ሶማሊላንድ ከሶማሊያ መነጠሏን ያወጀችበት 34ኛ ዓመት
ሰኞ፣ ግንቦት 11 2017ሶማሊላንድ ከሶማሊያ መነጠሏን ያወጀችበት 34ኛ ዓመት
ሶማሊላንድ ከሶማሊያ መነጠሏን ያወጀችበትና ራሷን እንደ ነጻ ሀገር የቆጠረችበት 34ኛውን "ብሔራዊ የነፃነት ቀን" ትናንት እሑድ ሀርጌሳ ላይ አክብራለች። ሶማሊያ የሉዓላዊ ግዛቷ አንድ አካል አድርጋ የምታያት ሶማሊላንድ፣ በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ ልዩ ልዩ ወታደራዊ ትዕይንቶችን አቅርባለች። በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ እ.ኤ.አ. ጥር 2024 የቀድሞው የሶማሊላንድ አስተዳደር ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የተፈራረመውና ለኢትዮጵያ የባሕር በር ያስገኛል የተባለው የመግባቢያ ስምምነት የት ደረሰ? ብለን ጠይቀናል።
"ሶማሌላንድ እና ኢትዮጵያ ስልታዊ አጋሮች ናቸው" ያሉ አንድ የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሥልጣን፣ አዲሱ አስተዳደር የመግባቢያ ስምምነቱን "ሊመለከተው አልቻለም" በማለት "ትክክለኛ" ያሉት ጊዜ ሲመጣ ከኢትዮጵያ ጋር "ወደፊት የምንጓዝባቸውን መንገዶች ለመመልከት ደስተኞች እንሆናለን" ሲሉ ተናግረዋል።
እንደ ሀገር ከየትኛውም ዓለም አቀፍ ተቋምም ይሁን ሀገራት እውቅና ያላገችው ሶማሊላንድ እ.ኤ.አ. ግንቦት 18 ቀን 1991 ከሶማሊያ በመነጠል ነጻ ሀገር መሆኗን ያወጀችበትን 34ኛ ዓመት "ብሔራዊ የነፃነት ቀን" ትናንት አክብራለች። ምንም እንኳን ሶማልያ የግዛቷ አንድ አካል አድርጋ የምትቆጥራት ቢሆንም። የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ እና አለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር ውስጥ ሦስተኛ ሰው የሆኑት ዋና ዳይሬክተር ሞሃመድ አብዱራህማን ይህንኑ ሥነ-ሥርዓት በተመለከተ ለዶቼ ቬለ ተከታዩን ብለዋል።ሶማሊላንድ የሥልጣን ርክክብ አደረገች
"የዘንድሮው ክብረ በዓል በጣም ጉልህ ነው። ከምርጫ ማግስት የሚከበር በመሆኑ፣ የሶማሌላንድ ሕዝቦች አንድነታቸውን፣ ብቁ መሆናቸውን፣ እውቅና ሊሰጣቸው እንደሚገባ፣ ጉዳያቸው መደመጥ ያለበት መሆኑን፣ በቀጣናው በጎ ኃይል መሆኗን እንዲሁም አለመረጋጋትን፣ ደህንነትን ማጣትን ሳይሆን ለመረጋጋት፣ ለዴሞክራሲ ሥርዐት ግንባታ እና በጎ አስተዳደር አስተዋፅዖ የምታደርግ መሆኑን የሶማሊላንድ ሕዝብ በድጋሚ ለአለም ያሳዩበት ውጤት በመሆኑ ነው"።
የመግባቢያ ስምምነቱ ጉዳይ ምን ላይ ደረሰ?
የኢትዮጵያ መንግሥት ከአንድ አመት ከአራት ወር በፊት ከሶማሊላንድ ጋር የባሕር በርን ለንግድና ለወታደራዊ አገልግሎት መጠቀም የሚያስችል የተባለለት የመግባቢያ ስምምነት ፈርሞ ነበር። ጉዳዩ የት ደረሰ ብለን እኒህን የሶማሊላንድ ባለሥልጣን እዚህ ሀርጌሳ ጠይቀናቸዋል። "ሶማሊላንድ እና ኢትዮጵያ ስልታዊ - ስትራቴጅካዊ አጋሮች፣ ጎረቤቶች መሆናቸውን እና ከኢትዮጵያ ጋር በጣም የጠበቀ ወዳጅነት እንዳለን ልብ ሊባል ይገባል። ብዙ ስምምነቶች እያደረግን ነው፣ ከዚህ በፊትም ብዙ ስምምነቶች ነበሩን።ሶማሊያ ለአሜሪካ ለመስጠት ያቀደችው ወደቦች እና አንድምታው
በሁሉም አቅጣጫ አጋር የምንሆንባቸውን መንገዶች መመልከታችንን እንቀጥላለን። እናም አዲሱ አስተዳደር ኢትዮጵያን ይጎበኛል። ልዑካንም ይልኩልናል። የሚለያየን ጉዳይ የሌለን ወንድማማች ሀገር ነን"። ባለሥልጣኑ "ትክክለኛ" ያሉት ጊዜ መቼ እንደሆነ ባይጠቅሱትም ግን ጉዜው ሲመጣ "ምናልባት አብረን [ከኢትዮጵያ] ወደፊት የምንጓዝባቸውን መንገዶች ለመመልከት ደስተኞች እንሆናለን"። ብለዋል።
"እ.ኤ.አ. በጥር 2024 በቀድሞው አስተዳደር [የሶማሊላንድ] የተፈረመውን የመግባቢያ ስምምነትን በተመለከተ መንግሥታችን ሊመለከተው አልቻለም። ግን ትክክለኛው ጊዜ ሲመጣ ምናልባት አብረን ወደፊት የምንጓዝባቸውን መንገዶች ለመመልከት ደስተኞች እንሆናለን። በዚህ ረገድ ግን እኛን የሚያገናኘን ከመግባቢያ ስምምነቱ እራሱ ይልቃል። እጅግ በጣም ታሪካዊ ስልታዊ- ስትራቴጂካዊ ግንኙነት አለን።
ኢትዮጵያ ሶማሌላንድን በጣም የቅርብ ወንድም ጎረቤት አድርጋ ትቆጥራለች። እኛም እንደዚያው ነው የምንቆጥራት። ለዚህም ነው አሁን ልዑካን አሉን። የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮ እዚህ አለን። በተጨማሪም ሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትም አለን"።የራስ ገዝዋ ሶማሊላንድ የፕሬዝዳንት ሥልጣን ርክክብ ድባብ ምን ይመስል ነበር?
የሶማሊላንድ እውቅና የማግኘት መሻት ቀጥሏል
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ለከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት እና ውዝግብ የተዳረጉበት ጉዳይ በቱርክ አሸማጋይነት መርገቡ እና ያንን ተከትሎ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች አዲስ አበባ እና ሞቃዲሾን መጎብኘታቸው ይታወሳል። ስድስት ሰላማዊ ምርጫዎችን አከናውና ሰላማዊ የስልጣን ርክክብ በማድረግ በዚህ የአፍሪካ ቀንድ ምሳሌ ነኝ የምትለው ሶማሊላንድ አሁንም እውቅና የማግኘት መሻቷን እንደምትገፋበት የውጭ ጉዳይ እና አለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር ዋና ዳይሬክተሩ ሞሃመድ አብዱራህማን ገልፀዋል።
"በመጀመሪያ ደረጃ ሁሉም ሰው የሶማሊላንድን ታሪክ እንደሚያውቅ፣ እና ደግሞ ማንም እውቅና አልሰጠም ማለት ሶማሌላንድ የለም ማለት እንዳልሆነ ሁሉም ልብ ሊል ይገባል። ሶማሌላንድ ከቀጣናው፣ ከአህጉሪቱ አልፎ ተርፎም ከበርካታ አገሮች ጋር በጥምረት የኖረ ኃይል ነው። በሁሉም ማዕዘን ለሚገኙ ዓለም አቀፍ አጋሮች፣ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ፣ ሶማሊላንዳውያን ወደ ዓለም የሚልኳቸውን መልካም ታሪኮች በቅርበት እንዲመለከቱ እና እንዲታዘቡ፣ እንዲሁም በመጨረሻም ሶማሊላንድ ማግኘት የሚገባትን ዲፕሎማሲያዊ እውቅና ለመስጠት ድፍረት እንዲያገኝ እንጠይቃለን"።የኢትዮጵያ እና የሶማሊላንድ ግንኙነት ዕድገት
ስድስተኛው የወቅቱ የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት አብዲራሕማን ሞሐመድ አብዱላሂ ከወራት በፊት በሰላም ሥልጣን ሲረከቡ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው የነበሩት በሶማሊያ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር "የሶማሌላንድ ሕዝብ ለዚህ ቀጣና ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ እና ለዓለም የእውነተኛ ዲሞክራሲ ሥርዐት ምሳሌ ሰጥቷል" በማለት ሀገራቸው ለወደፊትም ከጎናቸው እንደምትሆን ገልፀው ነበር።
ሰለሞን ሙጬ
ሸዋዬ ለገሠ
አዜብ ታደሰ