ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢነት የቀረበው ሹመት ፀደቀ
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 9 2016በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው የተሾሙት ወይዘሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ ሹመታቸው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀደቀ። ከስልጣናቸው በፈቃዳቸው በለቀቁትንና ቦርዱን በሰብሳቢነት ለአራት ዓመት ተኩል በመሩት ብርቱካን ሚደቅሳ ምትክ የትሾሙት አዲሷ ተሿሚ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሆነው ለሦስት ዓመታት ማግልገላቸው ተነግሯል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አዲሷ የተቋሙ የበላይ ኃላፊ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነፃና ገለልተኛ ሆኖ ሥራዎችን ማከናወኑን አጠናክሮ እንዲቀጥል፣ የታችኛው የመንግሥት መዋቅር ላይ ያለን የምርጫ ሂደት በእግባቡ እንዲያስፈጽሙ በማሳሰብ ሹመቱን በአብላጫ ድጋፍ አጽድቀዋል።
ወይዘሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ ማን ናቸው ?
በዛሬው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ከተገኙ 272 የምክር ቤቱ አባላት ሹመታቸው በአንድ ጽምጽ ተዐቅቦ የፀደቀው አዲሷ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሥልጣናቸውን በፈቃዳቸው የለቀቁትን ብርቱካን ሚደቅሳን ትክተው ይሠራሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ቦርዱን በሰብሳቢነት የሚመራ ሰው የሚመለምል ኮሚቴ አዋቅረው ምልመላ ከተደረገ በኋላ ተለይተው የቀረቡትን ሜላትወርቅ ኃይሉን ለቦርዱ የበላይ ኃላፊ እንዲሆኑ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሹመቱን እንዲያፀድቅ በምክር ቤቱ በመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ትስፋዬ በልጅጌ በኩል አቅርበዋል።
ተሿሚዋ "የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ሥራ በውጤታማነት ይመራሉ ተብሎ እምነት የተጣልባቸው" መሆኑን አቶ ተስፋዬ ገልፀዋል።
ከ30 ዓመት በላይ ሀገራቸውን ስልማገልገላቸው የተነገረላቸው አዲሷ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ በጉሙሩክ ባለስልጣን ፣ በግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ፣ በግል የሕግ ማማከር እና ስልጠና እና መሰል ሥራዎች በስፋት ልምድ ያላቸውና ያገለገሉ መሆናቸው ተግልጿል።
በሹመቱ ላይ ድምፀ ተአቅቦ ያደረጉትና የሐረሪ ክልል ተወካይ የሆኑ የምክር ቤት አባል ከዚህ በፊት የነበረው የቦርዱ አመራር "እንከኖች የነበሩበት ፣ የምክር ቤቱን ውሳኔ አልቀበልም የሚልና እምቢተኝነት የነበረበት" ምሆኑን ጠቅሰው አዲሷ ተሿሚም የእዚያ አመራር አባል ስልነበሩ ይህ እንዲታረም ሲሉ ጠይቀዋል። ሌሎች እባላት ደግሞ ተሿሚዋ ላይ ያላቸውን እምነት በመግለጽ ድጋፍ ሰጥተዋል።
ቦርዱ የአካባቢ ምርጫን እንዲያከናውን መጠየቁ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ የተሻለ ነፃና ገለልተኛ ምርጫ አድርጓል በሚል የመወደሱን ያህል፣ በፀጥታ ምክንያት በተለይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ በኦሮሚያ ክልል የወለጋ ዞኖች፣ በአማራ ክልል የተወሰኑ ቦታዎች ምርጫ ካለማድረጉ በላይ የአካባቢ ምርጫ ባለማድረግም ይወቀሳል። ምንም እንኳን ቦርዱ ፀጥታ የማስክበር ኃላፊነት የመንግሥት መሆኑን ቢገልጽም።
ቦርዱ የአካባቢ ምርጫ ላይ አሁንም ትኩረት እንዲያደርግ ለአዲሷ ትሿሚ በግልጽ ተነግሯል። ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ ለአራት ዓመት ተኩል የመሩት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚመራውን እና ሌሎች አዳዲስ ሕጎችን ከማውጣትና ተግባራዊ ከማድረግ ጀምሮ ሕዝበ ውሳኔዎችን በማከናወን ተጨባጭ በጎ ሥራዎችን ስለማከናወኑ ይታመናል።
አዜብ ታደሰ
እሸቴ በቀለ
ሰለሞን ሙጬ