የቆዳ በሽታ ከሆኑት አንዱ ስለሆነው ቡግንጅ ምን ያውቃሉ?
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 6 2017
ቡግንጅ ምንድነው?
ቡግንጅ በህክምና አጠራሩ ፉሩንክል ወይም ቦይል የሚባል ሲሆን ቆዳ ላይ የሚወጣ በጣም የሚያምም፤ አቀይ እባጭ የሚያስከትል የቆዳ ህመም ነው። ቡግንጅ በየትኛውም የዕድሜ ክልል ባሉ ወገኖች ላይ ጾታ ሳይለይ የሚያጋጥም የቆዳ በሽታ ነው። በአንዳንዶች ላይ ከበድ ያለ የህመም ስቃይ የሚያስከትለው የቆዳ በሽታ ቡግንጅ በባክቴሪያ አማካኝነት እንደሚመጣ የቆዳ ህክምና ባለሙያዎች ይገልጻሉ። ቡግንጅን የሚያስከትለው ተሐዋሲ በሳይንሳዊ ስሙ ስፊሎኮኩስ አውሪየስ ተብሎ ይጠራል። በቆሰለ ቆዳ፣ ወይም በተፋቀ ቆዳ ወይም እንዲሁ ባገኘው ቀዳዳ በቀላሉ ወደውስጥ መግባት የሚችል ተሀዋሲ ነው።
ምልክቱና የሚወጣበት የሰውነት ክፍል
ቡግንጅ የሚወጣበት የሰውነት ክፍል ላይ ጠጠር ያለ እና የቀላ እብጠት በማስከተል በውስጡ ፈሳሽ ይኖርበታል። ቡግንጁ የወጣበት አካባቢ ከፍተኛ ህመም የሚኖረው ሲሆን ለመንካት ጥንቃቄ ይፈልጋል። ቡግንጅ በየትኛውም የሰውነት ክፍል ላይ የሚወጣ የቆዳ በሽታ ነው። ሆኖም ግን በተለይ የቆዳ ቀዳዳዎች ባሉበት የሰውነት አካባቢ፤ እንደፊት፤ አንገት፤ ብብት፣ ብሽሽት እና መቀመጫ ላይ አዘውትሮ እንደሚወጣ የቆዳና እና የአባለዘር ህክምና ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር አኒሳ ይናገራሉ።
ቡግንጅ ይተላለፋል?
ቡግንጅ በቅርበት በሚደረግ ንክኪ ከሰው ወደ ሰው ሊተላለፍ የሚችል የቆዳ በሽታ እንደሆነነው የቆዳና እና የአባለዘር ህክምና ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር አኒሳ በፈቃዱ የገለጹልን። በተለይ ልጆች ለዚህ የተጋለጡ መሆናቸውንም አመልክተዋል። በተለይ በሽታ የመቋቋም አቅምን የሚያዳክሙ ህመሞች ያሉባቸው ወገኖች ይህ የቆዳ በሽታ ሊያጠቃቸው እንደሚችልም አስረድተዋል። ቡግንጅ ደጋግሞ ቆዳቸው ላይ የሚወጣ ወገኖች የግል ንጽሕናን ከመጠበቅ በተጨማሪ በባህላዊ መንገድ ለማከም ከሚደረጉ ሙከራዎች እንዲታቀቡ ይመክራሉ። ምክንያቱም በአግባቡ ካልታከመ ችግሩ ሊወሳሰብ እንደሚችል ነው ያሳሰቡት።
ህክምናው
ቡግንጅ ፊት ላይ ከወጣ ወደ ሀኪም መሄድ የግድ መሆኑን የሚጠቁሙ የህክምና መረጃዎች አሉ። በተለይም አብጦና አካባቢው ቀልቶ ትኩሳት የሚያስከትል ከሆነ ወደ ሀኪም ቤት መሄድ ይመከራል። ዶክተር አኒሳም እንዲሁ አንዳንዴ ከፍተኛ ህመም የሚያስከትል በሚሆንበት ጊዜ ወደ ሀኪም በመሄድ ተገቢውን ህክምና ማግኘት እንደሚገባ ነው የተናገሩት። በተለይ በሽታ የመቋቋም አቅም ከመዳከም ጋር ተያይዞ ቡግንጅ ደጋግሞ የሚወጣ ከሆነ ወደ ቆዳ ሀኪም በመሄድ ለዚሁ ተብሎ የሚታዘዙ ፀረ ተሐዋሲ መድኃኒቶች በሚገባ ተከታትሎ ጨርሶ መውሰድ እንደሚገባ ነው ያመለከቱት።
የቆዳና እና የአባለዘር ህክምና ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር አኒሳ በፈቃዱ ቡግንጅን አስመልክቶ ከአድማጭ ለተላከልን ጥያቄ የሰጡትን ዝርዝር ሙያዊ ማብራሪያ ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ።
ሸዋዬ ለገሠ
ነጋሽ መሐመድ