ማሕደረ ዜና፤ የእስራኤል፣ የአሜሪካና የኢራን የጦርነት ማግሥት የጦርነት ዝግጅት
ሰኞ፣ ሰኔ 23 2017ለጋዛ ለዉጥ የለም።እስከሬ-ቁስለኛ ረሐብተኛ መቁጠር።ቴሕራን ግን ሙቶችዋን በአደባባይ ሰልፍ ሸኘች።ቀበረችም።ቴል አቪቭም ነዋሪዎችዋን ዳግም ባደባባይ ማሰለፍ ቻለች።የእየሩሳሌም-ዋሽግተን-ቴሕራን መሪዎች በድል አድራጊነት መፎከር፣ ለተጨማሪ ዉጊያ መዛት-ማስፈራራታቸዉን ግን አላቆሙም።የኢራንን መደብደብ በቃል እያወገዙ፣ በገቢር ወደ እስራኤል የሚተኮስ የኢራን ሚሳዬልን ሲያከሽፉ የነበሩት አረቦች አሁንም አራምባና ቆቦ እየረገጡ ነዉ።አዉሮጶች የኢራንን መደብድም፣ የዉጊያዉን መቆምም እኩል ደግፈዉታል።የቃል-ድርጊት ተቃርኖ። የመገዳደል ፉከራ ዛቻና እብሪት መዘዝ የት ያደርስ ይሆን? ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ።
የጋዛ እልቂት፣ የቴል አቪቭ ቴሕራን እፎይታ
ለጋዛ ነዋሪዎች-በትናንትና በዛሬ መሐል ያለዉ ለዉጥ አንድም ሞት-አለያም በሽታና ረሐብ ነዉ።ያዉ እንደ ዓመት ከዘጠኝ ወሩ የእስራኤል ጦር የገደለ፣አካለ ጎደሎ ያደረገ፣ ቤት ንብረቱን ያወደመ፣ በረሐብ፣ በሽታ የሚያሰቃዉ ፍልስጤማዊ በፍርስራሽ በተሞሉ የጋዛ ሰርጥ ከተማ-መንደር-አዉራጎዳኖች እንደተሰጡ፣እንደተራወጡ ነዉ።
የእስራኤል ዜጎች ግን ሐማስ ያገታቸዉ ወገኖቻቸዉ እንዲለቀቁ ለመጠየቅ በአደባባይ የሚያደርጉትን ሠልፍ ለሁለት ሳምንት አቋርጠዉ ነበር።እስራኤልና ዩናይትድ ስቴትስ ከኢራን ጋር የገጠሙት ዉጊያ ሲቆም እንደገና ጀመሩ።ቴል አቪቭ።ቅዳሜ።
ሻሮን አሎኒ ኩኒ ከሐማስ እገታ ተለቅቀዋል።ባለቤታቸዉ ግን እንደታገቱ ነዉ።ለመሪዎቻቸዉ ጥያቄ አላቸዉ።
«ከኢራን ጋር የተደረገዉ ጦርነት በስምምነት ቆሟል።ከሊባኖስ ጋር የተረገዉ ጦርነትም በስምምነት ቆሟል።አሁን የጋዛ ጦርነት በሥምምነት የሚቆምበት ጊዜ ነዉ።ሁሉንም ታጋች ወደየቤቱ የሚመልስ ሥምምነት መደረግ አለበት።ታጋቾች ወዲ,ቤታቸዉ፣ የወደቁትም ወደ ሐገራቸዉ ወታደሮችም ወደ ቤተሰቦቻቸዉ የኔ ዴቪድም ለልጆቹና ለኔ መመለስ አለባቸዉ።»
የጋዛዉ እልቂት እንደቀጠለ ነዉ።ቴሕራኖች ግን እንደ ቴል አቪቮች ሁሉ ለ12 ቀናት ያናፈረባቸዉ የቦምብ ሚሳዬል ወጀቦ ገለል-ቀለል ሲልላቸዉ ሙቶቻቸዉን ቀበሩ።ቅዳሜ።
ቅዳሜ በይፋ ከተሸኙት ያንደኛዉ ሟች ሳይንቲስት የቅርብ ዘመድ ጀሚሊያሕ በሐዘኑ መሐል እልሕ፣ቁጭት እያተከተካቸዉ መሪዎቻቸዉን ያሳስባሉ።
«ጦርነት ጫሪዎች አይደልንም።ከተጠቃን ግን ከዚሕ ቀደም እንዳደረግነዉ ሁሉ አፀፋችን ከባድ ምናልባትም የከፋ ነዉ።መሪዎቻችን በፅናት እንዲቆሙ እንፈልጋለን።ጠላት ሙሉ በሙሉ እስኪወገድ ድረስ በዚሑ መቀጠል አለባቸዉ።»
ጀግናዉ ማነዉ?
ለጀሚላሕ በርግጥ ፋርሶች አትንኩኝ ባይ ናቸዉ።ለዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ለዶናልድ ትራምፕ ግን ጀግናዉ አንድም ራሳቸዉ አለያም የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቢንያሚን ኔታንያሁ ናቸዉ።ኔታንያሁ የታጋች እስራኤላዉያንን ሥቃይ ማራዘማቸዉ እንዲያበቃ እስራኤላዉያን በሰልፍ በሚጠይቁበት፣ የኢራን የጦር ጄኔራሎችን-ከእስረኞች፣ ሳይንቲስቶችን ከልጅ-ሚስቶቻቸዉ ሳይለዩ ማስገደላቸዉ፣ የኑክሌር ተቋማን ከመኖሪያ ሕንፃ ጋር ማስወደማቸዉን ኢራኖች በሚያወግዙበት መሐል ባለፈዉ ሳምንት ማብቂያ ትራምፕ በፃፉት መልዕክት «ቢቢን ተዉት» አሉ።«የጦር ጀግና ነዉ።»
በርግጥ ጀግናዉ ማነዉ?12 ቀናት የቆየዉን፣ከ600 በላይ ኢራናዉያንን፣ 28 እስራኤላዉያንን የገደለዉን፣ የሁለቱን ሐገራት ምጣኔ ሐብት ያሽመደ።መደዉን ዉጊያ ቀድማ የከፈተችዉ እስራኤል ናት።ዩናይትድ ድብደባዉን ፈቅዳለች፣ ኋላ ራሷ ቀጠላበታለች።አሁን የሚሞጋገሱት የሁለቱ ጥብቅ ወዳጅ መንግሥታት መሪዎች ኢራንን ለመደብደባቸዉ የሰጡት ምክንያት የቴሕራንን የኑክሌር ተቋማት ለማዉደም ነዉ።ወሕኒ ቤት የኑክሌር ተቋም ይሆን?
የጉልበተኞች እርምጃና አጓጉል አስተምሕሮቱ
በዓለም ላይ አዉዳሚዉን የአዉቶሚክ ቦምብ ለመጀመሪያም፣ እስካሁን ለመጨረሻም ጊዜ በከተሞች ላይ ያፈነዳች አንድ ሐገር አለች።ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ።በዓለም ላይ በይፋ ሳትናገር ግን ኑክሌር ቦምብ የታጠቀች ሌላ ሐገር አለች።እስራኤል።ሁለቱ ኑክሌር የታጠቁ መንግሥታት ሌላዉን መንግስት ተቆጣጣሪ ያደረጋቸዉ ማነዉ የሚሉ አሉ።መልሱ ግልፅና አንድ ነዉ።ጉልበት።ፈረንጆቹም ይሉታል።Mighte is Right።አረቦቹም« አል ሐቅ ፎቀል ቁዋ» ላሉ አሉ-ፍትሕ በጉልበት ነዉ-እንደማለት።
ካይሮ ግብፅ የሚገኘዉ የአል-ሐብቱር ጥናት ማዕከል ባልደረባ ዶክተር አዛ ሐሺም እንደሚሉት ግን ዓለም የጋራ ማሕበር ያስፈለገዉ የጉልበት ልክ ነዉ ዓይነት እርምጃ የሚያስከትለዉን እልቂት ለማስቀረት ነበር።
«ሌሎች መንግሥታት አንድን ሐገር ለማጥቃት ሲወስኑ፣ ያለ የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ዉሳኔ እርምጃ መዉሰድ ይቻላል የሚል መዘዝ ያስከትላል።ይሕ በዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ዘንድ ሁከትና ሥርዓተ አልበኝነት ይፈጥራል።ምክንያትም ተጠያቂ የሚሆን የለም።ይሕ ጦርነትም የኑክሌር ቦምብ ለመሥራት እሽቅድምድም ሊያስከትል ይችላል።ምክንያቱም ኢራን የኑክሌር ቦምብ ቢኖራት ኖሮ ጠንካራ ድብደባ አይደርስባትም ነበር የሚል አስተሳሰብ አሳድሯል።»
ሕግ አልባዋ አለም፣ የኢራን ገጠመኝ
ኢራን ለምዕራባዉያንና ለተባባሪዎቻቸዉ ወረራና ድብደባ በርግጥ እንግዳ አይደለችም።ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት በጋመበት ወቅት ቴሕራኖች ለማንም አንወግንም ብለዉ ነበር።ያኔ የጋራ ግንባር ፈጥረዉ የነበሩት ብሪታንያና ሶቭየት ሕብረት ግን ቴሕራኖችን «ከጀርመኖች ጋር ወግናችኋል» ብለዉ ኢራንን ወርረዋታል።
በ1951 (ዘመኑ በሙሉ እግአ ነዉ) በኢራን ምክር ቤት የተመረጡት ጠቅላይ ሚንስትር መሐመድ ሞሳዴቅ ብሪታንያ ጠቀም ያለ ገንዘብ የምትዝቅበትን የኢራንን የነዳጅ ሐብት በመንግሥት ቁጥጥር ሥር በማድረጋቸዉ የለንደን-ዋሽግተን ተሻራኪዎች ያደራጇቸዉ የጦር መኮንኖች ከሥልጣን አስወግደዋቸዋል።በ1980ዎቹ በዩናይትድ ስቴትስ፣ በምዕራብ አዉሮጳና በአረቦች የምትረዳዉ ኢራቅ ኢራንን ወርራ ለ8 ዓመት ወግታተለች።
«የዓለምን ሕግ የሚያስከብር» የተባለዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በ1950ዎቹም፣ በ1980ዎቹም ነበር።ዘንድሮም አለ።ወረራ፣ ጦርነቱና ጥቃቱን ለማስቀረት ግን የተከረዉ ነገር የለም።ኋላ ግዙፉን ድርጅት የመሠረቱት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ፍራንክሊን ዲ ሩዘቬልት፣ የሶቭየት ሕብረቱ መሪ ጆሴፍ ስታሊንና የብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ዊንስተን ቸርችል የመጀመሪያ ሥልታዊ ጉባኤያቸዉን ያደረጉት ቴሕራን ነበር።1943።ድንቅም አይደል።
በ2003 የዩናይትድ ስቴትስና የብሪታንያ ገዢዎች ኢራቅን ሲወርወሩ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤትን ደንብ፣ሕግና ማሳሰቢያን ጥሰዉ ነዉ።ኢራቅ ከተባበሩት መንግሥታት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ዉሳኔ ዉጪ መወረሯን ካንገትም ይሆን ካንጀት ፈረንሳይ፣ ሩሲያና ጀርመን ተቃዉመዉት ነበር።የሰማቸዉ የለም።የድርጅቱ ሐሳብ አፍላቂ፣ ግንባር ቀደም መስራቾች አንግሎ-አሜሪካኖች በከፈቱት ቀዳዳ ሩሲያ ከ11 ዓመት በኋላ ገብታ በ2014 የዩክሬን ግዛት ክሪሚያን፣ በ2022 ደግሞ ዩክሬንን ወርራለች።
ለዋሽግተን፣ ብራስልስ፣ ለንደን መሪዎች 2022 ላይ የዓለም ሕግ ተጣሰ።ሉዓላዊት ሐገር ተወረረች።እና ሞስኮዎችን በሁሉም አይነት ማዕቀብ ቀጡ።ዘመናይ ጦር መሳሪያቸዉን ለኪቭ ያግዙ ገቡ።አጥኚዎች እንዳሉት ዩናትድ ስቴትስ፣ የአዉሮጳ ሕብረት፣27ቱ አባላቱና ብሪታንያ ለዩክሬን ያስታጠቁት ጦር መሳሪያ ከመቶ ቢሊዮን ዶላር በላይ ያወጣል።
የኢራንና የIAEA ሚና
እስራኤልና ዩናይትድ ስቴትስ ኢራንን ሲደበድቡ ግን የአዉሮጳ መሪዎች የድብደባዉን ተገቢነት ለማስረዳት ሲባትሉ ነበር።ዉጊያዉ ሲቆም ደግሞ መቆሙን አወደሱ።እስራኤልና ዩናይትድ ስቴትስ የኢራንን የኑክሌር ተቋማት በዶናልድ ትራምፕ አገላለፅ «ሙሉ በሙሉና አንድም ሳይቀር አዉድመዋል።» አሁን ደግሞ ኢራን የኑክሌር ተቋማቷን በዓለም አዉቶሚክ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን (IAEA) እንድታስፈትሽ የእስራኤል-የዩናይትድ ስቴትስና የአዉሮጳ መሪዎች እያስፈራሩ ነዉ።ከወደመ ምኑ ነዉ የሚፈተሸዉ? የኢራን ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኢል ባጋሒም እንደሚሉት ኢራን ለፈታሾቹ ደሕንነት ዋስትና መስጠት አትችልም።
«ሰላማዊ የኑክሌር ተቋማችን ባለፈዉ ሰኞ እንኳን፣ ከ5ና ሥድስት ቀናት በፊት እየተደበደበ፣ተቋማቱን የሚፈትሹትን የIAEA ባለሙያዎችን ደሕንነት እንዴት እንድንጠብቅ ነዉ የሚፈለገዉ።»
እስራኤልና ዩናይትድ ስቴትስ በኢራን ላይ የከፈቱት ጥቃት የቱርክ ፕሬዝደንት ሬሴብ ጠይብ ኤርዶኻን እንዳሉት ነገ በሌላ ሐገር ላይ ላለመደገሙ ምንም አይነት ዋስትና፣ ገዢ ሕግም የለም።ቱርክ ጦር ጦር ኃይሏንና መሳሪያዎቿን እንድታጠናክር ኤርዶኻን አዝዘዋል።ኢራንና እስራኤል ያቃረጧቸዉ የአረብ ሐገራትም የየሩሳሌሙ የሒብሩ ዩኒቨርስቲ ባልደረባ ዚሞን ቮልፍ ጋንግ ፉክስ እንደሚሉት ከእስራኤልና ከአሜሪካ መለጠፋቸዉን እያረጋገጡ ግን ቀጠር ላይ እንደታየዉ ዋጋ እያስከፈላቸዉ ነዉ።
« የዓ,ረብ መንግስታት ባሁኑ የእስራኤልና የኢራን (ጦርነት) አጣብቂኝ ዉስጥ ገብተዋል።አንዳዶቹ ተሳትፈዋል።የኢራንን ሚሳዬል በማክሸፍ እስራኤልን ደግፈዋል።እርግጥ ከዮርዳኖስ በስተቀር ሌሎቹ በይፋ አልተናገሩትም።»
የአረብ እስራኤሎች ወዳጅ ጠላትነት ለብዙዎች ሚስጢር፣ ግራ አጋቢ የሚሆንበት ምክንያት በግርጥ ብዙ ያነጋግራል።የኢራን መደብደብ የሚያስከትለዉ መዘዝ ግን ወትሮም ሠላም ለማያዉቀዉ መካከለኛዉ ምሥራቅ ብቻ ሳይሆን ከኮሪያ ልሳነ-ምድር እስከ አዉሮጳ ለሚደርሰዉ ዓለም የሚተርፍ እንዳይሆን ታዛቢዎች ያሳስባሉ።
ነጋሽ መሐመድ
ኂሩት መለሰ