ማሻሻያ እየተደረገበት ያለው የምርጫ ቦርድ አዋጅ
ማክሰኞ፣ ጥር 27 2017የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከውይይቱ በተጨማሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአዋጁ ማሻሻያ ረቂቅ ላይ ሀሳባቸውን በጽሑፍ እስከ ትናንት ጥር 26 ቀን ድረስ እንዲያቀርቡ ጥር 4 ቀን ለፓርቲዎች በተናጠል በጻፈው ደብዳቤ አሳውቆ ነበር። ቦርዱ «በሕግ የተሰጡትን ሥልጣን እና ተግባራት በተሻለ አቅም እና ብቃት ለማስፈጸም ይረዳው ዘንድ» አዋጁን ማሻሻል እንዳስፈለገውም አስቀድሞ አስታውቋል።
የማሻሻያው ዝርዝር ጉዳዮች ምንድን ናቸው?
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስድስተኛውን ዙር ጠቅላላ ምርጫ ተከትሎ የተገኙ ያላቸውን የአፈፃፀም ልምዶችን፣ ችግሮችንና የፓለቲካ ፓርቲዎች የተወያዩባቸው ዋና ዋና ስምንት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የተነሱ ጭብጦችን ለማካተት ከጅምሩ ድጋፍና ትችት ያልተለየውን አዋጅ ማሻሻል እንዳስፈለገው አስታውቋል።
ዶቼ ቬለ የተመለከተውና 84 ገጾች ያሉት ማሻሻያ ተደርጎበት የቀረበው የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፓለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ፣ ስለ ፓርቲዎች ምዝገባ፣ መቋቋም፣ መተዳደሪያ ደንባቸው፣ ስለ ፓርቲዎች ውሕደት፣ ግንባር መፍጠር፣ መቀናጀት፣ ስለ ምርጫ አይነቶች እና ሂደቶች፣ የውጤት አገላለጽ እና ሌሎችም ዝርዝር ጉዳዮች የማሻሻያ አንቀጾችን ይዟል።
ቦርዱ ይህንን በተመለከተ ከሚያስተዳድራቸው ፓርቲዎች ጋር ጥር 8 እና 9 ተወያይቷል። በውይይቱ ከተሳተፉ ፓርቲዎች መካከል አንዱ ኢሕአፓ ነው።
በእሥር ቤት የሚገኙ የመምረጥ መብታቸው ያልተገፈፈ ሰዎች መምረጥ ይችላሉ
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከውይይቱ በተጨማሪ ፓርቲዎች ከጥር 4 ጀምሮ እስከ ትናንት ጥር 26 ድረስ ሀሳባቸውን በጽሑፍ እንዲያቀርቡ ዕድል ሰጥቷል። በረቂቅ አዋጁ ላይ 19 ገጾች ያሉት የማሻሻያ ሀሳብ ያቀረበው ኢሕአፓ ነባር «አዋጁ ቀድሞውኑም ለገዢው ፓርቲ ተመቻችቶ የተዘጋጀ ነው» ሲል ተችቷል። ይህም በመሆኑ «የዜጎችን በነፃ የመምረጥ እና የመመረጥ ዕድል አኮማትሯል፣ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ተሳትፎና ሚናን አኮስሷል» ብሏል። አሁን ካቀረባቸው የማሻሻያ ሀሳቦች መካከል የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት ጥቂቱን ጠቅሰዋል።
ማሻሻያ ረቂቁ «ጠቅላላ ምርጫን በተመሳሳይ ጊዜ ለማከናወን የማያስችል እንደ የፀጥታ ችግር፣ ወረርሽኝ፣ የተፈጥሮ አደጋ የመሰሉ ሁኔታዎች ሲኖሩ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር በመመካከር ምርጫውን በተለያየ ጊዜ ሊያደርግ ይችላል» ይላል። ማሻሻያው «በእሥር ቤት የሚገኙ የመምረጥ መብታቸው ያልተገፈፈ ዜጎች በልዩ ሁኔታ በሚቋቋም የምርጫ ጣቢያ ምርጫ የሚሳተፉበት ሁኔታ» እንደሚኖር አስፍሯል።
«የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሚያቀርቧቸው አጠቃላይ እጩዎች መካከል ቢያንስ 20 በመቶው ሴቶች ሊሆኑ ይገባል» ሲልም ይደነግጋል።
«እያንዳንዱ እጩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደር ከሆነ በሚወዳደርበት የምርጫ ክልል ከሚኖሩ መራጮች ሁለት ሺህ፣ ለክልል ምክር ቤት ከሆነ አንድ ሺህ የድጋፍ ፊርማ ማቅረብ አለበት።» የሚለውም በረቂቁ ተካትቷል። በፓርቲዎች ተወክለው ለምርጫ የሚወዳደሩ እጩዎች ዝርዝር መረጃ አስቀድሞ ለቦርዱ እንዲቀርብ መጠየቁ ግን ኢሕአፓን አላስደሰተም።
ማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ ላይ «በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያሉ መገናኛ ብዙኀንን ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የግል ዕጩዎች ያለ አድሎ የመጠቀም መብት አላቸው» የሚለው ተካትቷል። በተጨማሪም ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤውን ቢያንስ በየሦስት ዓመቱ ማድረግ እንዳለበት፣ «ጥሰት መፈፀሙ የተረጋገጠ የፖለቲካ ፓርቲን ቦርዱ ከምዝገባ ከመሰረዙ በፊት አምስት ዓመት ላልበለጠ ጊዜ ታግዶ እንዲቆይ ሊወስን ይችላል» የሚሉ ድንጋጌዎችም ተካተዋል። የኢሕአፓ ምክትል ፕሬዝዳንት ሃይማኖት አብርሃም ቦርዶ የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታዎች በማሻሻያው አልተመለከትም ሲሉም ለዴቼ ቬለ ገልፀዋል።
አዋጁ ባለፈው ዓመትም ማሻሻያ ተደርጎበታል
የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና ሥነ ምግባር አዋጅ «ኃይልን መሠረት ያደረገ የአመጽ ተግባር ውስጥ የተሳተፈ» ነገር ግን ይህንን ተግባር ማቆሙንና በሰላም ለመንቀሳቀስ መስማማቱን የገለፀ የፖለቲካ ቡድን ከሚመለከተው የመንግሥት ተቋም የሚሰጠውን ማረጋገጫ መነሻ በማድረግ «በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ» እንዲመዘገብ እድል ይሰጣል ሲል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግንቦት 27 ቀን 2016 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ጉባኤው አዋጁን ማሻሻሉ ይታወሳል። ይህንን ተከትሎም የሕወሓት ሕጋዊ ሰውነት ተመልሶለታል።
ሰሎሞን ሙጬ
ሸዋዬ ለገሠ
ነጋሽ መሐመድ