ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ዛሬ ጳጉሜን 3 ቀን በአዲስ አበባ ተጀመረ
ሰኞ፣ ጳጉሜን 3 2017ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ዛሬ ጳጉሜን 3 ቀን በአዲስ አበባ ሲጀመር የኢትዮጵያጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት እና የሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀመናብርት፣ የሀገራት መሪዎች እና ሌሎችም ታድመዋል። ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ የሚያደርጉት የገንዘብ ድጋፍ መቀዛቀዝ በታየበት በዚህ ወቅት በሚደረገው ጉባኤ በዚህ እና በቀጣይ የፖሊሲ አቅጣጫዎች ላይ ምክክር ይደረጋል ተብሏል።
በዚህ ጉባኤ ላይ የጀርመንን መንግሥት የወከለው ልዑክ በሀገሪቱ የፌዴራል የኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ሚኒስትር የፓርላማ ዲኤታ ፀሐፊ ዶ/ር ባርቤል ኮፍለር እየተመራ እየተሳተፈ ነው።
ቡድኑ ትናንት ምሽት አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘው የጀርመን ኤምባሲ አቀባበል ተደርጎለታል። በታዳሽ ኃይል ረገድ ለአህጉሩ ድጋፍ የሚያደርገው የጀርመን መንግሥት የኃይል አቅርቦት አማራጮችን ለማስፋት በተለይ የናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቪን መደገፉን እንደሚቀጥል ዶ/ር ባርቤል ኮፍለር ተናግረዋል።
የናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ የወንዙን ውኃ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ በመጠቀም ዘላቂ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማት እንዲኖር የሚሠራ ማዕቀፍ ነው።
"የናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭን ከጀርመን በኩል እየደገፍን ያለነው በናይል ወንዝ ሥር ባሉ ሀገራት መካከል የዓባይን ኃይል እና ውኃ ለመጠቀም መግባባት መኖር አለበት ብለን በፅኑ ስለምናምን ነው"። ሌላኛው የጉባኤው ተሳታፊ የጀርመን ልዑክ አባል የሀገሪቱ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር የአየር ንብረት፣ የተፈጥሮ ጥበቃ እና የኑክሌር ደህንነት ፀሐፊ ዮሼን ፍላሽባርዝ ናቸው።
"የአየር ንብረት ፋይናንስን በተመለከተ ባደጉት ሀገራት እና ሌሎችም ይህንን ለማድረግ ቃል የተገባለትን 300 ቢሊየን ወደ ተግባር ማስግባታችን ትክክል ነው ብዬ አስባለሁ። እናም የግል ባለሀብቶች ተጠቃሚነት ፍኖተ ካርታችን ሊሆን ይገባል። እኛ ቁርጠኞች ነን፣ ምንም እንኳን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ብንሆንም።" ሲሉ ሀገራቸው ለአየር ንብረት ለውጥ ያላትን ቁርጠኝነት ገልፀዋል።
በዚህ የልዑኩ የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ላይ የቀርቀሃ ሳይክል እና ዊልቸር እንዲሠራ ከጀርመን መንግሥት ድጋፍ ያገኘው ባንቡ ላብስ የተባለውን ድርጅት ያቋቋሙት አቶ አቤል ኃይለጊዮርጊስ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ሥራቸው የአየር ንብረት ለውጥ ላይ ጉዳት በማያባብስ መልኩ እንዲጠናከሩ "ትልቅ ድጋፍ ከጀርመን መንግሥት አግኝተናል" ብለዋል።
የጀርመን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ልዑክ በሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ መሳተፍ "ጀርመን ለአየር ንብረት ጥበቃ እና ለአፍሪካ አረንጓዴ ለውጥ ያላትን ቁርጠኝነት የሚያጎላ" መሆኑን የሚያሳይ ነው ተብሏል።
በተጨማሪም "በጀርመን እና በኢትዮጵያ እንዲሁም በአህጉር አቀፍ ተቋማት በአየር ንብረት፣ በአካባቢ እና በዘላቂ ልማት ዙሪያ ውይይት ለማድረግ ያስችላል" ተብሎ መሆኑን ከጀርመን ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
ሰለሞን ሙጬ
እሸቴ በቀለ
ማንተጋፍቶት ስለሺ