ማሕደረ ዜና፣ የኢትዮ-ሶማሊያ ወዳጅነት ካንጀት ወይስ ካንገት?
ሰኞ፣ የካቲት 24 2017
የኢትዮጵያና የሶማሊያን «አዲስ ፍቅር» ለማንፀባረቅ ባለፈዉ ጥር ተራዉ የአዲስ አበባ ነበር።ባለፈዉ ሐሙስ ደግሞ የሞቃዲሾ።አምና ይኽኔ ኢትዮጵያን በሚራገሙ፣ በሚያያወግዙ፣ ለዉጊያ በሚያቅራሩ ሠልፈኞች ተጨናንቀዉ የነበሩት የሞቃዲሾ አዉራጎዳኖች ባለፈዉ ሐሙስ የኢትዮጵያን መሪ በሚያወድሱ መፈክሮች፣ በሁለቱ ሐገራት መሪዎች ፎቶዎችና ባንዲራዎች አሸብርቁ።ሁለቱ ተጎራባች ሐገራት፣ ጠብ-ግጭት መጠላለፋቸዉን አቁመዉ ሠላም ለማዉረድ ከተስማሙ ለሕዝቡ እፎይታ፣ ተስፋ ሰጪ፣ ለአፍሪቃ ቀንድ ሠላምም ጠቃሚ ነዉ።በ2010 ማብቂያ አዲስ አበባና አስመራ፣ አምና አዲስ አበባና ሐርጌሳ የነበረዉን ከበርቻቻና ቱማታን ከዛሬ ዕዉነታ ጋር ለሚያነፃፅር ግን የአንካራ-አዲስ አበባ-ሞቃዲሾ መሪዎች መወዳደስ ካፍታ ሸብ-ረብ ማለፉን ቢጠራጠር በርግጥ አይፈረድበትም።የጉብኝ-አፀፋ ጉብኝቱን ምክንያት፣ጥርጣሬ፣ እንቅፋትና ዉጤቱን ባጭሩ እንቃኛለኝ።
የጉብኝት አፀፋ ጉብኝቱ መሰረት የሁለቱ ሐገራት መሪዎች ባለፈዉ ታሕሳስ መጀመሪያ አንካራ-ቱርክ ላይ የተፈራረሙት ሥምምነት ነዉ።ፕሬዝደንት ሐሰን ሼኽ ማሕሙድና ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ በቱርክ ፕሬዝደንት ሬሴፕ ጠይብ ኤርዶኻኝ ሸምጋይነት በተስማሙት መሠረት ሁለቱ ሐገራት በጠብ መፈላለጋቸዉን ያቆማሉ።ሠላም ለማዉረድ ይጥራሉ።ትብብራቸዉን ያዳብራሉም።
የአንካራዉ ሥምምነት ገቢር እየሆነ ነዉ
«የአንካራ መግለጫ» የተባለዉን ሥምምነት ገቢር ለማድረግ ይረዳሉ ከተባሉ እርምጃዎች አንዱ የሁለቱን መንግሥታት ዉይይት መቀጠል ነዉ።በይፋ እንደሚባለዉ ባለፈዉ ወር ፕሬዝደንት ሐሰን ሼኽ ማሕሙድ አዲስ አበባን፣ ባለፈዉ ሐሙስ ደግሞ ጠቅላይ ሚንስትር አዓብይ አሕመድ ሞቃዲሾን መጎብኝታቸዉ ዉይይቱ መቀጠሉን መስካሪ፣ መተማመንን ለማዳበርም ጠቃሚ ነዉ።
የሁለቱ ሐገራት የዉጪ ጉዳይ ሚንስቴሮች ባለሥልጣናት የዛሬ ሁለት ሳምንት ግድም «ቴክኒካዊ» ያሉትን ዉይይትም አንካራ ዉስጥ ጀምረዋል።የሶማሊያዉ ማስታወዊያ ሚንስትር ዳዉድ አዌስ እንደሚሉት ጉብኝት፣ አፀፋ ጉብኝቱና ዉይይቱ ሁለቱ መግሥታት በተገቢዉ ጎዳና እየተጓዙ ለመሆናቸዉ አብነት፣ መተማመንን ለመገንባት ጠቃሚም ነዉ።
«ታሕሳስ ላይ አንካራ ዉስጥ የተፈረመዉ የአንካራ መግለጫ፣ ሁለቱ ሐገራት ግንኙነታቸዉን እንዲያድሱ በግልፅ ያስቀምጣል።አሁን እዚያ ደረጃ ላይ ነን።አሁን መተማመን ለመገንባት ሥብሰባዎችና ዉይይቶችን እያደረግን ነዉ።ሥለዚሕ ነገሮች በተገቢዉ መንገድ እየተጓዙ ነዉ።»
ይሁንና ለዘመናት ከወዳጅነቱ እኩል ጠብ፣ ከመቀራረቡ ባልተናነሰ መራራቅ፣ ከመደጋገፉ መሰለመሳ መሻኮት ያልተለየዉ የሁለቱ ሐገራት ግንኙነት በቅርቡ ጨርሶ ፈርሶ፣ ዲፕሎማሲያዊ መበቃቀል ያስከተለዉ ኢትዮጵያ ወደብ ለመኮናተር አምና ታሕሳስ ከሶማሊላንድ ጋር የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረሟ ነዉ።
የኢትዮጵያና የሶማሊላንድ ስምምነት ተሰርዟል-ሚንስትር
የአዲስ አበባና የሞቃዲሾ መሪዎች የጠባቸዉን መሰረታዊ ምክንያት ሙሉ በሙሉ ማስወገዳቸዉን በይፋ ሳይናገሩ በወር እድሜ ለመወዳደስ፣ መተቃቀፍ መነፋፈቅ መድረሳቸዉ በርግጥ ጉድ አጃኢብ ማሰኘቱ አልቀረም።ማስታወቂያ ሚንስትር ዳዉድ አዌስ እንደሚሉት ግን ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ የተፈራረሙት የመግባቢያ ሥምምነት ተሰርዟል።
«ያ! ስምምነት አሁን ቆሟል።አንካራ ዉስጥ በተደረጉት ዉይይቶች ምክንያት ተሰርዟል።የቱርክ መንግስትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ባደረጉት የዲፕሎማሲ ጥረት መሠረት የሁለቱን ሐገራት ግንኙነት የሚያዉክ ነገር ሁሉ ዋጋ የለዉም ከሚል ማጠቃላያ ላይ ደርሰናል።በመግለጫዉም ተካትቷል።ይሕ ማለት የመግባቢያ ሥምምነቱን ዉድቅ አድርገን ከዚያ አዲስ የትብብር ምዕራፍ እንጀምራለን።»
አዲሱ የትብብር ምዕራፍ ለኢትዮጵያ ወደብ ሥለ ማስገኘት አለማስገኘቱ በግልፅ የሚታወቅ ነገር የለም።የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል የምክር ቤት አባልና የአፍሪቃ ቀንድ የፖለቲካ ተንታኝ ዶክተር አብዲ ቡባል እንደሚሉት ደግሞ መተማመንን ለመገንባት ከአዲስ አበባ-ሞቃዲሾ-አንካራ የሚባክኑት ባለሥልጣናት ወደብን በተመለከተ አሁንም አይተማመኑም።በአደባባይና በድብቅ የሚሉት ለየቅል ነዉ።
«የወደቡ ጉዳይ በሶማሊያ በኩልም በኢትዮጵያ በኩልም ለሕዝብ የሚገለጠዉና በፖለቲካ ዉይይቶች የሚሰጡት አስተያየቶች በጣም ልዩነት አላቸዉ።በኢትዮጵያ በኩል ለሕዝብ የሚገለጠዉ የራሳችን ወደብ እንደሚገኝ ዓይነት ነገር ነዉ።በሶማሊያ ደግሞ ኮሜርሻል ወይም ንግድን መሠረት ያደረገ እንጂ ሌላ ምንም የምናደርገዉ ነገር የለም የሚል ነዉ-ለሕዝብ የሚገለፀዉ።ሥለዚሕ----ሁለቱ ወገኖች አለመተማመን ይታይባቸዋል።»
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድና የቀድሞዉ የሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሒ አብዲ አምና የተፈራረሙት የመግባቢያ ሥምምነት ባንድ ወር ጊዜ ዉስጥ ገቢር ይሆናል ተብሎ ነበር።ተባለ ቀረ።ዓመት ከሁለት ወሩ።ተጠያቂ የለም።ጠያቂም።
የአምና ጠላት የዘንድሮ ወዳጅ
የሞቃዲሾ መሪዎች አምና ይኽኔ ኢትዮጵያን ከአሸባብ በላይ ለሶማሊያ አንድነት፣ሠላምና ደሕንነት የምታሰጋ በማለት በምክር ቤት ጭምር ሲያወግዟት ነበር።በቀድም ሐሙስ መሪዋን ያወድሱ ለመሪዋ ያስዘምሩ ገቡ።
የሁለቱ ሐገራት መሪዎች ጉብኝት፣ አፀፋ ጉብኝትና የባለሥልጣኖቹ ዉይይት ግብፅና ኤርትራን ከሞቃዲሾዎች ጎን ያሰለፈዉን ዉጥረት ማርገቡ በርግጥ አያጠያይቅም።የሶማሊያና የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ መገፋፋት አስቁሞ የኢትዮጵያ ጦር በሶማሊያ አዲስ የተዋቀረዉ የአፍሪቃ ሕብረት ሠራዊት አካል እንዲሆን ማድረጉም ጥሩ ነዉ።
በቅርቡ ምናልባት አዲስ አበባ፣ ሞቃዲሾና ጅቡቲን ለመጎብኘት ያቀዱትን የቱርኩን ፕሬዝደንት ሬሴብ ጠይብ ኤርዶኻንን ለማስደስትና ለማስተናገድም መጥቀሙ አይቀርም።ዶክተር አብዲ ሌላም ጥቅም አለዉ ይላሉ ምናልባት ዋና ጥቅም ግን ለሕዝብ ወይም ለሐገር ሳይሆን ለሁለቱ መሪዎች።
«ሌላዉ ዓብይም ኢትዮጵያ ዉስጥ በፕሬዝደንት ሐሰን ሼኽ ማሕሙድም ሶማሊያ ዉስጥ ከፍተኛ ችግር አለባቸዉ።ለዚሕም ይመስለኛል አሁን የሚያደርጉት ጉብኝት ዋናዉ ግፊቱ ከዉስጥ ያለዉ ጫና በሶማሊያ በኩልም ፕሬዝደንት ሐሰን ሼኽ ከፍተኛ ችግር ዉስጥ ነዉ ያለሉት የፌደራሉ መንግሥት ከአባል የፌደራል አባል ግዛቶች ጋር ያለዉ ግንኙነት ተበላሽቷል።በኢትዮጵያ በኩልም ግጭቶች አሉ፣ አለመረጋጋት አለ ኤኮኖሚዉን እናያለን።»
ሶማሊያ ዘንድሮ ኢትዮጵያ ደግሞ ለከርሞ ምርጫ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።የሶማሊያዉ ምርጫ ከዚሕ ቀደም እንደሚታወቀዉ በዉክልና ይሁን ወይም አንድ ሰዉ-አንድ ድምፅ የሚባለዉ ዓይነት በዉል አልታወቀም።ምርጫዉ በየትኛዉም መንገድ ሊደረግ ቢወሰን ምርጫዉን የሚያስፈፅመዉን ከፌደራል ግዛቶች የተወከለ ኮሚሽንን ፕሬዝደንት ሐሰን ሼኽ በትነዉታል።
በዚሕና በሌሎችም የፕሬዝደንቱ ርምጃዎች ቅር የተሰኙ ፑንትላንድን የመሳሰሉ ጠንካራ የፌደራሉ አባል ግዛቶች ፕሬዝደንቱን አጥብቀዉ እየተቃወሙ ነዉ።የጠቅላይ ሚንስትር ዓብይም መንግስት አማራና ኦሮሚያ ክልል የሚደረጉ ግጭቶችን ማስቆም፣ ትግራይ ዉስጥ ዘላቂ ሠላም ማስፈን፣ የኑሮ ዉድነትን መቆጣጠር አልቻለም።ወይም አልፈለገም
ጭቆና፤ ግፍና በደልን መሸከም የለመደዉ ኢትዮጵያዊ የግጭት፣ ዉዝግብ፣ የኤኮኖሚ ቀዉስ መባባስ፣ መራዘም ወይም መደራረብ እስካሁን ብዙም ያንገሸገሸዉ አልመሰለም።መከረኛዉ ሕዝብ የሐገር ዉስጡ ግጭት፣ዉዝግብ፣የኤኮኖሚ ቀዉስ አልበቃ ብሎት ሰሞኑን ደግሞ የአዲስና አበባና የአስመሮችን የቃላት እንኪያ ሰላንቲያን ክረት-ርግበት ማማተር ግን ሆኖበታል።
ከ2010 አጋማሽ ጀምረዉ በየአደባባዩ ሲተቃቀፉ፣ ሲወዳደሱ፣ ሲሞጋገሱ የነበሩት የአዲስ አበባና የአስመራ መሪዎች ለመፋቀራቸዉ ትክክለኛዉን ምክንያት ለየሕዝባቸዉ እንዳላሰወቁ ሁሉ አሁን ለመቃቃራቸዉም ምክንያታቸዉን አልተናገሩም።
በማያዉቀዉ ምክንያት ሲፋቀሩ ያጨበጨበ፣የዘመረዉ ሕዝብ በማያዉቀዉ ምክንያት ሲቃቃሩ ሕይወት፣አካል ደም ሐብቱን ለመገበር ይገደዳል።ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ ሞቃዲሾን በጎበኙ በሁለተኛዉ ቀን የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አዉጪ ግንባር (ONLF) ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የሚያደርገዉን ድርድርና ግንኙነት ማቋረጡን አስታዉቋል።
ONLF ባለፈዉ ቅዳሜ ባሠራጨዉ መግለጫ እንደሚለዉ የኢትዮጵያ መንግሥት እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር በ2018 ከግንባሩ ጋር የተፈራረሙን ሥምነት አፍርሷል።የፌዳራሉ መንግስትና የሶማሌ ክልላዊ መንግስት የግንባሩን ስም አጥፍተዋል።እንቅስቃሴዎቹን አግደዋል፣ አባላቱን አንገላትተዋል።በዚሕም ምክንያት «የሶማሌ ሕዝብ የራሱን እድል ራሱ የመወሰን መብቱ እንዲከበር፣ ፍትሕና ክብር እንዲያገኝ» ይላል መግለጫዉ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አዉጪ ግንባር የተለያዩ አማራጮችን ይፈልጋል።
የአፍሪቃ ቀንድ መሪዎች ሁሉምና ከሁሉም በላይ ናቸዉ
የአዲስ አበባ-ሞቃዲሾዎች ጠብ ባፍታ በወዳጅነት መለወጡ፣ የአዲስ አበባ አስመሮች ወዳጅነት በዉዝግብ መቀየሩ፣ የONLF መግለጫ፣ ኬንያ ከሱዳን ተፋላሚዎች አንዱን በግልፅ ማደራጀቷ---የአፍሪቃ ቀንድ ጤና ለማጣቱ ምሥክር ነዉ።ግን ለምን? እንደገና ዶክተር አብዲ
«የመንግሥታት ዴሞክራቲክ አለመሆን።በሕዝቦችና በኢስቲቱሽን አናላይዝድ የሆነ አካሔድ የሌለበት ቀጠና ነዉ። እና መንግስታት በመሪዎች ሥብዕና፣ የፖለቲካ ፍላጎትና የወደፊት ምኞች ላይ መሰረት ያደረገ አካሔድ ነዉ እየተኬደ ያለዉ----»
የሞቃዲሾዉ ዓለም አቀፍ አዉሮፕላን ማረፊያ በመጀመሪያዉ የሶማሊያ ፕሬዝደንት በአደን አብዱሌ ዑመር ስም ነዉ የተሰየመዉ።አደን አዴ ተብሎ።አደን አብዱሌ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ሐምሌ 1፣1960 በሕዝብ ተመርጠዉ ሥልጣን ያዙ።አብዱሌ የተከተሉት የኤኮኖሚ መርሕ አዲሲቱን ሶማሊያን የአፍሪቃ ስዊዘርላንድ የሚል ቅፅል አሰጥቷን ነበር።
ፕሬዝደንት አብዱሌ ሐምሌ 6፣ 1967 በተደረገዉ ምርጫ በሸርማርኬ ተሸነፉ።አብዱሌ ምንም ሳያንገራግሩ ሥልጣናቸዉን አስረክበዉ ከቪላ ሞቃዲሾ ወጡ።በአፍሪቃ ታሪክ በምርጫ የተሸነፈ መሪ ሥልጣኑን ሲያስረክብ ከላይቤሪያ ቀጥሎ አብዱሌ ሁለተኛዉ ናቸዉ።ዛሬ ከ65 ዓመት በኋላ ሶማሊያ፣ ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን ዴሞክራሲን ያዉቁት ይሆን?
ነጋሽ መሐመድ
ታምራት ዲንሳ