ስደተኞችን በባህር ጉዞ ከመስጠም ለሚታደጉ ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፍ እንዲቆም መወሰኑ
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 8 2017
በሜዴትራንያን ባህር በኩል በአነስተኛ ጀልባዎች ወደ አውሮጳ ለመግባት የሚሞክሩ ለአደጋ የተጋለጡ ስደተኞችን የሚታደጉ መርከቦች ድርጅቶች ከጀርመን መንግሥት በየዓመቱ ድጎማ ያገኙ ነበር። ይሁንና ይህ የገንዘብ ድጋፍ በአዲሱ የጀርመን መንግሥት ሊቋረጥ ነው። የዶቼቬለው ኦሊቨር ፒፐር እንደዘገበው ይህ በዚህ በጎ አድራጎት ተግባር የተሰማሩ ድርጅቶችን አስቆጥቷል ፤አሳዝኗል። የፕሮቴስታንት ቤክርስቲያን ጳጳስ ክርስቲያን ሽቴብላይን" «አንድም ሰው እንዲሰጥም መተው የለበትም።»ሲሉ ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል። Sea Eye የተባለው ስደተኞችን ከሜዴትራንያን ባህር የሚታደገው ግብረ ሰናይ ድርጅት ሊቀመንበር ጎርደን ኢዝለር እርዳታው መቆሙን ገዳይ ምልክት ብለውታል። በጀርመን ፓርላማ የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ ቡድን ሊቀ መንበር ብሪታ ሀስልማንም እርምጃውን ተችተዋል። ፖለቲከኛዋ እንዳሉት ጥምሩ መንግሥት ድጎማውን ሊያቋርጥ መወሰኑ በሜዴትራንያን ባህር የሚደርሰውን ሰብዓዊ ቀውስ እና የሰዎች ስቃይ እጅግ ማባባሱ እንደማይቀር መገመት ይቻላል ።
የጀርመን ክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረትና የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ ጥምር መንግስት ስደተኞችን ከሜዴትራንይ ባህር ላይ ለሚታደጉ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች የፋይናንስ ድጋፍ ሊያቋርጥ መሆኑ ጀርመን ውስጥ ተቃውሞ አስነስቷል። በመሰል የመታደግ ተግባር የተሰማሩ Sea-Eye, SOS Humanity, SOS Méditerranée, RESQSHIP, እና ሴንት ኤጊድዮን የመሳሰሉ ድርጅቶች በጎርጎሮሳዊው 2023 እና በ2024 ከጀርመን መንግስት በአጠቃላይ የ 2ሚሊዮን ዩሮ እርዳታ ተቀብለዋል። በጎርጎሮሳዊው 2025 ዓም ደግሞ 900 ሺህ ዩሮ የሚጠጋ ድጋፍ አግኝተዋል። የጀርመን ፌደራል መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዚህ በኋላ ግን ምንም ዓይነት ድጋፍ የመስጠት እቅድ የለውም።
የአዲሱ መንግሥት የመርኅ ለውጥ
አዲሱ የፌደራል ጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር »ዮሀን ቫደፑል ጀርመን ለሰብዓዊነት የምትቆም ሀገር መሆንዋ እንደሚታወቅ አጽንኦት ሰጥተው ይናገራሉ። ሆኖም ብዙውን ጊዜ ሰላማዊ ሰዎችን ከባህር ላይ አደጋ ለመጠበቅ ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ የሚከናወነውን ስራ በገንዘብ መደገፍ የመሥሪያ ቤታችን ስራ መሆን የለበትም ሲሉ ይከራከራሉ። የርሳቸው አቋም የመስሪያ ቤታቸው ድጋፍ በሌላ አቅጣጫ መሆን ይገባዋል የሚል ነው። «በኔ እምነት ሰዎችን ከባህር ላይ አደጋ ለመከላከል ገንዘብ መመደብ የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ተግባር አይደለም። በዚህ ረገድ ፖሊሲያችንን ቀይረናል። የኔ ፖሊሲ እነዚህን መሰል የስደተኞች እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ ለማረጋገጥ ዲፕሎማሲያዊ መንገዶችን መጠቀም ነው ዓላማው።»
የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንደሚሉት ጀርመን፣ የመሰደድ ፍላጎቱ ከፍተኛ በሆነበት ሱዳንንና ደቡብ ሱዳንን በመሳሰሉ ሀገራት እንቅስቃሴዋን ማጠናከር አለበት። የመስሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ክርስቲያን ቫግነር ደግሞ ሰዎችን መታደጉ ይቁም አይደለም የምንለው ይላሉ። «አስፈላጊ የሆነው ሰዎችን ከባህር ላይ አደጋ መታደጉ ስለመቀጠል አለመቀጠሉ ምንም አልተባለም። ዋናው ጥያቄ ይህ ተግባር በመንግሥት የገንዘብ ድጋፍ መሆን አለበት ወይ የሚለው ነው።» ብለዋል። በዚህ ዓመት ብቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በሜዴትራንያን ሲጎዙ ሰጥመው ሞተዋል።
በሜዴትራንያን ባህር ላይ የሚደረግ ጉዞ ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ የቅርብ ጊዜ መረጃዎች ያሳያሉ። ዓለም አቀፉ የፍልሰት ጉዳዮች ተከታታይ ድርጅት በምህጻሩ IOM እንዳለው ከዚህ ዓመት ጥር ወር አንስቶ በዚህ የጉዞ መስመር 748 ሰዎች መሞታቸው አለያም የደረሱበት አለመታወቁን መዝግቧል። በሜዴትራንያን ባህር በኩል ወደ አውሮፓ ለመሻገር ብዙውን ጊዜ በለንቋሳ ጀልባዎች የሚደረግ ጉዞ ከዓለም የበርካታ ስደተኞች ሕይወት የሚጠፋበት የስደት መስመር ነው። በድርጅቱ መረጃ መሠረት ከጎርጎሮሳዊው 2014 ዓም አንስቶ በዚህ አቅጣጫ በተካሄደ ስደት ከ32 ሺህ በላይ ሰዎች ወይ ሞተዋል አለያም የደረሱበት አልታወቀም ። በጉዳዩ ላይ ለዶቼቬለ ቃለ ምልልስ የሰጡት SOS Humanity የተባለው ግብረ ሰናይ ድርጅት የፖለቲካ ጉዳዮች ቃል አቀባይ ማሪ ሚሼል የጀርመን መንግሥትን ውሳኔ ግልጽ አሳዛኝና አሳፋሪ ውሳኔ ሲሉ ኮንነውታል።
«ስለዚህ "በተለይ አሁን ያለው የጀርመን መንግስት ሰብአዊ እርዳታን እንደሚጠብቅ እና ሰብአዊ ርምጃዎችን እንደሚከታተል በጥምረት ስምምነቱ ላይ ማስቀመጡን ስናስብ ይህ በማዕከላዊ ሜዴትራንያን ሰብዓዊ መብቶችን በግልጽ ያዋረደ አሳዛኝ ውሳኔ ነው ።ሁለት ሚሊዮን ዩሮው ጥሩ የሚባል ድጋፍና ለሚሳደዱ ሰዎች ትንሽም ቢሆን ትብብርን የሚፈነጥቅ ተስፋ ነበር።
የስደተኞች ሕይወትን የመታደግ ዘመቻዎችን በገንዘብ መደገፍ አስቸጋሪ እየሆነ ነው
መቀመጫውን ቤርሊን ያደረገው የእርዳታ ድርጅቱ SOS Humanity በሜዴትራንያን ባህር ላይ Humanity 1 የተባለውን መርከቡን በማሰማራት ለአስር ዓመታት በዚሁ የስደት መስመር ሲጓዙ ሕይወታቸው ለአደጋ የተጋለጡ ስደተኞችን የመታደግ ዘመቻ ሲያካሂድ ቆይቷል። በድርጅቱ መረጃ መሠረት በዚህ ጊዜ ውስጥ ድርጅቱ ባካሄዳቸው በነዚህ ዘመቻዎችም ከ38 ሺህ በላይ ስደተኞችን ሕይወት ታድጓል።
እናም ሚሼል እንዳሉት የጀርመን ፉደራል መንግስት የገንዘብ ድጋፍ መቋረጥ ለ SOS Humanity የፋይናንስ ችግር የሚያስከትል እርምጃ ነው። "በእኛ ትንበያ መሰረት የሕይወት አድን መርከባችን ሂውማንቲ 1 በገንዘቡ ሁለት የማዳኛ ስራዎችን ልንደግፍ እንችል ነበር. ይህ ማለት አሁን በእርግጥ በልገሳ ላይ ክፍተት አለ።ነገር ግን ከህብረተሰቡ መካከል እያገኘን ባለው ሰፊ ማህበራዊ ትብብር እና ድጋፍ ላይ በጣም ተስፋ እናደርጋለን."
ባለፈው ግንቦት ማሪ ሚሼል እንደ ሰብዓዊ መብት ታዛቢ ከHumanity 1 እና SOS Humanity መርከቦች ጋር ተጉዘው ነበር። በወቅቱም መርከቦቹ በባህር ላይ ችግር ከገጠማቸው ጀልባዎች 297 ስደተኞችን መታደግ ችለው ነበር። ስደተኞቹን ከታደጉ በኋላም ላስፔዝያ ራቬና እና ባሪ ወደተባሉት የጣሊያን ወደቦች ሊወስዷቸው ችለዋል። ያም ሆኖ በሜዴትራንያን ባህር ላይ የሚከናወነው ይህን መሰሉ የሰዎችን ሕይወት የመታደጉ ስራ እጅግ አስቸጋሪ እየሆነ ነው። ይህም የጀርመን መንግስት ከዚህ ቀደም ይሰጥ የነበረውን እርዳታ ለመቀነስ በመወሰኑ ብቻ ሳይሆን አሁን በአውሮፓ በተፈጠረው የፖለቲካ ሁኔታ ምክንያትም ጭምር መሆኑን ሚሼል ያስረዳሉ።
"ባለፈው አመት ከጊዜ ወደ ጊዜ ያስተዋልነው ከለላ በሚሹ ሰዎች ላይ ለሰው ልጅ የማይገባ ተግባር መፈጸምን ነው። እነዚህ ሰዎች መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶቻቸውን ተነፍገዋል። በሜዴትራንያን ባህር ላይ እንዲሞቱ ብቻቸውን ተጥለዋል። ይህ በሰው ልጅ ላይ ሊፈጸም የማይገባ ተግባር፣ ሰብዓዊ እርዳታ ወደሚያደርጉ ፣ሰላማዊ ሰዎች ከባህር ላይ አደጋ ወደሚታደጉ ድርጅቶች ተሸጋግሯል። »
የአውሮጳ ኅብረት በሜዴትራንያን ባህር በኩል ወደ አውሮፓ ለመሻገር የሚሞክሩ ስደተኞችን ቁጥር ለመቀነስ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ የሚያወጡ ስምምነቶችን በጎርጎሮሳዊው 2017 ከሊብያ በ2023 ደግሞ ከቱኒዝያ ጋር ተፈራርሟል።ይሁን እንጂ በስምምነቶቹ በዚህ መስመር የሚካሄድ ስደትን እንደተፈለገው መቀነስ አላስቻሉም።
በሜዴትራንያን ባህር ከመስጠም ተርፈው በታደጓቸው መርከቦች ላይ መሳፈር ከቻሉት ስደተኞች አብዛኛዎቹ ሊቢያ ሳሉ ሰውነታቸው ላይ የደረሱባቸው በደሎች ምልክቶች ይታያሉ። ከሚፈጸምባቸው በደሎች ውስጥ በላያቸው ላይ ቀዝቃዛ ውሐ መቸለስ በእንጨትና በብረት ዱላዎች እንዲሁም በፕላሲትክ ውሐ ማጠጫዎች መደብደብ እና ሰውነታቸው ላይ ሽጉጥ መተኮስ እና አስገድዶ መድፈር ይገኙበታል። ከዚህ በደል አምልጠው በደካማ ጀልባዎች ወደ አውሮጳ ጉዙ የሚጀምሩ ስደተኞች መንገድ ላይ ከሚገጥማቸው የመስጠም አደጋ ከሚታደጓቸው የግብረ ሰናይ ድርጅቶች መርከቦች በተለይ የጀርመኖቹ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ያገኙት የነበረው ድጋፍ እንዲቋረጥ መወሰኑ ብዙዎችን አሳስቧል። ድርጅቶቹ ደጋግመው እንዳሳሰቡት እርዳታውን ማቋረጥ በስደተኞቹ ላይ በሜዴትራንያን ባህር ላይ ሞት እንደመፍረድ የሚቆጠር ነው።
ኦሊቨር ፒፐር / ኂሩት መለሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ