ሶማሊያ ለአሜሪካ ለመስጠት ያቀደችው ወደቦች እና አንድምታው
ሰኞ፣ መጋቢት 22 2017ሮይተርስ የዜና ወኪል ባለፈው ዓርብ ተመለከትኩ ያለው የሶማሊያው መንግስት ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃሙድ ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናለድ ትራምፕ የላኩት ደብዳቤ ከሁለት ሳምንታት በፊት ቀደም ብሎ የተጻፈና አሜሪካ የባሊዶግሌ እና በርበራ አየር ጣቢያ እንዲሁም የበርበራ እና ቦሳሶ ወደቦችን በብቸኝነት እንድታስተዳድር ግብዣ ያቀረበ ነው፡፡
ምንም እንኳ ለጊዜው የሶማሊያ ባለስልጣናት በጉዳዩ ላይ ማረጋገጫ ባይሰጡም፤ ሞቃዲሾ ስልቱን የነደፈችው ምናልባትም በተለይም ራስ ገዝ ግዛቶቿ ሶማሌላንድ እና ፑንትላንድ ዓለማቀፍ እውቅና አግኝተው ከሶማሊያ በመውጣት አገር እንዳይሆኑ በማለም እንደሆነ እየተነገ ነው፡፡
የምስራቅ አፍሪካን ጂኦፖለቲካዊ እና ቀጣናዊ ጉዳዮችን በመከታተል በሚሰጡት ትንተና የሚታወቁት የፖለቲካ ተንታኝ አብዱራሃም ሰይድ ሶማሊያ ለአሜሪካ የጻፈችው የወደቦች ማስተዳደር ግብዣው ሶስት ነገሮችን የሚያመላክት ሊሆን እንደሚችል ይገመታል ባይ ናቸው።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሶማሊያ ጉብኝት አንድምታ
“አንደኛው የትራምፕ አስተዳደር ምናባትም ለሶማሊላንድ የአገርነት እውቅና እንዳይሰጥ በመስጋት ነው፡፡ ሁለተኛ ከዚህ በፊት ኳታር ሳውዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ስከቧት አሜሪካ ትልቁን ወታደራዊ ታቢያ በወደቧ እንድትገነባ በማድረግ ስጋቷን እንደገታችው ሁሉ ሶማሊያም በተለይም የኢትዮጵያ ወደብ ላይ እያሳየች ያለው ፍላጎት ስላሰጋት ይህንኑን ዘላቂ እልባት ለመስጠት ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡ ሶስተኛው ደግሞ እነዚህ ለአሜሪካ እንዲሰጡ ግብዣ የቀረበባቸው ወደቦች በሶማሊላንድ እና ፑንትላንድ አከባቢ እንደመሆናቸው ግዛቶቹ በሶማሊያ ፌዴራላዊ ግዛቶች ስር እንዲገቡ በማሰብ” ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል፡፡
በርግጥ ሶማሊያ ለአሜሪካ ያቀረበችላት የወደብ ማስተዳደር ጥያቄ በራስ ገዟ ሶማሊላንድ ወዲያው ነበር ተቃውሞ የገጠመው፡፡ ሀርጌሳ ቁልፍ ወደቧ የሆነው በርበራ በሶማሊያ መንግስት ለአሜሪካ መቅረቡን
በመንቀፍ ከኤዴን ባህረሰላጤ ጋር ቅርበት ያላት ስትራቴጂካዊ ስፍራዋ በርበራ የሞቃዲሾ ግዛት ባለመሆኗ ሶማሊያ ልታዝበት አይገባም በማለት ሀሳቡን ነቅፋለች፡፡
ሶማሊያ ለአሜሪካ በጻፈችው ደብዳቤ የወደቦቹ በአሜሪካ መተዳደር ዩናይትድ ስቴት ሽብርተኝነትና አክራሪነትን ለመዋጋት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ብትልም የሶማሊላንድ ውጭጉዳይ ሚኒስትር አብድራሃማን ዳህር አደን ተጻፈ በተባለው ደብዳቤ ላይ በሰጡት ምላሽ ሀሳቡን መጥፎና የማይሳካ በማለት አሜሪካ ሞኝ ስላልሆነች ወደ በርበራ ስትመጣ ከማን ጋር መደራደር እንዳለባት ታውቃለች ብለዋል፡፡
ከጎርጎሳውያኑ 1991 ጀምሮ ላለፉት 34 ዓመታት የሶማሊያ ራስገዝ ግዛት ሆና የቆየችው ሶማሊላንድ የፕሬዝዳት ትራምፕ ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ የአገርነት እውቅናውን እየተጠባበቀች ነው፡፡
ማሕደረ ዜና፣ የኢትዮ-ሶማሊያ ወዳጅነት ካንጀት ወይስ ካንገት?
ታዲያ ሶማሊያ ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ ለማስተዳደርና ለመጠቀም የወጠነችውን የሶማሊላነድ ግዛቱን ወደብ ክፉኛ የተቃወመችው ሶማሊያ አሁን ወደቦቹን ለምን ለአሜሪካ ለመስጠት ወደደች የተባሉት የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናው ተንታኝ አብዱራሃማን ሰይድ፤ “ወደቡ በኪራይም ይሁን በሌላ አንዴ በኢትዮጵያ ቁጥጥር ስር ከገባ ኢትዮጵያ ላትወጣ ስለምትችል አከባቢውንም ወደ ኢትዮጵያ ግዛት እንዳትጠቀልል ነው የሶማሊያ ትልቁ ስጋት፡፡ አሜሪካ ግን እንደ ካታር እና ጅቡቲ ወታደራዊ ካምፕ ያለ የቀጣናውን ደህንነት ብቻ የሚቆጣጠሩበት ነው ሊሆን የሚችለው በማለት” ሶማሊያ ለምን የኢትዮጵያን ተቃውማ ለአሜሪካ ለመስጠት እንደወደደች አብራርተው አስረድተዋል፡፡
የአሜሪካ የሶማሊላንድ እና ፑንትላንድ ግዛቶች ወደብ እንድታስተዳድር መጠየቅ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ያጠናከሩት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እና የወደብ ጥያቄ ላይ የሚኖረውስ አንድምታ ምን ይሆን? አቶ አብዱራሃምን ይህን ብለዋል፡፡ “የወደብ ባለቤት አገራት ኢትዮጵያ ወደብ እንድታገኝ ሳይሆን የወደብ አገልግሎት እንድታገኝ ስለሆነና ጥቁሙም ለሁሉም ስለሚሆን በዚህ ላይ ጉዳት የለውም” በማለት ነው አስተያየታቸውን የሰጡት፡፡
ሥዩም ጌቱ
እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሠ