የCOP25 ተስፋ እና ስጋት
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 7 2012በጎርጎሪዮሳዊው 1992ዓ,ም ሪዮ ዴጄ ኔሮ ብራዚል ላይ ሃገራት ተሰብስበው የበካይ ጋዞች ቅነሳ መደረግ እንዳለበት ተስማምተው የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ማዕቀፍን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተዋዋሉ። ይህን መንደርደሪያ በማድረግም በዚሁ የዘመን ቀመር በ1997 የኪዮቶ ውል የሚባለውን ሙቀት አማቂ ጋዞችን የመቀነስ ስምምነትም አጸደቁ። ውሉ በዋናነት የበለፀጉት ሃገራት ወደከባቢ አየር የሚለቁትን የበካይ ጋዞች መጠን እንዲቀነሱ በሕግ የሚጠይቅ ቢሆንም ዋነኞቹ የከባቢ አየር በካዮች ዩናይትድ ስቴትስ እና ቻይና በዚህ ባለመሳተፋቸው የተፈለገውን ያህል ውጤት አላስገኘም። በመሃሉ የኪዮቶ ስምምነት የተገደበለት ጊዜ ለማለቅ ሲቃረብ ዶሐ ቀጠር ላይ በተካሄደው COP 18 ሃገራት የኪዮቶ ውል እስከ 2020 እንዲራዘም ተስማሙ። ከዚህ በተጨማሪም ተሰብሳቢዎቹ በደርባን ደቡብ አፍሪቃ በተካሄደው COP 17 በተወሰኑት መሠረት ሁሉን አቀፍ እና ሕጋዊ አስገዳጅነት ያለው አዲስ ሙቀት አማቂ ጋዞችን የመቀነስ ስምምነት እንዲዘጋጅ ያሳለፉት ውሳኔ አጠናከሩ። በዚህ መሠረትም በጎርጎሪዮሳዊው በ2015 ዓም ፓሪስ ፈረንሳይ ላይ ዋነኛ በካይ የሚባሉት አሜሪካ እና ቻይና የተካተቱበት የዓለም የሙቀት መጠን ከሁለት ዲግሪ በታች እንዲሆን ሃገራት በየበኩላቸው ለመቀነስ የሚችሉትን ይፋ ለማድረግ ተግባብተው ጉባኤያቸውን አጠናቀቁ። ከፓሪስ ቀጥሎ በተካሄዱት ተከታታይ ዓመታዊ ጉባኤዎች ዩናይትድ ስቴትስ ከፓሪስ ውል እንድትወጣ ያደረጉት የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ርምጃ ጥላ ቢያጠላባቸውም ተስፋ የሚሰጡ አዎንታዊ መሻሻሎች እየታዩ ዘንድሮ ላይ ደርሷል። የኪዮቶ ስምምነት የተራዘመው እስከመጪው ጎርጎርዮሳዊ ዓመት 2020 ድረስ መሆኑን በልብ ይዞ የዘንድሮው የጉባኤ ውጤት ሲመዘን በእርግጥም የጉባው ሊቀመንበር እንዳሉት ብዙም ላያስደስት ይችላል። ለአንድ ሳምንት በዚህ ጉባኤ የተሳተፉ የኢትዮጵያ አካባቢ፣ ደን እና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን በደን ዘርፍ ውስጥ የበካይ ጋዞች ልቀት ቅነሳ ዘርፍ ናሽናል ዴብ ፕላስ ፕሮግራም ውስጥ የሚሠሩት ዶክተር ይተብቱ ሞገሥም የተጠበቀውን ያህል ውጤት አለመገኘቱን ይናገራሉ።
«በእርግጥ የተጠበቀውን ያህል ውጤት የለም ዘንድሮ ላይ። ዞሮ ዞሮ ብዙ ሃገሮች የተለያዩ ፍላጎት ነው የሚያሳሉት። የፍላጎቶች አለመገናኘት ያው ወደ አንድነገር ማምጣት አይቻልም። ምክንያቱም የመቶ ዘጠና ምናም ሃገራት ድርድር ነው፤ አንድም ሀገር ካፈነገጠ ማንኛውም ውጣኔ ወይም ሕግ አይወጣም በዚህ ፕሮሰስ ውስጥ እናም አስቸጋሪ ነው የሚሆነው።
ተሰብሳቢዎቹ መስማማት ያልቻሉት በተለም በፓሪሱ ስምምነት በአንቀፅ ስድስት ላይ የሰፈረው ደግሞ ሃገራት ቃል የገቡትን የበካይ ጋዞች ቅነሳ ተግባራዊ የማድረግን ቁርጠኝነት ይመለከታል። ይህ ጉባኤ ቀናት ጨምሮ እሁድ ታኅሣስ 5 ቀን ቢጠናቀቅም ሃገራት የሚጠበቅባቸውን ይፋ አድርገው መግባባት ባለመቻላቸው ጉዳዩ በይደር በመጪው ዓመት ግላስጎው ብሪታንያ ላይ ለሚካሄደው ጉባኤ በይደር መሻገሩን ዶክተር ይተብቱ ያመለክታሉ። እንዲያም ሆኖ ግን ጉባኤው በጥቅሉ ከስኬት የራቀ ነበር ማለት አይቻልም እንደ እሳቸው እምነት። በተለይም ማኅበረሰቡ ያለው ግንዛቤ እና የሃገራት መሪዎችም ከባቢ አየርን የሚበክሉ ጋዞችን ለመቀነስ ፖለቲካዊ ውሳኔ መውሰድ እንዲችሉ ጫና የማድረጉ እንቅስቃሴ አዎንታዊ ጎን ነው ባይ ናቸው።
እሳቸው እንደሚሉትም ኢትዮጵያ እንዲህ ያለውን ድጋፍ አግኝታ ደኖቿን መከባከብ እና ማልማት ከቻለች የተሻለ የደን ሽፋን ይኖራታል ይህ ማለት ደግሞ የተሻለ ድርቅ የመቋቋም አቅም ማግኘት ማለት ነው። የከባቢ አየር ብክለትን ለማጽዳት በኢንዱስትሪ ያላደጉት ሃገራት የደን ልማታቸውን በማጠናከር የበለፀጉት ሃገራት ወደ ከባቢ አየር የሚለቁትን ሙቀት አማቂ ጋዝ የመቀነስ አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ መነጋገር ከተጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል። የካርቦን ንግድ ይሉታል። በአንድ ወገን የደን ልማቱ ባለቤቶቹን ዝናብ እየሳበ ከድርቀት በመከላከል መጥቀሙ ሳይዘነጋ። ሆኖም በዚህ ጉባኤ ይህና ሃገራት የአየር ንብረት ለውጡ ካስከተለው ተፅዕኖ ጋር ተላምደው እና ተቋቁመው ለመኖር የሚያስችላቸው የ100 ሚሊየነን ዶላር ጉዳይም እንዲሁ ምንም አዲስ ነገር ሳይገኝበት የተራዘመው ስብሰባ ተሰብሳቢዎቹን አድክሞ መጠናቀቁ ታይቷል። በዚህም ታዛቢዎች የከባቢ አየርን ብክለት ለመቀነስ ያስችላል የተባለው ዓመታዊ ጉባኤ፤ ምንም እንኳን ለአስተናጋጁ ሀገር በቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ ገቢ ማስገኘቱ ባይካድም፤ ተሰብሳቢዎቹ በሚጓጓዙባቸው መንገዶች የሚለቀቀው ሙቀት አማቂ ጋዝ በራሱ ለብክለቱ አስተዋፆ እያደረገ ነው ሲሉ ይተቻሉ። ዶክተር ይተብቱ ሞገሥ ግን ይህን አይቀበሉትም።
የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተረሽም እንዲሁ በCOP 25 ጉባኤ ውጤት ማዘናቸውን ይፋ አድርገዋል። «ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ለአየር ንብረት ቀውስ መፍትሄ በማበጀቱ ረገድ፤ ለውጡን የመግታት፤ ተላምዶ ለመኖር እና ገንዘብን በማቅረቡ ረገድ ላለው ጥረት የተሻለ ተስፋ የሚሰጥበትን አጋጣሚ አልተጠቀመበትም።» ነው ያሉት ዋና ጸሐፊው። እንዲያም ሆኖ በመጪው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2020 ሃገራት ሳይንስ እንዲያደርጉ ያመለከተውን ለመፈፀም ቁርጠኛ ሆነው ተግባራዊ በማድረግ ለ2050 ከካርቦን የጸዳ እና ከ1,5 ዲግሪ ያልበለጠ የከባቢ አየር ሙቀት እንዲኖር ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ጠንክረው ለመሥራት መወሰናቸውን አስታውቀዋል። በዘንድሮው ጉባኤ ወደ 200 ከሚሆኑ ሃገራት የተውጣጡ ከ27 ሺህ የሚበልጡ ተሳታፊዎች ማድሪድ ላይ ተሰባስበው በየዘርፉ ሲነጋገሩ እና ሲደራደሩ ሰንብተዋል። የዚህ ዓመቱ የአየር ንብረት ተመልካች ጉባኤ ያሳደራቸው ወሳኝ ነጥቦች በመጪው ዓመት ስብሰባው በሚስተናገድባት ግላስጎ ከጥቅምት ወር መጨረሻ እስከ ኅዳር ወር 2013 አጋማሽ መልስ ያገኛሉ ተብሎ ተስፋ ተጥሏል። ለሰጡን ማብራሪያ ዶክተር ይተብቱ ሞገሥን እናመሰግናለን።
ሸዋዬ ለገሠ
እሸቴ በቀለ