COP 27፤ ተግባራዊ እርምጃ ቢጠበቅም ድርድሩ ቀጥሏል
ማክሰኞ፣ ኅዳር 6 2015የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ተከታታይ ጉባኤ COP በመባል የሚታቀው ማለት ነው ባለፈው ሳምንት እሑድ ጥቅምት 27 ቀን 2015 ዓ,ም ሻርም ኤል ሼክ ግብጽ ውስጥ በይፋ ተጀምሯል። ያለፈውን ዓመት ጉባኤ ማለትም COP 26ን ግላስጎው ላይ ያስተናገደችውን እና ለአንድ ዓመት የጉባኤው ሊቀመንበር የነበረችው ዩናይትድ ኪንግደም የመድረኩ ሊቀመንበርነቷን ትናንት ለግብጽ አስረክባች።
የአየር ንብረት ለውጥን የሚከታተለው ጉባኤ አፍሪቃ ውስጥ ሲካሄድ ዘንድሮ ሁለተኛው ነው። ቀደም ሲል በጎርጎሪዮሳዊው 2011 COP 17ን ደቡብ አፍሪቃ ደርባን ላይ አስተናግዳለች። አፍሪቃ ምንም እንኳን ለከባቢ አየር ብክለት የምታደርገው አስተዋጽኦ አነስተኛ ቢሆንም የአየር ንብረት ለውጥ መዘዝ ግንባር ቀደም ተጠቂ ናት። በኢንዱስትሪ ያላደጉ ሃገራት ጉዳቱን ለማካካስ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖውን ለመቋቋም የሚያስችላቸውን ሥራ መሥራት እንዲችሉ የገንዘብ ድጋፍ ሲጠየቅ፤ ለብክለቱ ታሪካዊ ተጠያቂነት ያለባቸው ሃገራት ደግሞ ለዚህ በየዓመቱ መቶ ሚሊየን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብተው ተግባራዊ እርምጃ አልታየም። ለዚህም ነው ወጣቶቹ ከተለያዩ ሃገራት ሻርም ኤል ሼክ ተሰባስበው ባካሄዱት ሰልፍ «ገንዘቡን አሳዩን» ሲሉ በጉባኤው የተሰባሰቡ በኢንዱስትሪ ያደጉት ሃገራት ቃል የገቡትን በተግባር እንዲያሳዩ ጥሪ ያቀረቡት።
በዚህ ጉባኤ መክፈቻ ላይ ንግግር ካደረጉት መካከል እንደተጠቆመው ከ7 ዓመት በፊት ፓሪስ ፈረንሳይ ላይ የተካሄደው COP 21 ላይ ሃገራት የዓለም የሙቀት መጠን ከ1,5 ዲግሪ እንዳይበልጥ የበካይ ጋዞች ቅነሳ ስምምነት ተደረሰ፤ ካቶቪስ ፖላንድ እና ግላስኮ ዩናይትድ ኪንግደም ላይ ደግሞ የአፈጻጸሙ ዕቅድ ወጣ፤ አሁን ከሻርም ኤል ሼክ ግብጽ ደግሞ ተግባራዊ ወደማድረጉ ይወስደናል ተብሎ ይጠበቃል።
ዘንድሮ ግብጽ ባስተናገደችው በCOP 27 ላይ ተስፋ ያሳደሩ ነገሮች ቢታዩም በተቃራኒው አሳሳቢ ጉዳዮችም መኖራቸው ነው የተሰማው። የጉባኤው ተሳታፊ በአውሮጳ የደን ተቋም ከፍተኛ የደን ተመራማሪ እና የዓለም አቀፍ የደን አስተዳደር ቡድን ሰብሳቢ ዶክተር ይታገሱ ተክሌ በዚህ ጉባኤ ላይ ያስተዋሉትን አዎንታዊ ነጥብ ሲገልጹ «በአየር ንብረት ለውጥ መዘዝ ለደረሰው ጉዳት ማካካሻ የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ» ማድረግን የሚመለከት ሃሳብ ቀርቦ መነጋገሪያ መሆኑ በዘንድሮው ጉባኤ ትልቅ እርምጃ ነው ብለዋል። ሌላው በዚህ ጉባኤ ላይ መነጋገሪያ የሆነው የግብርናው ዘርፍ ነው። ወደ ከባቢ አየር ከሚለቀቁት በካይ ከሚባሉት ጋዞች ከካርቦን ቀጥሎ የሚጠራው ሜቴይን ነው። ሜቴይን ከግብርናው ዘርፍ የሚገኝ እንደመሆኑ በተለይ ባለግዙፍ ከብት እርባታ ባለሀብት የሆኑት ሃገራትን ይነካል። ይህ ጉዳይ በCOP 27 ላይ መነጋገሪያ መሆኑን ዶክተር ይታገሱ ትልቅ እርምጃ ነው ይላሉ።
ባለፉት የአየር ንብረት ለውጥ ተከታታይ ጉባኤዎች ብዙ ሲባልበት የነበረው ከቅሪተ አጽም የሚገኙ የኃይል ምንጮች አጠቃቀም ቅነሳ የሚያስተጓጉል እርምጃ ታይቷል።
ምንም እንኳን ለሁለት ሳምንት በሚካሄደው ጉባኤ ላይ የታዩ አዎንታዊ ጉዳዮች ቢኖሩም ብዙዎቹ ሃገራት ግን ከሚወስዷቸው ተገቢ ውሳኔዎች ወደ ኋላ የማለት አዝማሚያን ማሳየታቸው ምናልባት ከጉባኤው በሚጠበቀው ውጤት ላይ አሉታዊ ጫና ሊኖረው እንደሚችም አንስተዋል።
ከኮፐንሃገኑ ጉባኤ አንስቶ ለከባቢ አየር ብክለት ታሪካዊ ኃላፊነት አለባቸው የሚባሉት በኢንዱስትሪ ያደጉት ሃገራት የተለያዩ ቃል የገቧቸው ውሳኔዎች ቢኖሩም በተግባር የሚታይ ነገር አለመኖሩ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ሁሉ የሚታዘቡት ነው። ወደ ተግባር ለመግባት ቀላል እንደማይሆን የሚናገሩት ዶክተር ይታገሱ ከጤና፣ ከፍትህ እንዲሁም ከኤኮኖሚ ጋር መያያዙ የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅ አመልክተዋል።
ባለፈው ሳምንት እሑድ በይፋ የተጀመረው የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ተከታታይ ጉባኤ በተለይ ለአፍሪቃውያን የጉዳት ማካካሻው ድጋፍ፣ ከግዙፍ የግብርናው ዘርፍ የሚወጣውን ብክለት ስለመቆጣጠ መነጋገር መቻሉ በCOP 27 ትልቅ እርምጃ መሆኑን ነው ዶክተር ይታገሱ አጽንኦት የሰጡት። በተቃራኒው ደግሞ የነዳጅ እና ጋዝ ምርት እንዲቀጥል የሚያስተባብሩ ተሳታፊዎች በርክተው መገኘታቸው እንዲሁም የዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት ለሚደረጉ ውሳኔዎች በሰበብነት እየቀረበ እንቅፋት መሆኑን ታዝበዋል። በግብጽ የተካሄደው የCOP 27 ጉባዌ ውጤት እና የደረሰበት ነጥብ የፊታችን ዓርብ ኅዳር 9 ቀን 2015 ዓም ይፋ እንደሚደረግ ይጠበቃል። የቀጣዩ ጉባኤ ማለትም የCOP 28 አስተናጋጅ ሳውድ አረቢያ ናት። ለሰጡን ማብራሪያ የጉባኤው ተሳታፊ በአውሮጳ የደን ተቋም ከፍተኛ የደን ተመራማሪ እና የዓለም አቀፍ የደን አስተዳደር ቡድን ሰብሳቢ ዶክተር ይታገሱ ተክሌን እናመሰግናለን።
ሸዋዬ ለገሠ
ታምራት ዲንሳ