ለሦስት ወር የሚሸፍን የእቃዎች መግዣ የውጭ ምንዛሪ ክምችት መኖሩ ተገለፀ
ዓርብ፣ ሰኔ 20 2017ብሔራዊ ባንክ ለ3 ወር የተጠጋ የሸቀጦች እና የአገልግሎት ገቢ ክፍያ የሚሸፍን የውጭ ምንዛሪ ክምችት እንዳለው ተገለፀ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ3 ወር የተጠጋ የሸቀጦች እና የአገልግሎት ገቢ ክፍያ ለመሸፍን የሚያስችል ደረጃ ላይ መድረሱን የባንኩ ገዢ ማሞ ምህረቱ ገለፁ።
የባንኩ ብሔራዊ "የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ክምችት በሦስት እጥፍ አድጓል" ያሉት ገዢው ባንኩ ከውጭ ለሚገቡ ዕቃዎች ብቻ ከሦስት ወር በላይ ክፍያ መሸፈን የሚያስችለው መጠባበቂያ ክምችት እንዳለው ተናግረዋል።
ባንኩ በሚቀጥለው ሳምንት ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋምና ከአለም ባንክ 750 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደሚለቀቅለትም ኃላፊው ዛሬ የተቋማቸውን የ11 ወራት የሥራ አፈጻጸም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሲያቀርቡ አስታውቀዋል።የኢትዮጵያ መንግሥት የዋጋ ግሽበትን የተመለከቱ አሐዞች የገበያውን እውነታ ምን ያክል ያሳያሉ?
ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ንረትን ከ10 በመቶ በታች ለማውረድ የያዘውን ውጥን እስኪያሳካ ድረስ "ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ" መተግበሩን እንደሚቀጥልም ተገልጿል።
የብሔራዊ ባንክ ገዢ ማሞ ምህረቱ የሚመሩት ባንክ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ክምችት የ235 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡን ጠቅሰዋል። ከሸቀጦች፣ ከአገልግሎት ንግድ፣ ከውጭ ከሚላክ፣ ከእርዳታ እና ብድር እንዲሁም ከኢንቨስትመንት የሚመጣው የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ጨምሮ በጥቅሉ ወደ 32.1 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ስለማለቱ፣ ይህም "ተዓምራዊ የሚባል ለውጥ" እንደሆነ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ አማካይ የዋጋ ንረት 14.4 በመቶ ነው ተብሏል፣ በባንኩ ገዢ ዘገባ መሠረት። ይህንን ከ10 በታች ለማውረድ የገንዘብ አስተዳደር ሥርዓትን ማጥበቅ፣ ምርትን ማሳደግ፣ የሸቀጦችን ፍሰትን ማሳለጥ እና ድጎማ ትኩረት የሚደረግባቸው መሆኑ ተመላክቷል። የውጭ ምንዛሪ ክምችት እና አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዕቅድ
ባንኩ የዋጋ ንረትን ለመቋቋም ሲባል በዚህ ዓመት "ለመንግሥት ምንም አይነት ቀጥታ ብድር አልሰጠም" ያሉት አቶ ማሞ ባንኩ በእነዚህ ወራት 531 ቢሊዮን ብር ከገበያ መሰብሰቡንም አመልክተዋል። እንዲያም ሆኖ የዋጋ ንረቱ የምግብ እና ምግብ ነክ ሸቀጦች ላይ ቅናሽ አላሳየም ብለዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ለውጡን ተከትሎ የተጠበቀው የሕጋዊ እና የትይዩ ገበያው ልዩነት አለመቀነሱ ይልቁንም የብር ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መዳከም መስተዋሉን በተመለከተ ከቋሚ ኮሚቴው ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ማሞ ልዩነቱ "መሠረታዊ በሆነ መልኩ" ቀንሷል የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ሆኖም ይህ ሁኔታ በተወሰነ መልኩ መኖሩ እንደማይቀር አብራርተዋል።
ብሔራዊ ባንክ በሚቀጥለው ሳምንት ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋምና ከአለም ባንክ 750 ሚሊዮን፣ በቀጣዩ ዓመት ደግሞ 1 «አንድ» ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደሚለቀቅለት በዚሁ መድረክ ተነግሯል። የባንኮች ብድር የመስጠት ገደብ ላይ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴው መስከረም ላይ ከተወያየ በኃላ ውሳኔ ይሰጥበታልም ተብሏል። ብሔራዊ ባንክ በውጭ ምንዛሪ ተመን ለውጥ ምክንያት 10.5 ቢሊዮን ብር ኪሳራ ደርሶበታል የሚለውን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ማብራሩያ ሰጥተዋል።የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሸቀጥ ለሚያስገቡና ለተጓዦች የሚፈቀደዉን የውጭ ምንዛሪ መጠን ጨመረ
"ብሔራዊ ባንክ የትርፍ መሥሪያ ቤት አይደለም። የውጭ ምንዛሪ ለውጡ ከመካሄዱ በፊት በብር ያለው ንጽጽር [የባንኩ ሀብት] ያለው የብር መጠን የተለያየ ነው። በዚህ የተነሳ ይህ 10.5 ቢሊዮን ብር ልዩነት አለ። ይህ ተጨባጭ የሆነ ኪሳራ ሳይሆን በዳግም ግመታ የመጣ እውን ያልሆነ ኪሳራ ነው። ስለዚህ አበድሮ የከሰረው ነገር የለም"። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በፋይናንስ ዘርፍ በቀጣዩ ዓመት ለግብርና፣ ለመኖሪያ ቤት፣ ለጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፎች ትኩረት እንደሚሰጥ፣ የውጭ ባንኮችን ለመሳብ እንደሚተጋ፣ የግዴታ የግምጃ ቤት ግዥን እንደሚያስወግድም አስታውቋል።
ሰለሞን ሙጬ
አዜብ ታደሰ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሔር