ሰሜን እና ደቡብ ወሎ አዲስ ያገረሸው ግጭት እና የአርሶአደሮች ስጋት
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 8 2017በአማራ ክልል በመንግስትና በፋኖ ሀይሎች መካከል እንደ አዲስ በክረምቱ መግቢያ ጊዜ ያገረሸዉ ጦርነት የእርሻ ስራችን ተረጋግተን እንዳንሰራ አድርጎናል አሉ አርሶደሮች
አርሶደሮቹ ከዘር ወቅት እስከ አጨዳ ባለዉ ጊዜ ጦርነቱ እየፈጠረብን ባለዉ ተፅኖ ተገቢዉን ምርት ማግኘት አልቻልንም ብለዋል
የአማራ ገበሬዎች ስሞታ
የክረምት ዝናብን ጠብቆ አርሶና ከስቦ የሚኖረው አርሶ አደር በአማራ ክልል በመንግስትና በፋኖ ሀይሎች መካከል በሚደረገው ጦርነት ዘንድሮም ለ2ኛ ጊዜ የክረምት የእርሻ ሥራቸውን ለመከወን እንደተቸገሩ ገበሬዎቹ ይናገራሉ፡፡ በደቡብ ወሎና ሰሜን ወሎ ዞን ነዋሪ የሆኑ አርሶ አደሮችም የከባድ መሳሪያ ተኩስና ጦርነቱ የእርሻ ሥራችንን በትክክለኛው ጊዜ ለመከወን ከልክሎናል ይላሉ፡፡
‹‹ከባድ መሳሪያ ሲያስወነጭፉ ክረምት ነው አሁን ነው መዝራት የምንችለው ግን ምንም መስራት አልቻልንም፤ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ነው ያለነው ዝናቡ ካለፈ ምንም ማድረግ አንችልም፡፡ ገበሬው ማረስ አልቻለም፤ ምን እንደምናደርግ ጨንቆናል፤ ወደ ማን አቤት እንበል፡፡››
ደቡብ ወሎ ዞን 380 ሺህ ህዝብ የምግብ ድጋፍ ይፈልጋል ተባለ
በጦርነቱ አርሶደሮች ለሞት ተዳርገዋል
ሁለት አመታትን የተሸጋገረው በአማራ ክልል እየተካሄደ የሚገኘው ጦርነት በእርሻ ቦታ ላይ ላሉ አርሶ አደሮች ሞቱ ምክንያት አንደሆነም ነው አርሶ አደሮቹ የሚናገሩት፡፡
‹‹ ገበሬው ዘር እንኳን መዝራት አይችልም፤ ጨንቆታል፤ ጦርነቱ ሰብሉ ደህና በቅሎ እያለ ያጠፋል፤ አልሆነ ቦታ ላይ ከባድ መሳሪያ ይወነጨፍበታል፤ ገበሬው እዚያው እርሻ ቦታ ላይ እያለ እያጨደ ይሞታል፡፡››
በክረምቱ ገበሬው የእርሻ ሥራውን ለመከወን ብቻም ሳይሆን የተቸገረው የቤት እንስሶች ጭምር ሜዳው ወጥተው መዋል ያልቻሉበት ሁኔታ ነው ያለው በማለት አርሶ አደሮቹ ይገልፃሉ፡፡
‹‹አስቸጋሪ ነው እንኳን ለመዝራት ለማረስ ቀርቶ ለመውጣትም አስቸጋሪ ነው፤ እንስሳት መውጣት አይችሉም እኛም መውጣት አልቻልንም››
ወቅታዊ ሁኔታዎች ያዳከሙት የላሊበላ የቱሪዝም እንቅስቃሴ
የወጣት ገበሬዎች መዋከብ
በተለይም ቤተሰቦቻቸውን በእርሻ ሥራ ለማገስ የሚወጡ ወጣቶች በሁለቱም ሀይሎች ማዋከብ እንደሚደርስባቸው ይናገራሉ፡፡
‹‹አሁን አዝመራ እንደፈለግን መሰብሰብ አልቻልም፣ ይሄኛው ሲመጣ ይሄኛው ይመጣል፡፡ ወጣት ካዩ መከላከያዎቹ ፋኖ ነህ ይላሉ፤ ፋኖው ሲገባ መከላከያ በዚህ አለ በዚህ የለም መረጃ አምጣ እያሉ ግዴታ ያስገድዱናል፡፡›› ‹‹ መንግስት ያመጣልንን እርዳታ ነበር እሱንም አምጡ ይሉናል››፡፡
ጦርነቱ ከክረምቱ መግባት ጋር ተያይዞ እንደ አዲስ የተቀሰቀሰበት የላስታ አካባቢም ባለፉት ቀናቶች በቀጠለው ጦርነት ስራ ለመስራት መቸገራቸው ነው ኗሪዎች የሚናገሩት፡፡
‹‹ከ23 ጀምሮ አንድ ሳምንት ነበር ወደ ገጠሩ ጦርነት አሁን ይህንን 3 ቀን ቆመ ብለን ነበር፡፡ ትናንት ጠዋት መጥተው አጫጩኸውት ሄዱ፤ እየተቸገረም ቢሆን አይቀርም፤ ካለፈ አለፈ ነው፡፡ ሌላ ክረምት ይመጣል አትል፤ ክረምቱ ሳያልፍ በፍርሃት ውስጥም ቢሆን ያርሳል የሚችለውን ያደርጋል፡፡››
በኢትዮጵያ አሳሳቢው የተፈናቃዮች ይዞታ ተስፋና መፍትሄው
በቂ ግብአት ቢቀርብም ጦርነቱ አርሶደሩን እየፈተነ ነዉ
ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ መደበኛ የእርሻ ሥራውን በተገቢው መንገድ ለመከወን ተቸግሮ የቆየው የሰሜንና ደቡብ ወሎ አርሶ አደሮችም አሁን ላይ የሰላሙ ሁኔታ ባልተረጋገጠባቸው አካባቢዎች ላይ አርሶ አደሩ መቸገሩን የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አህመድ ጋሎ ይገልፃሉ፡፡
በደቡብ ወሎ የተፈናቃዮች መጠለያ የህክምና አገልግሎት ማጣት
‹‹የደላንታ ቆላማ አካባቢዎች፣ አምባሰል ደጋማ አካባቢው እንዲህ አይነት ችግር ያለባቸው አካባቢዎች ናቸው፡፡ እነሱ አካባቢዎች ላይ ግብዓት እያደረስን ነው፤ የፀጥታ ችግር ያለባቸው አካባቢዎች ላይ ያለው አሁንም ቢሆን መሰረታዊ ችግር አርሶ አደሩ እየገጠመው ነው፡፡ ይህ ደግሞ አርሶ አደሩን እያጎሳቆለው ጭምር ነው፡፡ በወቅቱ እንዳያርስ፣እንዳያጭድ፣ እንዳይወቃ፣ ወቅቱን ጠብቆ እንዳይዘራ ግጭቱን ሆን ብለው የሚቀሰቅሱት አርሶ አደሩ ሊዘራ፣ሊያጭድ ሲል ነው፡፡››
ባለፉት 2 ዓመታት ከግብዓት እና ቴክኖሎጂ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ተፈትኖ የቆየው የግብርናው ዘርፍ አሁንም በአማራ ክልል በሚካሄደው ጦርነት አርሶ አደሩ በተገቢው መንገድ የእርሻ ሥራውን ለመከወን መቸገሩ ነው የተገለፀው፡፡
ኢሳያስ ገላው
ታምራት ዲንሳ
ማንተጋፍቶት ስለሺ