ሰላም የራቃቸው የኦሮሚያ አካባቢዎች ነዋሪዎች ስጋት
ሰኞ፣ መስከረም 7 2016በኦሮምያ ክልል በቀጠለው የጸጥታ መደፍረስ ክፉኛ መፈተናቸውን በክልሉ የሰላም እጦቱ በተስፋፋባቸው አከባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ተናገሩ። ነዋሪዎቹ የሰላም ጥሪ እያቀረቡ ነው።
የምስራቅ ወለጋ ኪረሙ ወረዳ ነዋሪ ከአስር በላይ ቤተሰባቸውን ሲያስተዳድሩ ከነበሩበት የኪረሙ ገጠራማ ስፍራ መተዳደሪያቸው የሆነውን ግብርና አቋርጠው ወደ ወረዳዋ ከተማ ከተሰደዱ ሁለት ዓመት አልፎ ወደ ሶስተኛው እየገሰገሰ ነው ይላሉ። እኚህ አርሶ አደር ከጥንትም ተወልደው በኖሩበት በዚህ ስፍራ በርግጥም ከአከባቢው ማህበረሰብ ጋር በትብብር እንጂ በጥላቻ እንደማይተዋወቁም ያወሳሉ፡፡ የዛሬ ሶስት ዓመታት ገደማ በአከባቢያቸው የከፋው የታጣቂዎች እንቅስቃሴ እና የፖለቲካ መዘበራረቅ ግን ከሚወዱትና መተዳደሪያቸው ከሆነው ቀዬያቸው እንዳስወጣቸውና ለእርዳታ እጃቸውን እንዲዘረጉ እንዳስገደዳቸውም ጠቁመዋል፡፡ አርሶ አደሩ አሁን የናቀፈቀን ከምኑም በላይ ሰላም ነው ባይም ናቸው፡፡ “እዚህ ያደረሰን መገፋፋቱ ነበር፡፡ ከምንም በላይ ሰላም ነው የሚሻለን፡፡ ከከተማ አንድ እርምጃ ወጥተን እኮ ማረስ አይታሰብም፡፡ ሰላምን በተስፋ እየተጠባበቅን ነው ያለነው፡፡” ጨፌ ኦሮሚያ ጉባኤ እና የፀጥታ ጥያቄ
ሌላው የዚሁ ወረዳ ነዋሪ በሰጡን አስተያየታቸው አሁንም ከተስፋው ይልቅ የሚያሰጋቸው ድባብ ነው በአከባቢው የሚንዣብበው፡፡ ለደህንነታቸው ሲባል ስሜ ይቆይ ብለው አስተያየታቸውን የሰጡን እኚሁ ነዋሪ በተለይም ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ዓርብ ጠዋት በአጎራባች ወረዳቸው ጊዳ አያና ውስጥ ሰላማዊ ህብረተሰብን በሚያጓጉዝ አንድ ተሽከርካሪ ላይ የደረሰው የታጣቂዎች ጥቃት ስጋታቸውን ከፍ ካደረጉ ክስተቶች ናቸው፡፡ “ታጥቀው ሰላማዊ ህዝብንም ጭምር የሚሳድዱ ታጣቂዎች በዚህም በዚያም እየተንቀሳቀሱ ስለሆነ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ነን፡፡”
እንደ አስተያየት ሰጪው በዚህች ወረዳ አሁን በገጠሩ ሰዉ የለም፡፡ መሬቱም ጦም አድሯል፡፡ አቅም የፈቀደለት ሻል ወዳሉ ከተሞች ርቆ ሲሰደድ አቅም ያልፈቀደለት በዚያው በወረዳ ከተማ ተቀምጦ የሚሰፈርለትን እርዳታ እህል እየተቀበለ ህይወቱን ይገፋል፡፡ ግን ደግሞ ይላሉ ነዋሪው “ህዝቡ አሁንም ሰላሙ ይመለስልናል በሚል እምነቱን በመንግስት ላይ ጥሎ ይጠባበቃል፡፡”
በዚሁ ዞን በሌላኛዋ ወረዳ ጊዳ አያና ላይ የተሻለ ሊባል የሚችል አንጻራዊ ሰላም መኖሩን የሚገልጹት የጊዳ ከተማ ነዋሪ ደግሞ፤ ዓርብ ጠዋት በወረዳው በተጓዦች ላይ ታጣቂዎች በወሰዱት ጥቃት ሰላማዊ ሰዎች በገፍ መገደላቸው ከፍተኛውን ስጋት አጭሯል ይላሉ፡፡ “እኛ ጋ የተሻለ ሰላም ነበር፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን መንገድ እንኳ ሲንጓዝ ያለ ጸጥታ ኃይል እጀባ አደጋው ይከፋል፡፡ አርብ ንጹሃን ተጓዦች ላይ የደረሰው አደጋ ለዚህ ማሳያ ነው፡፡”ጨፌ ኦሮሚያ ጉባኤ እና የፀጥታ ጥያቄ
በአከባቢው የሚገኙ እንደ ኪረሙ፣ ጃርደጋ ጃርቴ እና አሙሩ ያሉ ወረዳዎች በግጭት መናጣቸው ወደ ወረዳቸውም ጫናውን እያመጣ መሆኑን እኚው ነዋሪ ያስረዳሉ፡፡ “የተለያዩ ስያሜ ዘው በጫካ መሽገው ህዝቡን የሚስጨንቁ ታጣቂዎች በአከባቢው አሁንም ትልቁ ስጋት ናቸው፡፡ አርሶ አደር ለርሃብ እየተዳረገ፤ ሆስፒታል ያለ መድሃኒት እየቀረ ነው በዚህ ወረዳ፡፡”
መንግስት በአከባቢው ሊወስድ ይገባል ያሉት ጸጥታን የማስከበር እርምጃ ደግሞ ለአከባቢው ሰላም መስፈን ብቸኛው አማራጭ ነው ይላሉም፡፡ “በአከባቢው ታጣቂዎች የት የት እንዳሉ ስለሚታወቅ መንግስት በነዚያ ስፍራዎች ሰላም የማስከበር ሃላፊነቱን ቢወጣ ምናልባል ሰላሙ ሊመጣ ይችላል፡፡”ከመዲናዋ አዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ 180 ኪ.ሜ ገደማ በሚገኘው ምእራብ ሸዋ ዞን ግንደበረት ወረዳ ከአራት ዓመታት ወዲህ ቤተሰቦቼን መጠየቅ አልቻልኩም የሚሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ደስታ ዲንቃ አሁንም የጸጥታ ችግሩ የአከባቢውን ህብረተሰብ ለተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውሶች የዳረገ ነው ይላሉ፡የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት የሰላም ጥሪ
“ሸቀጦች በቤት እንስሳት ወደ ሚጋዙበት ዘመን ተመልሰናል፡፡ ከጸጥታው ችግር የተነሳ ዘመናዊ ትራንስፖርት የለም፡፡ ወላድ እናት በአስቸኳይ የተሸለ ህክምና ታገኝ ብትባል እንካ ትራንስፖርት መንግድ ባለመኖሩ የተሻለ ዕድል አይገጥማትም፡፡” የክልሉ ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታና እልባቱን በማስመልከት ከክልሉ ፀጥታ አስተዳደር እና ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊዎች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ዶይቼ ቬለ ያደረገው ጥረት ለዛሬ አልሰመረም፡፡ ባለፈው ሳምንት የአዲስ ዓመት መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድርግ መልእክት ያስተላለፉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ግን ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት የዓመቱ የመንግሥት ትልቁ አቅጣጫ መሆኑን በንግግራቸው አመልክተው እንደነበር ይታወሳል።
ስዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ