ሰሜን ኢትዮጵያ እያየለ የመጣው ፖለቲካዊ ውጥረት፦ ውይይት
እሑድ፣ ሐምሌ 13 2017በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም ጦርነት የመቀስቀሱ ሥጋት እንዳጠላ በርካቶች ይናገራሉ ። ከዓመታት በፊት ትግራይ፤ አማራ እና አፋር ክልሎችን ያዳረሰው ጦርነት በብዙ መቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት አስገብሯል ። አስከፊው ጦርነት በርካቶችን ለአካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ዳርጓል፤ በንብረት ላይም ብርቱ ጥፋት አድርሷል ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሰሞኑ ባቀረቡት ማብራሪያ፦ «የፌዴራል መንግሥት ትግራይ ክልል ውስጥ ዳግም ጦርነት እንዲጀመር ፍላጎት እንደሌለው» ገልጠዋል ። ሆኖም አዝማሚያ መኖሩን በመጥቀስ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ባለሃብቶች እና ኤምባሲዎች በፍጥነት ይህንን እንቅስቃሴ እንዲያስቆሙ አሳስበዋል ።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች እና ሌሎች ልኡካን ረቡዕ ዕለት ለአንድ ቀን ወደ መቐለ ከተማ አቅንተው የዛኑ ዕለት ወደ አዲስ አበባ ተመልሰዋል። ልዑካኑ በፌደራሉ መንግሥት እና በሕወሓት መካከል ስለተፈጠረው ውጥረት ከተለያዩ የክልሉ ባለሥልጣናት እና የማኅበረሰብ አካላት ጋር ምን እንደተነጋገሩ ይፋ ባይሆንም በዝግ መወያየታቸው ተዘግቧል ።
ዐርብ ዕለት ደግሞ፦ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ አዲስ አበባ ውስጥ ከትግራይ ክልል የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች፣ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባላት፣ የተለያዩ ሲቪል ተቋማት ተወካዮች እና ምሁራን ጋር በወቅታዊ ፖለቲካዊ፣ የፀጥታ እና ኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን በማኅበራዊ የትስስር ገጻቸው ዐሳውቀዋል ።
ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ "ዕርቅ እና ሰላም" በሚል ርእስ ከትግራይ የተለያዩ የማሕበረሰብ ክፍሎች ጋር ስላደረጉት ውይይት በትግርኛ ባሰራጩት ጽሑፍ "በምክክር እንዲሁም ሰጥቶ መቀበል የሚመጣ ሰላም መሰረቱ ጽኑእ ነው" ሲሉ ገልፀዋል።
ጄኔራል ታደሰ ወረደ የሚመሩት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በአፋር ክልል ካሉ ታጣቂዎች ወደ ትግራይ ክልል ማንኛውም ትንኮሳ የሚመጣ ከሆነ ተጠያቂው የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ነው ሲል ከሰሞኑ አስጠንቅቋል ። አማራ ክልል ውስጥም የኢትዮጵያ መከላከያ ከፋኖ ጋር የሚያደርገው ውጊያ እንደቀጠለ ነው ። «በሰሜን ኢትዮጵያ እያየለ የመጣው ፖለቲካዊ ውጥረት» የዛሬው የመወያያ ርእስ ነው ።
በውይይቱ መንግሥት ተሳታፊ እንዲመድብ ለጠቅላይ ሚንሥትር ጽ/ቤት ይፋዊ የኢሜል ግብዣ ልከን ነበር፥ ውይይቱን እስካደረግንበት ጊዜ ድረስ ግን ምላሽ አላገኘንም ። የውይይቱ ተሳታፊዎች፦
-
ዶ/ር ገብረየሱስ ተክሉ፦ በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የማኅበራዊ ሳይንስ እና ሥነ ጽሑፍ ተባባሪ ፕሮፌሰር
-
አቶ አብድራህማን ሠይድ፤ የቀፍሪቃ ቀንድ ፖለቲካ ተንታኝ
-
አቶ ገለታው ዘለቀ፦ የፖለቲካ ተንታኝ
-
ጋዜጠኛ ሚሊዮን ኃይለሥላሴ በመቐለ የዶይቸ ቬለ ዘጋቢ ናቸው ።
ሙሉ ውይይቱን በድምፅ ማጫወቻው በኩል ማድመጥ ይቻላል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሠ