«ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ትጥቅ እስኪፈታ እንፋለማለን»፦ የሱዳን ጦር
ረቡዕ፣ መጋቢት 24 2017በሱዳን ጦር ሠራዊት እና በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል ለዓመታት በቀጠለው ውጊያ የኃይል ሚዛኑ እየተቀየረ ነው ። የሱዳን ፕሬዚደንት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ትጥቅ ካልፈታ ውጊያው ይቀጥላል ብለዋል ።
ለሁለት ዓመት ግድም በዘለቀው የሱዳን የርስ በርስ ጦርነት ካርቱምን ተቆጣጥሮ የቆየው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር (RSF) ከሰሞኑ በዋና ከተማዪቱ ተደጋጋሚ ሽንፈት እየደረሰበት ነው የሚሉ መረጃዎች እየወጡ ነው ። የሱዳን ዋና ከተማ ካርቱምን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠሩን የገለጠው የሱዳን ጦር ሠራዊት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ትጥቅ እስካልፈታ ድረስ ውጊያው እንደሚቀጥል ዐሳውቋል ። የፈጥኖ ደራሹ መሪ ጄኔራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ በቅጽል ስማቸው «ሔሜድቲ» ጦራቸው ከካርቱም ጠቅልሎ መውጣቱን እሑድ ዕለት አረጋግጠዋል ።
«ካርቱምን ለቅቀን መውጣታችንን አረጋግጥላችኋለሁ ። በፈጣሪ ፈቃድ ግን እንደውም ጠንከር ባለ ቆራጥነት፣ ኃይል እና ተጨማሪ ድሎች ወደ ካርቱም እንመለሳለን ።»
የሱዳን ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን የሱዳን ጦር ሠራዊት ጦርነቱ የሚያከትመው ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ትጥቅ ፈትቶ እጅ እስከሰጠ ድረስ ብቻ ነው ብለዋል ። ያም እውን እስኪሆን ድረስ ጦራቸው ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን መውጋቱን እንደሚቀጥል ዝተዋል ።
«የተወደዳችሁ የሱዳን ሕዝቦች፦ ጦርነቱን የማክተም እና የሰላም መንገድ አሁንም ክፍት ነው ። በአሸባሪው ሚሊሺያዎች ቁጥጥር ስር በተለይም ኤል ፋሺር ውስጥ የሚገኙ ሕዝባችን ሥቃይ፤ መከበባቸው እና መገደላቸው ብሎም በአገሪቱ ሰላምን የማስፋፋት እና የማረጋገጥ አስፈላጊነት ይህ ሁሉ ሊሆን የሚችል ነው ። እናም መንገዱ ግልጽ ነው፥ ይህም ሚሊሺያዎቹ ጦር መሣሪያቸውን ካወረዱ ነው ።»
ከዋና ከተማዪቱ የተባረረው የፈጥኖ ደራሹ ኃይል በሚቆጣጠራቸው ቦታዎች ከጦር ሠራዊቱ ጋር ውጊያ መቀጠሉን እና ወታደሮችን መግደሉን ዐሳውቋል ። ደቡብ ኮርዶፋን ግዛት ውስጥ በሚገኘው ክሆር አል ዳሌብ ክልል ውስጥ ከዐሥር በላይ የሱዳን ጦር ሠራዊት ወታደሮችን መግደሉን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ሰኞ ዕለት ገልጧል ።
ካርቱምን የተቆጣጠረው የሱዳን ጦር እና ተጠናክሬ ዳግም መመለሴ አይቀርም ሲል የሚዝተው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል ውጊያ በቀጠለባት ሱዳን የነዋሪው ቁም ስቅል ተባብሷል ። በሱዳን የርስ በርስ ጦርነት ከ12 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከመኖሪያ ቀዬያቸው ተፈናቅለዋል ። በሺህዎች የሚቆጠሩትም መገደላቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዐሳውቋል ። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉም፦ ከርስ በርስ ጦርነቱ ባሻገር ሱዳን ውስጥ ብርቱ የረሐብ አደጋ መከሰቱኑንም ተመድ ይፋ አድርጓል ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሠ