ሱዳን፦ ከመከራ ወደ ሌላ መከራ
ቅዳሜ፣ ጳጉሜን 1 2017ሱዳን ውስጥ ከሰሞኑ በደረሰ ብርቱ የመሬት መንሸራተት ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል ። እስከ ሐሙስ ድረስ በነበረው ቆጠራ ምዕራብ ሱዳን የዳርፉር ግዛት ውስጥ በምትገኘው ታራሲን መንደር ከሟቾች መካከል አስክሬናቸው የተገኘው የ370 ሰዎች ነው ። በጦርነት በምትታመሰው የዳርፉር ግዛት ተራራማ በሆነው ጀበል ማራ ውስጥ በምትገኘው ታራሲን መንደር ኃይለኛ ዝናብ ያስከተለው የመሬት መንሸራተት እካባቢውን እንዳልነበረ አድርጎታል ።
በታራሲን መንደር በሕይወት የተረፈው አንደ ሰው ብቻ ነው
አስደንጋጩ አደጋ በደረሰበት አካባቢ በአብዛኛው የጦርነት ተፈናቃይ ሱዳናውያን ይገኙበት ነበር ተብሏል ። የመሬት መንሸራተቱ መንደሪቱን እንዳለ መቅበሩን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል ።
በታራሲን መንደር በሕይወት የተረፈው አንደ ሰው ብቻ መሆኑን አካባቢውን ከረዥም ጊዜ አንስቶ የተቆጣጠረው የሱዳን ነጻነት ንቅናቄ/ጦር (SLM/A) አማጺ ቡድን ይፋ አድርጓል ። የሱዳን ነጻነት ንቅናቄ/ ጦር በተቆጣጠረው አካባቢ የሲቪል ባለሥልጣን የሆኑት ሙጂብ አል-ራህማን አል-ዙባይር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አስቸኳይ ርብርብ እንዲያደርጉ ተማጽነዋል ።
«ለዓለም አቀፋዊ እና አካባቢያዊ ተቋማት ጥሪ አቅርበናል ። በአገሪቱ ውስጥ እና ከውች ለሚገኙ የጉዳቱ ሰለቦች ቤተሰቦች ሐዘናችንን እንገልጣለን ።»
ባለፈው ሳምንት እሁድ ዳርፉር ታራሲን መንደር ውስጥ የተከሰተው የመሬት መንሸራተት ከመድረሱ በፊት በአካባቢው ብርቱ ዝናም ይወርድ እንደነበር ተዘግቧል ። የእሁዱ የመሬት መንሸራተት በሱዳን የተፈጥሮ አደጋ የቅርብ ጊዜያት ታሪክ አስከፊው መሆኑ ተገልጧል ።
የርዳታ ርብርብ እንዲደረግ ጥሪ ተላልፏል
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ቃል አቀባይ ሽቴፋን ዱጃሪች ዳርፉር ሱዳን ውስጥ በመሬት መንሸራተት የደረሰው ጉዳት መጠነ ሰፊ መሆኑን በመግለጥ ለርዳታ መንቀሳቀሳቸውን ተናግረዋል ።
«ሱዳን ውስጥ የሚገኙት ምክትል የሰብአዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ሉካ ሬንዳ በመሬት መንሸራተት ለተጎዱት ድጋፍ ለማድረስ እኛ እና አጋሮቻችን እየተንቀሳቀስን መሆኑን ተናግረዋል። OCHAም እንዲሁ ምንም እንኳን ጀበል ማራ እጅግ ኋላቀር የሱዳን ግዛት ቢሆንም ከተባባሪዎቻችን ጋር በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ ለማቅረብ እየሠራ ነው። ከሰሜን ዳርፉር ግዛት ያሉትን ጨምሮ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች በሚካሄደው ግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎችንም እያስተናገደ ነው። የሰብአዊ ርዳታ ተባባሪዎችን ኃይለኛ ዝናብ ሱዳን ውስጥ በያለበት ያስከተለውን መጠነ ሰፊ ጉዳት ያውቃሉ ።»
የርዳታ ሠራተኞች አህዮችን እንደመጓጓዣ እየተጠቀሙ ነው
በሱዳኑ አደጋ ከጠፋው ሕይወት ባሻገር፤ መሠረተ ልማቶች ላይ ብርቱ ጉዳት በመድረሱም የርዳታ ሠራተኞች አህዮችን እንደመጓጓዣ እየተጠቀሙ መሆኑም ተዘግቧል ። ለእሁዱ የመሬት መንሸራተት ሰበብ መሆኑ የሚነገርለት ዝናም እና ጎርፍ በታራሲን መንደር እንደቀጠለ ተጠቅሷል ። ያም በመሆኑ ለመጓጓዣ ከአህዮች ጭነቶች ውጪ አማራጭ አልተገኘም ።
ከማራ ተራራማ ሥፍራዊች ከብርቱው ዝናም እና ጎርፍ በኋላ መሬቱ ከተራራማ ሥፍራዎች ተገምሶ ሲደረመስ ማጥ እና ኮረት እንደ ጎርፍ የታርሲን መንደርን አጥለቅልቋል ። ይህ የተፈጥሮ አደጋc ላለፉት ሦስት ዐሥርተ ዓመታት በእርስ በእርስ ጦርነት በምትታመሰው ሱዳን የርዳታ ጥገኛ በሆኑ ነዋሪዎች ላይ የሰብአዊ ቀውሱን ይበልጥ አባብሶታል ።
ሱዳን ውስጥ ቢያንስ በ21 አካባቢዎች ብርቱ ዝናም እና ጎርፍ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ጉዳት ማድረሱ ተዘግቧል ። ምናልባትም መሰክረም ወር ላይ ያልተጠበቀ ርጥበታማ የዐየር ንብረት ሲከሰት ወረርሺኞች እንዳይቀሰቀሱም ባለሞያዎች ከወዲሁ ፍራቻቸውን ገልጠዋል ። ሱዳን፦ ከመከራ ወደ ሌላ መከራ ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
እሸቴ በቀለ