የምክክር ኮሚሽኑ በዋሽግተን ዲሲ ያካሄደው መድረክ
ሰኞ፣ ነሐሴ 26 2017የምክክር ኮሚሽኑ በዋሽግተን ዲሲ ያካሄደው መድረክ
የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣በሰሜን አሜሪካ እና አካባቢው ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልድ ኢትዮጵያዊያን ጋር አጀንዳ የማሰባሰብ መድረክ ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ አካሄደ። የኮሚሽነሩ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ለዶቼ ቬለ እንደገለጹት፣የውይይት መድረኩ ወደፊት ወደ ኢትዮጵያ ሄደው በሀገራዊ ምክክር መድረክ ጉባኤ ላይ የሚሳተፉ ተወካዮችም የተመረጡበት ነው። ኮሚሽኑ ባለፈዉ ቅዳሜ በዋሽንግተን ዲሲ ዋተር ጌት ሆቴል ያዘጋጀው አጀንዳ የማሰባሰብ መድረክ፣አዳራሽ ውስጥ በተገኙ ተሳታፊዎችና በበይነመረብ አማካኝነት የተካሄደ ነበር።
የውይይቱ ተሳታዎች
በዚሁ የውይይት መድረክ ላይ በመላ ዩናይትድ ስቴትስና የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን መሳተፋቸውንኘሮፌሰር መስፍን ተናግረዋል። ''ከዋሽንግተንና አከባቢው ብቻ ሳይሆን፣ከመላው አሜሪካ የመጡ ፣ካሊፎርኒያ፣ከሎስአንጀለስ፣ ከሚኒ ኒሶታና ከተለያዩ ስቴቶች የመጡ፣በርካታሰ ሰዎችን በማግኘት ከእነሱ ጋር የሙሉ ቀን ጊዜ ነበረን። ''
የትኩረት አጀንዳዎች
በምክክር መድረኩ ላይ የተነሱ ዋና ዋና ሃሳቦችን በተመለከትም ዋና ኮሚሽነሩ እንደሚከተለው አስረድተዋል። ''ከሰዐት በኋላ በተለይ፣በቡድን በቡድን በየማኀበረሰቡ ተደራጅተው ለሀገራችን የሚጠቅሙ፣የጋራ ተስፋችንን የጋራ ራዕያችንን በትክክል ማስኬድ ካለብን ችግሮቻችን ናቸው። አንዳንዶቹ ለግጭት የዳረጉን ሌሎቹ እንደውም አልፈው ተርፈው ጦርነት ውስጥ ያስገቡን ናቸው ያሏቸውን በሙሉ በጋራ፣በተለይ ደግሞ በቀጥታ ከውጭ አገር ኑሮ ጋር በተያያዘ፣የዳይስራውንና በኢትዮጵያ ያለውን መንግሥት የሚኖራቸውን ግንኙነት፣የእነሱን መብት ለህዝባቸው ሊያደርጉ የሚችሉትን አስተዋጽኦ በተመለከተ ብቻ ብዙ ዝርዝር አጀንዳዎቻቸውን ወደፊቱ ተለቅመው የሚወጡ ሰጥተውን ይህንን ተረክበናል። ''
ወደፊትም እነዚህ ተሳታፊዎች፣በተሰጣቸው ኮታ መሰረት የራሳቸውን ትራንስፖርት ወጪ በመሸፈን፣ኢትዮጵያ ሄደው በሃገራዊ የምክክር ጉባኤ ላይ የሚሳተፉ ተወካዮች እና ተጠባባቂዎቻቸውን መምረጣቸውንም ከፕሮፌሰር መስፍን ገለጻ ለመረዳት ትችሏል። በምክክር መድረኩ ላይ ከተሳተፉት መካከል፣ በዋሽንግተን ዲሲ ነዋሪ የሆነው አቶ አንተነህ አብረሃም የመድረኩን ፋይዳ በተመለከተ አስተያየቱን ሰጥቶናል። ''ሀሳባችን እንዲሰማ፣እንዲካተት አገር ውስጥ በሚደረገው ሁኔታ እንደሀገር ሰው፣እንደ ኢትዮጵያዊ እድንሳተፍ እንድንቆጠር፣ ዋናው ትኩረት ደግሞ እኛ መገለል የለብንም የሚለው ነገር ነው በአብዛኛው ዲያስፖራው ትኩረት የሰጠው። '' የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን የኦሮሚያ አጀንዳን አሰባሰብ ማጠናቀቁ
የኮሚሽኑን የዋሽንግተን ዲሲ መድረክ ለማክሸፍ ከሰሞኑ ተቃዋሚዎች እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የሰንበቱ ሲሆን፣በዕለቱም በአዳራሽ እና ከስብሰባ አዳራሽ ውጪ የተቃውሞ ድምጻቸውን አሰምተዋል።
የፖለቲካ ተንታኝ አስተያየት
በጉዳዩ ላይ ዶቼ ቬለ አስተያየት የጠየቃቸው የፖለቲካ ተንታኝ አቶ ገለታው ዘለቀ፣ ኢትዮጵያ አሁን የምክክር ጊዜ ላይ እንደማትገኝ ገልጸው፣ኮሚሽኑ የሃገሪቱን ችግር ሊፈታ የሚችልበት ተቋማዊ ቁመና ላይ አለመሆኑን አስረድተዋል። 'አሁን ያለው ምዕራፍ የምክክር ጊዜ ሳይሆን፣እነዚህ ነፍጥ ያነሱ ጠብመንጃ ያነሱ ኃይሎች ጋር ድርድር ነው መደረግ አለበት። ድርድር ተደርጎ የተኩስ አቁም ተደርሶ፣ከእዛ ሰው ወደ ነፍሱ፣ወደ ልቡ ሲመለስ ያንጊዜ ደግሞ ወደ ምክክር እንመጣለን። አሁን በዚህ ሁሉ ጥይት መኻከል ስለፌዴሪል ስርዓቱ ልናወራ እንችላለን?ፋኖን ትተነው፣እዚህ ውጭ ሃገር ያለውን ተቃዋሚን ትተነው፣የተወሰኑ ሰዎች ተሰባስበው በሚስማሙ ሰዎች ብቻ ተመካክረው ምንም ለውጥ ሊያወጡስለማይችሉ' ነው የምንቃወመው። ''
ኮሚሽኑ ከምስረታው ጀምሮ እንከኖች እንዳሉበት ያወሱት አቶ ገለታው፣ገለልተኛ አለመሆኑ ከኅብረተሰቡ ዘንድ አመኔታን እንዳያገኝ አድርጎታል ብለዋል። ዋና ኮሚሽነሩ ግን ስለኮሚሽኑ ያልተገቡ ያሏቸው አሉባልታዎች እና ውዥንብሮች ቢናፈሱም፣የዋሽንግተን ዲሲው ስብሰባ በስኬት መጠናቀቁን አመልክተዋል።
ታሪኩ ኃይሉ
አዜብ ታደሰ
እሸቴ በቀለ