበር።
መልከ መልካም፣ ፈጣን፣ቀልጣፋ ግን ቀበጥባጣዉ ወጣት ካባቱ ቀድሞ በመኪና አደጋ ሞተ።ጥር 1994 31 ዓመቱ ነበር። ዕድሜም የጤና እጦትም የተጫጫናቸዉ ፕሬዝደንት ሐፊዝ አል አሰድ አልጋቸዉን ለሁለተኛዉ ወንድ ልጃቸዉ ከማዉረስ ሌላ ሌላ ምርጫ አልነበራቸዉም።ሰኔ 10 ቀን 2000 ሞቱ።
ቀዉለል፣ ረጋ፣ ነፍነፍ-ለሥልለስ፣ አፈር ደግሞ ካይኑ ሰበር የሚለዉ የዓይን ቀዶ ሐኪም «ያባቱን አልጋ ወረሰ እንዳይባል» እንዳይባል የሶሪያ ሐገ መንግሥት በልኩ እስኪከለስ፣ እሱዉ ከሱዉ ጋር የተወዳደሩበት ምርጫ እስኪደረግ አንድ ወር ጠበቆ በ99.29 ከመቶ ድምፅ ምርጫዉን አሸነፈ ተባለና የሶሪያ አረብ ሪፐብሊክ ፕሬዝደንት፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ፣ የአረብ ሶሻሊስት ባዓዝ ፓርቲ ማዕከላዊ ዕዝ ዋና ፀሐፊ ሆነ።ሐምሌ 10።2000።
34 ዓመቱ ነበር።ግን ይኽን ሁሉ ሥልጣን ይዞ መቼም አንተ አይባልም።እንግሊዝ (ለንደን) የተማሩ፣ ፈረንሳይኛን በመጠኑ፣ እንግሊዝኛን አቀላጥፈዉ የሚናገሩ፣ ሐኪም፣ በIT ዕዉቀት የተካኑ፣ ኮምፒዉተር የሚወዱ ምናልባትም ለምዕራባዉያን የሚወግኑ እየተባሉ በሚንቆለጳጳሱበት በዚያዉ ሰሞን ለንደን ተወልዳ ያደገች፣እዚያዉ ለንደን የኮምፒዉተር ሳይስና የፈረንሳይኛ ሥነ-ፅሁፍን ያጠናች ቆንጆ አገቡና የለንደን-ፓሪሶችን የማሕበረ-ፖለቲካ ሥርዓትን ሳይከተሉ አይቀርም የሚሉ የምዕራባዉያን መላመቺዎችን መላ አጠናከሩት።
እዚያ ሐገራቸዉ ደግሞ እንደ አዲስ መሪ ወግ የተራ ሕዝባቸዉን ስሜት ለማወቅ ከዘየዱት ብልሐት አለባበስ፣ መልካቸዉን-ቀየርየር፣ አጀባቸዉን-ቀነስ፣ ጓዛቸዉን-አነስ እያደረጉ እንደ ተራ ሰዉ ተራ ምግብ፣ ሻሒ ቤትም፣ ግሮሰሪ፣ የገበያ አዳራሽ፣ የስፖርት ማዘዉተሪያም ብቅ ማለት አንዱ ነበር።
የየዋሁ ባለግሮሰሪ ምኞት
በ2001 የታተመ ፅሑፍ እንዳመለከተዉ፣ አሰድ አንድ ቀን ከሶስት አጃቢዎቻቸዉ ጋር ሆነዉ አንዱ አነስተኛ ግሮሰሪ ይገቡና ለስላሳ፣ ቡናም ሻሒም እያሉ እንደ ጓደኛሞች ሲጨዋወቱ፣ የሌሎችንም ጭዉዉጥ ሲያጮልጉ ቆይተዉ ሒሳብ ለመክፈል አስተናጋጁን ይጠይቃሉ።
ሒሳብ መቀበያ ባንኮኒ ላይ ሆኖ ከሩቅ ሲያየቸዉ የነበረዉ የግሮሰሪዉ ባለቤት «የረጅሙ ሰዉዬ ተከፍሏል።የሌሎቹን ተቀበል።» ብሎ አስተናጋጁን አዘዘ።አስተናጋጁም የተባለዉን ካደረገ በኋላ እንግዶቹ ሊወጡ ሲሉ አንዱ ወደ ባለግሮሰሪዉ ዞር ብሎ
«የሱን ሒሳብ ለምን ተዉከዉ» በማለት ይጠይቃል።ባለቤቱም «እሱ አዲሱን መሪያችንን ይመስላል።አዲሱን መሪያችንን ሥለምደወደዉ ሒሳቡን እኔ እከፍላለሁ።» በማለት ይመልሳል።
«አሰድ ቃል አልተነፈሱም።» አሉ ያኔ የፃፉ፣ አሰመሳዩ አጃቢ ግን «እኔም አዲሱ መሪያችንን እወደዋለሁ።» አለና ለመዉደዱ ምክንያት ያለዉን ተናግሮ ባለግሮሰሪዉ መሪዉን የሚወድበትን ምክንያት ጠየቀዉ።«ወጣት ነዉ።ዶክተር ነዉ።የሰዉ ዓይንን ከመጥፋት ማዳን የሚችል ሰዉ ኢንሻአላሕ ሐገሩን እንዳትጠፋ ማዳን አያቅተዉም ብዬ ነዋ።» እያለ ምክንያቱን ይዘረዝር ገባ።
የአሰድ ጅምር ሙከራ
ጀርመናዊዉ የፖለቲካ ተንታኝ ቪንተር በቅርቡ እንዳሉት በሽር አል አሰድ በተለይ የምጣኔ ሐብትን ተሐድሶ ማድረጉ ተሳክቶላቸዋል፣ ሙስና፣ አምባገነናዊ አገዛዝ፣ የፖለቲካ፣ ፀጥታና ዲፕሎማሲዉ ግን አልሆነላቸዉም።
«የምጣኔ ሐብቱን ሥርዓት ነፃ በማድረጉ ረገድ ሁነኛ እርምጃ ወስደዋል።የፀጥታ ኃሉን፣ የአምባገነናዊ ሥርዓቱን መዋቅር ለመለወጥና ሙስናን ለማስወገድ ግድ ያደረጉት ነገር አልነበረም።»
በሽር አል አሰድ ያባታቸዉን «ዙፋን» እንዲወርሱ ትምሕርታቸዉን አቋርጠዉ ወደ ሐገራቸዉ ከተመለሱ ከ1995 ፕሬዝደንት እስከሆኑ ድረስ ፣ ከዚያ በፊት ብዙም የማይጥማቸዉን ፖለቲካ ተለማምደዋል።ባጭር ጊዜ የኮሎኔልነት ማዕረግ ተለጥፎላቸዉ ሊባኖስ የሰፈረዉን የሶሪያ ጦር በበላይነት አዘዋልም።
ይሁንና እስራኤል እንደ ሐገር ከተመሠረተች ከ1948 ጀምሮ በየጊዜዉና በፍጥነት የሚለዋወጠዉን የመካከለኛዉ ምሥራቅን ኮምፓስ የለሽ የፖለቲካ ማዕበልን እንዳመጣጡ ለመዋኘት ያባታቸዉን አስተዳደግ፣ የመዋጋት-ማዋጋት ብቃትና የፖለቲካ ሴራ ክሒሊን ከቤተ-መንግሥቱ ጋር መዉረስ በርግጥ አልቻሉም።ጊዜም አላገኙም።
በ2000 ኃምሌ ሥልጣን እንደያዙ ከአንዳድ ምዕራባዉያን የተሰዘረዉን የቢሆኔ ትንታኔ፣ የተራ ዜጋቸዉን አድናቆት፣ የምክር ቤታቸዉን ጭብጨባ፤ የባለሥልጣኖቻቸዉን ታዛዥነት ጥልቀት-ግልብነት፣ ተለዋወጩን ግን አደገኛዉን የፖለቲካ ጥልፍልፍ በቅጡ አስተንትነዉ ሳያበቁ ሥልጣን በያዙበት ዓመት ከመጀመሪያዉ የሐገር ዉስጥ ተቃዉሞ ጋር ተጋፈጡ።
ተቃዉሞዉ የኩርዶች ዓመፅ፣ የሱኒ ሙስሊሞች ቅሬታ፣ የግራ ፖለቲካ አቀንቃኞችን ደባ ብቻ አልነበረም።ሁሉንም የሚመስል ግን አንዱንም ያልሆነ፣ ደራሲዎችን፣ሙሕራንን፣ የሙስሊም ወንድማማቾች መሪና አባላትን ያስተናበረ ነበረ።ስሙም የደማስቆ መፀዉ (ስፕሪግ) ወይም Rabīʻ Dimashq) አሉት።
ሶሪያ የኃያል፣ ቱጃሮች፣ የአክራሪ ለዘብተኞች መፋለሚያ ምድር
በአባታቸዉ አገዛዝ ያቄሙ፣ የታመቁ፣ በሥልጣን መወራረሱ የተከፉ ወገኖች የአዲሱን መሪ በቅጡ ያልጠና አገዛዝ ከዉስጥ ሲገተግቱት፣ የመካከለኛዉ ምሥራቅ የፖለቲካ፣ የስለላ፣ የጦርና የዲፕሎማሲ ጥልፍልፍ ይተበትባቸዉ ገባ።በ2011 ሖምስ ላይ የተቀጣጠለዉ ሕዝባዊ አመፅ ደግሞ በርግጥ የዘመነ-ሥልጣናቸዉ መጨረሻ-መጀመሪያዉ ሆነ።
አመፁ ባጭር ጊዜ ወደ ነፍጥ ዉጊያ ተለዉጦ ያቺ ጥንታዊ የሥልጣኔ ለም ምድር፣ ያቺ ሥልታዊ የጀግኖች፣ መፍለቂያ-መገደያ፣ የብልሆች መንሰሪያ-መክሰሪያ ሥፍራ፣ ያቺ አማላይ የኃያላን መንገሺያ፣ መዉድቂያም ሐገር የዘመኑ ኃያል፣ ቱጃሮች፣ የምሥራቅ-ምዕራቦች፣ የአክራሪ ለዘብተኞች የጦር አዉድ ሆነች።ሳዑዲ አረቢ፣ ቀጠር፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ዮርዳኖስ፣ ከሺአይቲ ኢራን፣ ከሊባኖስ ሒዝቡላሕ ጋር፣ እስራኤል-ከኢራን፣አክራሪ ሙስሊሞች ከለዘብተኞች፣ ቱርክ ከኩርዶች፣ አሜሪካና ተከታዮቿ ከሩሲያ ጋር በቀጥታም በተዘዋዋሪም ሶሪያዉያንን ያፋጁባት ገቡ።
የአረቦች፣ የፋርሶች፣ የቱርኮች ገንዘብ፣ ተዋጊዎች፣ የአሜሪካ፣ የአዉሮጳ፣ የሩሲያ ጦር መሳሪያ፣ የሁሉም ሰላዮች ለ13 ዓመታት የተራኮቱባት ሶሪያ ወድማለች።ተሽመድምዳለች።ከግማሽ ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝቧ አልቋል።12 ሚሊዮን ሕዝብ አንድም ተሰዷል አለያም ተፈናቅሏል።
የሰዉ ዓይንን ከመጥፋት የሚያድኑት ሐኪም ሐገራቸዉን ከጥፋት አቶን ሞጅረዉ ክሳይ፣ ፍርስራሽ፣ ትቢያዋን ተረማምደዉ ዉልቅ አሉ።የአሰድ ዉድቀት የሞስኮ፣ የቴሕራን፣ የሒዝቡላሕ ሽንፈት፣ የሪያድ፣ዶሐ፣ አቡዳቢ፣አንካራ፣ የዋሽግተን፣ ቴል አቪቭ፣ ለንደን፣ ፓሪስ፣ በርሊኖች ድል መሆኑ በርግጥ አላከራከረም።ደማስቆን የተቆጣጠሩት፣ አሕመድ አል ሻራ ግን ድሉ የመላዉ ሙስሊም፣ያካባቢዉ ሐገራት ሁሉ ነዉ ይላሉ።
«ይሕ ድል ወንድሞቼ ለመላዉ ሙስሊም አዲስ ታሪክ ማለት ነዉ።ይሕ ድል ለአካባቢዉ በሙሉ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ነዉ።»
የባዐዝ ፓርቲ ፍፃሜ፣ የአረብ አንድነት መንፈስ መጨረሻ
አዲሱ የታሪክ ምዕራፍ ለሙስሊሞች፣ ለአካባቢዉ ወይም ለአረቦች፣ለሶሪያም መጥቀም መጉዳቱን መስካሪዉ በርግጥ የጊዜ ሒደት ነዉ።አዲሱ ታሪክ በ1950ዎቹ ከደማስቆ እስከ ሰነዓ፣ ከባግዳድ እስከ ሱዳን በመላዉ ዓረብ ዝናዉ የናኘዉ፣ ኢራቅን ለአርባ ዓመታት ያክል፣ ሶሪያን ከስልሳ ዓመት በላይ የገዛዉ፣ የአረብ ሶሻሊስት ባዓዝ ፓርቲ ፍፃሜ መሆኑ ግን አላከራከረም።
ከመጀመሪያዉ የዓለም ጦርነት ፍፃሜ በኋላ ጥንታዊዉን የአረብ አንድነትን ለመመለስ ኃይማኖትን፣ ምሑራንን፣ የጦር መኮንኖችን መሠረት ያደረጉ የተለያዩ አስተሳሰቦች በአረቡ ዓለም ተፈጥረዋል።የጎሉት በ1920ዎቹ አጋማሽ ግብፅ ዉስጥ የተመሠረተዉ የሙስሊም ወድማማቾች ማሕበረሰብ፣በ1940ዎቹ ሁለተኛ አጋማሽ ይፋ የሆነዉ የበዓዝ ፓርቲና በ1950ዎቹ ናስራዊ የሚባለዉ የገማል አብድናስር የአረብ ብሔረተኛ አስተሳሰብ ነዉ።
የአንግሎ-አሜሪካ መሪዎች በ1945 አዳሲ ባቋቋሙት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካይነት እስራኤልን ለመመስረት በሚጥሩበት በ1947 ደማስቆ ላይ የተመሠረተዉ የአረብ ሶሻሊስት ባዐዝ ፓርቲ ከሌሎቹ ይበልጥ ፖለቲካ ላይ ያነጣጠረ፣ በአረቡ አለም ፈጥኖ የተሰራጨ ሶሪያና ኢራቅ ዉስጥ ለሥልጣን የበቃም ነዉ።
የሶሪያ በሳል የፖለቲካ አዋቂዎች ሚካኤል አፍላቅ፣ ሳላሕ አል ዲንና ዘኪ አል አር-ሱሲ የመሠረቱት ፓርቲ የአረብ አንድነትን፣ ነፃነትንና ሕብረተ-ሰባዊነትን ወይም ሶሻሊስትን የሚሰብክ፣ ለሐይማኖት ያልወገነ፣ ፀረ ኢፔሪያሊስት በመሆኑ ከአረብ ቱጃሮች፣ ከነገሥታት፣ ከሐማኖት ሰባኪዎችና ከምዕራቡ ካፒታሊስታዊ ዓለም የገጠመዉ ተቃዉሞ ከባድ ነበር።
ፓርቲዉ ከፖለቲከኞች ይልቅ የጦር መኮንኖች እጅ መዉደቁም የፖለቲካ አስተሳሰቡን አወላክፎታል።ገና ከምስረታዉ የአረብ ብሔረተኝነትን የሚፃረሩ፣ ሕብረተሰባዊነትን የሚጠሉ፣ በኃይማኖት ስም የሚገዙ አረቦችም፣ ምዕራባዉያንም፣ እስራኤሎችም ከዉስጥም ከዉጪም ሲገዘግዙት፣ እርስበርስ ሲያላትሙት 50 ዓመት አስቆጥረዉ በ2003 ኢራቅን በግልፅ ወርረዉ ፓርቲዉን ባግዳድ ላይ ገደሉት።ባለፈዉ ወር ደግሞ ደማስቆ ላይ ቀበሩት።
የአረቦችና የምዕራባዉያን ድጋፍ
የአረብ የአንድነት መንፈስም ለጊዜዉ የአረብ-ሊግ በተባለዉ ሙት ማሕበር አስከሬን ላይ ተቋጠረ።ሶሪያም አዲሱ ገዢዋ «አዲስ« ባሉት የታሪክ ምዕራፍ በአል አሰድ ሥርዓት ተገደሉ የተባሉ የሙቶችዋን አፅም እየለቀመች፣የተሰወሩትን እየፈለገች፣ ፍርስራሽ ዉዳሚዋ መሐል ተሞሸረች።ርዕሰ ከተማ ደማስቆ የአረብ፣ የቱርክ፣ የአዉሮጳ፣ የአሜሪካ መንግሥታት አዲሲቱን ሶሪያ ለመርዳት የሚገቡትን ቃል በመመዝገብ፣ ጎብኚ ባለሥልጣናት ለማስተናገድ ጠብ እርግፍ እያለች ነዉ።
ሶሪያን ለረጅም ጊዜ የገዛዉ የኦስማን ቱርክ ሥርዓት በ1920 በአረብ-ፈረንሳይ፣ ብሪታንያ ሕብር-ጦር ሲሸነፍ ቀዳማዊ ንጉስ ፈይሰል አል ሁሴይን ቢን አሊ አል ሐሺማይት ነግሠዉ ነበር።ፈይሰል በነገሱ በወራት ዉስጥ በብሪታንያ ርዳታ የዘመተዉ የፈረንሳይ ጦር የሐሺማይቱን ንጉስ ከሥልጣን አስወግዶ ሶሪያና ቅኝ ይገዛ ገባ።
ባለፈዉ አርብ ደማስቆን የጎበኙት የፈረንሳይ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዤን ኖኤል ባሮ በጣም አስከፊ ያሉት የሐገራቸዉ ቅኝ ገዢዎች አረባዊቱን ሶሪያ ከአረቦች እጅ በኃይል ቀምታ ከ20 ዓመታት በላይ ቅኝ የመግዛትዋ አስከፊ ታሪክ ሳይሆን ሶሪያዊዉ አሰድ-በሶሪያዎች ላይ ያደረሱት ግፍ ነዉ።
«ሶሪያዉያን ሐገራቸዉን በበሽር አል አሰድ ሥርዓት ተቀምተዉ ረጅም ዓመታት አስቆጥረዋል።ሐገሪቱ በዚሕ ሥርዓት ወድማለች፣ ታግታለችም።ሶሪያዉያን የሐገራቸዉ ባለቤት የሚሆኑበት ወቅቱ አሁን ነዉ።ይሕ እዉን የሚሆነዉ ደግሞ የተለያዩ ማሕበረቦች የሐይማኖና የፆታ ጭቆና ሳይኖርባቸዉ ሁሉም የሚወከሉበት በፖለቲካዊ ሽግግር ሲደረግ ነዉ።»
ከፈረንሳዩ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጋር አብረዉ አዲሶቹን የደማስቆ ገዢዎች ያነጋገሩት የጀርመንዋ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አናሌና ቤርቦክም ለወደፊቷ ሶሪያ የሚበጀዉ ሁሉም የሚወከሉበት የፖለቲካ ሥርዓት ነዉ ብለዋል።
«ለወደፊቷ ለሶሪያ የተሻለ የሚሆነዉ፣ ሁሉን አካታች፣ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር፣ ዕርቅና ዳግም ግንባታ ማድረግ ነዉ።ይሕ ፣ሁሉንም የጎሳና የኃይማኖት ቡድናትን ያካተተ፣ የወንድና የሴቶችን እኩልነት የጠበቀ ምክክርን ይጠይቃል።ሕገ መንግሥት (በማርቀቅና መፅደቁ) ሒደትም ሆነ በወደፊቱ የሶሪያ መንግሥት ምሥረታ ሁሉም ወገኖች መሳተፍ አለባቸዉ።»
ከ1990ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ ከኢትዮጵያ እስከ ደቡብ አፍሪቃ፣ ከኢራቅ እስከ አፍቃኒስታን፣ ከኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ እስከ ሊቢያ የነበሩ ቀዳሚ ሥርዓቶችን ማዉገዝ፣ ለአዳዲሶቹ ሥርዓቶች ድጋፍ የመስጠት ቃል ለሶሪያዎችም እየጎረፈ ነዉ።በተለይ ምዕራባዉያን መንግሥታት አዲሶቹ የሶሪያ ገዢዎች ሠላም፣እኩልነት፣ ፍትሕ፣ ዴሞክራሲ እንዲያስርፁ፤ ሐገራቸዉን ዳግም እንዲገነቡም እየመከሩ ነዉ።
አዲሲቱ ሶሪያ
ይሁንናምዕራባዉያን መንግሥታት በሶሪያ ላይ የጣሉትን ማዕቀብ እስካሁን አላነሱም።ደማስቆ ድረስ እየሔዱ የሚያናግሯቸዉ አዲሶቹ የሶሪያ ገዢዎች በሚመሩት ሐያት ተሕሪር አሽ-ሻም (HTS) ንም በአሸባሪነት እንደፈረጁት ነዉ።
አዲሱ የሶሪያ ገዢ አሕመድ አል-ሻራ ለሙስሊሞችም፣ ለአካባቢዉ ሐገራትም አዲስ የታርክ ምዕራፍ መጀመሩን የዛሬ ወር ግድም ሲያበስሩ የእስራኤል ጦር የሶሪያን ግዛት በቦምብ ሚሳዬል ያጋይ ነበር።የፈረንሳይና የጀርመን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ሶሪያዎች ሐገራቸዉን በአል አሰድ አገዛዝ ለረጅም ዘመናት መቀማታቸዉን ደማስቆ ላይ ሲናገሩ ሥለጎላን ኮረብታ የማንነት መጥቀስ በርግጥ አላስፈለጋቸዉም።
የፓሪስ-በርሊን ዲፕሎማቶች ለሶሪያዎች ያደረጉት የሰላም የእኩልነት ጥሪ እንዴትነት ሲተነተን ዛሬ የእስራኤል ጦር ተጨማሪ የሶሪያ ግዛቶችን መያዙ እየተዘገበ ነዉ።ወይዘሮዋ ምሥክር ናቸዉ።
«ታሕሳስ 8 ሥርዓቱ ሲወድቅ፣ አሁን እንደምታዩት የእስራኤል ታንኮች የአስተዳደሩን ሕንፃ ተቆጣጠሩት።ብዙ ጊዜ ኻህን አርናቤሕ ይገባሉ፣ አል በአዝ ከተማ በሚገኘዉ የአስተዳደር ተቋማትም ገብተዋል።የመኖሪያ መንደሮች አልገቡም።ግን ብዙ ጊዜ የወሰን መስመሮችን እየጣሱ መሐል ከተማዉ ድረስ ገብተዋል።»
አዲሱ የሶሪያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አሰድ አል-ሺባኒ የአረቦችን ድጋፍ ለማግኘት ሪያድ፣ዶሐን ጎብኝተዉ ዛሬ አቡዳቢ ገብተዋል።ግን የድሕረ-በሽር አል አሰዷ ሶሪያ በርግጥ የሶሪያዎች ነች? ቸር ያሰማን።
ነጋሽ መሐመድ
እሸቴ በቀለ