ለትግራይ ተፈናቃዮችና ችግረኞች የሚሰጠዉ ርዳታ ማነስ ያስከተለዉ ሥጋት
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 28 2017የእርዳታ መቀነስ እንዲሁም በነፃ ይቀርቡ የነበሩ ሕክምና እና ሌሎች አገልገሎቶች መቋረጣቸው ተከትሎ በትግራይ የሚገኙ እርዳታ ፈላጊዎች በተለይም ተፈናቃዮች በከፋ አደጋ ላይ እንደሚገኙ ገለፁ። በትግራይ የሚገኙ ተፈናቃዮች ወደቀዬአቸው ለመመለስ ከሚደረግ ጥረት በተጨማሪ በሕይወት የሚያስቆይ ድጋፍ እንዲቀጥልም የክልሉ ግዚያዊ አስተዳደር ጥሪ ያቀርባል።
የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደርቁጥራዊ መረጃ እንደሚያመለክቱት በክልል ተፈናቃዮች ጨምሮ 2 ነጥብ 4 ሚልዮን ህዝብ አስቸኳይ ሰብአዊ እርዳታ ይፈልጋል። ይህ ባለፉት ዓመት ከነበረው የእርዳታ ፈላጊ ህዝብ መጠን በተወሰነ መልኩ መቀነስ ቢታይበትም አሁንም በክልሉ ያለ ሰብአዊ ቀውስ አሳሳቢ መሆኑ ማሳያ መሆኑ ይገለፃል። በተለይም በትግራይ የተለያዩ መጠልያ ጣብያዎች ያሉ ተፈናቃዮች በወሳኝነት የሚሹት ይህ ድጋፍ በዓለምአቀፍ ደረጃ በተፈጠሩ ለውጦች ምክንያት የመቋረጥ እንዲሁም የመቀነስ አደጋ አንዣቦበታል።
በጦርነት ምክንያት ከምዕራብ ትግራይተፈናቅለው በአክሱም የሚገኙ ተፈናቃዮች እንደሚሉት፥ በተለይም ካለፈው የካቲት ወዲህ ለተፈናቃዩ በነፃ ይቀርቡ የነበሩ እርዳታዎች እና አገልግሎቶች አብዛኞቹ ተቋርጠዋል። ተፈናቃዩ እንዲሁም በአክሱም የሚገኙት ተፈናቃዮች አስተባባሪው አቶ ካሕሳይ አሳየህኝ፥ በተለይም በተለያዩ አገልግሎቶች መቋረጥ ምክንያት ተፈናቃዮች እየሞቱ ነው ይላሉ።
አቶ ካሕሳይ በተለይም የሕክምና አገልግሎቶች መቋረጣቸው ተከትሎ ከየካቲት ወር ወዲህ ባለው ሁኔታ የህፃናት እና የአዛውንቶች የሞት መጠን ጨምሯል ብለዋል።
የትግራይ ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮምሽን እንደሚለው በክልሉ ለበርካቶች እርዳታ የሚያቀርቡ ድርጅቶች የካቶሊክ እርዳታ አገልግሎት እንዲሁም የዓለም ምግብ መርሐግብር መሆናቸው የሚገልፅ ሲሆን፥ የካቶሊክ እርዳታ አገልግሎት ብቻ በትግራይ በየወረ ለ1 ነጥብ 2 ሚልዮን ህዝብ የምግብ እርዳታ እንደሚያቀርብ ይገለፃል። የእርዳታ ድርጅቱ በትግራይ ለሚሰጠው እርዳታ ሙሉ በጀቱ ደግሞ በዩኤስኤ አይዲ የሚሸፈን መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፥ የበጀቱ ቀጣይነት አደጋ ላይ መውደቁ ተከትሎ የሰብአዊ እርዳታው አቅርቦት ለአደጋ ተጋልጧል።
ከተለያዩ አካባቢዎችየጠየቅናቸው እርዳታ ፈላጊዎች በተለይም ተፈናቃዮች፥ የምግብ እርዳታ መጠን መቀነሱ ያነሳሉ። ከሽረ የተፈናቃዮች መጠልያ ያነጋገርናቸው የእድሜ ባለፀጋው አቶ ወልደሚካኤል አረፈ ወርሓዊ የምግብ ራሽኑ ቀንሶ ከአስራ አምስት ኪሎ ወደ አስራሁለት አሁን ደግሞ ወደ ዘጠኝ መውረዱ ተናግረዋል።
ጦርነት፣ የተራዘመ ፖለቲካዊ እና ማሕበረ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንዲሁም የተፈናቃዮች ችግር በትግራይ ያለው የእርዳታ ፈላጊዎች መጠን ከፍተኛ እንዳደረገው የሚያነሱት የትግራይ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮምሽን ኮምሽነር ዶክተር ገብረህይወት ገብረእግዚአብሔር፥ በትግራይ መፍትሔ የሚሹ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን ያነሳሉ።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
ነጋሽ መሐመድ
ማንተጋፍቶት ስለሺ