ሜርክል እና ፓርቲያቸው ሴዴኡ
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 2 2011የጀርመኑን የክርስቲያን ዴሞክራቶች ህብረት ፓርቲ በምህጻሩ CDU ን ለበርካታ ዓመታት በሊቀመንበርነት የመሩት የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ከፓርቲው ሊቀመንበርነት ተሰናብተዋል። በምትካቸውም ፓርቲው የሜርክል ምርጫ የነበሩትን አነግሬት ክራምፕ ካረንባወርን በሊቀመንበርነት መርጧል።
«መራሂተ መንግሥት ወይም የፓርቲ መሪ ሆኜ አልተወለድኩም።ሁሌም የመንግሥት እና የፓርቲ ሥራዬን በክብር ማከናወን እና አንድ ቀን በክብር መሰናበት ነበር የምፈልገው።አሁን አዲስ ምዕራፍ መክፈቻ ጊዜ ነው። ዛሬ በዚህ ሰዓት በዚህ ወቅት በአንድ ስሜት በምስጋና ስሜት ተሞልቻለሁ። ለኔ ይህ ትልቅ ደስታ ትልቅ ክብር ነው። በጣም አመሰግናለሁ።»
የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ባለፈው አርብ በሰሜናዊቷ የጀርመን ከተማ በሀምቡርግ በተካሄደው በክርስቲያን ዴሞክራት ህብረት በጀርመንኛው ምህጻር CDU ጉባኤ መክፈቻ ላይ ከፓርቲው ሊቀመንበርነት ሲሰናበቱ ያደረጉት ስሜት ነኪ ንግግር ነበር። ሜርክል የመሰናበቻ ንግግራቸውን እንዳበቁ ጉባኤተኞቹ ከመቀመጫቸው ተነስተው ያለማቋረጥ ለ8 ደቂቃ ያህል ነበር በጭብጫባ አድናቆታቸውን እና ምስጋናቸውን የገለጹላቸው፤ ከመካከላቸው «እናመሰግናለን አለቃችን»የሚሉ ጽሁፎችንም ከፍ አድርገው ያሳዩ ጉባኤተኞችም ነበሩ።
ከፓርቲያቸው ሊቀመንበርነት የዛሬ ሳምንት አርብ በክብር የተሰናበቱት ሜርክል የዛሬ 18 ዓም ሃላፊነቱን ሲረከቡ ከርሳቸው እንደቀደሙት መሪዎች ብዙም እምነት የተጣለባቸው አልነበሩም። ከምክንያቶቹ መካከል ወጣት መሆናቸው እና ትውልድ እድገታቸው ትምሕርታቸውም በቀድሞዋ ምሥራቅ ጀርመን መሆኑ እንደነበሩ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ እና የህግ ባለሞያው ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ ያስረዳሉ። ሆኖም ይህ አስተሳሰብ ትክክል እንዳልነበረ ሜርክል ባለፉት 18 ዓመታት በተግባር ማሳየት ችለዋል በዶክተር ለማ አስተያየት።
የሜርክልን አነሳስ ስንቃኝ የክርስቲያን ዴሞክራት ህብረት ፓርቲን ለ25 ዓመታት የመሩት የቀድሞው የጀርመን መራሄ መንግሥት ሄልሙት ኮል፣ ሜርክልን ለፓርቲው አመራር በማብቃት ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ። ኮል መሠረታቸው ምሥራቅ ጀርመን የሆነውን ወጣቷን ሜርክል ኮትኩተው አሁን ለደረሱበት ደረጃ መሠረት የጣሉ ባለውለታቸው ናቸው ማለት ይቻላል። ይሁንና ሜርክል ኮል በባንክ ተጠራቅሞ በተገኘ በሚስጥራዊ መንገድ ለድርጅቱ በተሰጠ ገንዘብ ምክንያት ውዝግብ ውስጥ ሲገቡ የኮልን ስህተት በይፋ አጋለጡ። ይህም ብዙ ደጋፊ ለማግኘት እና ራሳቸውን ችለው ለመቆም ረድቷቸዋል።የበርሊኑ ወኪላችን ይልማ ኃይለ ሚካኤል እንደሚለው እርምጃው ፓርቲውንም ከውድቀት ለማዳን አስችሏቸዋል።
ሜርክል በመሰናበቻ ንግግራቸው እንዳሉት ለ18 ዓመታት በሊቀመንበርነት የመሩት ሴዴኡ ተለውጧል። ይህም በርሳቸው እይታ ጥሩ ውጤት ነው ። እርግጥ ነው የፓርቲው መሪ ከሆኑ ወዲህ የመሀል ቀኙ ሴዴኡ የቀድሞው ሴዴኡ አይደለም ባዮች ጥቂት አይደሉም። በተለይ ተቃዋሚዎቻቸው በአመራር ዘመናቸው ፓርቲውን ወደተለያዩ ፓርቲዎች አጀንዳዎች በመሳብ የሌሎችን ሀሳብ ወስዶ ተግባራዊ በማድረግ ይተቿቸዋል። ይህ እውነት መሆኑ የሚገልጹት ዶክተር ለማ አካሄዳቸው ግን አዋጥቷቸዋል ይላሉ
ባለፉት ዓመታት በዚህ አቅጣጫ እነዚህን የመሳሰሉ ትችቶች ቢቀርቡባቸውም ፣ሜርክል ከውሳኔያቸው ዝንፍ ሳይሉ በጀመሩት አቅጣጫ የመጓዝ ልምዳቸው ለየት ያደርጋቸዋል። ይህ ለስኬት ካበቃቸው እና ፓርቲውንም ለ18 ዓመታት እንዲመሩ ካስቻሏቸው ምክንያቶች አንዱ መሆኑን ይናገራል ይልማ። በአመራር ዘመናቸው ካሳለፏቸው ውሳኔዎች፣ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ስማቸውን ከፍ አድርገው ከሚያስነሱት እና አሻራቸውን ከተዉባቸው መካከል ዋና ዋና የሚባሉትን ይልማ እንዲህ ያስታውሳል። ከዚሁ ጋር አባቶች ሕጻናት ልጆቻቸውን እንዲንከባከቡ ለማበረታት የተወሰዱት እርምጃዎች ይጠቀሳሉ። በሴዱኡ ሊቀመንበርነት ዘመናቸው እነዚህን በመሳሰሉ ውሳኔዎቻቸው ከሚታወሱት ከሜርክል ስንብት በኋላ ሴዴኡ ችግሮች ሊያጋጥሙት ይችላሉ የሚሉ ስጋቶች ይሰማሉ። በተለይ ርሳቸው ሥልጣኔን እለቃለሁ ካሉ በኋላ በኋላ የተፈጠሩ ልዩነቶች እንዳይሰፉ ያሰጋል። ሆኖም ዶክተር ለማ አዲሷ የፓርቲው ሊቀመንበር አነግሬት ክራምፕ ካረንባውር ያካበቱት ልምድ ችግሩን ለመፍታት ይረዳቸዋል የሚል እምነት አላቸው። ባለፈው ሳምንት ከፓርቲያቸው ሊቀመንበርነት የተሰናበቱት የ64 ዓመትዋ አንጌላ ሜርክል እስከ ጎርጎሮሳዊው 2021 ዓም ድረስ በመራሄ መንግሥትነት ሥልጣናቸው ላይ እንደሚቆዩ አስታውቀዋል።
ኂሩት መለሰ
እሸቴ በቀለ