ማሕደረ ዜና፣ የኢራን-አሜሪካ ድርድር ጠብ-ግጭቱን ያበርድ ይሆን?
ሰኞ፣ ሚያዝያ 6 2017በ1967 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) በዩናይትድ ስቴትስ ሙሉ ድጋፍና ፈቃድ ተጀመረ።የኢራን የኑክሌር መርሐ-ግብር። በ2015 በዩናይትድ ስቴትስ መሪነት፣ በምዕራብ አዉሮጶች ትብብር፣ በሩሲያና ቻይና ተሳትፎ፣ በኢራን ፈቃድ መርሐ-ግብሩ እንዲቆም ተስማሙ።በ2018 በዩናይትድ ስቴትስ ዉሳኔ-ስምምነቱ ተሻረ።ዩናይትድ ስቴትስ ተባባሪ፣ተከታይ፣ተሳታፊዎችን ጥላ ስምምነቱን ብቻዋን እንዳፈረሰችዉ ሁሉ ዘንድሮ ብቻዋን ኢራንን ጠይቃ፣አስፈራርታና ዝታ የዋሽግተንና የቴሕራን ባለሥልጣናት አዲስ ድርድር ጀመሩ።ሊቀጥሉም ተስማሙ።ይግባቡ ይሆን?አዲሱ ድርድር መነሻ፣ የዋሽንግተን-ቴሕራን ወዳጅ-ጠላትነት ቁንፅል ታሪክ ማጣቀሻ---የሊቢያ አብነት መድረሻችን ነዉ።
የኢራን ሥርዓት፣ የምዕራባዉያን ዉግዘትና አፀፋዉ
የፈረንሳይ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዤን-ኖኤል ባሮ እንዳሉት ዛሬ ላክሰምበርግ ላይ ተሰየመዉ የአዉሮጳ ሕብረት የዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ምክር ቤት በኢራን ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ በመጣሉ ፓሪሶች ተደስተዋል።
«ኢራንን በተመለከተ የፖለቲካ እስረኞችን አያያዝ መርሕን በሚወስኑ ወገኖች ላይ ማዕቀብ እንዲጣል እንወስናለን።ማዕቀቡ እንዲጣል ባለፈዉ የምክር ቤቱ ስብሰባችን ላይ ሐሳብ አቅርቤ ነበር።ዛሬ የሺራዝ ወሕኒ ቤትን ጨምሮ በሰባት ሰዎችና በሁለት ተቋማት ላይ ማዕቀብ እንዲጣል በመስማማታችን ተደስቻለሁ።እርምጃዉ ወቅታዊ ነዉ።ምክንያቱም አንዳድ የፈረንሳይና የአዉሮጳ ዜጎች የታሰሩበት ሁኔታ በጣም አሳፋሪ፣ በዓለም አቀፍ ህግ ከማሰቃየት የሚቆጠር ነዉ።»
የፈረንሳዩ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር እንዳሉት የኢራን ገዢዎች ተቃዋሚዎቻቸዉን የሚያስሩ፣ የሚያሰቃዩ፣ ዓለም አቀፍ ሕግጋትን የሚጥሱ፣ ጨቋኞች ይሆኑ ይሆናል።ጨቋኙን የአያቶላሆች ሥርዓት የመሠረቱና የመሩት አያቶላሕ ሩሆላሕ ሆሚኒይና ተከታዮቻቸዉ የቴሕራንን ቤተ-መንግስት የተቆጣጠሩት በፈረንሳዮች ድጋፍና ይሁንታ መሆኑን የፈረንሳዩ ከፍተኛ ዲፕሎማት አለመጥቀሳቸዉ እንጂ የሐቅ ፈላጊዉ ሕቅታ።
ዩናይትድ ስቴትስ መራሹ ዓለም የኢራን አያቶላሆችን ሥርዓት ጨቋኝነት፣ሰብአዊ መብት፣ ፍትሕና ዴሞክራሲያዊ ጥያቄን ረጋጭነት ባወገዘ-ባወሳ ቁጥር ብዙዎቹ የኢራን ጉዳይ ተንታኞች ደጋግመዉ እንደሚሉት ኢራኖች ዴምክራሲያዊ ሥርዓትን በ1952 ጀምረዉት ነበር።በሕዝብ የሚወደዱ፣ በምክር ቤት የተመረጡ፣ ፍትሐዊ ሥርዓትን ለማስፈን አንድ-ሁለት ያሉትን ጠቅላይ ሚንስትር መሐመድ ሞሳዴግን በመፈንቅለ መንግስት ከሥልጣን አስወግደዉ የሻሕ መሐመድ ሬዛ ፓሕሌቭን ዙፋን ያጠናከሩት አሜሪካና ብሪታኒያ ነበሩ።
ለዋሽግተን-ቴልአቪቭ ተባባሪዎችና ለቴሕራኖች የረጅም ጊዜ ጠብ፣ ቁርቁስ፣ በቅርብ ዓመታት ደግሞ ኢራቅን፣ ሶሪያን፣ጋዛን፣ ሊባኖስን፣ የመንን ለሚያወድመዉ ተዘዋዋሪ ጦርነት ምክንያቱ ዓለምን በበላይነት የመግዛት ፍትጊያ፣ የጥቅም ሽሚያ፣ የርዕዮተ ዓለም ልዩነት ወዘተ እየተባለ የሚዘረዝር ብዙ ነዉ።አንዱ ምናልባትም ግልፅ ምክንያት የሚሰጥበት ቴሕራኖች አንድ ቀን አዉዳሚዉን ጦር መሳሪያ ከታጠቁ ለአሜሪካና ለተከታዮችዋ በቀላሉ አይገዙም የሚለዉ ሥጋት መሆኑን ለማወቅ ግን በርግጥ ተንታኝ አያስፈልግም።
ኢራን መዘዘኛዉን የኑኬሌር መርሐ ግብርን በ1967 የጀመረችዉ በዩናይትድ ስቴትስ የቴክኖሎጂ፣ ዕዉቀት፣ ፖለቲካዊ ድጋፍና ፈቃድ ነዉ።ዩናይትድ ስቴትስ አዉቶሚክ ለሰላም በምትለዉ መርሐ መሠረት ለኢራን የፈቀደችዉ የኑክሌር መርሐ-ግብር በጥናትና ምርምር ሲጥመለመል ዋሽግተንና የአዉሮጳ-አረብ-እስራኤል ተባባሪዎች አቅፈዉና ደግፈዉ ያኖሯቸዉ የሻሕ ሥርዓት ተወገደ።1979።
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ትናንት «የተለያዩ ቡድናት» ያሏቸዉን የኢራን መንግስት ተቃዋሚዎችን አነጋግረዋል።
«ኢራንንም በሚመለከት እሱም ሌላ መንገድ ነዉ።ከኢራን የተለያዩ ቡድናት ሰዎች ጋር ተገናኝቻለሁ።በኢራን ጉዳይ በጣም በፍጥነት እንወስናለን።»
የሙጃህዲያን ኢ-ኻሊቅ (MEK)ን ሚና
ትራምፕ የሚወስኑትን ጉዳይ ምንነት፣ ያነጋገሯቸዉ ሰዎች የሚወክሏቸዉን ቡድናት ማንነት አልተናገሩም።ከ1960ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ የኢራን-አሜሪካ-እስራኤል-ምዕራባዉያንን ወዳጅ-ጠላትነት፣ የኢራን እስላማዊ አብዮትን ሒደት፣ የኢራን-ኢራቅን ረጅም ጦርነትም ሆነ ኢራንን የኑክሌር መርሐ ግብርን የሚያዉቅ ወይም ማወቅ የሚሻ የሙጃህዲያን ኢ-ኻሊቅ (MEK)ን ሚና ካላጤና በርግጥ ዕዉቀት-ፍላጎቱ የተሟላ አይሆንም።
በ1965 ሐኒፍነጂድና ባዲዛዳገን የተባሉት የቴሕራን ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የመሠረቱት የፖለቲካ ፓርቲ ከጅምሩ የሻሁን ሥርዓት ለማስወገድ፣አሜሪካንን ጫና ለማጥፋት፣ ብዝበዛና ጭቆናን ለማስወገድ ያለመ ነበር።ቡድኑ ኾሜይኒ ከሚመሯቸዉ እስላማዊ አብዮተኖች ጋር ተባብሮ በ1979 የሻሁን ሥርዓት አስወገደ። በ1980ዎቹ ከአዲሶቹ ገዢዎች ጋር ተጣልቶ ከኢራቅ ጋር አብሮ ይወጋቸዉ ያዘ፣ ከኢራቆች ጋር የመሠረተዉ ወዳጅነት ሲፈርስ፣ ሊያጠፋቸዉ ከዛተባቸዉ፣ ከተዋጋ፣ እነሱም በአሸባሪነት ከፈረጁት ከዩናይትድ ስቴትስ-እስራኤልና ምዕራብ ምዕራዉያን ጋር ተወዳጀ።
የሙጃህዲያን ኢ-ኻሊቅ (MEK)ና የቡድኑ ምክር ቤት መሪዎች ኢራን በ1967 ከአሜሪካ ባገኘችዉ ድጋፍ የጀመረችዉን የኑክሌር መርሐ ግብርን ወደ ኑክሌር ቦምብ መስሪያነት ለመቀየር ናታንዝና አራክ ዉስጥ በድብቅ እያብላላች መሆኑን ለዓለም አረዱ።ወይም አበሰሩ።ነሐሴ 2003።ዋሽግተን።
ሲሞን ሔርሽና ኮኒ ብሩክ የተባሉት መርማሪ ጋዜጠኞች እንደፀፋት የሙጃህዲያን ኢ-ኻሊቅ መሪዎች የቴሕራኖችን ሚስጥር እንዲያጋልጡ የገፋፏችዉ መረጃዉንም የሰጧቸዉ የእስራኤል ባለሥልጣናት ናቸዉ።መረጃዉ ከየትም መጣ ከየት በ2001 አፍቃኒስታንን፣በ2003 ኢራቅን ወርረዉ በጦርነት ማግሥት ከጦርነት የተመሠጉት የፕሬዝደንት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ መስተዳድርና ተባባሪዎቹ የተቀረዉን ዓለም ከጎናቸዉ ለማሰለፍ መረጃዉን ከማራገብ፣ ቴሕራኖችን ከማስፈራራት አንዳዴም ከማባበል ባለፍ ሶስተኛ የዉጊያ ግንባር መክፈት በርግጥ አልቻሉም።
በኢራን ላይ የሚጣለዉ ማዕቀብ እየተደራረበ፣ ዉዝግብ፣ ዛቻ፣ ቀጥታና ተዘዋዋሪ ግጭት ጦርነት፣ ግድያዉም እንደናረ ቀጠለ።ሙጃህዲያን ኢ-ኻሊቅና እስራኤል ባያምኑም ብዙዎች እንደሚሉት አንዳቸዉ ከሌላቸዉ ጋር መረጃ እየተመጋገቡ በርካታ የኢራን ሳይቲስቶችን ገደሉ።የዚያኑ ያክል የዩናይትድ ስቴትስ የቅርብ ወዳጆች ብሪታንያ፣ ፈረንሳይና ጀርመን ከኢራን ጋር ይደራደሩ ነበር።
የድርድር-ሥምምነት፣ የማዕቀብ፣ የዛቻ ቁርቁስ ድርድሩ አዙሪት
በሰበብ አስባቡ ደንበር-ገተር የሚለዉ የቴሕራን አዉሮጶች ድርድር ሁነኛ ዉጤት ባያመጣም በድርድሩ ዩናይትድ ስቴትስ፣ የአዉሮጳ ሕብረት፣ ሩሲያና ቻይና እንዲካፈሉበት መሠረት መጣሉ በ2015 ለተደረገዉ ስምምነትም እገዛ ማድረጉ አይካድም።ስምምቱን ብዙዎች ቢደግፉትም እስራኤልና ሳዑዲ አረቢያን የመሳሰሉ የዩናይትድ ስቴትስ የቅርብ ወዳጆችና ዶናልድ ትራምን የመሳሰሉ የአሜሪካ ቀኝ ፅንፈኛ ፖለቲከኞች አልተቀበሉትም።
ዓለም ዩናይትድ ስቴትስን አስቀድማ በዩናይትድ ስቴትስ ፍላጎት፣ፈቃድና ይሁንታ እንድተመራ የሚፈልጉት ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የፕሬዝደንት ኦባማ መስተዳድር የተስማማበትን፣ ብዙዎች የደገፉ፣ያደነቁትን ስምምነት አሽቀንጥረዉ ጣሉት።ግንቦት 8፣ 2018።
«ስምምነቱ ደካማ ድርድር ነዉ የተደረገበት።ኢራን ሥምምነቱን ሙሉ በሙሉ ብታከብርዉ እንኳን ሥርዓቱ ባጭር ጊዜ ዉስጥ ኑክሌር ለመታጠቅ ተቃርቧል።ስምምነቱ ያስቀመጠዉ የጊዜ ገደብ ደንብ ተቀባይነት የለዉም።ይሕ ስምምነት ባለበት እንዲቀጥል ከፈቀድሁ፣ መካከለኛዉ ምሥራቅ ዉስጥ የኑክሌር ጦር መሳሪያ እሽቅድምድም ይጀመራል።ሥለዚሕ ዩናይትድ ስቴትስ ከኢራን የኑክሌር ስምምነት መዉጣትዋን ዛሬ አስታዉቃለሁ።»
«አጭር ጊዜ» ስንት ሰዓት፣ ሥንት ቀን፣ ሥንት ዓመትስ ይሆን? ትራምፕ ያዉቁታል።ኢራን ስምምነቱን አከበረችም ጣሰች «ባጭር ጊዜ ትታጠቀዋለች» ያሉት የኑክሌር ቦምብ ግን ዘንድሮም በሰባተኛ ዓመቱ የለም።ከ2015 ስምምነት በፊት የነበረዉ ድርድር ግን ከያኔ ተደራዳሪዎች ብሪታንያ፣ፈረንሳይ፣ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ጀርመንና የአዉሮጳ ሕብረትን አግልሎ በዋሽግተንና በቴሕራን ባለሥልጣናት መካከል እንዳዲስ ተጀምሯል።
የኢራን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አባስ አራግቺ እና የዩናይትድ ስቴትስ የመካከለኛዉ ምሥራቅ ጉዳይ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ባለፈዉ ቅዳሜ ኦማን ዉስጥ ያደረጉት የስማበለዉ ድርድር የፈጀዉ ጊዜ 2፣ተኩል ነዉ።በድርድሩ ማብቂያ የሁለቱ ሐገራት ባለሥልጣናት ላጭር ጊዜ ሠላምታ ተለዋዉጠዋልም። ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የልዩ መልዕክተኛቸዉን ዘገባ ከደመጡ በኋላ ትናንት እንዳሉት ድርድሩ ጥሩ ነዉ።
«ከሆነ ዉጤት ላይ እስከምትድረስ (መናገር) ብዙ ጥቅም የለዉም።ብዙም መናገር አልፈልግም።ግን ጥሩ ይሆናል።የኢራን ሁኔታ በጣም ጥሩ ይሆናል።»
የኢራን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አባስ አራግቺ ለድርድር፣ ዉይይት አዲስ አይደሉም። ቅዳሜ እንደ ሚንስትር ያደረጉትን ድርድርም «ገንቢ» ብለዉታል።
«እንደ መጀመሪያ ዙር ገንቢ ግንኙነት ነበር።የተደረገዉ በጣም በተረጋጋና በመከባበር መንፈስ ነዉ። ያልተገባ ቋንቋ አልተነገረም።ሁለታችንም ወገኖች፣ በሁለቱም ወገን ተቀባይነት ያለዉ ስምምነት ላይ እስኪደረስ ድረስ ድርድሩን በእኩልነት ደረጃ ለመቀጠል ሁለታችንም ተስማምተናል።»
ቀጣዩ ድርድር የፊታችን ቅዳሜ ሮም ይደረጋል ተብሏል።
የኔታንያሁ ቅደመ ግዴታ፣ ሊቢያ አብነት
የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕኢራን የቀረበላትን የቀጥታና የአንድ-ለአንድ ድርድር ጥያቄ ካልተቀበለች አሜሪካ እንደምትወራት ሲያስጠነቅቁ ነበር።የቅዳሜዉ ድርድር የተደረገዉ ቀጠታ አይደለም በሥማበለዉ እንጂ።ትራምፕ በኢራንን ላይ በሚዝቱበት መሐል ዋይት ሐዉስን የጎበኙት የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቢኒያሚን ኔታንያሁ ከኢራን ጋር የሚደረገዉ ድርድር ለስምምነት ከበቃ ስምምነቱ «የሊቢያን የኑክሌር መርሐ ግብርና የአዉዳሚ ጦር መሳሪያዎችና ያስቆመዉ ዓይነት መሆን አለበት።» ብለዋል
የቴሕራኑ ዳግማዊ ሰይፍ አል ኢስላም ቃዛፊ ማንነት አይታወቅም።የትሪፖሊዉ ሰይፍ አል ኢስላም ግን አባቱ አብዝተዉ የሚወዱት፣ ለንደን እስኩል ኦፍ ኤኮኖሚስት የተማረ፣የዓለም የኤኮኖሚ መድረክ የሸለዉ፣ከ2000 ጀምሮ በምዕራባዉያን ዘንድ ለዉጥ አራማጅ እየተባለ ይወደስ፣ይሞገስ፣ ይደነቅ ነበር።አልጋቸዉን ሊያወርሱት ተዘጋጅተዋል የሚባሉትን አባቱን አግባብቶ ሊቢያ የነበራትን የኑክሌር መርሐ ግብር በሙሉ ዘጋች።አዉዳሚ ጦር መሳሪያዎችዋን በሙሉ ለአለም የአዉቶሚክ ተቆጣጣሪ ድርጅት አስረከበች።በ2003።
በ8ኛ ዓመቱ የምዕራባዉያኑ የጦር ተሻራኪ ድርጅት (ኔቶ) ጦር የሰይፍ አል-ኢሳላምን ወድሞች፣ቤተሰብና ዘመዶችን አንድ በአንድ ገደለ።በስተመጨረሻ በኔቶ የሚደገፉት የሊቢያ አማፂያን የትሪፖሊዉን የ40 ዘመን ጠንካራ ገዢ ሙዓመር ቃዛፊን ሲርት አጠገብ ጭዳ አደረጓቸዉ-ጥቅምት 2011።ሰይፍ አል ኢስላም ለዓመታት በየበረሐ፣አሸዋ፣ጉድባዉ ሲሽለኮለክ ቆየ።ታሰረ።ሞት ተፈረደበት።ተሻረለት።ተፈታም።አሁንም በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ይታደናል።ሊቢያም ፈረሰች።
ኢራንስ ኔታንያሁ እንዳሉት ዳግማዊት ሊቢያ ትሆን ይሆን?
ነጋሽ መሐመድ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር