ጀርመን፥ የሙኒኩ የፀጥታ ጉባኤ እየተካሄደ ነው
ዓርብ፣ የካቲት 7 2017የዓለም ፀጥታ ላይ የሚመክረው 61ኛው የሙኒክ የፀጥታ ጉባኤ የዓለም መሪዎች እና ከፍተኛ ባለስልጣናት በተገኙበት ዛሬ በደቡብ ጀርመን የሙይንሽን ከተማ ተጀምሯል ። ለሦስት ቀናት የሚቆየው ይህ ጉባኤ ዩናይትድ ስቴትስ በዩክሬኑ ጦርነትና በመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳዮች ላይ ጉልህ የፖሊሲ ለውጥ ባደረገችበት ወቅት የሚካሄድ ነው ። ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካን የፕሬዚደንትነትን መንበረ ሥልጣን ዳግም በተቆጣጠሩበት እና ጀርመን ውስጥ የፍልሰተኞች ጉዳይ እጅግ አነጋጋሪ በሆነበት ወቅት ጉባኤው መካሄዱ ይበልጥ ትኩረት ስቧል ። በጉባኤው የተገኙት የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄ ዲ ቫንስ በጉባኤው ባሰሙት ንግግር፦ ዴሞክራሲን ለመጠበቅ የሕዝብን ማንኛውም ድምፅ መስማት ያስፈልጋል ብለዋል ።
«ብሪታንያ እና በመላው አውሮጳ ነጻ ንግግር እየተሸረሸረ ነው ብዬ እፈራለሁ ።»
የሙይንሽኑ ጉባኤ፦ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) አባል አገራትን ጨምሮ የዓለማችን ወታደራዊ መሪዎች እና የመከላከያ ኢንዱስትሪ አመራር የሚገኙበት ግዙፍ ጉባኤ ነው ። የዩክሬን ጦርነትም ዐቢይ አጀንዳ በሆነበት የዘንድሮው ጉባኤ የዩክሬን ፕሬዚደንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪን ጨምሮ የ60 የአገራት መሪዎች እንደሚካፈሉበት ተዘግቧል ። የጀርመን መራኄ መንግስት ዖላፍ ሾልስ ትናንት በሩስያ-ዩክሬን የሰላም ንግግር ላይ በሰጡት አስተያየት፦ ዩናይትድ ስቴትስና ሩስያ የሚያካሂዱት ማናቸውም የሰላም ንግግር ዩክሬንና አውሮጳን የማያካትት ሊሆን አይገባም ብለዋል ። የአውሮጳ ኅብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር ኡርዙላ ፎን ዴር ላየን በበኩላቸው፦ «የዩክሬን ውድቀት የአውሮጳ መዳከም ነው» ሲሉ ተደምጠዋል ። በሙይንሽኑ ጉባኤ የእንግዶች ዝርዝር ውስጥ ከ100 በላይ ሚኒስትሮችም እንደሚገኙበት ታውቋል ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሠ