መንግሥት ከአማፂያን ጋር እንዲደራደር የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠየቁ
ዓርብ፣ ሐምሌ 18 2017የፌዴራል መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ የትጥቅ ግጭትእያካሄዱ ካሉ ኃይላት ጋር ድርድር እንዲያደርግ ለሁለት ቀናት ቢሾፍቱ ውስጥ ውይይት ያደረጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠየቁ።የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትና ሰላም ሚኒስትር «ያዘጋጁት ነው» በተባለው ውይይት ላይ መንግሥት "ከፋኖም፣ ከሸኔም ጋር መነጋገርና ወደ ድርድር ማምጣት ቢቻል ዘላቂ ሰላም ማስፈን ይቻላል" የሚል አቋም መራመዱን ከተሳታፊዎች የአንደኛው ፓርቲ መሪ ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።
የፖለቲካ ድርጅቶቹ ረቡእ እና ሐሙስ ያደረጉትን ውይይት ካጠናቀቁ በኋላ ሰላምን ለማስፈን ይረዳል ያሉትን "የቢሾፍቱ ቃል ኪዳን" የተባለ ሰነድ አዘጋጅተው መፈረማቸው ታውቋል።ላለፉት ሁለት ቀናት ቢሾፍቱ (ደብረ ዘይት) ውስጥ ሰላም በማስፈን ረገድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊኖራቸው በሚገባ ኃላፊነት ላይ 50 ያህል ፓርቲዎች አንድ አንድ ተወካዮቻቸው የተሳተፉበትን ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱ ከተሳተፉት አንዱ የሆኑት የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር መብራቱ ዓለሙ (ዶ/ር) ለዶቼ ቬለ እንዳሉት ኢትዮጵያ የገባችበት የፀጥታ መናጋት እና ዜጎች እየተጋፈጡት ያሉት የእርስ በርስ ግጭት ከመነጋገሪያ ጉዳዮች መካከል ነበር።
"በሃገራችን ላይ ያለው አሁናዊ የፖለቲካ ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረስ፣ ግጭቶች ሰፋፊ በምንላቸው ክልሎችም ኦሮሚያን አማራን፣ ትግራይን እንዲሁም በቤኒሻንጉል በጋምቤላ በተለያዩ ቦታዎች ግጭቶች መኖራቸው፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይህንን በዝምታ ማየት የለባቸውም፤ ቢያንስ ዜጎች በሰላም ወጥተው እየኖሩ አይደለም፣ ሥራቸው አሁን ደግሞ የእርሻ ወቅት ነው። አርሶ አደሩ ወጥቶ ካላረሰ ቀጣይ ዓመት ላይ ረሃብ ሊገጥመን ስለሚችል ቢያንስ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሰላም አምባሳደር ሆነው መንቀሳቀስ አለባቸው" በሚል ላይ ሰፊ ምክክር ተደርጓል ብለዋል።
ሌላኛው የውይይቱ ተሳታፊ ፓርቲ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ሲሆን የድርጅቱ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ማሙሸት አማረ በሀገሪቱ አውዳሚነታቸው ከፍተኛ የሆኑ ያላባሩ ጦርነት እና ግጭቶች ለመጪው ጠቅላላ ምርጫ ብርቱ እንቅፋት እንደሚሆኑ ተጠቅሶ ውይይት መደረጉን ጠቅሰዋል።
የግጭቶች ምንጭ ናቸው የተባሉ ችግሮች መዘርዘራቸውንና "የማያሠሩ ሕጎች፣ የፖለቲካ ሥርዓቱ የሚመራበት መንገድ" ተጠቃሾች እንደነበሩ ገልፀዋል።
"የብሔር ፖለቲካው ከመጠን በላይ በመብዛቱ እና ኢትዮጵያዊ አንድነትን የረሳ እና ማንነት ላይ ብቻ ያተኮረ በመሆኑ ይህ በራሱ የችግር ምንጭ ሆኖ በመገኘቱ፣ መሻሻል፣ መታረም የሚገባቸው ነገሮች እስካልታረሙ ድረስ የሰላማዊ ኹኔታው የመምጣቱ ነገር አስቸጋሪ እንደሚሆን" ተነጋግረናል ብለዋል።
የፌዴራል መንግሥት ከታጣቂዎች ጋር ድርድር እንዲያደርግ በዛ ካሉ ፓርቲዎች ጥያቄ መቅረቡን መብራቱ ዓለሙ (ዶ/ር) ገልፀዋል።
"በሀገራቸው ውስጥ እየተፋለሙ ያሉ ኃይሎች ቢያንስ መንግሥትም ሆደ ሰፊ ሆኖ እንደ ፕሪቶሪያው [የፌዴራል መንግሥት እና የሕወሓት ድርድር] ከፋኖም፣ ከሸኔም፣ ከተለያዩ አካላት ጋር ወደ ሰላምና ወደ ድርድር መምጣት ቢቻል ዘላቂ ሰላምን ማስፈን ይቻላል"።
መንግሥት ከሁሉም በላይ ግጭቶችን በማስቆም ረገድኃላፊነቱን እንዲወጣ፣ ተፈናቃዮች ወደ አካባቢያቸው እንዳመለሱ፣ በእሥር ላይ ያሉ የፖለቲካ ተዋናዮች እንዲፈቱ ማድረግ እና ጅማሮው እንዲታይ በሰፊው ተጠይቋል ያሉት አቶ ማሙሸት ድርድር ዐቢይ ጉዳይ እንደነበር ጠቅሰዋል።
"ዜጎች ከመሞታቸው፣ ከመሰደዳቸው፣ ከመፈናቀላቸው በፊት ነገሮች ሁሉ በንግግር፣ በውይይት፣ በስምምነት መፈታት እንዳለባቸው፤ ሕወሓት እና ፌዴራል መንግስት የሚያደርጉትን የሰሞኑን እሰጥ አገባ ማቆም እንዳለባቸው እና ወደ ንግግር ወደ ውይይት መመጣት እንዳለበት ዳግም ጦርነት እንዳይከሰት እና ሃገሪቱን አስከፊ ሁኔታ ውስጥ እንዳይከታት ማድረግ፤ ከፋኖ ጋራ ከኦነሠ ጋራ ከሌሎችም ጠመንጃ ይዘው ከሚፋለሙ ኃይሎች ጋራ ተገቢው ጥሪ ተደርጎ የፖለቲካ ድርድር እንዲደረግ ስምምነት ላይ ተደርሷል"።
ሰለሞን ሙጬ
አዜብ ታደሰ