ማሕደረ ዜና፣ የትራምፕ መርሕ፣ርምጃና ዉሳኔ ልማት ወይስ ጥፋት
ሰኞ፣ የካቲት 3 2017የአዉሮጳ ሥልጣኔ፣ ሐብት፣ ጉልበት መሠረት የሆነችዉ ሮማ «በአንድ ቀን አልተገነባችም» ይላሉ አዋቂዎች።ባንድ ቀን አልፈረሰችምም።ለሮማ ጥንካሬ፣ ዓለምን ላስገበረ፣ ለማረከ ሐብት ጉልበት ዕዉቀቷ መጠርቃት ከጋዩስ ኦክታቪዮስ ቱሪኑስ (አጉስቶስ) እስከ አንቶኒኑስ ፒዮስ የነበሩ በርካታ ገዢዎችዋ እንደሚወደሱ ሁሉ ለዉድቀትዋ ከሉቺዩስ ኤሊዉስ ኮሞዱስ እስከ ኔሮ ክላዉዲዉስ አጉስቱስ ጀርማኒኩስ ያሉት ይወቀሳሉ።እንደ ጥንታዊቱ ሮማ ሁሉ የዘመኑን ዓለም የመሪነት ልዕልና የተቆጣጠረችዉ ዩናይትድ ስቴትስ በዕለታትና በጥቂቶች አልተገነባችም።ተወዳጅ ፖለቲካዊ ሥርዓቷ፣ አስፈሪ ጉልበቷ፣ አማላይ ዕዉቀት፣ ሐብቷም አሁንም እንዳለ ነዉ።የ47ኛ ፕሬዝደንቷ መርሕና እርምጃ ግን ለዘመናችን ከአጉስቶስ ይልቅ ወደ ኮሞዱስ እንዳያዳላ አዋቂዎችን እያሰጋ ነዉ።የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የሰሞኑ ጥቅል መርሕ ዉሳኔና ተቃዉሞዉ መነሻ፣ ንፅፅሩ ማጣቃሻ እንድምታዉ መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።
የአሜሪካ ወርቃ ዘመን
ጥር 20፣ 2025 (ዘመኑ በሙሉ እግአ ነዉ) 45ኛዉ የአሜሪካ ፕሬዝደንት 47ኛዉ ሆነዉ ዳግም ሥልጣን ያዙ።የአሜሪካ ወርቃማ ዘመን ተጀመረ አሉም።
«የአሜሪካ ወርቃማ ዘመን አሁን ተጀመረ።ከዛሬ ጀምሮ ሐገራችን ትጎመራለች፣ በመላዉ ዓለም ትከበራለች።ሁሉም መንግስታት የሚቀኑብን እንሆናለ።»
ቱጃሩ ፖለቲከኛ የጀርመን-ስኮትላንድ ስደተኞች ልጅ ወይም የልጅ ልጅ ናቸዉ።የአሜሪካንን ወርቃማ ዘመን ለማንፀባረቅ የመጀመሪያ ኢላማቸዉ ያደረጉትን ግን ሥደተኞችን ነዉ።በየሐገራቸዉ ከሚደርስባቸዉ ጥቃት፣ግፍና በደል አሜሪካንን እንደ መሸሸጊያ ቆጥረዉ ወይም እንደ ጥሩ የኑሮ አማራጭ ጓጉተዉ፣ ወደዉ፣ሰርተዉ ለመኖር አልመዉ የተሰደዱ የዉጪ ዜጎችን «ሕገ ወጥ እያሉ እያስጋዙ ነዉ።
አሜሪካ ሁሉም የሚቀናባት ሐገር የማድረግ እርምጃ
ዩናይትድ ስቴትስን ሁሉም የሚቀናባት ሐገር ለማድረግ ዕቅዳቸዉ ስኬት ደግሞ ፣ አሜሪካ የዓለም ዕዉቀት፣ ሥልጣኔ መሪ ለመሆኗ በአብነት ለሚጠቀሱ ዩኒቨርስቲዎቿ መንግስት ለምርምርና ጥናት ይሰጥ የነበረዉን 4 ቢሊዮን ዶላር ድጎማን አቋርጠዋል።በ2015 ፓሪስ የተፈረመዉን የዓይር ንብረት ለዉጥ ዓለም አቀፍ ስምምነትን አፍርሰዋል።
ዩናይትድ ስቴትስን ከዓለም ጤና ድርጅት አባልነት አዉጥተዋል።ከ1960ዎቹ ጀምሮ የዩናይትድ ስቴትስ ደግ-ለጋሽነት አብነት፣ የአሜሪካ መታወቂያ-መመስገኛ የነበረዉን የርዳታ ድርጅት USAIDን ዘግተዋል።ዝርዝሩ ይቀጥላል።የብዙዉ ዉሳኔ-እርምጃ ዕቅዳቸዉ መሠረት ግን ትራምፕ እንደሚሉት የአሜሪካን ከማንም በላይ ማስቀደም ነዉ።
«በትራምፕ አስዳደር ዘመን በእያንዳዷ ቀን አሜሪካን አስቀድማለሁ።»
አሜሪካ ትቅደም ተደነቀ።ተጨበጨበለትም።
«ሉዓላዊነታችን ዳግም ይረጋገጣል።ደሕንነታችንም ይከበራል።»
ግሪንላንድን መማረክ፣ ካናዳን መጠቅለል፣ ፓናማ ቦይን---
የአሜሪካ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ፣ ግሪንላንድን ከዴንማርክ፣ የፓናማ ቦይን ከፓናማ ለመቀማት፣ ካናዳን ለመጠቅለል የሜክሲኮ ሰላጤን በአሜሪካ ሥም ለመሰየም እየዛቱ ነዉ።
«ምክንያቱም ይበልጥ ታላቅ፣ ጠንካራ፣የተሻለ እና አስተማማኝ ያደርገናል።ግሪንላንድ ለብሔራዊ ደሕንነታችን፣ለዓለም ደሕንነት፣ለዓለም ሠላም ታስፈልገናለች።ይሕን ማድርግ አለብን።ከናዳን በተመለከተ ምን ማድረግ እንዳለብን እናያለን።ይሁንና የካናዳ ሕዝብ የሚከፍለዉ ግብር ትንሽ ነዉ።ብዙ አይከፍልም።ለጦር ኃይል ብዙ አይከፍሉም።ብዙ ግብር የማይከፍሉት በነሱ ላይ ሊደርስ ከሚችለዉን ጥቃት እኛ (አሜሪካኖች) ይከላከሉልናል ብለዉ ሥለሚያስቡ ነዉ።»
ከ177 ቅድመ ልደተ ክርስቶስ እስከ 192 ታላቁን የሮማ ኢምፓየር የገዛዉ ቄሳር ሉቺዩስ ኤሊዉስ ኮሞዱስ የታሪክ አዋቂዎች እንደሚሉት ሮማን ይበልጥ ታላቅ ለማድረግ በሚል ፈሊጥ የጦር ጄኔራሎቹን፣የፖለቲካ አዋቂዎች ምክር፣ የሕግ መወሰኛ (ሴኔቱም) ሐሳብ አሽቀንጥሮ ጥሎት ነበር ይላሉ።
በየሥፍራዉ ያቆማቸዉ ሐዉልታት የፈጣሪ-መሰል ሥልጣን ባለቤት፣ በአካል ብቃት፣ ጉልበት ጥንካሬዉ የማይበገር-ከፊል መልዕክ-ከፊል ሰዉ ብጤ ያስመስሉትም ነበር።የእብሪት፣ ማን አሕሎኝነት፣ግለኝነት፣ የአይበገሬነት ቅዠቱ እንደ ዘመኑ የፖለቲካ እርምጃ ታላቁን ቄሳር ሲያስገድል-የታላቂቱ ሮማ ዉድቀትም ይጣደፍ ያዘ።
ዶናልድ ትራምፕ በርግጥ ኮሞዱስን ዓይደሉም።የሚሉ የሚያደርጉትም ደጋግመዉ እንዳሉት አሜሪካን ይበልጥ ታላቅ፣አንደኛ፣ የታፈረችና የተከበረች ለማድረግ ነዉ።ለዚሕ ሕልም ይባል ቅዠታቸዉ ስኬት ሲሻቸዉ ግዛት፣ ሲያሰኛቸዉ ስም ለመቀማት እየዛቱ፣ ሲፈልጋቸዉ የሚጋዙ ሥደተኞችን እንዲቀበሉ እያስፈራሩ ደግሞ ሌላ ጊዜ ቀረጥ እየጨመሩ አሜሪካንን ካናዳ፣ ሜክሲኮ፣ ኮሎምቢያ፣ ፓናማ ከመሳሰሉ የቅርብ፣ ታማኝ ጎረቤቶቿ ጋር እያላተሟት ነዉ።
ትራምፕ በካናዳና ሜክሲኮ ሸቀጦች ላይ የጣሉት ጭማሪ ግብር አፀፋ ርምጃ ካስከተለ በኋላ ለጊዜዉ ቆሟል።ይሁንና የካናዳ ጠቅላይ ሚንስትር ጁስቲን ትሩዶዉ እንዳሉት ለትራምፕ የመጨረሻዉ መፍትሔ ካናዳን መጠቅለል ነዉ።
«ትራምፕ በአዕምሯቸዉ ያለዉ ቀላሉ መንገድ ሐገራችንን መዋጥ ነዉ።ይኽ አስተሳሰባቸዉ እዉነት መሆኑን ከሳቸዉ ጋር ባደረግሁት ንግግር ተረድቻለሁ።»
ካናዳ የአሜሪካ የቅርብ ጎረቤት ብቻ ሳትሆን፣ አሜሪካ የምትመራዉ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ)፣ የቡድን ሰባትና የሌሎች ድርጅቶችና ማሕበራትም አባል ናት።ግሪንላንድ የዴንማርክ ግዛት ናት።ዴንማርክ የኔቶ አባል ናት።
ፍልስጤሞችን ከጋዛ ማሰደድ-ጋዛን መግዛት
ለፍልስጤምና እስራኤሎች የዘመነ- ዘመናት ጠብእንደ ዓለም ልዕለ ኃያል፣ ሥልጡን ሐገር መሪ አግባቢ መፍትሔ ሲጠበቅባቸዉ ስደተኞችን ከሐገራቸዉ የሚያስግዙት ትራምፕ፣ ፍልስጤሞች ከጋዛ ሰርጥ እንዲሰደዱ ጠየቁ።የቅኝ ገዢዎች በደል፣ ግፍና ምዝበራ በሚወገዝ፣በሚኮነን፣በሚነቀፍበት በ21ኛዉ ክፍለ ዘመን ጋዛን ለመግዛት መቁረጣቸዉን አስታወቁ።
»ጋዛን ለመግዛትና ባለቤት ለመሆን ቆርጫለሁ።ዳግም ግንባታን በተመለከተ ከግዛቲቱ ከፊል የመካከለኛዉ ምሥራቅ ሐገራት እንዲገነቡ እስንሰጣቸዉ ይሆናል።ሌሎች ወገኖች በኛ የበላይነት ሊያደርጉት ይችላሉ።እኛ ለመቆጣጠር ቆርጠናል፣ እንወስደዉና ሐማስ ዳግም ወደ አካባቢዉ እንዳይመለስ እናደርጋለን።ሥፍራዉ ሰዉ የሚመለስበት አይደለም።የፍርስራሽ ሥፍራ ነዉ።»
ሰዉ የሚመለስበት ሥፍራ ካልሆነ ሐማስ እንዴት ይመለስበታል።ወይስ ሐማስ የሰዎች ስብስብ አይደለ ይሆን? ትራምፕ ምን ተስኗቸዉ።ፍልስጤሞችን የማሰደድ፣ ጋዛን የመግዛት ዕቅዳቸዉን ግን ከእስራኤል መሪዎች በስተቀር የአረብ፣የቱርክ፣ የፋርስ፣ የአዉሮጳ መንግሥታት በግልፅ ተቃዉመዉታል።እስራኤል በ1948 ሥትመሠረት በ5 ዓመት እድሜያቸዉ ከትዉልድ መንደራቸዉ ተፈናቅለዉ ዛሬም ካንዱ መጠለያ ጣቢያ ወደ ሌላዉ የሚንከራተቱት የጋዛዉ ነዋሪ ሙስጠፋ አል ጋዛር ግን ሁሉንም አሉት።
«ለሚስተር ትራምፕ የምነግረዉ መፍትሔ አለሕ ብዬ ነዉ።መፍትሔዉ እኛን ከማሰደድ ይልቅ የሁለት መንግሥታት መፍትሔ ነዉ።ወደ ተወለድኩባት ሐገሬ እመለሳለሁ።እዚያዉ እሞታለሁ።ወደ ሌላ ሐገር ጨርሶ አልሔድም።የተፈጠርነዉ እዚሕ ነዉ።እዚችዉ ምድር እንሞታለን።»
ደቡብ አፍሪቃ በእርዳታ፣ ICCን በማዕቀብ መቅጣት
ሰዬዉ በዚሕ አላበቁም።የደቡብ አፍሪቃ መንግሥት የሐገሪቱን የመሬት ሐብት በፍትሐዊ መንገድ ለማከፋፈል ያወጣዉን ሕግ በመቃወም ዩናይትድ ስቴትስ ለደቡብ አፍሪቃ የምትሰጠዉ ርዳታ እንዲቋረጥ ወስነዋል።
በአፓርት ሐይድ ሥርዓት በጥቂት ነጭ አገዛዝ ሲረገጥ፣ ሲገደል፣ በድሕነት ሲማቅቅ ዘመናት ያስቆጠረዉ ጥቁርና ክልስ ደቡብ አፍሪቃዊ ከሐገሪቱ ሕዝብ 96 ከመቶ ይሆናል።ነጩ 4 በመቶ።ከሐገሪቱ ለም መሬት ጥቁሩ የሚያስተዳድረዉ ግን 5 በመቶ ነዉ።የተቀረዉን የሚቆጣጠሩት አንድም መንግሥት አለያም ነጮቹ ናቸዉ።
የደቡብ አፍሪቃ መንግሥት እንደሚለዉ ባለፈዉ ጥር የፀደቀዉ የመሬት ይዞታ ማሻሻያ ሕግ በአብዛኛዉ መንግሥት ከሚቆጣጠረዉና እስካሁን ካልለማዉ መሬት የተወሰነዉ መሬት ለሌላቸዉ የሐገሪቱ ጥቁር ዜጎች እንዲከፋፈል የሚፈቅድ ነዉ።
በነጭ ዘረኞች አገዛዝ ዘመን ደቡብ አፍሪቃ ተወልዶ ያደገዉአሜሪካዊ ቱጃር ኤሎን ማስክ የሚያማክራቸዉ ዶናልድ ትራምፕ የደቡብ አፍሪቃ ነጮች ሐብታቸዉ «ተወረሰ» አሉ፣ ተጨቆኑ፣ ተገፉ፣ ተበደሉ።
«ደቡብ አፍሪቃ ዉስጥ በጣም መጥፎ ነገር እየተፈፀመ ነዉ።መሪዎቹ መጥፎ ነገር፣ ዘግናኝ ነገር እያደረጉ ነዉ።ጉዳዩን እየተመረመረ ነዉ።ከተጣራ በኋላ ደቡብ አፍሪቃ የምታደርገዉን በትክክል እናዉቃለን።መሬት እየወሰዱ፣ እየወረሱ ነዉ።ከዚሕ የባሰ ነገርም እያደረጉ ሳይሆን አይቀርም።»
ባይጣራም፣ ባይመረመርም እርምጃዉ መጥፎና ዘግናኝ መሆኑን መረዳት ለታላቂቱ ሐገር ታላቅ መሪ አልገደደም።እና ዩናይትድ ስቴትስ ለደቡብ አፍሪቃ የኤድስና የሳንባ ነቀርሳ ሕሙማን የምትሰጠዉን ርዳታ አቆሙ።
የደቡብ አፍሪቃዉ የማዕድንና የነዳጅ ሐብት ሚንስትር ለትራምፕ ርምጃ አጭር መልስ አላቸዉ።እንበረከክም የሚል።
«በሐገራችን አቅም፣ በምጣኔ ሐብታችን ደረጃና ልዕለ ኃያል በመሆናቸዉ ምክንያት ለዩናይትድ ስቴትስ እርምጃ አንበረከክም።እያስፈራሩን ነዉ።ግን መጋፈጥ አለብን።»
የ78 ዓመቱ ሐብታም ፖለቲከኛ ግን ትልቅ ሐገራቸዉን ከዓለም የማግለል፣ የመነጠል፣ የማላተም እርምጃቸዉን ቀጠሉ።ባለፈዉ ሳምንት የዓለም ብቸኛ የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት (ICC) ባለሥልጣናት፣መርማሪዎችንና ተባባሪዎቻቸዉን በማዕቀብ ቀጠሉ።ምክንያት ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት የአሜሪካና የእስራኤል መሪዎች ወይም ዜጎችን በወንጀል መጠርጠር፣ መክሰስና መመርመር የለበትም የሚል ነዉ።አሜሪካም እስራኤልም የፍርድ ቤቱ አባል አይደሉም።
የትራምፕን እርምጃ ከማንም ቀድመዉ የአሜሪካ ታማኝ፣ የቅርብ ወዳጆች ብሪታንያ፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይን ጨምሮ 79 መንግስታት አዉግዘዉታል።ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈዉ 21 ቀናት ዉስጥ የወሰዷቸዉ እርምጃዎች፣ ያሰለፏቸዉ ዉሳኔዎችና ያፀደቋቸዉ ትዕዛዛት ነባሩን የዓለም ፖለቲካዊ ሥርዓት ግራ ቀኝ ያላጉ፣ የአሜሪካንን ተቀባይነት የሸረሸሩ፣ እርዳታ ተቀባዮችን፣ ሰጪዎችንም የሚጎዳ ነዉ።የተቀረዉ ዓለም በያለበት «አንድ እግር በርበሬ----»ን በተናጥል ከማላዘን ባለፍ እስካሁን ሰብሰብ ብሉ ጠንካራ አፀፋ ለመስጠት አልቃጣም ወይም አልቻለም።ትራምፕም ቀጥለዋል።መጨረሻቸዉ ነዉ-ናፋቂዉ።
ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሠ