ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ የሻከረ ግንኙነታቸውን ለማሻሻል እየሠሩ መሆናቸው
ቅዳሜ፣ የካቲት 22 2017ሁለቱ መሪዎች አንካራ ቱርክየ ላይ በፕሬዝደንት ረሲፕ ጠይብ ኤርዶኻን አማካኝነት ለወራት ሲወዛገቡበት የቆዩትን ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችውን የመግባቢያ ሰነድ ወደጎን አድርገው ወታደራዊ ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማምተዋል። ለጋራ ጥቅሞቻቸውም ትብብራቸውን እንደሚያጠናክሩ መሪዎቹ በመግለጫቸው አስታውቀዋል።
የሶማሊያ ኢትዮጵያ ግንኙነት
የሶማሊያ ጉብኝታቸውን አስመልክተው በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ገጻቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ፤ «ውይይታችን እንደ ሰላም እና ፀጥታ፣ ኢኮኖሚ፣ ዲፕሎማሲ እና በጋራ ልንገነባቸው ስለምንችላቸው የመሠረተ ልማት ሥራዎች ያሉ ቁልፍ ጉዳዮችን የተመለከተ ነበር።» በማለት ገልጸዋል። የአፍሪቃ ቀንድ በሀብት የበለጸገ መሆኑን ያስታወሱት አብይ፤ የአካባቢው ሃገራት ያለውን ሀብት ለጋር እድገት ሊጠቀሙበት ይገባል በማለት ነው ያሳሰቡት። ቀጠናዊ ትብብር ቁልፍ እንደሆነ በማመልከትም ይኽን እውን ለማድረግ ከሶማሊያ ጋር ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን አመልክተዋል።
የሁለቱን ሃገራት ወቅታዊ ግንኙነት አስመልክቶ ዶቼ ቬለ አስተያየታቸው የጠየቃቸው በውጭ ጉዳይ ተቋም የአፍሪቃ ጉዳዮች የሥራ ክፍል ኃላፊ እና ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ግዛቸው አስራት የኢትዮጵያን የውጪ ጉዳይ ፖሊስ፣ ከጎረቤት ሃገራት ጋር በትብብር መሥራትን ያስቀድማል ብለዋል።
ከኢትዮጵያ የባሕር ከወደብ ፍለጋ ጋር በተገናኘ በወሰደችው ርምጃ በሁለቱ ሃገራት መካከል ተፈጥሮ የነበረው የከረረ አለመግባባት አናካራ ላይ በውይይት ከለዘበ ወዲህ አስተማማኝ ነው ባይባልም በአፍሪቃው ቀንድ ያንዣበበው ውጥረት የረገበ መስሏል። በአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ አለመግባባቶች ሲከሰቱ ቀጣናውን ከውጥረት የመታደግ አካሄድ ብዙም እንደማይታይ የተናገሩት የአፍሪቃ ጉዳዮች የሥራ ክፍል ኃላፊ እና ከፍተኛ ተመራማሪው ዶክተር ግዛቸው፤ የቱርክየን ሚና በአዎንታዊነት ያነሳሉ።
የአንካራው ስምምነት
አንካራ ላይ በፕሬዝደንት ረሲፕ ጠይብ ኤርዶኻን አማካኝነት ከወራት ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ በኋላ ፊት ለፊት የተገናኙት የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ መሪዎች የሰላም ስምምነት ተፈራርመዋል። የስምምነቱ መሠረት ሊሆን የሚችለውም ሁለቱም ሃገራት ላነሷቸው ዋነኛ ጉዳዮች መፍትሄ በጋራ መፈለግ ነው። ለዚህም ቀደም ሲል ከአንድ ወር በፊት የሶማሊያው ፕሬዝደንት ለአፍሪቃ ሕብረት ጉባኤን አስታከው አዲስ አበባ በመገኘት የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ጋር ተነጋግረዋል። የኢትዮጵያውም መሪም በዚህ ሳምንት በተመሳሳይ መቃዲሾ ተገኝተዋል። የመሪዎቹ በየጊዜው መገናኘትም ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ የሚረዱ ውይይቶችን ለማካሄድ እንደሆነ ይታመናል። ዶክተር ግዛቸውም ይህኑ ያጠናክራሉ።
የአፍሪቃ ቀንድ የሽብር ስጋት
ይህ በእንዲህ እንዳለ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ጉብኝት በማስመልከትም በመቃዲሹና አካባቢው ከፍተኛ የጸጥታ ጥበቃ እንደነበር ነው የተዘገበው። ሶማሊ ጋርዲያን እንደዘገበው ረቡዕ ዕለት ምሽት ዋና ዋና መንገዶች ተዘግተው ተሽከርካሪዎችም ከእንቅስቃሴ ታግደው ነበር። በርካታ የሶማሊያ ፓርላማ አባላት ወደቤታቸው በሚመለሱበት ጊዜ መወቂያቸውን ሁሉ እያሳዩም በፀጥታ ኃይሎች እንዲቆሙ መደረጋቸውን ዘገባው አመልክቷል። ሆኖም እንደዘገባው እሳቸው ከመድረሳቸው ጥቂት ቀደም ብሎ ዋና ከተማ መቃዲሹ ላይ የሞርታር ጥቃት ደርሷል። ከየት በኩል እንደተተኮሰ ግልፅ ባይሆንም በዋና ከተማዋ አደን አብዴ አውሮፕላን ማረፊያ ላይም ሞርታር ተተኩሷል። ከተተኮሱት 11 ቅንቡላዎች አንዱ ከፍተኛ እንግዶች በሚገቡበት አካባቢ የመኪና ማቆሚያ ስፍራ መውደቁን እማኞች ለዜና ምንጩ ገልጸዋል። ጥቃቱ በደረሰበት ወቅት ፕሬዝደንት ሀሰን በአውሮፕላን ማረፊያው እንደነበሩ የሶማሊያ ብሔራዊ ቴሌቪዥንን የጠቀሱ ዘገባዎች አመልክተዋል። ሆኖም የሶማሊያ መንግሥት ስለጥቃቱ ምን አስተያየት አለመስጠቱ ነው የተነገረው። የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩም አልተዘገበም። አሸባብ ለጥቃቱ ሀላፊነት ወስዷል። ቀደም ብሎ ሐሙስ በማለዳም ቡድኑ ከመቃዲዮ 30 ኪሎ ሜትር ርቀር ላይ በምትገኘው ስልታዊ ከተማ ባላድ ላይ ጥቃት ሰንዝሮ ለአጭር ጊዜም ተቆጣጥሯት እንደነበረም ዘገባው ጠቅሷል።
ሁለቱ መሪዎች መቃዲሹ ላይ ከመገናኘታቸው አስቀድሞ የሶማሊያ መንግሥት ስለኢትዮጵያ መሪ ጉብኝት ባወጣው መግለጫ መሪዎቹ በአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ የሽብር እንቅስቃሴን በጋራ ስለመዋጋት ስለሚያደርጉት ትብብር እንደሚነጋገሩ ጠቁሟል። ዶክተር ግዛቸው ቀጣናዊ የደኅንነት ጉዳይ የሶማሊያ ብቻ አይደለም ባይ ናቸው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ትናንት ዓርብ በወቅታዊ ሀገራዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር የተደረገው ጥረት በተለይም በፖለቲካ ዲፕሎማሲ ማዕቀፍ ውስጥ ውጤታማ ነው ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አመልክቷል። ቃል አቀባዩ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የመቃዲሹ ጉብኝትም የዚህ ማሳያ እንደሆነም ነው የጠቆሙት። አክለውም የሁለቱም ሃገራት ሁለንተናዊ እድገት እርስ በርስ የተሳሰሩ መሆናቸውን ጠቁመው፣ የሶማሊያ ደኅንነት የኢትዮጵያን መረጋጋት በቀጥታ የሚነካ እንደሆነ ገልጸዋል። አዲስ አበባ እና መቅዲሹ የሻከረ ግንኙነታቸውን ለማሻሻል በሚጥሩበት በዚህ ወቅት ውዝግቡን የጋበዘው ከፑንትላንድ ጋር የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ ጉዳይ ፍጻሜው ግልጽ እንዳልሆነ ነው ዘገባዎች ያመለከቱት።
ሸዋዬ ለገሠ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር