ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የደቡብ አፍሪቃ አቻቸውን አሳጡ
ሐሙስ፣ ግንቦት 14 2017ፕሬዝዳንቱ ነጭ ደቡብ አፍሪቃውያን የዘር ማጥፋት ወንጀል ሰለባ እንደሆኑ የሚገልጹ ቪዲዮ በማሳየት እና የኅትመት ውጤቶችንም በማጣቀስ ፕሬዝዳንት ራማፎሳንና አስተዳደራቸውን ከስሰዋል። የፕሬዝዳንቱ ክስ እስካሁን በተለያዩ ገለልተኛ አካላት እውነትነት እንዳለው መንም ማስረጃ ያልቀረበበት ቢሆንም፣ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ግን የሁለቱን ሃገራት ግንኙነት እስኪያሻክር ድረስ ጫና ማረጋቸውን ቀጥለዋል።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በኋይት ሐውስ ቢሮዋቸው ውስጥ የደቡብ አፍሪቃው ፕሬዚዳንት ሲረል ራማፎሳን በአደባባይ የማሳጣት ተግባር ፈጽመዋል። ፕሬዝዳንቱ ነጭ ደቡብ አፍሪቃውያን የዘር ማጥፋት ወንጀል ሰለባ እንደሆኑ የሚገልጹ ቪዲዮ በማሳየት እና የኅትመት ውጤቶችንም በማጣቀስ ፕሬዝዳንት ራማፎሳንና አስተዳደራቸውን ከስሰዋል። የፕሬዝዳንቱ ክስ እስካሁን በተለያዩ ገለልተኛ አካላት እውነትነት እንዳለው ምንም ማስረጃ ያልቀረበበት ቢሆንም፣ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ግን የሁለቱን ሃገራት ግንኙነት እስኪያሻክር ድረስ ጫና ማረጋቸውን ቀጥለዋል።
በኋይት ሐውሱ የፕሬዳንት ትራምፕ ቢሮ ውስጥ ከዩክሬይኑ ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ጋ የታየው እሰጣ ገባ ትላንት ከደቡብ አፍሪቃው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ጋ ተደግሟል። በአሜሪካና በደቡብ አፍሪቃ መሃከል ያለውን የዲፕሎማሲያዊ ትስስር ለማጠናከር ወደ ዋሽንግተን የዘለቁት የደቡብ አፍሪቃው ፕሬዝዳንት እሳቸው ያልጠበቁት፥ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ግን አስቀድመው የተዘጋጁበት፥ ኋይት ሐውስን ወደ ሲኒማ ቤት የቀየረ፥ በቪዲዮና በተለያዩ የኅትመት ውጤቶችም የታጀበ፥ የደቡብ አፍሪቃ ነጭ ዜጎች ላይ የዘር ማጥፋት ተፈጽሟል የሚል ውንጀላ ላይ ያተኮረ ማፋጠጥን አስተናግደዋል። ፕሬዝዳንት ትራምፕ መብራቱን አስጠፍተው፤ በደቡብ አፍሪቃ ፓርላማ ውስጥ የመሬትን ፍትኃዊ ክፍፍል አስመልክቶ የተደረጉ ንግግሮች እንዲሰሙ አድርገዋል።
ደቡብ አፍሪቃ ከአፓርታይድ ወደ ሰላማዊ ሽግግር ባደረገችው ጉዞ ውስጥ ቁልፍ ሚና የነበራቸው ፕሬዝዳንት ራማፎሳ፣ ትራምፕ የቪዲዮውን መልዕክትና፣ የታተሙ ጽሑፎችን እየጠቀሱ ነጮች በአሰቃቂ ሁኔታ እየተገደሉ እንደሆነ ሲናገሩ በጽሞና ነው ያደመጡት።
ይሄው የትራምፕ የማሳጣት ተግባር ጉዳዩን የበለጠ አጉልቶ የመገናኛ ብዙኃን ትኩረት እንዲያገኝ ታስቦ እንደሆነ ተነግሯል። እናም የቪዲዮውን ተዕይንት ተከትሎ ፕሬዝዳንት ትራምፕ እንዲህ ነጮቹን አጥላልተው የሚናገሩት የሃገሪቱ ፓርላማ ውስጥ ያሉ ሰወች መሆናቸውን ገልጸው፣ መንግስት ጥቁሮች መሬትን እንዲወስዱ፣ በዚህ ሂደትም ነጮች እንዲገደሉ አግዟል የሚል እንድምታ የያዘ ሃሳብ ሰንዝረዋል። የዶናልድ ትራምፕ ዲፕሎማሲ በአፍሪቃ
ፕሬዝዳንት ራማፎሳም በቪዲዮው ላይ የታየው ሐሳብ የመንግስት ፖሊሲ አለመሆኑንና ደቡብ አፍሪቃ የሃሳብ ነጻነት ያለባት የመድብለ ፓርቲ ሃገር መሆኗን አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ በዚህ ብቻ አላበቁም። ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በነጮች ላይ ያነጣጠረ የዘር ማጥፋት ቢኖር ኖሮ አብረዋቸው የመጡት፣ የደቡብ አፍሪካ የግብርና ሚኒስትርን ጨምሮ ሶስት ነጭ የልኡካን ቡድን አባላቶቻቸው አብረዋቸው ሊመጡ እንደማይችሉ አሳውቀዋል።
ደቡብ አፍሪቃ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው ሕዝብ ጥቁር ሲሆን ከ8% በታች ደግሞ ነጭ ነው። ይሁን እንጂ 8 በመቶ ብቻ የሚሆኑት ነጭ ደቡብ አፍሪካውያን በሃገሪቷ ውስጥ ካለው መሬት ውስጥ ከ70 በመቶ በላይ የግል መሬት ባለቤቶች ናቸው። ይሄ ደግሞ ከሰላሳ አመት በፊት ያበቃው የአፓርታይድ ስርዓት ትቶት ያልፈው፣ ዛሬም ድረስ የዘለቀ ጦስ ነው።
ራማፎሳና መንግስታቸው እነዚህን ታሪካዊ የፍትሕ መዛባቶች ለማስወገድ የመሬት ባለቤትነት ማሻሻያወችን እያደረጉ ቢሆንም፣ ሰወችን የማፈናቀል ፖሊሲወችን ግን ተፍጻም እንዳላደረጉ ነው የሚናገሩት። የተለያዩ አለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን እና አምነስቲ ኢንተርናሽናልን ጨምሮ ሌሎች አለም አቀፍ ተቋማት፣በነጮች ላይ ሥርዓታዊ ጥቃት ወይም "የዘር ማጥፋት ዘመቻ" መኖሩን የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ አላገኙም።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከዚሁ እሰጣ ገባ አስቀድሞ ከደቡብ አፍሪካ ከመሬታቸው ተፈናቀልን ያሉ ነጭ ደቡብ አፍሪካውያንን በስደተኝነት መቀበላቸውና በደቡብ አፍሪካ መንግስት ላይ ከፍተኝ ጫና ሲፈጥሩ መቆየታቸው ይታወቃል። ወደኋላ 40 አመታት መለስ ብልን ብናይ ደግሞ እ.ኤ.አ በ1984 ዓ.ም በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ሮናልድ ሬገን፣ ከኖቤል የሰላም ተሸላሚውና ከፀረ-አፓርታይድ ትግል አራማጁ አርክ ቢሾፕ ዴዝሜን ቱቱ የቀረበላቸውን በደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ አገዛዝ ላይ ማዕቀብ የመጣል ጥያቄ አልቀበልም ብለው ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተው ነበር።
አበበ ፈለቀ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ