መሐመድ ሐምዳን ደጋሎ የሱዳን ትይዩ መንግሥት መሪ ሆነው ቃለ-መሐላ ፈጸሙ
እሑድ፣ ነሐሴ 25 2017መሐመድ ሐምዳን ደጋሎ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ከተወሰኑ ታጣቂ ቡድኖች ጋር የመሠረተው ትይዩ መንግሥት መሪ ሆነው ቃለ-መሐላ ፈጸሙ። ሔሜቲ በሚል ቅጽል ሥማቸው የሚታወቁት ደጋሎ 15 አባላት ያሉትን ፕሬዝዳንታዊ ምክር ቤት ለመምራት ቃለ-መሐላ የፈጸሙት ትላንት ቅዳሜ እንደሆነ ተመሠረተ የተባለው ትይዩ መንግሥት አስታውቋል።
የሱዳን ሕዝቦች ነጻ አውጪ ንቅናቄን አንድ አንጃ የሚመሩት አብደል አዚዝ አል-ሒሉ የመሐመድ ሐምዳን ደጋሎ ምክትል ሆነዋል። የቀድሞዉ የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት አባል መሐመድ ሐሰን አል-ታይሺን ተመሠረተ የተባለው መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተሾመዋል።
ደጋሎ የሚመሩት ፕሬዝዳንታዊ ምክር ቤት ሌሎች 13 አባላት ቃለ-መሐላ መፈጸማቸውን ትይዩው መንግሥት ያሠራጨው መግለጫ ይጠቁማል። የምክር ቤቱ አባላት ነባር እና ትይዩው መንግሥት የመሠረታቸው አዳዲስ ግዛቶችን እንዲያስተዳድሩ የተሾሙ አገረ ገዥዎች ናቸው።
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ኦማር አል በሽር ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ የተመሠረተውን ሉዓላዊ ምክር ቤት በሊቀ-መንበርነት እና ምክትል ሊቀ-መንበርነት ይመሩ በነበሩት መሐመድ ሐምዳን ደጋሎ እና የብሔራዊ ጦሩ አዛዥ አብደል ፋታኅ አል-ቡርኻን መካከል የተፈጠረው ልዩነት ሱዳንን ለብርቱ ጦርነት ዳርጓታል። ደጋሎ የተወሰኑ ታጣቂዎችን በማስተባበር የመሠረቱት መንግሥት ሀገሪቱን ለሁለት እንዳይሰነጥቃት ያሰጋ ነው።
ደጋሎ “የሰላም እና የአንድነት መንግሥት” መመሥረታቸውን ያስታወቁት ባለፈው ሚያዝያ ወር ነበር። ይሁንና የአፍሪካ ኅብረት እና የአረብ ሊግ ለደጋሎ መንግሥት ዕውቅና እንደማይሰጡ አስታውቀዋል። ግብጽ እና ጅቡቲም ከዚህ ቀደም የደጋሎን ትይዩ መንግሥት ተቃውመው ነበር።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይል መሪ ሱዳንን ለሁለት እንዳይሰነጥቅ ያሰጋውን ትይዩ መንግሥት ለመምራት ቃለ-መሐላ የፈጸሙት በዳርፉር ግዛት በምትገኘው የኒያላ ከተማ ነው። በዳርፉር ግዛት ከሚገኙ ትልልቅ ከተሞች አንዷ የሆነችው ኒያላ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መቀመጫ ሆኖ እያገለገለች ትገኛለች። ከተማዋ ትላንት ቅዳሜ በድሮኖች ጥቃት እንደተፈጸመባት ሬውተርስ ዘግቧል።
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል አብዛኛውን የዳርፉር ግዛት የሚቆጣጠር ቢሆንም ታሪካዊቷን የኤል-ፋሽር ከተማ በእጁ ለማስገባት ከሱዳን ብሔራዊ ጦር እና አጋር ታጣቂዎቹ ጋር እየተፋለመ ይገኛል። የተወሰነው የኮርዶፋን ግዛት አነስተኛ የብሉ ናይል ግዛት በታጣቂ ቡድኑ ቁጥጥር ሥር ከሚገኙ መካከል ናቸው።
መቀመጫውን በፖርት ሱዳን ያደረገው መንግሥት በአንጻሩ በምሥራቅ፣ በማዕከላዊ ሱዳን፣ በሰሜን እና በብሉ ናይል ግዛት የሚገኙ አካባቢዎችን ይቆጣጠራል። በሱዳን መደበኛ ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል ከ28 ወራት ገደማ በፊት ውጊያ ከተቀሰቀሰ ወዲህ መሐመድ ሐምዳን ደጋሎ እምብዛም አይታዩም።
አርታዒ ታምራት ዲንሳ