125ኛው የአድዋ የድል በዓል ዝክር በጀርመን
ማክሰኞ፣ የካቲት 30 2013125ኛውን ዓመት የአድዋ የድል በዓል በዙም ኢንተርኔት መርሃግብር በልዩ ልዩ ዝግጅቶች በዘከረው በጀርመን የኢትዮጵያውያን የውይይትና የትብብር መድረክ ለአዲሱ ትውልድ ጥሪ ተላለፈ። በኢትዮጵያ አዲሱ ትውልድ ጥቃቅን ልዩነቶቹን በሰለጠነ ውይይት ፈትቶና ከፈጠራ እንዲሁም ከጥላቻ ትርክቶች እንዲርቅ በውይይቱ ተጠይቋል። ይልቁንስ አዲሱ ትውልድ አያት ቅድመ አያቶቹ በአድዋው ጦርነት በአንድነት ዳር እስከዳር ተንቀሳቅሰው በከፈሉት የሕይወት መስዋዕትነት ያስረከቡትን ሀገር ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የማስጠበቅ ታሪካዊ ኃላፊነት እንዳለበት ተገልጧል።
125ኛውን ዓመት የአድዋ የድል በዓል በዙም ኢንተርኔት መርሃግብር በልዩ ልዩ ዝግጅቶች በዘከረው በጀርመን የኢትዮጵያውያን የውይይትና የትብብር መድረክ ላይ የተካፈሉ የበዓሉ ታዳሚዎች መላው ኢትዮጵያውያን በውጭ ኃይላት ከፍተኛ ተፅዕኖ እየተደረገበት የሚገኘው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ፕሮጀክት ግንባታ እንዲጠናቀቅ፣ የሀገር ዳር ድንበር እንዲከበርና መጪው ሀገራዊ ምርጫም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የዜግነት ድርሻውን እንዲወጣ እንዲሁም ኢትዮጵያ አሁን ላይ በውስጥም በውጭም የተጋረጠባትን የህልውና አደጋ በሕብረት እንዲመክቱ ጥሪ አስተላልፈዋል:: የውይይቱ የክብር እንግዳ በፍራንክፈርት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጄነራል አቶ ፈቃዱ በየነ ለኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ምስረታ ጉልህ ድርሻ ያለውና የአንድነታችን ስኬት የሆነው ይህ ዓለም ሁሉ የሚዘክረው ታሪካዊ ድል ላለፉት 84 ዓመታት ተገቢው ትኩረት ሳይሰጠው ቆይቷል ነው ያሉት:: የአድዋ ድል በዓል መሪዎች በራሳቸው በጎ ፈቃድ የሚያከብሩት ሳይሆን ዘመን ተሻጋሪ አኩሪ በዓላችን ሆኖ እንደ ዘንድሮ ሁሉ ለወደፊቱም በድምቀት ሊከበር እንደሚገባውም አስገንዝበዋል : :በዚሁ ዝግጅት ላይ በኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳይም ላይ ውይይት ተካሂዷል።
125ኛውን የአድዋ የድል በዓል ለመዘከር በጀርመን የኢትዮጵያውያን የውይይትና የትብብር መድረክ ባዘጋጀው የዙም የኢንተርኔት የውይይት መርሃግብር ኢትዮጵያ የጥቁር ሕዝቦችና የመላው አፍሪቃውያን ሁሉ የሁልጊዜም ኩራት በሆነው የአድዋው ጦርነት ለድል የበቃችው "በአጼ ምኒልክ የክተት አዋጅ የተጠራው የነጻነት ትግል ሁሉንም የሀገሪቱ የሕብረተሰብ ክፍሎች ዳር እስከዳር በአንድነት ያሳተፈ እንዲሁም የሀገር ሉዓላዊነት ላይ የተቃጣ ፍትሃዊ ጦርነት በመሆኑ ነው" ሲሉ የውይይቱ ተሳታፊዎች ገልፀዋል:: የውይይቱ የክብር እንግዳ በፍራንክፈርት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጄነራል አቶ ፈቃዱ በየነ ለኢትዮጵያ ሀገረ-መንግሥት ምስረታ ጉልህ ድርሻ ያለውና የአንድነታችን ስኬት የሆነው ይህ ዓለም ሁሉ የሚዘክረው ታሪካዊ ድል ላለፉት 84 ዓመታት ተገቢው ትኩረት ሳይሰጠው ቆይቷል ነው ያሉት:: የአድዋ ድል በዓል መሪዎች በራሳቸው በጎ ፈቃድ የሚያከብሩት ሳይሆን ዘመን ተሻጋሪ አኩሪ በዓላችን ሆኖ እንደ ዘንድሮ ሁሉ ለወደፊቱም በድምቀት ሊከበር ይገባዋል ያሉት አቶ ፈቃዱ የአሁኑ ትውልድም በምጣኔ ኃብት ማማ ወደ ከፍታ በሚያሸጋግረንና ለአገልግሎት እንዳይበቃ የውጭ ኃያላት ከፍተኛ ተፅዕኖ በሚደረግበት የሕዳሴው ግድብ ሕዝባዊ ፕሮጀክት ላይ ሙሉ ድጋፉን በማጠናከር የቀደሙ ጀግኖች አያቶቹን ታሪክ ሊደግም ይገባዋል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ጠላትን ድል ማድረግ ታሪካችን ነው ያሉት ቆንስል ጄነራሉ "አሁን ላይ አንዳንድ ኃይላት የሱዳንን ጦር የድንበር ወረራ ምክንያት አድርገው ጉዳዩን በማጦዝ ወደ ግጭት እንድንገባ ቢገፉንም ችግሩ በሰላማዊና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ብቻ ነው ሊፈታ የሚችለው" ሲሉም ተናግረዋል:: በመርሃግብሩ ላይ በሃገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያም ጥልቅ ውይይት ተካሂዷል:: ከኢትዮ-ሱዳን የድንበር ውዝግብ ጋር በተያያዘ "እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር በ2006 ዓ.ም የቀደመው የሕወሃት አስተዳደር ከ 12 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ለሱዳን በምስጢራዊ ስምምነት ከኢትዮጵያ ግዛት ከመተማ ደለሎ መሬት ቆርሶ መስጠቱ ይነገራል:: ይህን ትልቅ ሃገራዊ ጉዳይ ፓርላማው አውግዞ መሬቱ እንዲመለስ ጥረት ካለማድረጉም ሌላ አሁንም ከ 50ሺህ ሄክታር የሚልቅ ተጨማሪ መሬት በሱዳን ተወሯል:: የኢትዮጵያ መንግስት ውዝግቡን በውይይትና በዲፕሎማሲ እፈታዋለሁ ቢልም ሱዳን ከአልፋሻግ የእርሻ መሬት አልፋ ግድቡ ያለበትን የቤኒሻንጉል ክልል ጭምር የቀድሞ ግዛቴ ነበር በማለት ላይ ትገኛለች።
ከዚህ በተጓዳኝ የአሜሪካና የሩሲያ የባሕር ኃይል የጦር መርከቦች ከቀናት በፊት ፖርት ሱዳን ማረፋቸ እንዲሁም በአካባቢው የሚታየው የግብጽና የተለያዩ የአረብ ሃገራት ጣልቃ ገብነት ማየሉ ኢትዮጵያ መሬቱዋን ሊያሳጣት አይችልም ወይ? በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ "ወታደራዊ ኃይላችንን ማጠናከር አለብን" እያሉና የሀገር ሉዓላዊነት ተወሮ በሺዎች የሚቆጠሩ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን በቅርቡ ወደ ደቡብ ሱዳን ጁባ እና ሶማሊያ በሰላም አስከባሪነት መላኩስ አግባብ ነው ይላሉ?" ስንል አቶ ፈቃዱን ጠይቀናቸው ነበር።
ቆንስላ ጄኔራሉ "የኢትዮጵያ የምንጊዜም ፍላጎት የሁለቱ ሀገራት የድንበር ውዝግብ በሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ መንገድ እንዲፈታ አስፈላጊውን አማራጭ ሁሉ መጠቀም ያ የማይሳካ ከሆነ ግን የዓለም አቀፍ ህግጋትም ድጋፍ ስለሚኖራት የግዛቷን ሉዓላዊነት በኃይል ለማስከበር ትገደዳለች" ሲሉ አብራርተዋል:: የአሜሪካና የሩሲያ የጦር መርከቦች በቀይባህር አካባቢ የሚያደርጉት እንቅስቃሴም የንግድና የኃይል አሰላለፍ ሚዛናቸውን ለማስጠበቅ የሚደረጉት ጥረት እንጂ ከድንበር ግጭቱ ጋር አንዳችም ግንኙነት የለውም ሲሉ ተናግረዋል።
የመንግሥት ዋንኛ ተቀዳሚ ተግባር የዜጎችን ሰላም ማስጠበቅ ቢሆንም ዛሬም መንግስት ወደ ሃገር እንዲገቡና በሰላማዊ ትግል እንዲንቀሳቀሱ በፈቀደላቸው ታጣቂዎች ጭምር አሁን ድረስ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በየዕለቱ የዜጎች ግድያና ማፈናቀል እንደቀጠለ ነው:: ይህን ችግር መቅረፍ ያልተቻለው ለምንድነው ? በትግራይም መንግስት ወሰድኩት ካለው የህግ ማስከበር ሂደት ጋር በተያያዘ ዓለማቀፉ ማህበረሰብ ስለሚያነሳቸው የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት በተገቢው ሁኔታ አለመዳረስና የመብት ጥሰቶች የመንግስት ምላሽ ምንድነው ስንልም አቶ ፈቃዱን ጠይቀናቸው ነበር።
"ከለውጡ በፊት በኦሮምያና በሶማሌ ክልሎች የድንበር ግጭት በሚልዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ተፈናቅለዋል:: በኦሮምያና ደቡብ ክልል፣ በጉጂና ጌዶ በሲዳማና ወላይታ፣ በጉራፈርዳ፣ በኮንሶ፣ በበቤኒሻንጉል ክልልም በአማራ፣ በኦሮሞና በሌላውም የማህበረሰቡ ክፍሎች ላይ ነዋሪውን ከመኖሪያ ቀዬው ማፈናቀል፣ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እና ግድያዎች ሲፈፀሙ ነው የቆዩት:: አንዳንድ የሀገሪቱን ሰላም ለማደፍረስ በውጭ ኃይላት ጭምር የሚደገፉ ቡድኖች ረጃጅም እጆች ከዚህ እኩይ የጥፋት ድርጊት ጀርባ ነበሩ:: እነዚህ ኃይላት አሁን ላይ አቅማቸው በእጅጉ ተዳክሟል ዩህ እንጂ አሁንም አልፎ አልፎ ግጭቶች መፈናቀሎችና ግድያዎች እየተስተዋሉ ነው።
በሌላ በኩል በተለይም መንግሥት ከሕዝቡ ጋር ተቀናጅቶ የሚያከናውነውን እና ሀገሪቱንም ሕዝቡንም ከድህነት ያላቅቃል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ግዙፉን የሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታ ለማደናቀፍ ከሱዳን ጭምር የሚወነጨፉ ኃይላት በሕዝቦቻችን ላይ አሰቃቂ ግድያና ማፈናቀል እየፈፀሙ ይገኛሉ:: መንግሥታችን ከጠነከረ ሕዝቡም ከመንግሥት የፀጥታ ኃይላት ጋር እጅና ጓንት ሆኖ ከሰራ ችግሩ ከስር መሰረቱ ይቀረፋል የሚል እምነት ነው ያለኝ" በማለት አቶ ፍቃዱ ገልፀዋል:: በተረፈ የኢትዮጵያን ሰላምና ዕድገት የማይመኙ አካላት አንዳንድ ዓለማቀፍ ተቋማትና የመብት ተሟጋቾች ጭምር ከፍተኛ የተቀናጀ የፈጠራ ዘመቻ ከፍተዋል መንግሥትና ሕዝቡ በጋራ ይህን በሀገር ህልውና ላይ የተቃጣ አፍራሽ እንቅስቃሴ በሕዝባዊ እንቅስቃሴ እንደሚመክቱ እምነት አለኝ ሲሉም ከዶይቼ ቨለ ጋር ባደረጉት ቃለ-መጠይቅ ተናግረዋል።
የመርሃ ግብሩ አዘጋጅ በጀርመን የኢትዮጵያውያን የውይይትና የትብብር መድረክ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ዘለዓለም ደበበ ማህበሩ ዘመን ተሻጋሪውን የአድዋን ድል ከመዘከር ባሻገር በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ሰላምና ዲሞክራሲ እንዲሰፍን፣ መጪው ሀገራዊ ምርጫ ስኬታማ እንዲሆን ብሎም የዜጎች መብትና የመኖር ዋስትና እንዲከበር እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች ለተፈናቀሉ ወገኖች መርጃ የገቢ መርሃግብር በማዘጋጀት አያሌ የተግባር እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ ይገኛል ነው ያሉት::አዲሱ የኢትዮጵያ ትውልድ ጥቃቅን ልዩነቶቹን በሰለጠነ ውይይት ፈቶና ከፈጠራ እንዲሁም ከጥላቻ ትርክቶች ርቆ አያት ቅድመ አያቶቹ በአድዋው ጦርነት በአንድነት ዳር እስከዳር ተንቀሳቅሰው በከፈሉት የሕይወት መስዋዕትነት ያስረከቡትን ሀገር ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የማስጠበቅ ታሪካዊ ኃላፊነት እንዳለበትም ጠቅሰዋል።
የታሪክ ምሁሩና የፓን አፍሪቃኒዝም ፍልስፍና አቀንቃኝ ፕሮፌሰር ማሞ ሙጬም በውይይት መድረኩ ላይ አምና የአድዋ የድል በዓል 124ኛ ዓመት በደቡብ አፍሪቃ ፕሪቶሪያ ከተማ በተከበረበት ወቀት ተጋባዥ እንግዳ የነበሩት የቀድሞ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ታቦ ምቤኪ "አፍሪቃን በቅኝ ግዛት ለመቀራመት ጀርመን በርሊን ላይ እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር ህዳር15, 1884 ዓ.ም የመከሩት የአውሮጳውያን ሀገራት ኢትዮጵያ የጣልያንን ወራሪ ጦር ድል ማድረጓ ከተሰማ በኋላ ሌሎች በቅኝ ግዛት የተያዙ ሀገራትንም ለነጻነት ያነሳሳል በሚል ስጋት ከፍተኛ ብስጭትና ቁጭት ውስጥ ገብተው አጼ ምኒልክንና እቴጌ ጣይቱን ለመግደል የበቀል ሴራ ጠንስሰው እንደነበር " ማውሳታቸውን ገልፀዋል።
የውይይቱ ታዳሚዎች የአፍሪቃውያን የጥቁር ሕዝቦች ኩራት የሆነውን አድዋ ጦርነት መላው ሕዝባችን በጋራ ዳር እስከዳር በአልገዛም ባይነትና የሀገሬ ሉዓላዊነቴ አይደፈርም በሚል ጀግንነት በቁጭት ተንቀሳቅሶ ያስገኘው ታሪካዊ ድል መሆኑ የተወሳ ሲሆን የዛሬውም ትውልድ የመላው ሕዝባችን ቅርስ የሆነውና ከድህነት የሚያወጣን የሕዳሴው ግድብ ብሔራዊ ፕሮጀክት አገልግሎት መስጠት እንዳይጀምር የውጭ ኃይላት የሚሸርቡብንን ሴራ በንቃት በመዋጋት ግድቡ እስኪጠናቀቅ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ በሱዳን የተወረረብንን ድንበር በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረውን ምርጫ እንዲያግዝና መንግሥት ተፎካካሪዎችና ሕዝቡም መጪው ሃገራዊ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ይሆን ዘንድ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ ጥሪ አስተላልፈዋል:: በመርሃ ግብሩ ላይ የአድዋን ድል የሚዘክሩ ታሪካዊ መዛግብትን መሰረት ያደረጉ ልዩ ልዩ መልዕክቶች ሽለላዎችና ግጥሞችም ቀርበዋል።
እንዳልካቸው ፈቃደ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ