ማሕደረ ዜና፣ የኢትዮጵያ ፈርጀ ብዙ ቀዉስ ማብቂያ ያገኝ ይሆን?
ሰኞ፣ ሐምሌ 21 2017የትግራይ ፖለቲከኞች የገጠሙት ዉዝግብወደ ነፍጥ ፍጥጫና የአደባባይ ሠልፍ እየናረ ነዉ።የአማራና የኦሮሚያ ክልሎችን የሚያዉከዉ ጦርነት፣ግጭትና ሥርዓተ-አልበኝነት እንደቀጠለ ነዉ።የአፋር፣ የአፋር-ሶማሌ ድንበር፣ የበኒ ሻንጉል-ጉሙዝና የጋምቤላ አካባቢዎች በሰላምና ግጭት መሐል እየዋዠቁ ነዉ።የኢትዮጵያና የሶማሊያ ወዳጅነት መቀጠል-አለመቀጠሉ በካይሮ-አቡዳቢ-አንካራ-አስመሮች ፍላጎት ላይ የተንጠለጠለ ነዉ።የኢትዮጵያና ኤርትራ አዋሳኝ ድንበር ግን እልቂት ሊወልድ በዳግም ጦርነት ምጥ ያጣጥራል።አንዳዶች ምናልባት ከግጭት-ቀዉስ-ሥጋቱ አትራፊዎች «ሟርተኞች» ይሉ ይሆናል።ሥጋቱ ተወግዶ «ማርተኞቹ» ቢሳሳቱ በርግጥ «እስየዉ» ባሰኘ ነበር።አለማሰኘቱ እንጂ ቀቢፀ ተስፋዉ።የኢትዮጵያና ያካባቢዋ ሁለንተናዉ ቀዉስ ምክንያቱና መፍትሔዉ ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ አብራችሁን ቆዩ።
የሕዳሴ ግድብ ምርቃት፣ የጋስና ማዳበሪያ ምርት ተስፋ
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ ዐሕመድ በቅርቡ እንዳሉት መንግሥታቸዉ ታላቁን የሕዳሴ ግድብ በመጪዉ መስከረም ያስመርቃል።የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት በአሜሪካ ገንዘብ የተሰራ ብለዉታል።የግብፅ ገዢዎች ደግሞ ግድብ መገንባቱን «ዓለም አቀፍ ሕግን የጣሰ» ማም-ምን አለ ምን ለኢትዮጵያዉያን 13 ዓመት የተለፋበት፣ ቢሊዮነ-ቢሊዮናት ብር የፈሰሰበት፣ብዙ ተስፋ የተጣለበት ግድብ ለዉጤት መብቃቱ በርግጥ ታላቅ ደስታ ነዉ።
ኢትዮጵያ ከኦጋዴን ምድር ጋስ የምትቀዳበት፣ ማደበሪያ የምታመርትበት ጊዜም ሩቅ ዓይደለም ተብሏል።የተባለዉ ከተደረገ ለኢትዮጵያዉያን ሌላ ደስታ-እንጂ ሌላ ሊባል አይችልም።
ርዕሠ-ከተማ አዲስ አበባን ጨምሮ በየከተሞቹ የተያዘዉ «የኮሪዶር ልማት» የተሰኘዉ ግንባታ የየከተሞቹን ዉበት-ማራኪነት መጨመሩ አያነጋግርም።ግንባታዉ የከተማይቱን ነዋሪዎች ፍላጎትና ተቃዉሞን ከቁብ አለመቁጠሩ አነጋግሮ ሳያበቃ፣ እንደ ነባር ነዋሪዎችዋ ፍላጎት ሁሉ ክረምቱንም የዘነጋዉ ግንባታ ለአዲስ አበባ ያጎናፀፈዉ ማራኪ-ሳቢ ዉበት በዕለት ደራሽ ዉኃ መበከሉ እንጂ ቁጭቱ።ሐብትም ወድሟል።
ከበኒ-ሻንጉል ጉሙዝ እስከ አዲስ አበባ፣ ከድሬዳዋ እስከ ኦጋዴን ያለዉ የልማት ዕድገት ተስፋ፣ የዉበት-ምቾት ብዜት አዲስ አበባ ላይ የሚዘረዘረዉ ሐኪሞች፣ አስተማሪዎች፣የግብርና ባለሙያዎች፣ ሌሎች የመንግሥት ሰራተኞችና አነስተኛ ነጋዴዎችም ጭምር ኑሮ በመወደዱ ምክንያት፣ በዶክተር ሙከረም ሚፍታሕ አገላለፅ፣ «ነብስ ዉጪ ነብስ ግቢ» መቃረጣቸዉን በሠልፍ ጭምር በሚናገሩበት ወቅት የመሆኑ ሐቅ እንጂ ሕቅታዉ።
«በኢትዮጵያ ዘመናዊ የፖለቲካ ኤኮኖሚ ታሪክ ዉስጥ እንዳሁኑ አይነት ቻሌንጅ ገጥሞን አያዉቅም።በኔ እድሜ ዉስጥ እንደዚሕ ዓይነት ነገር ገጥሞኝ አያዉቅም፣ሲቪል ሰርቫንቱ አብዛኛዉ በሚባል ደረጃ ነብስ ዉጪ ነብስ ግቢ ትግል ዉስጥ ነዉ።አዲስ ነዉ።አደገኛም ነዉ።አደገኛ ነቱ ሰዎች ጤነኛ የነበሩ ሰዎች መንገድ ላይ እያወሩ ሲሄዱ ይታያሉ።---»
የጦርነት ማግሥት ጦርነትና ሥጋት
በ2013 ትግራይ ላይ የተጫረዉ ጦርነት በሁለት ዓመት ዕድሜ በትንሽ ግምት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ፈጅቷል።አካሉ የጎደለ፣ የተፈናቃለ፣ የተደፈረችና የተሰደደዉ በአንዳዶች ግምት ከሁለት እስከ 5 ሚሊዮን ይደርሳል።በቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሐብት ንብረት አዉድሟል።
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ኮሎጂ መምሕር፣ አጥኚና የፖሊሲ ጉዳይ አማካሪ ዶክተር ሙከረም ሚፍታሕ እንደሚሉት የትግራዩ ጦርነት በሰዉ ሕይወት፣ አካልና ኑሮ ላይ ካደረሰዉ ጉዳት በተጨማሪ ኢትዮጵያ ዉስጥ አሁን ለሚታየዉ የምጣኔ ሐብት ድቀት አንዱ ትልቅ ምክንያት ነዉ።
«በትግራይ የተካሄደዉ ጦርነት ኢትዮጵያን እንደ አንድ ሐገር መንግሥት ከፍተኛ የሆነ ዋጋ ያስከፈለ ጦርነት ነዉ።የኢትዮጵያን የዉጪ ምንዛሬ ክምችት ያንኮታኮተ ነዉ።ለእያንዳዱ ሚሳዬልና ለከባድ መሳሪያዎች የወጣዉ ገንዘብ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ነዉ----ሐገሪቱን በብዙ ወደ ኋላ የጎተተ ነዉ።---»
ኢትዮጵያዉያን ለመጠየቅም-ለመጠያያየቅም ጊዜ ማጣታቸዉ ነዉ ዚቁ።በነሻንጉል-ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ አፋር-ሶማሌ ድንበር የነበሩት ግጭትና ጥቃቶች በጊዜ ሒደት ቢረግቡም የትግራይ ፖለቲከኞች ጦርነቱ በቆመ ማግሥት እርስበርስና ከፌደራሉ መንግሥት ጋር የገጠሙት ዉዝግብ ብዙዎች እንደሚፈሩት ቃታ ከሚያስብበት ደረጃ ላይ ደርሷል።
በጦርነቱ ወቅት ከትግራይ ክልል ቀጥሎ ክፉኛ የተጎዳዉ አማራ ክልል በጦርነቱ ማግሥት ከሌላ ግጭት ተመስጓል።ከትግራዩ ጦርነት በፊት የተጀመረዉ የኦሮሚያ ክልል ግጭት፣ በዘር ላይ የተመሰረተ ጥቃትና-አፀፋ ጥቃትም ቀጥሏል።ባለፈዉ ሳምንት ቢሾፍቱ ላይ ተሰብሰበዉ ከነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት መካከል የቦሩ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶክተር መብራቱ ዓለሙና የመላዉ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የዉጪ ግንኙነት ኃላፊ ማሙሸት አማረ ለአዲስ አበባዉ ወኪላችን እንደነገሩት መንግስት ከአማፂያን ጋር እንዲደራደር ተሰብሳቢዎቹ ጠይቀዋል።
የተደረሰበትን ሥምምነት የኢትዮጵያ መንግስትና ተፋላሚዎቹ መቀበል አለመቀበላቸዉ ያዉ ለጊዜ ሒደት የሚተዉ ነዉ።የቢሾፍቱ ጉባኤተኞች ዉሳኔ በተሰማ ሳልስት ካዉከስ በሚል የጋራ ስብስብ የመሠረቱት ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ደግሞ ኢትዮጵያ ዉስጥ ሰላምና ፀጥታ ባለመስፈኑ በመጪዉ ዓመት ሊደረግ የታቀደዉ ምርጫ እንዲራዘም ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ሥልጣን የያዙ ይሁኑ ተቃዋሚዎች ምን አሉ-አደ,ረጉ፣ የርስበርሱ ግጭት፣ጥቃት፣ ግድያ፣ እገታ፣ዘረፋና ስርዓተ አልበኝነት ግን ለኢትዮጵያዉያን የአዘቦት ትርዒት እስኪመስል ድረስ እንደቀጠለ ነዉ።የመንግሥት ባለሥልጣናትና ደጋፊዎቻቸዉ የቀዉሱን ንረት፣የሚያደርሰዉን ጥፋትና ምናልባት መፍትሔዉን የሚነግሯቸዉን ሁሉ የዚሕ ወይም የዚያ ጎሳ፣ ቡድንና ፓርቲ አባል እያሉ ከመፈረጅ ባለፍ እስካሁን መፍትሔ መስጠት አልቻሉም።ወይም አልፈለጉም።
የኢትዮጵያና የጎረቤቶቿ አለመግባባት
የኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብታዊ ድቀት፣ የኑሮ ዉድነት፣ የሥራ አጡ ቁጥር ንረት፣ ግጭት፣ ጥቃትና ምሥቅልቅሉ ኢትዮጵያዉያን ላይ የሚያደርሰዉ ጥፋት፣ ጉዳትና ሥጋት አልበቃ ያለ ይመስል ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሐገራት ጋር የገጠመችዉ አተካራ ሌላ ጭንቀት ሆኗል።ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር በተፈራረመችዉ የወደብ ኮንትራት የመግባቢያ ስምምነት ሰበብ የአዲስ አበባና የሞቃዲሾ ባለሥልጣናት የገጠሙት ዉዝግብ በቱርክ ሸምጋይነት ረግቧል።
ይሁንና በካይሮ የሚደገፉት የሞቃዲሾ መሪዎች ከአዲስ አበባ አቻዎቻቸዉ ጋር አሁንም በቀጥታም በተዘዋዋሪም እየተሻኮቱ ነዉ።የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የምክር ቤት አባልና የፖለቲካ ተንታኝ ዶክተር አብዲ ቡባል እንደሚሉት ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት በተለይም ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ የሚከተሉት መርሕ በሞቃዲሾዎች ብቻ ሳይሆን በሌሎችም የአካባቢዉ ሐገራት መሪዎች ዘንድ በጥርጣሬ አንድ ዓይን እየታየ ነዉ።
«ከሶማሊላንድ የሚነሳ ጫና አለ።ባለፈዉ በሙሴ ቢሒ መንግሥት ላይ አይተናል።ከሶማሊያ የሚነሳ ጫና አለ።በተለይ ፓርቲ ኮለርሊ የጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ መርሕ ከጅቡቲም ጋር ---»
ከአሥመራ የተሰማዉ ደግሞ ከሌሎቹ የጠነከረ ነዉ።ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ኢትዮጵያ ኤርትራን ለመዉረር ተዘጋጅታለች በማለት በሶስት ወራት ዉስጥ ለሁለተኛ ጊዜ አስጠንቅቀዋል።የኤርትራ ገዢዎች በሕግ ከታገደዉ ከህዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ህወሓት) ጋር ማበራቸዉም በሰፊዉ እየተዘገበ ነዉ።
የሩቅ ሐይላት ጣልቃ ገብነት
የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለዉን ጠብ ግብፅና ሶማሊያ ከኤርትራ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከኢትዮጵያ ጎን ቆመዉ እያጋገሙት ነዉ።የአስመራና የአዲስ አበባ ፖለቲከኞች በዉጪ ግፊት ተደፋፍረዉ ጦርነት ከገጠሙ ዶክተር ሙከረም እንደሚሉት መዘዙ ቀላል አይሆንም።
«አሁን ደግሞ ለጦርነት ከግራም ከቀኝም የሚታዩ አንዳድ ምልክቶች አሉ።ከኢትዮጵያም ከአካባቢዉም፣ ከዓለም አቀፉ ማሕበረሰብም ጥረት ተደርጎ መያዣ ካልተበጀላቸዉ---»
ቱርክ ዉስጥ ከተደረገዉ መፈንቅለመንግሥት እስከ ሶማሊያዉ ግጭት፣ ከግብፁ መፈንቅለ መንግሥት እስከ ሊቢያው ጦርነት፣ ከትግራይ ጦርነት እስከ ሱዳን ዉጊያ በየስፍራዉ ጣልቃ የሚገቡት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ገዢዎች ድጋፍ ይሁን ተቃዉሞ ጥንቃቄ የሚያሻዉ ይመስላል።
ኢትዮጵያ በፊዉዳል ሥርዓት ትገዛ-14 ጠቅላይ ግዛት ይኑራት፣ በሶሻሊስት ርዕዩተ ዓለም ትመራ-14 ክፍለ ሐገራትና ሶስት ራስ ገዝ አስተዳደር-ይኑራት፣ የካፒታሊስቱን ሥርዓት ትከተል፣ የሊብራሎችን- ብዙ የብሔር ብሔረሰቦች ክልሎች ይኑራት ከምጣኔ ድቀት፣ ከፖለቲካ ዉዝግብ፣ ከጦርነት ተለይታ አታዉቅም።
የሰሜን ግዛቷን ነፃነት የያኔ ገዢዎችዋ ይሉት እንደነበረዉ «ለሰላም ስትል» ትፍቀድ ወይም በጦርነት ትሸነፍ፣ የብሔር-ብሔረሰቦች ፌደሬሽን ትመሥረት ወይም ሌላ ሕዝቧ ሁሌም ሠላም፣ልማትና ብልፅግናን እንደናፈቀ ነዉ። ምክንያቱ ብዙ ያነጋግራል።አሁን የሚታየዉን ሁለንተናዊ ቀዉስ የሚስተካከል ግን ታዛቢዎች እንደሚሉት ዘመነ-መሳፍንት ከሚባለዉ ዘመን ወዲሕ በጥንታዊቱ ሐገር የረጅም ዘመን ታሪክ ታይቶ አይታወቅም።እና እስከ መቼ? ቸር ያሰማን።
ነጋሽ መሐመድ
ታምራት ዲንሳ